Wednesday, July 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

እንዲህ ነበርን እንዲህ ብንሆንስ

ከገነት ዘውዴ ወልደዮሐንስ

ሁሌም ወጣት ፈጣን አዕምሮ ያለው ላመነበት ሞትን የማይፈራ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ታዲያ ከራሱ በላይ አገሩንና ወገኑን የሚወድ፣ የእሳት አሎሎ ወዳልሆነ ቦታ እንዳይወረወር ማስገንዘብ ያለብን በለጋ ዕድሜው ላይ መሆን አለበት፡፡ ታሪክ ለመናገር ሳይሆን ያለፈውንና የአሁኑን ሁኔታ በማገናዘብ ለውጡ እንዳይቀለበስ ለመጠቆም ነው፡፡

የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ሲወድቅ የተተካው የደርግ መንግሥት ለሕዝብ ቆሜያለሁ ከማለት የዘለለ የርዕዮተ ዓለምም ሆነ አገርን የመምራት አቅም አልነበረውም፡፡ ታዲያ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ የነበሩ ተማሪዎች ያቋቋሟቸው ኢሕአፓና መኢሶን ሶሻሊዝምን ቢደግፉም በጥቃቅን ልዩነቶች ራሳቸውን አንድ ማድረግ አቅቷቸው እርስ በርሳቸው ሲናቆሩ ነበር፡፡

ደርግ አመራሩን ወዴት እንደሚያደርግ በተቸገረበት ወቅት ኢሕአፓ (የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ) እና መኢሶን (የመላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ) ወደ አገር ውስጥ ገቡ፡፡ ደርግ ከአስረኛ ክፍል በላይ ያለውን ተማሪ የአገዛዙን መሠረት እስኪያጠናክር ተማሪውንና አስተማሪውን በየገጠሩ በተነው፡፡ በየከተማው በየገጠሩ መበተን ለኢሕአፓና መኢሶን ተመቻቸው፡፡ ወጣቱን በሶሻሊዝም መረብ በየፊናቸው ማጥመድ ጀመሩ፡፡ መኢሶን ደርግን በመደገፍ መሥራት ጀመረ፡፡ ኢሕአፓ ደርግን በመቃወም ፀና፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ሁለቱም ሐሳባቸውን በራዲዮ፣ በጋዜጣና በመጽሔት በነፃነት ያቀርቡ ነበር፡፡ ብዙም ሳይቆይ የመኢሶን ሐሳብ እንዳሻው በፈለገው የመገናኛ ብዙኃን ሲፈስና መኢሶንም ሕጋዊ ንቅናቄ ሲሆን ኢሕአፓ ግን ወደ ሕቡዕ ገባ፡፡

በዚህ ወቅት ብዙ ወጣቶችና የሠራተኛ ማኅበሮች ከኢሕአፓ ጎን ሲቆሙ መኢሶን የሚደግፉ ወጣቶችና የሠራተኛ ማኅበሮችም ነበሩ፡፡ በ1969 ዓ.ም. መስከረም 13 ቀን ኢሕአፓ በጠራው ሰላማዊ ሠልፍ ላይ የተገኙ ወጣቶች በአዲስ አበባ ፖሊስ ጣቢያዎችና በወህኒ ቤት ጭምር ታሠሩ፡፡ ከዚያ ቀን ጀምሮ የኢሕአፓ አባል መታደን ጀመረ፡፡ በዚያው ዓመት የመኢሶን አባል የሆኑ ጥቂት ካድሬዎች ተገደሉ፡፡ ከዚያ በፊት በየእስር ቤቱ  የኢሕአፓ አባሎች በስውር ተገድለዋል፡፡ ደርግ በአዋጅ ‹‹በአንድ ታጋይ ሺ አናርኪስት እንገላለን›› በማለት በመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጠ፡፡ ከዚህ በኋላ የኢሕአፓን ሐሳብ ያሰበ ያሳሰበ እየተባለ ከየቤቱና ከየመንገዱ በመላው አገሪቱ መታፈስ ጀመረ፡፡ ‹‹የስታሊን በትር›› የሚባለው ቀይ ሽብር በወጣቱ ላይ በረዶ እንደቀላቀለ ዝናብ ወረደበት፡፡ እስራቱ፣ ግርፋቱ፣ ስቃዩ፣ ሞቱ የሰው ልጅ አዕምሮ ከሚቀበለው በላይ ነበር፡፡ በየቤቱ ለቅሶ ሆነ፣ ኢሕአፓ ተዳከመ፣ ደርግ የኢሕአፓን መዳከም ሲገነዘብ ከጎኑ የነበረውን መኢሶንን መምታት ጀመረ፡፡ ሰደድ (አብዮታዊ ሰደድ)፣ ኢጭአት (የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል)፣ ወዝ ሊግ (የወዝ አደር ሊግ) እና  ማሌሪድ (ማርክሳዊ ሌኒናዊ ሪቮሊሽናዊ ድርጅት) ሌሎችም ንቅናቄዎች በደርግ አደራጅነት ተደራጅተው ነበር፡፡

