Friday, July 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲሱ የግብርና ኮርፖሬሽን ያጣመራቸው ሥራዎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከደርግ መንግሥት ጀምሮ በአገሪቱ የእርሻ ሥራ ላይ በግብዓትም በቴክኖሎጂም ድጋፍ እንዲያደርጉ፣ ግብርና ወደ ሜካናይዜሽን ተግባር እንዲቀላቀል ያስችሉ ዘንድ ተቋቁመው ከነበሩ መካከል ከሰሞኑ ተዋህደው የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሚባል መንግሥታዊ የልማት ድርጅት የመሠረቱ አምስት ድርጅቶች አሉ፡፡ እንደ አዲስ የተቋቋመው ድርጅት ከዚህ ቀደም በግብርና ሚኒስቴር ሥር የነበሩ ተቋማትን በመጠቅለል ሲመሠረት፣ ዘመናዊ የግብርናና የደን ውጤቶች ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ተጠሪነት ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ነው፡፡ ድርጅቱ በሁለት ቢሊዮን አራት መቶ አርባ ሚሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል ሲቋቋም፣ የተከፈለ ካፒታሉም 610 ሚሊዮን ብር መሆኑ ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት፣ የተፈጥሮ ሙጫ ምርትና ገበያ ድርጅት፣ የግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅራቢ ድርጅት፣ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ድርጅት፣ እንዲሁም የእርሻ መሣሪያዎች የቴክኒክ አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር የሚባሉትን የልማት ድርጅቶች ጠቅልሎ በመያዝ ራሱን የቻለ የልማት ድርጅት ሆኖ ተመሥርቷል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች መካከል የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎትን ማስፋፋት አንዱ ሲሆን፣ የእርሻና የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ጥገና የመስጠት፣ ሲለውም የማከራየት ተግባራትን እንዲወጣም ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የእርሻ መሣሪያዎችንና መለዋወጫዎችን፣ የኮንስትራክሽን መሣሪያዎችን፣ እንዲሁም የአግሮ ኬሚካሎችን ከአገር ውስጥና ከውጭ ገዝቶ ለሽያጭ እንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡
የአዳዲስና የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ላይ የአዋጭነት ጥናት ከማካሄድ በተጨማሪ፣ የዲዛይንና የቴክኖሎጂ መረጣ ሥራዎችን ማከናወን ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በኮርፖሬሽኑ አመሠራረት፣ አሁን በሚገኝበት ደረጃና ወደፊት ያከናውናቸዋል ተብለው ስለሚጠበቁ ዝርዝር ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ብርሃኑ ፈቃደ የኮርፖሬሽኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ከፍያለው ብርሃኑን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አምስት ድርጅቶችን በማዋሃድ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የተባለውን መሥሪያ ቤት ማቋቋም ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ምንድን ነው?

