Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኔልሰን ማንዴላ 100ኛ ዓመት የተንፀባረቀው ፓን አፍሪካኒዝም

በኔልሰን ማንዴላ 100ኛ ዓመት የተንፀባረቀው ፓን አፍሪካኒዝም

ቀን:

አራት መቶ ሺሕ ዜጎችን ለዕልቂት የዳረገውን፣ ወደ አውሮፓና አጎራባች አገሮች ለመሸሽ ሲጥሩ ውኃ የበላቸው ስደተኞች፣ በባህር ላይ የተንሳፈፉ ሕፃናትን አሳዛኝ ፍፃሜ ለተመለከተ፣ የእርስ በርስ ጦርነቱ የአንድን አገር ሥልጣኔና ታሪክ እንዳልነበር አድርጎ አመድ ማድረጉን ላጤነ የሰላም ዋጋ በገንዘብ የሚተመን ሳይሆን የህልውና ጉዳይ እንደሆነ አይጠፋውም፡፡

በጥቂት ጊዜ ውስጥ የአንድን አገር ታሪክና ሥልጣኔ እንዳልነበርና ወደፊትም እንዳይኖር አድርጎ አመድ ያደረገው ጦርነት አሁንም ድረስ አስከፊ ዕልቂቶችን እየፈጠረ ይገኛል፡፡

በሰላም ፍትሕና ዕርቅ ለዕድገትና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ናቸው፡፡ ሰላም ከሌለ ፍትሕ ልማትም አይሳካም፡፡ ዴሞክራሲ፣ ነፃነትና ሰብዓዊ መብትም ሊኖሩ አይችሉም፡፡ ሰዎች እንደ ግለሰብ ወይም እንደ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ የሚሹትን የኑሮ አቅጣጫ መከተል የሚችሉት ሰላም፣ ፍትሕና አገራዊ መግባባት የሰፈነበት ፖለቲካዊ ሥርዓት ሲኖር ነው፡፡

የአፍሪካ ኅብረት የሰብዓዊና የሕዝቦች መብቶች ኮሚሽነር ሰለሞን አየለ (ዶ/ር) በሰላም ዙሪያ የሚሠራው የአማኒ ድርጅት መሥራችና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እርስ በርስ የሚናቆሩ ወይም የሚጋጩ አካላት ያሉበት ማኅበረሰብ ውስጥ ሰላምን ማስፈን የሚቻለው ሁሉም ሰው የሚገባውን ቦታ ሲያገኝ ብቻ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡  

ይህም ማለት አንዱ ሌላውን አሸንፎ የበላይ የመሆን አካሄድ ሳይሆን፣ ሁሉም ቦታ አግኝቶ የሚፈልገውን ፖለቲካ አቅጣጫ ለመከተል በዚያም ላይ ተመሥርቶ ሥልጣን የመያዝ ፍላጎቱንም ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ መያዝ ሲችል ነው፡፡

የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዚዳንትና የዓለም ተምሳሌት የሆኑ ኔልሰን ማንዴላ 100ኛ ዓመት የልደት በዓልን አስመልክቶ ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም . በተካሄደው ውይይት ወቅት ዶ/ር ሰለሞን በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አንዱ ሌላው ካልጠፋ እኔ ሰላም አላገኝም የሚል ተጠየቅ (ሎጂክ) እስካለ ድረስ ሰላም በምንም ዓይነት መልኩ ሊመጣ አይችልም፡፡

‹‹የአንዱ መኖር የእኔ አለመኖር መሆን የለበትም፣ ሁላችንም አብረን ተጠቃሚ መሆን የሚያስችለን ሥርዓት መፍጠር መቻልና ለዚህም ቦታ ማግኘት ይገባናል የሚል አስተሳሰብ ሊኖር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ካልመጣና የአንደኛው መኖር የሌላው ጉዳት ተደርጎ እስከተወሰደ ድረስ ሰላም አይመጣም፤›› ያላሉ፡፡

