– የሙስናና የግብር ወንጀሎች ምርመራ ለፖሊስ እንዲተላለፍ መታቀዱ ላይም ጥያቄ ተነስቷል
ፍትሕ ሚኒስቴርን ከአስፈጻሚ አካላት ማቋቋሚያ አዋጅ በመሰረዝ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የማቋቋም እንቅስቃሴ ላይ የፓርላማው የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያዘጋጀው መድረክ ላይ የተገኙ የሕግ ባለሙያዎች፣ ፍትሕ ሚኒስቴር እንዳለ ሆኖ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንዲቋቋም ሐሳባቸውን አቀረቡ፡፡
መጋቢት 13 ቀን 2008 ዓ.ም. ለፓርላማ ቀርበው ለቋሚ ኮሚቴው ለዝርዝር ዕይታ ከተመሩት ረቂቅ አዋጆች መካከል የአስፈጻሚ አካላት ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ ላይ የፍትሕ ሚኒስቴርን ማቋቋሚያ መሰረዝ አንዱ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ነው፡፡
ይህ ረቂቅ አዋጅ የተበተኑ የዓቃቤ ሕግ ሥልጣኖችን በአንድ በመሰብሰብ የሚያደራጅና የፍትሕ ሚኒስቴር ሠራተኞችን ለሚያደራጀው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሚያስተላልፍ ነው፡፡ በመሆኑም የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን የዓቃቤ ሕግነት ሠራተኞች በሙሉ ወደሚቋቋመው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንዲዛወሩ፣ እንዲሁም የእነዚህ ተቋማት ወንጀል የመመርመር ሥልጣን ወደ ፌዴራል ፖሊስ እንዲተላለፍ በረቂቁ ተካቷል፡፡
በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሕዝባዊ ውይይት መጋቢት 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ያደረገው የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፍትሕ ሚኒስቴር እንዳለ ሆኖ እንዲቀጥልና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ራሱን ችሎ የመክሰስ ሥልጣን ኖሮት ብቻ እንዲደራጅ፣ የሕግ ባለሙያ ከሆኑ የውይይቱ ተሳታፊዎች ሐሳብ ቀርቦለታል፡፡
ሐሳባቸውን ካቀረቡ በርካታ ባለሙያዎች መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግና አስተዳደር ጥናቶች ኮሌጅ መምህር የሆኑት አቶ ሲሳይ መንግሥቴ፣ ‹‹የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ የተቋሙ ኃላፊነት ተደርገው የተካተቱት የወንጀል ፖሊሲ ማውጣት፣ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች፣ የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ፣ መንግሥትን ማማከርና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ከፍትሕ ሚኒስቴር ወስዶ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከመስጠት ይልቅ፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዋነኛ ሥራው መክሰስ ሆኖ ክሱ ላይ አትኩሮ መሥራቱ አይሻልም ወይ?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት አማካሪ ሆኖ ሌሎች ክስ ከመክሰስ ውጪ ያሉ ሠራተኞችን ይዞ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግና አስተዳደር ጥናቶች ኮሌጅ መምህርና ጠበቃ የሆኑት አቶ ስሜነህ ኪሮስ በበኩላቸው በሰጡት ተመሳሳይ ሐሳብ፣ ‹‹ፍትሕ ሚኒስቴር ራሱን ችሎ የመንግሥት የሕግ አማካሪ ሆኖ ቢቆም?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ባለድርሻ አካላት ደግሞ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ረቂቅ ላይ የሙስናና የግብር ወንጀሎችን የመመርመር ሥልጣን ለፌዴራል ፖሊስ የመስጠቱ አግባብነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የምርመራ ክፍል ባልደረባ አቶ ፀጋዬ ወልደ ሩፋኤል በሰጡት አስተያየት፣ ከግብር ጋር የተያያዙ ወንጀሎች ምርመራ የሚጀመረው ከኢንተለጀንስ ቡድኑ በሚመጣ መረጃና በምርመራ ኦዲት በሚመጣ መረጃ መሆኑን ጠቅሰው፣ እነዚህን ቡድኖች ነጥሎ ምርመራውን ለፌዴራል ፖሊስ መስጠት የምርመራው ጥራትና ውጤታማነት ያስተጓጉላል የሚል ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡
በተመሳሳይ ሐሳባቸውን የሰጡት የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባልደረባ፣ ሙስናን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ልምዱ በአብዛኛው የሚያሳየው የምርመራ ሥራው ለፀረ ሙስና ተቋም የተተወ መሆኑን ነው ብለዋል፡፡
የሰጡት ምክንያትም የምርመራ ሥራው ከሥራ አስፈጻሚው ገለልተኛ በሆነ ተቋም ሊመረመር ይሻላል በሚል ነው፡፡
በተጨማሪም ፌዴራል ፖሊስ አሁን ባለው ከፍተኛ የወንጀል ምርመራ ሥልጣንና ወንጀል መከላከል ተልዕኮ ላይ የሙስናና የግብር ወንጀሎችን እንዲመረምር መፍቀድ፣ በከፍተኛ ሁኔታ ጉልበታም አያደርገውም ወይ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡ ለፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ ዕድል የሰጡ ሲሆን፣ ሚኒስትሩ በሰጡት አስተያየት በሌሎች አገሮች ጠቅላይ ዓቃቤን ሕግ ለብቻ፣ ፍትሕ ሚኒስቴርን ለብቻ የሚያደርጉ ቢሆንም ሁለቱንም በአንድ ማደራጀትን ደግሞ አይከለክልም ብለዋል፡፡
‹‹የአደረጃጀት ጉዳይ መንግሥት ወቅታዊ ዓላማውን የሚያስፈጽምበት የታክቲክ ጉዳይ ስለሆነ፣ ሁለቱን አካላት ይበልጥ እንዲናበቡ የሚያደርግ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በዓቃቤ ሕግ ላይ የሚፈጠረው የሥራዎች መደራረብ የተሻለ ውጤት እንዳይመጣ ያደርጋል የሚለው ሥጋት መነሳቱ ችግር እንደሌለው፣ ነገር ግን ለሥጋቱ መሠረታዊና ግልጽ የሆነ አደረጃጀት ይፈጠራል ብለዋል፡፡
ከፀረ ሙስና ኮሚሽንና ከገቢዎችና ጉምሩክ ጋር በተያያዘ የተነሱ ጉዳዮች በዋናነት የሚፈቱት ግንዛቤን በመፍጠር፣ ማለትም ሙስናን የማይሸከም ትውልድና የታክስ ማጭበርበርን የሚጠየፍ ማኅበረሰብ በመፍጠር እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
‹‹ፖሊስ እንዲመረምር የተሰጠውን ሲያልፈሰፍስ ሲገኝ ለምን ብሎ መጠየቅ የሚቻልበት ኃላፊነት ለዓቃቤ ሕግ ይሰጣል፡፡ እስካሁን ድረስ የነበረው አሠራር ግን ተቃራኒ ነው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ዓቃቤ ሕግም በቀረበለት የምርመራ ውጤት በተገቢው መንገድ ተከራክሮ የማያስቀጣ ከሆነ፣ ፖሊስ ዓቃቤ ሕግን አንቆ መያዝ የሚችልበትን አሠራር ለመፍጠር ነው እየሞከርን ያለነው፤›› ብለዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በወቅቱ ከተደረገው ውይይት በርካታ ግብዓቶችን ማግኘቱን ገልጾ፣ በሌሎች መድረኮችም ረቂቅ አዋጁን የማዳበር ሥራ እንደሚያከናውን አሳውቋል፡፡