የኢሕአፓም ሆነ የመኢሶን አባላት አቅምና ጉልበት ያላቸው በየአቅጣጫው በአገሪቱ ድንበር ተሰደዱ፡፡ ከሁለቱም ወገን በየመንገዱ የሞቱ ብዙ ናቸው፡፡ የቀረው ወጣትና ሕዝብ ዕጣ ፈንታ በየእስር ቤቱ መሰቃየትና እንደ ውሻ በየመንገዱ መጣል ነበር፡፡ የተለያዩ መፈክርም እላዩ ላይ ይለጠፍበት ነበር፡፡ መንገላታትና ስቃይ ሐዘን የዕለት ተዕለት ኑሮ ሆነ፡፡ የአገሪቱም ብርቅዬ ልጆች ካለ ፍርድ በየወህኒ ቤቶቹ ተቀበሩ፡፡ ወጣት ምሁራን ያለርህራሄ ተጨፈጨፉ፡፡ ለጋ ወጣቶች አካላቸው በድብደባ ቆሰለ፣ በየቦታውም ተገድለው ተጣሉ፡፡ ያንን ጊዜ ማስታወስ ራስን ያስጠላል፡፡ ሁሉም ለአገር አስቦ ቢሆንም መቻቻልና ለጋራ አገር በጋራ ማሰብ ስላልተቻለ የታየው ብርሃን ጠፍቶ በወታደራዊ አገዛዝ ወደቅን፡፡ የተሰደደውም እየተንገላታ በሁለተኛ ዜግነት በሰቀቀን መኖር ጀመረ፡፡

ከደርግ ውድቀት በኋላም የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁስሉ ሳይሽር በዘር የሚከፋፈል ሥርዓት መጣብን፡፡ ይህ ደግሞ ካለፈው የባሰና በዘር በመከፋፈል ይኼ የኔ ብቻ በማለት የኢትዮጵያን አንድነት ደግፎ የቆመውን ምሰሶ ማነቃነቅ ጀመረ፡፡ ብዙ ሰብዓዊ መብትን የሚጋፉ ከሕገ መንግሥቱ ውጪ ለአገዛዝ እንዲያመቹ ብዙ አዋጅና መመሪያዎች ወጡ፡፡ ለፍትሕ ለአንድነት የጻፉ፣ ያቀነቀኑ ታሰሩ፡፡ ከኢትዮጵያዊነት በላይ ዘረኝነት ገዘፈ፡፡ ኢትዮጵያዊነትና አንድነት ኮሰሰ@ ሕዝቡ ተስፋ በቆረጠበት ወቅት ኢትዮጵያን ከሚያስተዳድረው ከኢሕአዴግ ግንባር ያልተጠበቀ ብርሃን ታየ፣ በጉም በተሸፈነ ሰማይ እንደሚወጣ ፍንትው ያለ ፀሐይ ወጣ፡፡

እግዚአብሔር ይመስገን በየመድረኩ በየቦታው አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነትን መስማት የነበረውን ሥጋት አቀለለው፡፡ የቋንቋ ልዩነት ሳያግደው ተዋዶና ተጋብቶ ተዋልዶም ደስታና ሐዘኑን በመጋራት ነው የኖረው፡ አብሮነቱን የሚያለመልምበትን፣ ሥጋቱን የሚገፍለት ክቡር ዶ/ር ዓብይ አህመድና ክቡር አቶ ለማ መገርሳን በማግኘቱ ሆ ብሎ ለውጥን ተቀበለ፡፡ የታሰሩ እየተፈቱ ሲሆን ‹‹አሸባሪ›› ለተባሉ ግንባሮችና ንቅናቄዎች የአብረን እንሥራ ጥሪ ቀረበ፡፡