አቶ ከፍያለው፡- የግብርና እርሻ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 368/08፣ ከታኅሳስ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ የጀመረ ነው፡፡ ከተቋቋመ ገና ሁለት ወር ተኩል የሚሆነው የመንግሥት የልማት ኮርፖሬሽን ነው፡፡ ሲቋቋምም በመንግሥት በርካታ ኃላፊነቶች ተሰጥተውታል፡፡ የተቀናጀ የግብርና ቴክኖሎጂና ግብዓት ለአርሶ አደሩም ሆነ በግብርናው መስክ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ለማቅረብ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ሲቋቋም ቀደም ሲል አምስት የልማት ድርጅቶች ማለትም በየራሳቸው፣ በተነጣጠለ መንገድ በግብርና ሥራ ውስጥ ይሳተፉ የነበሩ ድርጀቶችን መብትና ግዴታ በመውረስ የተቋቋመ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ድርጅት አምስቱ ድርጅቶች ይሠሩት የነበረውን ሥራ በአንድ ወጥ፣ በአንድ መስኮት በማቀናጀት ለደንበኞች አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ ቀደም ሲል አንድ በግብርና ዘርፍ የተሰማራ ባለሀብት ወይም አርሶ አደር የእርሻ ቦታ እንዲዘጋጅለት ቢፈልግ፣ እኛ መሬት ዝግጅት እንለዋለን ይህንን መሬት ለእርሻ ለማዘጋጀት የእርሻ መሣሪያዎችና የቴክኒክ አገልግሎት የሚባል ድርጅት ሊያግዝ ይመጣል፡፡ መሬቱ እንዲታረስ ሲፈለግ እርሻ ሜካናይዜሽን ይሄዳል፡፡ ከታረሰ በኋላ ዘር ለማግኘት ወደ ኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት ይሄዳል፡፡ ለዚያው ዘር ማዳበሪያ ቢፈልግ የኢትዮጵያ ግብዓት አቅራቢ ድርጅት ጋ ይሄዳል፡፡ ለሰብሉ ፀረ አረም ወይም ፀረ ተባይ ቢያስፈልገው ወይ ወደ ግብርና ግብዓት ይሄዳል ወይም ወደ እርሻ መሣሪያዎች ይሄዳል፡፡ ሁለቱም ጋ ስላለ፡፡ ሰብሉ ካደገ በኋላ ለማሳጨድና ለማስወቃት አሁንም እርሻ መሣሪያዎች ጋ ይሄዳል፡፡ ስለዚህ እነኚህ ድርጅቶች ናቸው አሁን አንድ ሆነው እንዲዋሐዱ የተፈለጉት፡፡ ስለዚህ እነዚህ ድርጅቶች አንድ በመሆናቸው በቅድሚያ ደንበኛው ከአንድ ቦታ ሁሉንም አገልግሎቶች ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው እንዲያገኝ ይረዳዋል፡፡ ሁለተኛ እነዚህ ድርጅቶች አንድ በመሆናቸው በተለይ ኮርፖሬት አመራሩ በአንድ መዋቅር ውስጥ ይሆናል፡፡ አንድ አመራር ይሆናል፡፡ ከፍተኛ የሰው ኃይል ቁጠባ ይፈጠራል፡፡ ለምሳሌ የአስተዳደር ኃላፊ፣ የፋይናንስ ኃላፊ፣ የኦዲት ኃላፊ፣ የሕግ አግባብ ኃላፊ የሚባሉት ከፍተኛ አመራር መዋቅሮች በአምስቱም ድርጅቶች ውስጥ ነበሩ፡፡ የየራሳቸው የሰው ኃይል ነበራቸው፡፡ አሁን በኮርፖሬሽን ደረጃ ሲደራጅ ግን የሰው ኃይሉ በአንዳንድ ሰው ይወከላል፡፡ ስለዚህ ኮርፖሬት የሰው ኃይል አመራሩ የተቆጠበ የሰው ኃይል ይጠቀማል ማለት ነው፡፡ ሌላው በኦፕሬሽን ሥራ ላይ ይሰማራል ማለት ነው፡፡ ኮርፖሬት ፋይናንሱም የሁሉንም ፋይናንሶች በማቀናጀትና በመደጋገፍ ሥራ ላይ እንዲውል ያደርጋል፡፡

ሪፖርተር፡- አምስት ሰፋፊ ድርጅቶችን ወደ አንድ ማምጣጡ እርስዎ እንደገለጹት ጠቀሜታዎች ይኖሩታል፡፡ ነግር ግን የዚያኑ ያህል ፈተናዎችም ይኖሩታል፡፡ ከዚህ በፊት በሌሎች ድርጅቶች ላይ ይህ ሲሆን ዓይተነዋል፡፡ የድርጅቶቹ የመዋቅር ልዩነትም ውህደታቸውን አክብዶት እስኪግባቡ ድረስ ረዥም ጊዜ የወሰደባቸው መሥሪያ ቤቶች አሉ፡፡ የእናንተስ ኮርፖሬሽን ከዚህ አኳያ ከሥጋት ነፃ ነው ማለት ነው? 