ጦርነት ውስጥ ያሉ ሰዎች ሊያውቁት የሚገባ ነገር ቢኖር ትግሉ የሚካሄዴው እርስ በርስ አብሮ ለመኖር የሚያስችል አካሄድ ለማምጣት ነው? ወይስ ደግሞ አንደኛውን አጥፍቶ እኛ ብቻ እንኑር የሚል እሳቤ የያዘ ነው? የሚለውን ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ ብቻ እንኑር የሚለው አካሄድ ሰላምን በፍፁም አያመጣም፡፡

ለምንድነው ኃይልን እንደ አማራጭ አድርገው የወሰዱት ተብሎ ሊጠየቅ እንደሚገባ፣ ለዚህ ዓይነቱ ጥያቄ የጋራ መግባባት እስካልመጣ ድረስ ሰላምን መፍጠር አዳጋች እንደሆነ፣ ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ሁኔታ መፍትሔ ናቸው ከሚባሉት መካከል ዋነኛው የጋራ መግባባት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

እንደ ኮሚሽነሩ ማብራሪያ ከሆነ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ እጅግ በጣም አስደንጋጭ ሁኔታ ተከስቶ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በፍቅር፣ በይቅር ባይነትና በመደመር ወደ ሰላምና መረጋጋት ለመቀየር ተችሏል፡፡ አሁን ያለው ወይም ሁኔታ ተጠናክሮ የጋራ መግባባት ሊፈጠር የሚቻለው ደግሞ ሥልጣን ላይ ባሉ አካላት መልካም ፈቃድ ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በጋራ በሚያደርጉት ተሳትፎ ጭምር ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የፈጠሩት አጋጣሚም ዘለቄታ ያለው መግባባትን፣ አብሮነትንና ሰላምን ሊያመጣ የሚችለው ሌላው አካሄድ ደግሞ የሕግ የበላይነትን አግባብ ያደረገና በነፃ ተቋማት ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ ሲኖር ነው፡፡ ተቋማቱ በቅጡ እንዳይሠሩ እንቅፋት የሆኑ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችና አሠራሮች እንዲወገዱ ማድረግም ለሕግ የበላይነት መስፈን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ነው የተናገሩት፡፡

የአገርና የአንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ፣ እንዲሁም ያሉት ችግሮች ምንድናቸው? በምን መልኩ ነው መፍትሔ መምጣት የሚቻለው በሚሉ ነገሮች ላይ በጋራ አቅጣጫ ለመስጠት የሚያስችል የእርቅ ጉባኤ መካሄድ አስፈላጊ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ጉባኤ ውጤታማ የሚሆነው በተወሰኑ ተቋማት፣ ግለሰቦች ብቻ በመመራት ሳይሆን በተለይም በልዩ ልዩ ምክንያቶች ከፖለቲካዊ፣ ከኢኮኖሚውና ከማኅበራዊ ኑሮ ማዕከልነት ዳር ላይ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ባካተተና ባሳተፈ መልኩ ሲከናወን ነው፡፡

በደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ በተከናወነው በዚሁ የክብ ጠረጴዛ ጉባኤ ላይ ፓን አፍሪካኒዝም፣ ዴሞክራሲና ልማት፣ ሰላም፣ ፍትሕና እርቅ፣ የወጣቶች ስደትና ሥራ እጦት በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ ያተኮሩ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡  

የፓንአፍሪካኒዝምን ውይይት የመሩትና በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የአፍሪካ ቀንድ ፓናል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ አብዱል መሐመድ በተለይ ከሪፖርተር ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ፣ ፓንአፍሪካኒዝም አፍሪካውያንና በአውሮፓ የሚገኙ ጥቁር  ዳያስፖራዎች የቅኝ አገዛዝንና ጭቆናን ለመገርሰስ የሚያደርጉት ንቅናቄ ዕውን የሚሆነው ተለያይተው ሳይሆን በአንድነት ከተባበሩ ነው ከሚል ፍልስፍና የመጣ ፅንሰ ሐሳብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የሚኖሩ ጥቁር ዳያስፖራዎችና በአሜሪካ የጥቁር ነፃነት ንቅናቄ መሪዎች ለመጀመርያ ጊዜ በማንችስተር ከተማ ስብሳባ አድርገው ከባርነት ቀንበር ለመውጣትና በዓለም ደረጃ ተሰሚነት ያለው ውጤት ማምጣት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ለመወያየት በቅተዋል፡፡ በዚህም ስብሰባ የጋና የመጀመርያው ፕሬዚዳንት የነበሩት ክዋሜ ንኩሩሜህ (ዶ/ር) ተገኝተው እንደነበር ነው የጠቆሙት፡፡