ክቡር ዶ/ር ዓብይ አህመድ በየመድረኩ የሚያደርጉት ንግግር ቁስልን የሚያጠግ፣ ተስፋን የሚሰጥ በመሆኑ በአዲስና አበባ በየክልሉ የድጋፍና የምሥጋና ሠልፍ መካሄዱ ምስክር ነው፡፡ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በተደረገው ሠልፍ ቦንብ ፈንድቶ ንፁኃን ሕዝብ ላይ የደረሰው አደጋ ግን አሳዛኝ ነው፡፡ መወገዝም አለበት፡፡ መስዋዕትነት ተከፈለ፡፡ የተከፈለው መስዋዕትነት ለመላ ኢትዮጵያ ሕዝብ የአንድነታችን ምሰሶ ለማስጠበቅ ነው፡፡ ለሞቱት እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ይማር ለቤተሰባቸውም መጽናናትን ይሰጥልን፣ ለተጎዱትም እግዚአብሔር ቁስላቸውን ይጠግንልን ይማርልን፡፡

‹‹የሺ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ›› እንደሚባለው ከላይ የዘረዘርኩት ያለፈው ታሪክ በዚህ የጋዜጣ ጽሑፍ ተገልጾ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ባጭሩ ለማስገንዘቢያ እንዲሆን እንጂ እንደሚታወቀው በአገር ውስጥ በዘር፣ በኅብረ ብሔር የተደራጁ ብዙ ፓርቲዎች አሉ፡፡ እንዲሁም አገር የጋራችን ነችና አብረን እንሥራ ተብለው የመጡም የሚመጡም ንቅናቄዎች፣ ግንባሮችና ፓርቲዎች ይኖራሉ፡፡

ለኢትዮጵያ ወጣቶችና ሕዝብ አደራ የምለው ማንኛውም ፓርቲ፣ ንቅናቄ፣ ግንባር ከመደገፋችን በፊት ጊዜ ወስደን አካሄዱን እንይ፡፡ ነገሩ እስኪጣራ ኃይላችን እንዳይከፋፈለ አገር እንዳትፈርስ የለውጡን መሪ ክቡር ዶ/ር ዓብይን እንደግፍ፣ በስድሳዎቹ እንደሆነው ለውጡ እንዳይቀለበስ፡፡

ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የመጣችሁ ፓርቲዎች፣ ንቅናቄዎች፣ ግንባሮች፣ አባላት ከመመልመላችሁ በፊት በአንድነት ሆናችሁ ምከሩ፣ ጥቃቅን ችግሮቻችሁንና ልዩነታችሁን ለአገር፣ ለወገን ብላችሁ እንደ ሌላው አገር በሁለት፣ በሦስት በመጠቃለል በሰከነ ሁኔታ ተደራጁ፡፡ አገር ከሌለ ቤት የለም፤ የሚያስተዳድሩትም የሚመሩትም ሕዝብ የለም፡፡ ሀብት ንብረትም ይወድማል፡፡ የመንና ሶሪያን፣ ጎረቤቶቻችንም መመልከት ይገባል፡፡ ሁላችሁም አሸናፊ የምትሆኑበትን ምረጡ፡፡

የስድሳዎቹ ለውጥ መቀልበስ ዋናው ምክንያት በጊዜው የነበሩት ፓርቲና ንቅናቄ እርስ በርሳቸው በመሻኮታቸው ደርግ ክፍተት በማግኘቱ ነበር፡፡ ለወቀሳ ሳይሆን ያለፈውን ለማስታወስ ነው፡፡

ለሁላችንም አገራችን ነች፣ ለማንም አትቀርብም ለማንም አትርቅም፡፡ ለሁላችንም የጋራ በመሆኗ በጋራ ከዘረኝነትና ከቂም፣ ከስሜታዊነትና ከሃይማኖት ልዩነት በፀዳ በአንድነትና በፍቅር ለሕዝብ እንድትቆሙ የታየው የለውጥ ብርሃን እንዳይዳፈንና ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይሄድ ሁሉም የሕዝብ አደራ አለበት፡፡

ብዙ ምሁራን ከሕዝቡም ከወጣቱም ከፓርቲዎች፣ ከንቅናቄዎችም ከግንባሮችም እንዳላችሁ አውቃለሁ፡፡  ኢትዮጵያ ለሁላችንም የጋራችን ናት፡፡ አባቶቻችን ‹‹ጋን በጠጠር ይደገፋል›› እንደሚሉት በሐሳብ እንደጋገፍ ለማለት ነው የዚህ ጽሑፍ ዓላማ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles