ባለፉት 25 ዓመታት የአገር ግንባታ ጉዞዎች እየፈጩ ጥሬ፣ እያፈሰሱ መልቀምና እየታጠቁ መሮጥ የበዛባቸው በመሆናቸው፣ ከማፍረስና መልሶ ከመገንባትና አገር ዋጋ የሚያስከፍሉ ስህተቶችን በተደጋጋሚ ከመፈጸም መውጣት አልተቻለም፡፡ ዘንድሮ በወርኃ መስከረም መጨረሻ ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአዲሱ መንግሥት ካቢኔያቸውን ሲያዋቅሩ፣ መንግሥታዊ ተቋማትን ለማደራጀት አዲስ አዋጅ ወጥቶ ነበር፡፡ በዚህ አዋጅ መሠረት ተቋማት እንደገና ተደራጅተውና በአዲሱ በጀት ተካተው የጥቂት ወራት ጉዞ ከተደረገ በኋላ፣ በቅርቡ የፍትሕ ሥርዓቱን እንደገና የማደራጀት ሥራ የሚያስጀምር የማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ወጥቷል፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ የአስፈጻሚውን አካል በተደጋጋሚ ለማደራጀትና ለማጠናከር ተብሎ ከ20 የማያንሱ አዋጆች መውጣታቸው አይዘነጋም፡፡ በተለይ የፍትሕ ሥርዓቱ ለቁጥር የሚያታክቱ የመዋቅር ማስተካከያዎችና የማደራጀት ሒደቶች ውስጥ በማለፍ የሚስተካከለው የለም፡፡ ለዚህ ሁሉ ትልቁ ምክንያት ደግሞ መደማመጥ አለመኖሩ ነው፡፡
ችግሩ ምንድነው? አገሪቱ ባለሙያዎች አጥታ ነው? በደቦ እንሥራ የሚሉ ወዳጆች ጠፍተው ነው? ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ልምድና ተሞክሮዎች ስለሌሉ ነው? የባለሙያ እጥረት እንዳይባል በርካታ ምሁራንና ባለሙያዎች አሉ፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ በነገሠው ፍራቻ ሳቢያ የልቡን መናገር የሚችል፣ እውነታውን የሚያስረዳና ለአገር ግንባታ የሚጠቅም ሐሳብ የሚያፈልቅ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ከአንገት በላዩን በአደባባይ፣ ከአንገት በታቹን በሹክሹክታ እንዲወራ ለማድረግ ባለመቻሉ፣ በልብ ያለውን በሹክሹክታ ከአንገት በላይ የሆነውን ደግሞ በአደባባይ የሚናገሩ በዝተዋል፡፡ መደማመጥ ጠፍቶ ችግር በዝቷል፡፡ በአገሪቱ ያለውን የሠለጠነ የሰው ኃይል በአግባቡ መጠቀም እንዳይቻል ልብ በልብ መነጋገር አቅቷል፡፡ የባቢሎን ግንበኞች በዝተዋል፡፡ እንክትካች ጎራዎችን በመፍጠር እንደ እባብ ካብ ለካብ መተያየት የዘመኑ ፈሊጥ ሆኗል፡፡ እንዲህ ዓይነት የአገር ግንባታ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ ለዚህም ነው የፍትሕ ሥርዓቱን እንደገና ለማደራጀት እንቅስቃሴ ሲጀመር መሠረቱ እንዳይደረመስ መጠንቀቅ የሚያስፈልገው፡፡ ዋናው ጉዳይ ደግሞ በፅሞና መደማመጥ ነው፡፡
በተለያዩ ጊዜያት አዋጆች ሲወጡ ከተለያዩ አገሮች ልምዶች መቀሰማቸው ይነገራል፡፡ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውም ይወራል፡፡ የወጡት አዋጆች አላሠራ ብለው አገር ሲያተራምሱ ወደ ማሻሻያ ወይም ለውጥ ይገባል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማደራጀት ከአምስት አገሮች ልምድ መቀሰሙ ተነግሯል፡፡ ልምድ የተቀሰመባቸው አገሮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ቀረቤታ ምን ይመስላል? የእነሱ ልምድ እዚህ አገር ካለው ታሪካዊ ሁኔታ፣ የሕዝብ አኗኗር ዘይቤ፣ ከወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችና ከመሳሰሉት ጋር ያላቸው መስተጋብር እንዴት ተገምግሟል? ከአውሮፓና ከሰሜን አሜሪካ ይልቅ ተስፋ ሰጪ ጉዞ ያሳዩ የአፍሪካ አገሮች ልምድ ይበልጥ ትኩረት ተደርጎበታል? ብዙ ጥያቄዎች ማንሳት ይቻላል፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ በአገሪቱ የረጂም ዓመታት ልምድ፣ ዕውቀትና በተግባር የተረጋገጠ ተሞክሮ ያላቸው ባለሙያዎች ተሳትፎስ ለምን ይገደባል? ከሕዝብ አስተያየት ማዳመጫ መድረኮች በተጨማሪ ለምን በረቂቅ ዝግጅቶች ላይ የእነዚህ ባለሙያዎች ተሳትፎ አይካተትም? ለመደማመጥ ከፍተኛ ትኩረት ካልተሰጠ በስተቀር የአገር ግንባታ እንዴት ይሳካል?
