Monday, October 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊበሦስት ክልሎች በደረሰ ጎርፍ የ18 ሰዎች ሕይወት አለፈ

  በሦስት ክልሎች በደረሰ ጎርፍ የ18 ሰዎች ሕይወት አለፈ

  ቀን:

  – በርካታ ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም

  ሰሞኑን በሦስት ክልሎች የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ፣ የ18 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተረጋገጠ፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡

  የብሔራዊ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሰሞኑን የተከሰተው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው የአማራ ክልል ወልዲያ፣ የአፋር ክልል መጋሌ ወረዳዎችና የኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ጅግጅጋ አካባቢ ናቸው፡፡

  እስካሁን በጎርፍ አደጋ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ጅግጅጋ አካባቢ 15፣ በአፋር ደግሞ የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ይህ የሟቾች ቁጥር እስከ ማክሰኞ መጋቢት 27 ቀን 2008 ዓ.ም. የተረጋገጠ ቢሆንም፣ በደረሰው አደጋ የሟቾች ቁጥር ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ተገምቷል፡፡ በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ ሰዎች እስካሁን የገቡበት እንዳልታወቀ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

  የጉዳቱን መጠን ምን ያህል እንደሆነና በሕይወትና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳትና ሌሎች ተጨማሪ መረጃዎችን ለማሰባሰብ አደጋው ወደተከሰተባቸው አካባቢዎች ባለሙያዎች መላካቸውን የገለጹት አቶ ምትኩ፣ እስከዚያው ግን በአደጋው ለተፈናቀሉ ወገኖች ለዕለት ዕርዳታ የሚሆን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች የተላኩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከዚህም በኋላ የሚያስፈልገውን ዕርዳታ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተነግሯል፡፡

  ከአየር ንብረት ለውጡና ከበልግ መግባት ጋር በተያያዘ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየጣለ ያለው ዝናብ ጉዳት እንዳያደርስ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ተገልጿል፡፡

  ወቅቱ የበልግ ዝናብ የሚጥልበትና በተለያዩ አካባቢዎችም የምሽቱ የአየር ጠባይ ዝናባማ ስለሚሆን፣ በተለይ በተደጋጋሚ ጎርፍ ለሚከሰትባቸው አካባቢዎች የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ እንደሚሰጥ ከአቶ ምትኩ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

  የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ የሚሰጠውን መረጃ ተንተርሶ አደጋ ሊከሰትባቸው የሚችሉ ገጠራማ አካባቢ ነዋሪዎች ወደ ከፍተኛ ሥፍራዎች እንዲወጡ ይደረጋል ተብሏል፡፡ በከተሞች አካባቢም የቱቦዎች ጠረጋ፣ የተዘጉ ቱቦዎች መክፈት ሥራ እንዲከናወንና ቅድመ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጥ በማድረግ፣ የጎርፍ አደጋውን ለመቀነስ ይሠራል ተብሏል፡፡ መረጃውም በባህላዊ የመረጃ ቅብብሎሽና በየአካባቢው ባሉ ማኅበራዊ ሬዲዮ ጣቢያዎች ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img