Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹የሀብቴ የእግር አሻራ. . .››

‹‹የሀብቴ የእግር አሻራ. . .››

ቀን:

የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት (ኢቱንድ) መሰንበታቸውን የቱሪዝሙን አባት ገብተ ሥላሴ ታፈሰን ዘከረ፤ አሰበ፡፡ ሠዓሊና ገጣሚው የኢቱንድ ዋና ዳይሬክተር አሰፋ ጉያም ስንኞችን አሠረ፡፡

‹‹የሀብቴ እግር አሻራ ከስሜን – ባሌ ተራሮች

ከአክሱም ሐውልት – ከጎንደር – ቤተ መንግሥቶች

ከላሊበላ – ከሼህ ሁሴን – ከሐረር ግንቦች

ዛሬም – ነገም ይኖራሉ – የጋሼ ሀብቴ የፎቶ አልበሞች፡፡››

ደራሲ አሰፋ ‹‹ሀብቴ አልሞተም›› በሚል ያቀረበው ግጥሙ የዘከራቸው አቶ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ (1919-2009)፤ የኢትዮጵያን ማራኪ የተፈጥሮ ገጽታና የሕዝቡን ባህል፣ ታሪክ፣ አኗኗርና ትውፊት ወደ ቱሪዝም ምርት እንዴት መቀየር እንደሚቻል ያመላከቱና ዛሬ በብዙ ሺሕ ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መተዳደሪያ የሆነውን የዕደ ጥበብና ሥነ ጥበብ ምርትና ሽያጭ የንግድ ሥራ ፈር ቀዳጅ ናቸው ሲል ኢቱንድ ገልጿቸዋል፡፡

‹‹የዕደ ጥበብና ሥነ ጥበብ ባለሙያዎችን በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ ሙያቸውን እንዲያበለፅጉና በሥራዎቻቸውም ባህላዊ አሻራቸው እንዳይጠፋና ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፤›› ሲልም አክሏል፡፡

የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብቶች በዓለም ዙሪያ ለማስተዋወቅ ከነበራቸው ኃላፊነቶች ባሻገር በአገሪቱ እየተዘዋወሩ የቱሪዝም ፀጋዎችን በፎቶግራፍ በማንሳት፣ ፖስተርና ፖስት ካርዶች በማሳተም በሰፊው ማስተዋወቃቸው የሚነገርላቸው አቶ ሀብተ ሥላሴ፣ ለአገር ኢኮኖሚ ግንባታ አስፈላጊ የሆነውን የውጭ ምንዛሪ ለማፍራት እንዲቻል ከቀረጥ ነፃ ሸቀጦች መደብር በመመሥረትም ይወሳሉ፡፡

ለዚህ ተግባራቸው ከአገራዊ ክብር ባለፈ ዓለም አቀፉ የቀረጥ ነፃ ማኅበር (Tax Free World Association)፣ በዓለም የቀረጥ ነፃ ሽያጭ ሥራ የተጀመረበትን 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ ባከበረበት አጋጣሚ የአቶ ሀብተ ሥላሴን ስም በአክብሮት ከማንሳት አልተመለሰም፡፡

‹‹በ1950ዎቹ መጨረሻ (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) በአፍሪካ በማይጠበቅ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊ የቀረጥ ሽያጭ ሥራ ተቋቁሞ ነበር፡፡ ይህ ዕውን ሊሆን የቻለው ደግሞ ሰው ጥረት ነበር፡፡ ይህ ሰው ደግሞ በአንድ ሀብተ ሥላሴ ታፈሰ ነበር፡፡ ሀብተ ሥላሴ የመንግሥት ሠራተኛ የነበረ ቢሆንም የነፍሱ ጥሪ ግን ሥራ ፈጠራ ነበር፡፡››

‹‹የማያልቅ የወርቅ ማዕድን›› የሚባለውን የኢትዮጵያ ውበት በቱሪዝም መስክ ተጠቃሚ ለመሆን የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የሥራ ሚኒስትር የነበሩት ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ባቀረቡት ሐሳብ የንጉሡን ትዕዛዝ ተቀብለው 56 ዓመት በፊት ሥራ የጀመሩት አቶ ሀብተ ሥላሴ፣ የኢትዮጵያ ቱሪስት ድርጅት በእንግሊዝኛ አጠራሩ ኢቲኦ (ETO) መሥርተውና በዋና አስተዳዳሪነት ፈና ወጊ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ ከድርጅቱ ዕድገት ጋር ሥራው እየሰፋ በመሄድና ዓለም አቀፍ ዕውቅናም በማግኘቱ የድርጅቱ ምክትል ሚኒስትር፣ ቀጥሎም በማስታወቂያና ቱሪዝም ዘመን ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው አገልግለዋል፡፡

የድርጅቱን የሥራ መመርያዎች አዘጋጅተው ፈር ከማስያዛቸው ሌላ ለኢንዱስትሪው ዘመናዊ መልክ በመስጠት ረገድ ያበረከቱት አዕምሮአዊ ሥራ እጅግ የሚደነቅ ነው፡፡ ለዚህም ከሚሰጡት ማስረጃዎች አንዱ ‹‹ኢትዮጵያ 13 ወር ፀጋ›› (Ethiopia Land of 13 Months of Sunshine) የሚለው ልዩ የቱሪዝም መጠሪያ ሆኖ እስከ ቅርብ ጊዜ ሲያገለግል የነበረው ዋነኛው ተጠቃሽ ሥራቸው ነው፡፡