ከድህነት አረንቋ ውስጥ ለመውጣት የምትዳክር አገር ለፍታ ያስተማረቻቸው ባለሙያ ልጆቿ አስተዋጽኦ ካላገዛት የት መድረስ ትችላለች? በአንድ ዓመት ውስጥ ሦስት ጊዜ አስፈጻሚ አካላትን ማደራጀት ውስጥ ሲገባ ጊዜ፣ ሀብት፣ ባለሙያ፣ ልምድና የመሳሰሉት መሠረታዊ ጉዳዮች ታሳቢ መደረግ አለባቸው፡፡ በተለይ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱንና የሕግ አስከባሪውን አካል በተመለከተ ማሻሻያ የቀረበበት ጉዳይ የሚያሳስበው ዓቃቤ ሕግ ወይስ ፍትሕ ሚኒስቴር የበላይ ይሁን የሚለው ሳይሆን፣ ሕግ የማስከበርና የማስፈጸም የመንግሥት ሥልጣን በሚገባ ከሕገ መንግሥቱ ጋር በመጣጣም ለተደራጀና ሥራውን ለሚያውቅ አካል ይሰጣል ወይ የሚለው ነው፡፡ የሕዝብ ጥያቄ የአንድ ባለ በጀት መሥሪያ ቤት ወይም ተቋም መኖር አለመኖር ሳይሆን፣ ልጓም ያለውና ተጠያቂነት ያለበት ሥርዓት ግንባታ ጉዳይ ነው፡፡ አለበለዚያ ሲነግሩት የማይሰማ፣ ተቆጪና ሃይ ባይ የሌለው፣ ወይም ሕዝብን የማይፈራ ‹‹ፈላጩ ቆራጩ›› የሚባል ዓይነት ተቋም ምሥረታ አገር ያጠፋል፡፡ ገደብ የተበጀለት፣ ለሕዝብ ተጠሪነትና ተጠያቂነት ያለበት የአገር ሥርዓት ግንባታ እንዲኖር መደማመጥ ያስፈልጋል፡፡
ሕግ የማውጣት ሥርዓት ሕግ የማክበር የውኃ ልክን እየተፈታተነ እንዳይሄድና ችግር እንዳይፈጠር ካልተደረገ፣ ‘የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው’ ዓይነት ከንቱ ተግባር ይበዛል፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታይቶ ለፓርላማ የቀረበ ረቂቅ የሕግ ሰነድ፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችንና የመንግሥት ሥልጣን አካላትን ጎራ ለይቶ እንዴት ያፋልማል? ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ ወዘተ ጎራ አስለይቶ ጥያቄ ሲያስነሳ የመደማመጥ መጥፋትን ማሳያ ነው፡፡ ለዚህም ነው ከልብ ፋታ ወስዶ አስተያየቶችንና ቅሬታዎችን በመቀበል ለተጨማሪ ውይይቶች መዘጋጀት የሚያስፈልገው፡፡ በተለያዩ አስፈጻሚ አካላት የተነሱትን ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከነቅሬታዎች ለመመርመር እንዲቻል የፅሞና ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ከአገሪቱ ታሪክ፣ ከሕዝብ ፍላጎት፣ ከተቋማቱ ጥንካሬና ድክመት አንፃር መታየት ያለባቸው ጉዳዮች በሚገባ መጤን አለባቸው፡፡ በረቂቅ አዋጁ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በፓርላማ የሕዝብ አስተያየት ሲደመጥ፣ የፌዴራል ፖሊስ የተሰጠው የመመርመር ሥልጣን መግዘፍና የሙያ ክህሎት የሚጠይቁት የፀረ ሙስናና የግብር ጉዳይን በፅሞና መመርመር ይጠቅማል፡፡ የባለሙያዎች ድጋፍም ሊታከልበት ይገባል፡፡ መደማመጥ ይኑር፡፡
አንድ የግል ድርጅት ወይም ማኅበር ለሚቀርፃቸው ፕሮጀክቶቹ አማካሪ ኩባንያ ቀጥሮ የአዋጭነት ጥናት በሚያስጠናበት በዚህ ዘመን፣ ለፓርላማ የሚቀርብ የሕግ ሰነድ የበርካታ ባለሙያዎችንና ባለድርሻ አካላትን ሳያካትትና ግራና ቀኙን ሳያይ ተዘጋጀ ሲባል እንደ አገር ሊያሳስብ ይገባል፡፡ አሁንም የፍትሕ ሥርዓቱን እንደገና የማደራጀት ጉዳይ ቀጣይ ውይይቶች የሚደረጉበት በመሆኑና የተለያዩ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ሐሳብና አስተያየት የሚደመጥበት እንደሆነ በማሰብ፣ የሚቀርቡ ምክረ ሐሳቦች ግምት ይሰጣቸው፡፡ አሁንም መደማመጥ ከምንም ነገር በላይ ጠቃሚ በመሆኑ የቀረቡት አስተያየቶች ቸል አይባሉ፡፡ ከዚህ በፊት የሕዝብም ሆነ የባለሙያ አስተያየቶችን ባላካተቱና በይድረስ ይድረስ በወጡ ሕጎች ምክንያት ምን ያህል አገሪቷ እንደተጎዳች ሁሉም ወገን ይረዳዋል፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት መንግሥታዊ አስፈጻሚ አካላትን በተደጋጋሚ በማደራጀት፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ብዙ ጊዜ በማዋቀርና አፍርሶ በመገንባት በርካታ ውጣ ውረዶች ታይተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሥልጣንና ኃላፊነታቸው ተዘርዝሮ የማቋቋሚያ አዋጅ ወይም ደንብ የሌላቸው አራት የአስፈጻሚ አካላት (በግብርና ዘርፍ) በጀት ተበጅቶላቸው ሥራ ላይ መኖራቸውን፣ ለፓርላማ የቀረበ የመንግሥት ጥናት ያመላክታል፡፡ ይህ ሁሉ ብክነትና ጥፋት ያለመደማመጥና ያለመናበብ ማሳያ ነው፡፡ አሁንም የፍትሕ ሥርዓቱን እንደገና ለማደራጀት የተጀመረው ሥራ መደማመጥ ይፈልጋል!