ኢትዮጵያም በቅኝ አገዛዝ መዳፍ እጅ ስላልነበረች እንደ ተምሳሌት ይጠቀሙባት እንደነበር፣ ኢትዮጵያ ነፃነቷን ለማስከበር እንደቻለች ሁሉ እኛም ለማድረግ አንችላለን የሚል አመለካከትና እምነት እንደነበራቸው፣ አንዳንድ ጊዜ የአፍሪካን የነፃነት እንቅስቃሴንም ከኢትዮጵያዊነት ጋር ያዋህዱት እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በፓንአፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ጥንስስ ውስጥ ኢትዮጵያ ተምሳሌታዊነት አርዓያነት እንዳላት፣ በፋሺስት ጣሊያን ወረራ በተካሄደባት ጊዜ በአሜሪካና በሌሎች አገሮች ውስጥ ያሉ ጥቁሮች ወረራውን ለመቀልበስ ፈቃደኛ እንደነበሩ፣ ይህ ዓይነቱን ተሳትፎ ለማድረግ ያነሳሳቸውም አንድ የቀረችንን ነፃ አገር በቅኝ ግዛት መዳፍ ውስጥ እንዳትወድቅብን የሚል የተቆርቋሪነት ስሜት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ኢትዮጵያ በፋሺስት በተወረረችበት ወቅት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ጄኔቭ ሊግ ኦፍ ኔሽን ቀርበው የግፍ ወረራውን ባሰሙበት ወቅት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አልነበረውም፡፡ ይኼንንም ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ፊታቸውን ወደ አፍሪካ ማዞር ጀመሩ፡፡ ይኼንንም ሊያደርጉ ያነሳሳቸው የአፍሪካ ነፃ መሆን የኢትዮጵያንም ነፃነት ያስከብርልናል፣ እንደ ምሰሶም ይሆናል ከሚል እምነት ነው፡፡ ለአፍሪካ አገሮች ነፃ መውጣት፣ እንዲሁም ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረት ብሎም ለአፍሪካ ኅብረት መቋቋም የኢትዮጵያ አስተዋፅኦ ወሳኝ እንደነበረ አቶ አብዱል አመልክተዋል፡፡

ኔልሰን ማንዴላ በሕይወት ዘመናቸው አፓርታይድን ለመገርሰስ የመረረ ትግል ሲያካሂዱ አፍሪካውያን እንደተባበሯቸው፣ ኢትዮጵያም መጥተው በውትድርና ሙያ እንደሠለጠኑ፣ ካለአፍሪካውያን ዕርዳታ ትግሉ በድል አድራጊነት ለውጥ እንደማይቻል በመገንዘባቸው የፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ለማራመድ እንደቻሉ ገልጸዋል፡፡

ከነፃነት በኋላ አገራቸውን በፕሬዚዳንትነት በመምራት ላይ እንዳሉ በየአገሩ እየተዘዋወሩ ምሥጋና ማቅረባቸውን፣ ከእንግዲህ ወዲህ የፓን አፍሪካኒዝም ፈተና ልማትና ዴሞክራቲክ ስቴት ለማምጣትና ግጭቶችን ለማስቆም በመታገል ላይ ያተኮረ መሆን አለበት የሚለውን አቅጣጫ በመከተል ይንቀሳቀሱ እንደነበር ከአቶ አብዱል ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...