አቶ ሀብተ ሥላሴ በቀጥታ ተሳትፈውባቸው ሥራ ላይ ከዋሉ ፕሮጀክቶች መካከል የሒልተን ሆቴል፣ የኢትዮጵያ ምግብ ዝግጅት ኢንስቲትዩት፣ ለፕሮሞሽን ሥራ የዋሉ አያሌ ዲዛይኖችና መጽሔቶችም ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በተለይ ኢትዮጵያን ለውጭው ዓለም ከማስተዋወቅ ረገድ ... 1967 የኤክስፖ ሞንትሪያል ካናዳ ኮሚሽነር፣ የአፍሪካ ትሬድ ፌር ናይሮቢ 1972 አዘጋጅና ኮሚሽነር ነበሩ፡፡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከነጋዴዎች ምክር ቤት ጋር በመተባበር በብዙ የአገር ውስጥ ኤክስፖዎች፣ ኤግዚቢሽኖችና በመጨረሻ ጎልድ ሜርኩሪ በተባለው ትሬድ ፌር ላይ ተካፍለዋል፡፡

አቶ ሀብተ ሥላሴን የተለዩ ልዩ የሥራ መሪ የሚያደርጋቸው የነበረን ወይም ያለን ተቋም ወይም ድርጅት ተቆጣጥሮ ማንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን ሥራ የመፍጠር ችሎታቸው ነው፡፡ አስቀድሞ የኢትዮጵያ ቱሪስት ድርጅት (ETO) ኋላ ላይ የቱሪዝም ኮሚሽን የተቋቋመበትን መሠረታዊ ዓላማ ማለት የአገሪቱን ሀብት ለውጭና ለአገር ቤት ተመልካቾች ማሳወቅ (ፕሮሞሽን) ሲሆን ሥራውን ለማከናወን ድርጅቱ አቅም ባነሰው ወቅት ገንዘብ ሊያስገኝ የሚያስችለውን የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅትን በማቋቋማቸው ይታወሳሉ፡፡ ዛሬ ይህ ድርጅት ቅርስና ባህል ከማስተዋወቁ በተጨማሪ በብዙ ሚሊዮን የሚገመት ትርፍ በውጪ ምንዛሪ በማስገኘት ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ከዚሁ ለፕሮሞሽኑ ሥራ ጋር ተደጋጋፊ የሆነውን የአገር ባህል ዕቃዎች ማምረቻ ድርጅት፣ እንዲሁም የመኪና ኪራይ ድርጅት (ብሔራዊ አስጎብኚ ድርጅት ኤንቲኦ) በመመሥረታቸው ድርጅቶቹ ገቢ ስብሰባ ላይ ብቻ ሳይሆኑ ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር አስችሏቸዋል፡፡

የአቶ ሀብተሥላሴ ዜና ዕረፍት ከመስማቱ 145 ቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ‹‹ለአቶ ሀብተሥላሴ ታፈሰ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ልማትና ዕድገት ላበረከቱት እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በክቡር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የተሰጠ›› የሚል ጽሑፍ የተቀረፀበት የመስተዋት ሰሌዳ ተበርክቶላቸዋል፡፡

በቅርቡ 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉን ያከበረውና በርሳቸው የተመሠረተው የኢትዮጵያ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት፣ በቅርቡ ሲዘክራቸው ባቀረበው ጽሑፍ ላይ እንዲህ ብሏል፡፡ ‹‹የቱሪዝም ማኅበረሰብ አቶ ሀብተ ሥላሴ ለኢንዱስትሪው የዋሉትን ውለታ መክፈል የሚችለው፣ እርሳቸው ይመኙት እንደነበረው ሀገራችን በቱሪዝም ፀጋዎቿ ልክ በሺዎች ሳይሆን፣ በብዙ ሚሊዮን በሚቆጠሩ ቱሪስቶች ስትጎበኝና ከኢንዱስትሪው ተገቢውን ጥቅም ስታገኝ ብቻ ነው፡፡››

‹‹አቶ ሀብተ ሥላሴ የተግባርና የፈጠራ ሰው ናቸው፡፡ ሐሳባቸው ትላልቅ ነገር ላይ ነው፡፡ ትንንሽን ትተው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ስለ ቢሊዮን ብር ዕቅድ ነው የሚያስቡት፤ ሁሌም አዳዲስ ነገሮች ይዘው ይመጣሉ፡፡ እስከ መጨረሻቸው ድረስ ከድርጅታችን ጋር የአባትና የልጅ ግንኙነት ነበራቸው፤›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አሰፋ ጉያ፣ በተራኪ ግጥማቸው ሀብተ ቱሪዝሙን ሀብተ ሥላሴን ማመሥጠራቸውን አላቆሙም፡፡

‹‹ማነው የሞተው? የምን ሟርት ነው?

ሀብቴ ሞተ ያለው ማነው?

የሥላሴ ሀብት ከቶ ማን ሊደፍረው?

ከአፋር – ዳሎል በረሃ – ከምዕራቡ ጫካዎች

ከቀይ ባሕር – ከዳህላክ – ከጣና ደሴቶች

ከስምጥ ሸለቆ – ከኒያ ውብ እንስት ገጾች

ዛሬም – ነገም ያበራሉ – የጋሼ ሀብቴ አሻራዎች፡፡

ከአዕዋፋትና – ከዱር እንስሶች

ከዕፀዋትና – ከጠበሎች

ከ13 ወራት – የብርሃን ፀጎች

ይዘልቃሉ ለዓመታት – የቱሪዝም አባት ቅርሶች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...