አቶ ከፍያለው፡- ፈተና የለውም ማለት አይቻልም፡፡ ድርጅቶቹን አዋህዶ አንድ ኮርፖሬሽን መፍጠር በርካታ ፈተናዎች አሉት፡፡ አንዳንዱ ፈተና ከሚገባው በላይ ፈታኝ ነው፡፡ በተለይ እንደ ሰው የአስተሳሰብና የባህሪን ጉዳይም የሚመለከት ነው፡፡ ለብቻህ ነው የምትተዳደረው፣ የምታስተዳድረው ስትለው የነበረውን አምስት ተቋም ወደ አንድ ስታወርደው፣ ሀብቱ ወደ አንድ አቅጣጫ ሲመጣ፣ አሠራሩ ወጥነት እንዲኖረው ሲደረግ፣ የኃላፊነት ደረጃው ከፍና ዝቅ ሲል ፈተና የለውም፣ አስቸጋሪ አይሆንም አይባልም፡፡ ሁሉም ነገር ፈተና አለው፡፡ አንዳንዱም ፈተና እንደ መልካም ዕድል ማየት ይገባል፡፡ ፈተናውን በቀጣይ ከረዥም ጊዜ ግብ አንፃር ሊገኝ ከሚችለው ጥቅም አኳያ መመዘን ያስፈልጋል፡፡ ፈተናው ዛሬ ላይ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ለማዋቀር አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፡፡ ይኼንን ታግለን ወደ መስመር ካስገባነው ግን ፈተናውን እናሸንፋለን፡፡ ሠራተኞችና ኃላፊዎች ጥቅሙን እንዲረዱ በማድረግ እናሸንፈዋለን፡፡ ፈተናው ከባድ ቢሆንም ልንወጣው እንችላለን የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡ ጠቀሜታው ግን እንደ አገር ትልቅ ነው፡፡ ይህች አገር በግብርና ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ያላት በጣም በርካታ ሕዝብ ያላት፣ በርካታ መሬቷ ከእርሻ ምቹ በመሆኑ የተንጠባጠበ ሀብት እዚያም እዚህም ይዞ በተናጠል እየታሰበ የሚሠራ ነገር በምግብ ራሳችንን ለመቻል፣ ልጆቻችንን የማይለምኑባት አገር እንድትሆን እንዲህ ያለውን ፈተና ካልተጋፈጥነው ልንወጣው አንችልም፡፡ ስለዚህ መመዘን ያለበት ጥቅሙና አሁን ያለው ፈተና ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ድርጅቶቹ ሲዋሃዱ ሊቀነስ የሚችል ሠራተኛ የለም፤ አይኖርም?

አቶ ከፍያለው፡- ወደ 2200 አካባቢ የሚቆጠሩ ሠራተኞች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ሠራተኞች በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ያሉና የተለያዩ ጥቅሞችን ያገኙ የነበሩ ናቸው፡፡ አንድ ወጥ ተቋም ሲሆን የቀነስ ይሆን ወይ? ደረጃዬ ዝቅ ይል ይሆን ወይ? ጥቅሜ ይቀነስ ይሆን ወይ? የሚል የተለያየ ግራ መጋባት መኖሩ አይቀርም፡፡ እነኚህ ሥጋቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቶቹ ሊዘጉ ነው፣ ሠራተኞች ሊባረሩ ነው፣ ሥራ ሊቀነስ ነው የሚሉ ሥጋቶችም ሊኖሩ እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ ይህ ኮርፖሬሽን ሲቋቋም መንግሥትም አስቦ ያቋቋመው ያሉትን ሠራተኞች ለማባረር አይደለም፡፡ እንደውም ይህ ደርጅት ሰፍቶ፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ፣ በርካታ ሥራዎችን እየፈጠረ በርካታ የሰው ኃይል የሚጨምር ተቋም ነው፡፡ የኮርፖሬሽኑ መቋቋም ሳይሆን የሠራተኛ መበተን ሥጋት የሚፈጥረው ድርጅቶቹ በተበጣጠሰ ኦፕሬሽን እንደቀድሞው ቢቀጥሉ ነበር፡፡ አንድ ቀን ድርጅቶቹ መንቀሳቀስ አቅቷቸው እስከ መዘጋትና ሠራተኛ እስከ ማሰናበት ሊደርስ የሚችል ሁኔታ ሊፈጠር ይችል ይሆናል፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ ሠራተኛ እያንዳንዷን ተናጠላዊ የግብርና ሥራ ሲሠራ ተቀናጅቶ፣ ከመነሻው ጀምሮ ባለጉዳይ ሆኖ፣ ከሥሩ ጀምሮ እየተካተተ ነው የሚሠራው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ያሉ ሠራተኞችም ሆኑ ኃላፊዎች ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው፣ ለትልቅ ኃላፊነት እንደታጩ አውቀው ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው ማስተማሩ ነው የሚሻለው፡፡ ስለዚህ ሠራተኛው እስከሠራ ድረስ የሥራ ዕድል ይሰጠዋል፡፡ ሠራተኛ መቀነስን እንደ ዓላማ ይዘን ኮርፖሬሽንኑን አልፈጠርንም፡፡ አጀንዳችን ውስጥም የለም፡፡ ሊያገልግል የሚችል የሰው ኃይል መፍጠር ግን ዋናው ጥያቄ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኮርፖሬሽኑ አሁን ላይ የሚገኝበት ደረጃ ምንድን ነው?

