‹‹ከአፕሊኬሽን ባለቤቶች ጋር መደራደር ሌላኛው አማራጭ ነው›› አቶ አንዱዓለም አድማሴ
ኢትዮ ቴሌኮምና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የኢትዮ ቴሌኮምን መሠረተ ልማት በሚጠቀሙ ቫይበርና መሰል የስልክ ጥሪ አገልግሎቶች ላይ ክፍያ ለመጣል፣ ወይም ሌሎች አማራጮችን ለመጠቀም እየመከሩ ነው፡፡
በኢንተርኔት አማካይነት የድምፅና የምሥል ጥሪዎችና መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ አፕሊኬሽኖች፣ ኢትዮ ቴሌኮም ከውጭ ጥሪዎች ማግኘት የሚችለውን ከፍተኛ ገቢ እንዳስቀሩበት ተገልጿል፡፡
እነዚህ የአፕሊኬሽን ዓይነቶች በተለይም በኢትዮጵያውያን ተጠቃሚዎች ዘንድ በስፋት የሚታወቁትን ቫይበርና ዋትስአፕ የመሳሰሉትን ለመቆጣጠር፣ ኢትዮ ቴሌኮም ‹‹ፖሊሲ ቻርጅ ኤንድ ኮንትሮል ሲስተም›› የተባለ ቴክኖሎጂ ባለቤት መሆኑን፣ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዱዓለም አድማሴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት ክፍያ ለማስከፈልም ሆነ በማጭበርበር ተግባር ላይ የተሰማሩትን ለመቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ ባለቤት ነን፡፡ ነገር ግን ክፍያ ለመጣል አልወሰንም፤›› ብለዋል፡፡
በእነዚህ አገልግሎቶች ላይ ክፍያ ለመጣል የብዙ አካላት ውሳኔን ማለትም የኢትዮ ቴሌኮም ቦርድን፣ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርን፣ እንዲሁም የመንግሥትን ውሳኔ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከአፕሊኬሽኖቹ ባለቤቶች ጋር መደራደርና ከዓመታዊ የትርፍ ድርሻቸው ክፍያ እንዲፈጽሙ መግባባት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ብቸኛው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ኢትዮ ቴሌኮም በመሆኑ፣ ከአፕሊኬሽን ባለቤቶች ጋር የክፍያ ድርድር ማድረግ ለኢትዮ ቴሌኮም ጠቀሜታዊ ፋይዳው የተሻለ ከሆነ ቀላል አማራጭ እንደሚሆን አቶ አንዱዓለም ጠቁመዋል፡፡
የቫይበርና የመሰል አፕሊኬሽኖች ጉዳይ በየትኛውም አገር አጨቃጫቂ መሆናቸውን የሚገልጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የወጣበትን የቴሌኮም መሠረተ ልማት ያለባለቤቱ ዕውቅናና ተጠቃሚነት የሚገለገሉና ከፍተኛ ትርፍ ለራሳቸው የሚያካብቱ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡
አንዳንድ አገሮች እነዚህን አፕሊኬሽኖች ሙሉ በሙሉ የሚዘጉ ሲሆን፣ ሌሎች አገሮች ደግሞ ክፍያ በመጣል አልያም የትርፍ ድርሻ ድርድር ውስጥ እንደሚገቡ ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ከተጠቀሱት አንዱን ለመምረጥ ሰፊ የትንተና ሥራ መሥራትና ለመንግሥት አቅርቦ ማስወሰንን እንደሚጠይቅ፣ በዚህ ረገድም ገና ውይይት በመካሄድ ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮ ቴሌኮም ‹‹ኢኪዩፕመንት አይደንቲቲ ሬጂስተር›› ማለትም ያልተቀረጡ የሞባይል ስልኮች ወይም የተሰረቁ የሞባይል ስልኮችን ከአገልግሎት ውጪ ማድረግ የሚያስችለው ቴክኖሎጂ ባለቤት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በመጪው ዓርብ ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ከተደረገ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ መሆን እንደሚጀምርም አቶ አንዱዓለም ገልጸዋል፡፡
ይህ ተግባራዊ ከተደረገ ሳይቀረጡ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ስልኮች አገልግሎት መስጠት የማይችሉ ሲሆን፣ ከደንበኞች የተሰረቁ ስልኮችንም ደንበኞች ሲያሳውቁ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
በመጪው ዓርብ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሚደረግ ውይይት በደንበኞች እጅ ላይ የሚገኙና አገልግሎት እየሰጡ ያሉ፣ ነገር ግን ያልተቀረጡ ስልኮች ዕጣ ፈንታና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