የአፍሪካ ንግድ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ በኢትዮጵያ የመድን አገልግሎት እንዲሰጥ፣ ኢትዮጵያም የኤጀንሲው አባል እንድትሆን የሚያደርግ አዋጅ ፀደቀ፡፡
አዋጁ የአፍሪካ ንግድ ኢንሹራንስ ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተከለለው የመድን አገልግሎት ሥራ ላይ የሚሳተፍ ብቸኛው ዓለም አቀፍ ድርጅት ያደርገዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችና ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች የተከለሉ የሥራ መስኮችን የሚደነግገው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 270/2005 አንቀጽ ሦስት ኢትዮጵያዊ ዜግነት ባላቸው ባለሀብቶች ብቻ የሚካሄዱ የሥራ መስኮች ብሎ ከሚዘረዝራቸው መካከል የባንክ፣ የኢንሹራንስና የአነስተኛ የብድር ተቋማት ይገኛሉ፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያን አባል የሚያደርገው የአፍሪካ ንግድ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ ማቋቋሚያ ስምምነት፣ ኤጀንሲው በኢትዮጵያ የመድን አገልግሎት እንዲያከናውን ፈቃድ ይሰጠዋል፡፡
ኤጀንሲው አገልግሎቱን በኢትዮጵያ ሲጀምር የቀጥታ መድን፣ የጠለፋ መድን፣ የጋራ መድንና ዋስትና መስጠት ያስችለዋል፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣው የኢንቨስትመንት አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ ቁጥር 270/2005 የኢንሹራንስ ሥራን ለኢትዮጵያውያን ብቻ ከመፍቀዱ በተጨማሪም፣ ብሔራዊ ባንክ ስለ ኢንሹራንስ ሥራ ያወጣው አዋጅ ቁጥር 746/2004 አንቀጽ 45 ከውጭ አገር መድን ሰጪዎች ጋር መዋዋል የተከለከለ ስለመሆኑ በሚገልጸው አንቀጽ 45 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ፣ ‹‹ብሔራዊ ባንክ በጽሑፍ ካልፈቀደ በቀር ውሉ የሚፈጸምበት ወይም የሚፈረምበት ሥፍራ የትም ቢሆን ስለአደጋ ወይም ስለሰው ወይም በኢትዮጵያ ስለሚገኝ ንብረት ወይም በኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጸም ለተገባ ግዴታ ወይም ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ዕቃዎች የሚሰጥ ማንኛውም ዓይነት የመድን ወይም የጉዳት ካሳ ውል፣ በዚህ አዋጅ መሠረት ፈቃድ ካልተሰጠው መድን ሰጪው ጋር መዋዋል አይፈቅድም፤›› የሚል ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡
የስምምነት ማፅደቂያ አዋጁ ለዝርዝር ዕይታ የተመራለት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የብሔራዊ ባንክና የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎችን በማነጋገር፣ የአፍሪካ ንግድ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ በኢትዮጵያ ቢቋቋም ጉዳት እንደሌለው ማረጋገጫ መገኘቱን የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ ወይዘሮ ገነት ታደሰ ለፓርላማው ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የአገር ውስጥ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የፖለቲካ፣ የአደጋ ሽፋንና የንግድ ክሬዲት አደጋ ሽፋን የማይሰጡ በመሆናቸው አዋጁ እንዲፀድቅ ባቀረቡት የውሳኔ ሐሳብ መሠረት፣ አዋጁ ማክሰኞ መጋቢት 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ፀድቋል፡፡