አቶ ከፍያለው፡- ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ እንዲቋቋም አዋጅ ሲወጣ ቢሮ የለውም፡፡ እንዴት እንደሚሠራም አይታወቅም፡፡ ምን መዋቅር እንደሚኖርም አይታወቅም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ይህንን ሥራ እንድንሠራ ኃላፊነት የሰጠው ለእኛ በመሆኑም ቢሮ የማደራጀት ሥራ ላይ እንገኛለን፡፡ ለጊዜው የመረጥነው ትልቅ ቢሮ ከመከራየት ይልቅ እዚሁ ባለው (ሳሪስ አቦ አካባቢ በሚገኘው የእርሻ መሣሪያዎች ድርጅት ግቢ ውስጥ) ተጣቦ መሥራትን ነው፡፡ የኮርፖሬት ቢሮው ከተደራጀ በኋላ የኮርፖሬሽኑ ጊዜያዊ መዋቅርን አፅድቀን ወደ ሥራ ገብተናል፡፡ ጊዜያዊ መዋቅሩ አንድ የኦፕሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚና አንድ የሀብት አመራር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ያሉት ነው፡፡ በኦፕሬሽን ምክትል ሥራ አስፈጻሚው ሥር አምስቱም ድርጅቶች እንደ ቢዝነስ ዩኒት የኦፕሬሽን ሥራቸውን ይሠራሉ፡፡ በሀብት አመራሩ ሥር የአምስቱም ድርጅቶች የፋይናንስ፣ አስተዳደር ሥራዎች፣ ንብረት አስተዳደር ሥራዎችና የመሳሰሉት ይመራሉ፡፡ በዚህ መልክ ጊዜያዊ መዋቅሩ ተዘጋጅቶ ሰዎችን የማሟላት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ ሥራው እየተጀማመረ ነው፡፡ የኮርፖሬሽኑ ሀብት ምን ያህል ነው? የሚለውን ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ጎን ለጎን የኮርፖሬሽኑ ቋሚ አደረጃጀት መመሥረት ስላለበትም ምን ዓይነት የሰው ኃይል እንደሚኖረው፣ ምን ዓይነት ሥራዎች ይኖሩታል የሚለውን ለኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶች አጥኚ ለሆነው የውጭ አማካሪ ተቋም በአጭር ጊዜ ጥናቱን አካሂዶ እንዲያመጣልን ተዋውለን ሰጥተነዋል፡፡ እስከ ሦስት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ጥናቱን ጨርሶ እንደሚሰጠን እናስባለን፡፡ ሌላው እየተሠራ የሚገኘው ዋና ሥራ የአምስቱ ድርጅቶችን ሒሳብ የሚመለከት ነው፡፡ የድርጅቶቹ ሒሳብ በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ አንዳንዱ የ2005 በጀት ዓመት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ አንዳንዱ 2007 በጀት ዓመት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ሒሳብ ማዘጋት ያስፈልጋል፡፡ ማዘጋት ብቻም ሳይሆን ኦዲት ማስደረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ የተለየ ትኩረት የሚሰጠው ሥራ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ እስከ ተቋቋመበት ጊዜ ድረስ ያለው የሁሉም ድርጅቶች ሒሳብ ተዘግቶ ኦዲት መደረግ ይኖርበታል፡፡ ይኼንን አጠናክረን እየሠራንበት ነው፡፡ ኦዲት ከተደረገ በኋላ በታኅሳስ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. የኮርፖሬሽኑ ሀብት ምንድን ነው? የሚለውን ማወቅ እንችላለን፡፡ ሌላው የኮርፖሬሽኑ የቀጣይ አምስት ዓመት አቅጣጫን የሚያመላክት ስትራቴጂክ ዕቅድ እየተሠራ ነው፡፡ በአዋጅ የተቀመጠለት ኃላፊነትና ግዴታዎች ላይ ተንተርሶ ከአምስት ዓመት በኋላ የት ነው የሚደርሰው? ምንድን ነው የሚሠራው? የሚለው፣ ብቃት አላቸው በምንላቸው የውስጥ ባለሙያዎች እየተሠራ ነው፡፡ ሌላኛው ሥራ የመዋቅር፣ የማደራጀት ሥራው ላይ ስንራኮት የኦፕሬሽን ሥራውን እንዳንዘነጋ አምስቱም ድርጅቶች ቀደም ሲል የገቧቸው ውሎች፣ የሚይዟቸው አዳዲስ ሥራዎች ሳይደነቃቀፉ እንዲሠሩ የመከታተልና የማስፈጸም ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ የዕለት ተዕለት ሥራው ሳይስተጓጎል በዚህ መልክ እንዲሠራ እየተደረገ ነው፡፡ ሌላው ሥራ ኮርፖሬሽኑን የማስተዋወቅ ሥራ ነው፡፡ ደንበኛው፣ ባለድርሻ አካላት ሊያውቁት ይገባል፡፡ ምን እንደሚሠራ ሊያውቁትና አገልግሎት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ የኮርፖሬሽኑን አዲስ ዓርማ የመቅረፅና ሌሎች በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአዋጁ ኮርፖሬሽኑ የሚቋቋምበት ካፒታል ከ2.4 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ሰፍሯል፡፡ ካፒታሉ ከእነዚሁ ከአምስቱ ድርጅቶች የሚውጣጣ ነው ወይስ መንግሥት የሚመድበው ገንዘብ አለ?

አቶ ከፍያለው፡- ሒሳብ መዝጋት አለብን የምልህ ለዚህ ነው፡፡ 2.4 ቢሊዮን ብር ካፒታል ተመድቦለታል፡፡ ከዚህ ውስጥ 610 ሚሊዮን ብሩ በዓይነትና በገንዘብ የተከፈለ ነው፡፡ ይህ ገንዘብ አሁን ድርጅቶቹ ያላቸው ንብረት ነው፡፡ ስለዚህ ሒሳብ መዝጋቱ ያስፈለገው እውነትም ይህ 610 ሚሊዮን ብር በእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ ይገኛል ወይ? የሚለውን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ሒሳቡ ሲዘጋ በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ያለው ሀብት በግልጽ ይታወቃል፡፡ እሱን ካወቅን በኋላ መንግሥት የፈቀደው 2.4 ቢሊዮን ብር በመሆኑ፣ ልዩነቱን የፕሮጀክት ሐሳብ በማቅረብ ወይ ከመንግሥት እንዲመደብልን እናደርጋለን አልያም ብድር እንበደራለን፡፡

ሪፖርተር፡- ኮርፖሬሽኑ ከስያሜው ጀምሮ በግብርና ሥራዎች ላይ ያተኮረ ተቋም ሆኖ ሳለ ተጠሪነቱ ግን ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ነው፡፡ ከልማት ድርጅትነቱ አኳያ ሲታይ የሚያስኬድ ሊሆን ይችላል፡፡ የሚሠራው ግን የግብርና ሥራዎችን በመሆኑ ለእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ተጠሪነት እንዳይኖረው ሲደረግ የሚፈጥረው የጥቅም ግጭት አይኖርም?

አቶ ከፍያለው፡- የተወሰ ግጭት አለው፡፡ አገልግሎት ስንጠየቅም ሆነ ስንሰጥ የሚታዩ ግጭቶች አሉ፡፡ አንዳንዱ እንደ በጀት መሥሪያ ቤት አድርጎ የማሰብና አገልግሎቱን ብቻ እንዲሁ በነፃ እንድንሰጣቸው የመፈለግ ስሜት ይፈጥርባቸዋል፡፡ ይሄ ኮርፖሬሽን ግን ሁለት ነገር ይዞ የቆመ ነው፡፡ በአንድ ወገን የልማት ሥራውን ፍትሐዊ በሆነ ዋጋ ማዳረስ ነው፡፡ ለትርፍ ብቻ ብሎ የሚሠራ አይደለም፡፡ ዋና ዓላማው የአገር ዕድገት ላይ መሥራት ነው፡፡ ይህም ሆኖ የቢዝነስ ኮርፖሬሽን ነው፡፡ ራሱን ችሎ ባልተጋነነ ትርፍ ወጪውን ችሎ ማኅበረሰቡን የሚያገልግል ኮርፖሬሽን ነው፡፡ በነፃ አገልግሎት አይሰጥም፡፡ በኪሳራም አግልግሎት አይሰጥም፡፡ ቢበዛ ግን ወጪን በሚሸፍን መጠን አገልግሎት ሊሰጥ ይችላል፡፡ ስለዚህ የልማት ሥራውን የሚደግፍ የልማት ኮርፖሬሽን ነው፡፡ መንግሥትን ከሚያገኘው ትርፍ የሚደግፍ ተቋም ነው፡፡ ሁሉም ተቋም በመንግሥት በጀት እንደማይተዳደር ይታወቃል፡፡ ለመንግሥት ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ ትንሽም ቢሆን አትርፈን፣ ልማቱንም ኢኮኖሚውን የሚደግፍ፣ ባለበጀት ያልሆነ የቢዝነስ ተቋም ነው፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘውና አቅም ሲኖረው ውጭ በመውጣት ጭምር ሊሠራ የሚችል ኮርፖሬሽን ነው፡፡ ሱዳንና ሶማሊያ በጦርነት ለረዥም ጊዜ የቆዩ አገሮች እንደመሆናቸው ጦርነት አቁመው ወደ ግብርና በሚመለሱበት ጊዜ ሰፊ የመሬት ዝግጅት ውስጥ መግባታቸው አይቀርም፡፡ ያንን ሥራ ተወዳደረን ብንሠራ እንደሌሎች አገሮች ኮርፖሬሽኖች ድንበር ዘለል ሆነን የመሥራት ፍላጎትም አለን፡፡

ሪፖርተር፡- በሜካናይዜሽን መስክ አገልግሎት ስትጠየቁ መሬቱን የማረስ፣ የማዘጋጃት ሥራ ትሠራላችሁ፡፡ በእርሻና በተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሥር የሚገኘው የግብርና ኢንቨስትመንት ዳይሬክቶሬት ደግሞ መሬቱን እያቀረበ ይቀጥላል ማለት ነው?

አቶ ከፍያለው፡- አዎን፡፡ ትንሽ ማብራራት ይኖርብኛል፡፡ የመሬት ዝግጅት እንደሚታሰበው ቀላል ሥራ አይደለም፡፡ በእርሻ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የሚመጡ ሰዎች የሚያስቡት የትራክተሩን ዋጋ፣ የሠራተኛውን ዋጋና የመሬቱን የሊዝ ዋጋ ነው፡፡ መሬቱን መመንጠር፣ ዳገት ቁልቁለቱን ማስተካከል፣ ለትራክተር እንዲመች አድርጎ መሬቱን ማዘጋጀት ትልቅ ወጪ የሚጠይቅ ሥራ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ጥለው የሚጠፉትም ለዚሁ ነው፡፡ ከባንክ ይበደሩና ሳይከፍሉ የሚጠፉበት አኳኋን በተግባር ታይቷል፡፡ ሥራው ትልቅ ነው፡፡ እርግጥ ባለሀብቱ እኛን ከጠየቀ እንሠራለን፡፡ በግለሰብ ደረጃም ይህንን ሥራ እንደኛ የሚሠሩ አሉ፡፡ እንደ ኢንዱስትሪ መንደር ሁሉ የግብርና ፓርክ ብሎ አዘጋጅቶ መስጠት ይቻል ይሆን ወይ? የሚል ሐሳብ አለን፡፡ ለምን ቢባል ለኢንቨስተሩ የተቀመጠ ቦታ አዘጋጅተህ ብትሰጠውና የመሬት ማልማቱን ሥራ በጊዜ ሒደት እንዲከፍል ቢደረግ ሳይደነብር እርሻውን አርሶ ወደ ግብርናው በአፋጣኝ ይሄዳል፡፡ አሁን ግን መሬቱንም ሳያዘጋጀው፣ ሳይመነጥርና ሳያስተካክል አምስት ስድስት ዓመት ይፈጅበታል፡፡ ቆይቶም ተስፋ ቆርጦ ሊሄድ ይችላል፡፡ ትራክተሩን ይዞ ወደ እርሻ እንዲሠራ ለማስቻል የግብርና ፓርክ ልክ እንደ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብንመሠርት፣ ለሰፋፊ እርሻዎች በተመረጡ ቦታዎች ላይ መሬቱን አዘጋጅተን ብንጠብቀው፣ ወደ ሥራ በቶሎና በቀጥታ ይገባ ከሆነ ብንሄድበት የሚል ሐሳብ አለን፡፡ ወደፊት ይህ ተቀባይነት ካገኘ ወደዚህ ሥራ እንገባለን፡፡ ሌላው ሰፋፊ እርሻዎች ካሉ በበሬ ወቅተህ በማጭድ አጭተህ ልትሠራ አትችልም፡፡ ከስኳር ልማት ጋር በተገናኘ በርካታ የሸንኮራ እርሻዎች እየተመሠረቱ ነው፡፡ ይህ በመሆኑ ለሰብልም ከአገዳም የሚሆኑ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በማምጣት ማላመድ የምናስበው ሥራ ነው፡፡ ከትራክተሩ እርሻ በተጨማሪ በበሬ የሚጎተቱ ማረሻዎችን የማስተዋወቅ ሥራም እንሠራለን ብለን እናስባለን፡፡

ሪፖርተር፡- የኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይም ሚና እንደሚኖርችሁ በአዋጁ ተጠቅሷል፡፡

አቶ ከፍያለው፡- እሱ ብዙ አይደለም፡፡ አንዳንዶቹ ለመሬት ዝግጅት የሚያስፈልጉ ከባድ መሣሪያዎችና ማሽነሪዎች ለኮንስትራክሽን ዘርፉም ያገለግላሉ፡፡ የእርሻ መሬቱን ስትሠራ አፈር በዶዘር ትጠርጋለህ፡፡ መንገድ ትሠራለህ፡፡ ትልልቅ ክሬኖች ታሰማራለህ፡፡ እነዚህ እኩል በእኩል ለኮንስትራክሽን ሥራውም ይውላሉ፡፡ ኮንስትራክሽን ውስጥ እንገባለን፣ ተጫርተን እንሠራለን ማለት ሳይሆን የመሬት ዝግጅት ሥራ በሌለበት ጊዜ ለኮንስትራክሽን ሥራዎች በሊዝ ልናከራይ እንችላለን ማለት ነው፡፡ ከባድ መሣሪያዎች በሎቤድ ተሽከርካሪዎች ነው፡፡ ክሬኖችም አሉ፡፡ የእርሻ ሥራው በማይኖርበት ጊዜ ሎቤዶቹ ሥራ ከሚፈቱ ለኮንስንትራክሽንና ለትራንስፖርት ሥራዎች እንዲውሉ የማድረግ፣ እንደተጨማሪ የቢነዝስ ሥራ የሚታይ ነው፡፡ በኮንስትራክሽን ዘርፍ መሰማራት ዋና ሥራችን አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡- ከአምስቱ አንዱ የዕጣንና ሙጫ ልማት ድርጅት ነው፡፡ በዚህ መስክ ምን የተለየ ነገር ትሠራላችሁ?

አቶ ከፍያለው፡- ከአምስቱ ድርጅቱ ለየት ያለው የዱር ሙጫ ልማትና ንግድ ድርጅት ነው፡፡ ከዱር ሙጫና ከዕጣን የሚገኘው ጠቀሜታ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ የሙጫና የዕጣን ምርቶች ለመድኃኒትነት፣ ለምግብነት፣ ለመጠጥ ኢንዱስትሪውና ለኮስሞቲክስ ዘርፎች ይውላሉ፡፡ ጎረቤት ሱዳን ከዚህ ዘርፍ በጣም በርካታ ጥቅም ታገኛለች፡፡ ሌሎችም የአፍሪካ ብዙ ጥቅም ያገኙበታል፡፡ አገሮች በእኛ አገር የደን ሀብት እንደሚፈለገው መጠን ባይሆንም ለሙጫና ለዕጣን ምርት ተስማሚ የሆኑ አካባቢዎች አሉ፡፡ የዕጣንና የሙጫ ዝርያዎችን ብናስፋፋ፣ ከእነሱም የሚገኘውን ከአርሶ አደሩም ብናገኝ እኛም አቀነባብረን ብንሸጠው፣ ወደፊት ኢንዱስትሪው ሲስፋፋ ለኢንዱስትሪው ግብዓትነት ብናውለው ትልቅ ጥቅም ይሰጣል፡፡ አለበለዚያ ይህ ድርጅት ብቻውን ቢቀር ወይ ወደ ግል ይዛወራል፣ አልያም ባክኖ ሊዘጋ ይችላል በማለት ከግብርና ሥራዎች ጋር ተቆራኝቶ እንዲሠራ ማድረጉ ታምኖበታል፡፡ የተቋሙ ዋና የሙጫና የዕጣን ምንጭ የሆነው ዛፍ ከግብርና ሥራ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ስለዚህ ሙጫና ዕጣን ድርጅት አሁን እየሠራ ያለው ሙጫዎችንና ዕጣዎችን ከገበሬው እየሰበሰበ፣ ክልሎችን አስፈቅዶ ከያዘው ደን ይሰበስባል፡፡ የሰበሰውን ወደ ውጭ ይልካል፡፡ ይህ ግን በግማሽ የሚከናወን ሥራ ነው፡፡ ወደፊት በኢንዱስትሪ ተቀነባብሮና እሴት ተጨምሮበት ቢመረትና ወደ ውጭ ቢላክ ትልቅ ጥቅም ያስገኛል፡፡ አገር ውስጥም ቢሆን ለብዙ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የመሆን ትልቅ አቅም ያለው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኮርፖሬሽኑ ውስጥ የታቀፉት ድርጅቶች በራሳቸው የሚታይ ወሳኝ ሥራ ሲሠሩ እንደነበር ይታመናል፡፡ መንግሥት በአብዛኛው ወደ ግል ሲያዛውር ነበር የሚታየው፡፡ ከዚህ አኳያ በኮርፖሬሽን ማዋሃዱ የተለየ ዓላማው ምንድን ነው? ምክንያቱም በዚሁ ዘርፍ ተመሳሳይ ሥራ የሚሠሩ የግል ድርጅቶች አሉ፡፡ ኮርፖሬሽኑ እንዲመጣ ሲደረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያመጣ የሚፈለገው የተለየ የተቀመጠለት አዲስ ነገር አለ?

አቶ ከፍያለው፡- አብዛኞቹ የልማት ድርጅቶች ወደ ግል እንዲዛወሩ ሲደረግና ሲሸጡ እንደነበር ይታወቃል፡፡ መንግሥት በግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አወቃቀር ላይ ግን አምስቱን ድርጅቶች ወደ ግል ከማዛወር ይልቅ በግብርናው ዘርፍ ላይ ካለው ዕድገት አኳያ በአገሪቱ ወደኋላ ሊመለስ የማይችል የማዳበሪያ ተጠቃሚነት ፍላጎት ተፈጥሯል፡፡ አርሶ አደሩ ማዳበሪያ መጠቀም ለምዷል፡፡ አርሶ አደሩ ወደኋላ ሊመለስ የማይችል ፍላጎት በምርጥ ዘር አጠቃቀም ላይ አሳድሯል፡፡ ምርጥ ዘር ባታቀርብለት እርሻ አይኖርም፡፡ አርሶ አደሩ በበሬ በማረስ ሕዝቡን ሊቀልብ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ሜካናይዝ የሆነ እርሻ መስፋፋት አለበት፡፡ ለዚህ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችና መለዋወጫዎች መቅረብ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ፍላጎቱ አለና፡፡ መንግሥት ይህንን ፍላጎት ማስተናገድ ይጠበቅበታል፡፡ ፍላጎቱን ለማስተናገድ ማን ሥራውን ይሥራ? ለሚለው የመንግሥት በጀት ላይ ጥገኛ ያልሆነ፣ ራሱ የሚተዳደር፣ ተወዳዳሪና ትርፋማ የሆነ ተቋም መፍጠር አለብን፡፡ ይህ ተቋም የአገር ውስጥ ፍላጎትን ብቻም ሳይሆን በሒደት ወደ ጎረቤት አገሮች በመዝለቅ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያስገኝ ሊሆን ይገባዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር በአዲስ አበባ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ያስተላለፉትን ምክር እዚህ ማንሳቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ተናግረው እንደነበረው ለሰፋፊ እርሻዎች የሚሰጠውን ያህል ትኩረት ለአነስተኛ ገበሬዎችም ቢሰጥ፣ እዚህን ገበሬዎች በማደራጀት ተገቢውን መሣሪያ በማቅረብ እንዲሠሩ ብታደርጉ ብለው ነበር፡፡ ኮርፖሬሽኑ እንዲህ ያሉትን ነገሮችን ታሳቢ አድርጓል?

አቶ ከፍያለው፡- አዎን፡፡ እንደውም የኮርፖሬሽኑ ትልቁ ዓላማው ይኼው ነው፡፡ የአገሪቱ አብዛኛው መሬት በአነስተኛ አምራቾች የተያዘ ነው፡፡ በዩኒየኖች የተያዘ መሬትም አለ፡፡ በሰፋፊ እርሻዎች የተያዘው በጣም ጥቂት ነው፡፡ አነስተኛ ገበሬዎች በቴክኖሎጂ መደገፍ አለባቸው፡፡ በበሬ ማረሱ ብዙ አምራች አያደርገውም፡፡ የተሻሻሉ ማረሻዎች ሊቀርቡለት ይገባል፡፡ ይህ ኮርፖሬሽን እንዲህ ያሉ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያስችለው ጥናት ሠርቶ ማቅረብ መቻል አለበት፡፡ ምርጥ ዘር በበቂ መጠን ሊቀርብለበት፣ ማዳበሪያ ቢገባ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ አገሪቱ የግብርና ኢኮኖሚ ተስፋዎች አነስተኛ ገበሬዎች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእርሻውና ከመሬቱ ጋር ያለው ቁርኝት የታወቀ ነው፡፡ ቁርኝነቱ መቀጠሉ እስካልቀረ ድረስ በቴክኖሎጂ እየታገዘ ብዙ ለማምረት የሚያስችል ሥራ መሥራት ይገባል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች