Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከሚለያየን የሚያመሳስለን አይበልጥም?

ሰላም! ሰላም! እንደምን ከርማችኋል? እነሆ በናፍቆት ስንጠባበቃት የነበረችው ቀን ደርሳልን ጉዟችን በይፋ ተጀምሮልናል፡፡ ዛሬም ሆነ ወደፊትም እኔና መላው ቤተሰቤ ለሰላም፣ ለፍቅርና ለእርቅ የማንደራደርና ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የምንሰጥ መሆኑን አክብሮት መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ማንጠግቦሽ እንዳለችኝ እኔም ጥላቻን ጠላሁት፡፡ ከጥላቻ የሚተርፈን መለያየትና ሰቀቀን እንጂ ምንም እንዳልሆነ ከሰሞኑ ሁኔታችንን እያየን ነው፡፡ አይደለም እንዴ?

የባሻዬ  ልጅ፣ ‹‹ማንም ከማንም አይበልጥም! ማንም ከማንም አያንስም! የምናንሰው ከእገሌ እበልጣለሁ ስንል ነው፤›› ብሎ የተናገረውን ባሻዬ ሰምተው፣ ‹‹ጠቅላዩ ሊጠቀሙበት የሚገባ ሁነኛ ንግግር ነው፤›› ሲሉ የልጃቸውን ሐሳብ አጠናከሩ፡፡ አሁንስ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ትንሽ አጋነነ አትበሉኝና፣ የውዷ ባለቤቴን የዘር ሐረግ ከየት እንደሆነ እንኳን በቅጡ አላውቀውም፡፡ የማውቀውና በየሰኮንዱ የማስታውሰው አንድ በምንም ኃይል ማይነቀነቅ ግዙፍ እውነት አለ፡፡ ይህም ማንጠግቦሽን እንደማፈቅራት ብቻ ነው፡፡

ባሻዬ ለዚህ ትልቅ ምስክር ናቸው፡፡ ‹‹እናንተ የተሳሰራችሁበት የፍቅር ገመድ እንዲህ በቀላሉ የሚበጠስ በወፍቾ የተገመደ አይደለም፤›› ነበር ያሉን፡፡ እውነት ብለዋል፡፡ ልጃቸው የጠቅላዩን ንግግር ተውሶ፣ ‹ከትንንሾች ጋር አንደመርም፤›› ሲለን ደግሞ፣ ትንንሾች ማናቸው? ብለን አፈጠጥንበት፡፡ እንግዲህ አዳዲስ ስሞች በየዕለቱ እየጎረፉ ስለሆነ፣ ከእነ የቀን ጅቦችና ፀጉረ ለውጦች ቀጥሎ ትንንሾች በሚል ስያሜ የተሰየሙት ማናቸው? ብለን ስንጠይቅ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ትንንሾች ብሎ የሰየማቸው፣ ‹‹ዘረኞች›› እንደሆኑ አበሰረን፡፡ ‹‹ማንነት ያለና የነበረ ወደፊትም የሚኖር ቢሆንም፣ እንደ ቅል እያንጠለጠሉት አንድነታችንን ሲሸረሽሩት ምን ልበል ታዲያ?›› ሲለን አጀብ አልን፡፡ አጀብ በሉ እንጂ፡፡

አዛውንቱና መካሪያችን ባሻዬ፣ ‹‹ዘረኞች ድሮም ነበሩ አሁንም ይኖራሉ፤›› ሲሉን ልጃቸው መልሶ፣ ‹‹ታዲያ ከዘረኞች ጋር ተደመሩ ነው የምትለን?›› የሚል አፋጣጭ ጥያቄ ለአባቱ አቀረበ፡፡ አባትየው፣ ‹‹እኛ የምናምነው በሰው ክቡርነት ነው፤›› ብለው ትንሽ አሰብ አድርገው፣ ‹‹በሰብዕናው ሰው የሆነ ፍጡር ከየትኛውም ዓለም ቢመጣ ልንቀበለው፣ ልንወደውና ልንደመር ዝግጁ ነን፤›› በማለት ሐሳባቸውን ሰነዘሩ፡፡ ልጃቸው፣ ‹‹ከቻይናም ቢሆን?›› የሚል ወሳኝ ጥያቄ ሰነዘረላቸው፡፡ እሳቸው ሆዬ፣ ‹‹ዞሮ ዞሮ ሰው ነው! ነጭ፣ ጥቁር እያሉ በቋንቋና በዘር መከፋፈል የሰው ውድቀት መገለጫዎች እንጂ፣ ማንም ከማንም እንደሚሻል ማሳያዎች አይደሉም፤›› ብለውን አረፉት፡፡ ይኼን ጊዜ ልጃቸው፣ ‹‹ስለዚህ የየትኛውንም አገር ሴት ባገባ ግድ የለህም ማለት ነው?›› ብሎ ለአባቱ ያላሰቡትን ጥያቄ አቀረበላቸው፡፡

ይኼን ጊዜ ባሻዬ፣ ‹‹ልጄ ሆይ ሥጋም ወደ አፈሩ ነፍስም ወደ አምላኳ በምትመለስበት ወቅት፣ ወይም በፍርድ ቀን በአምላካችን ፊት በምንቆምበት ወቅት …›› ብለው መናገር ሲጀምሩ፣ ሁላችንም በንቃት ጆሮአችንን አቆምን እሳቸውም ቀጠሉ፣ ‹‹እግዜሩ ኢትዮጵያዊያን በዚህ ጋ፣ ከኢትዮጵያዊያንም የእገሌ ዘር በዚህ በኩል፣ የእገሌ ዘር በዚያ እያለ ዋጋችንን የሚከፍለን ይመስልሃል?›› የሚል ጥያቄ አቀረቡለት፡፡ ልጃቸውም፣ ‹‹እንዴ አባዬ እኛ ኢትዮጵያዊያን እ . . . ›› ብሎ ሊያብራራ ሲል፡፡ ከአፉ ነጥቀው፣ ‹‹ተው ልጄ ተው! እዚሁ ይብቃን፡፡ ብለህ ብለህ ፈጣሪም ቤት ልትወስደው ተመኘህ?›› ብለው ሲጠይቁት እርሱም መልሶ፣ ‹‹ታዲያ ከነጮቹ ጋር ልንደመር ነው ማለት ነው?›› የሚል ጥያቄ ሰነዘረላቸው፡፡ ዘንድሮ ምን የማይጠየቅ አለ?

ባሻዬ በምላሹ ተገርመው፣ ‹‹እግዚአብሔር ዘር አልፈጠረም! እርሱ ድንበርንም አልፈጠረም! እርሱ የፈጠረው ሰውን ነው፡፡ ሰውንም ፈጥሮ ‹ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት› የሚል ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ የቀረውን ተንኮልና አሻጥር ሁሉ የፈጠሩት ሰይጣን ያደረባቸው ሰዎች ናቸው፤›› ሲሉ ጥልቅ ማሰላሰል ውስጥ ገባን፡፡ የእሳቸው ድንቅ ማብራሪያ ሰው ለሰው ወዳጅ ሆኖ ይኖር ዘንድ ተፈጥሮ ሳለ፣ ስለምንድነው ጠላት ሆኖ ያረፈው የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

ባሻዬ ቀጠሉ፣ ‹‹የሰው ትልቅ የለውም፣ ትንሽም የለውም፡፡ ትልቅም ትንሽም የሚያደርገው አስተሳሰቡ ነው፡፡ የተዋቀረበት ሐሳብ ነው የሚያሳንሰውም የሚያገዝፈውም፡፡ ሰው ክቡር ነው! ባይማርም፣ ባይሠለጥንም፡፡ አሁን ሰው አበሳውን እየበላ ያለው ክፉዎች በፈጠሩት ችግር ነው፡፡ ስለዚህ እኛ ለልጅ ልጆቻችን ችግር አናስቀምጥላቸው፡፡ ቢቻለን አጥሩን አፈራርሰን፣ ግድቡን ጨራርሰን፣ ነዳጁን አውጥተን፣ መንገዱን ገንብተን፣ ትምህርት ቤቶችን ሠርተንና የጤና ተቋማትን አደራጅተን በሰላም የሚኖሩባትን አገር ለማውረስ ነው ቀን ከሌሊት መታገል ያለብን፤›› የሚል መግለጫ አወጡ፡፡ እሳቸውን የሰጠን አምላክ ይመስገን እያልን በልባችን ማዳመጥ የለብንም?

ማንጠግቦሽ የባሻዬን ገለጻ ከሰማች በኋላ ተገርማ፣ ‹‹ታዲያ በዚህ ዓይነት ግሎባላይዜሽን የእግዜሩ ሐሳብ ነው በሉኛ?›› የሚል ጥያቄ ሰነዘረችላቸው፡፡ ትንሽ ፈገግ ብለው፣ ‹‹ድሮ እኔም እግዜሩ ሳይቀር የእኛ ብሔር አባል ይመስለኝ ነበር፤›› ሲሉ ፈገግ አሰኙን፡፡ የእርስዎ ይባስ አልኳቸው፡፡ እሳቸውም፣ ‹‹አየህ አንዳንዱ ጉዳዩን ሰማይ ቤት አድርሶት፣ እግዜርን ራሱ በቡድን ውስጥ አስገብቶ፣ የዘሩን ማሊያ አልብሶ ሊያጫውተው ይፈልጋል፤›› ሲሉን ግርምት ውስጥ ገባን፡፡ ባሻዬ የዘመናት ልምዳቸውን እያስኮመኮሙን ነው፡፡ ‹‹ይኼው እንግዲህ ከኢትዮጵያ አንድ ስንዝር ስናልፍ ለማይጠቅመንና እንኳንስ በብሔራችን፣ እንኳንስ በአገራችን ይቅርና ዓለም በጅምላ ጠቅልሎ አፍሪካ ተብለን እየተጠራን ባለንበት ዓለም ውስጥ እየኖርን ዛሬ ጎሳዬ፣ ገለመሌ . . . እያልን እንጨማለቃለን፤›› ሲሉ ባሻዬም አልመስል አሉኝ፡፡ እንዲህ ልክ ልካችንን የሚነግረን ደፋር አያስፈልገንም ትላላችሁ?   

በእርግጥም ይህንን መገለጥ ከዘመናት ልምዳቸው የቀሰሙት እንደሆነ ለመገመት አያዳግትም፡፡ የባሻዬ ልጅ ጉዳዩን ሲያጠናክር፣ ‹‹ነገሩን የባሰ አሳፋሪ የሚደርገው ይህንን ከንቱ የዘር ጥያቄ የሚነሳው በወንድማማቾች መካከል መሆኑ ነው፤›› ሲለን እኔም አንድ ሁለት ሰዎች አዕምሮዬ ውስጥ ከተፍ አሉ፡፡

ማንጠግቦሽ በበኩሏ፣ ‹‹የዘራችንን ቡልኮ አውልቀን ቀደም ሲል እትብታችንን የቀበርንበትን ቦታ ወስደን ልንቀብረው ይገባናል፤›› ስትል በልቤ ቆሜ አጨበጨብኩላት! ታዲያ እኔስ ምኔ ሞኝ ከውዷ ባለቤቴ ሐሳብ ላይ ተንጠልጥዬ ይህንን እያልኩ ዛሬን እንሰነባበት፡፡ ዳግም መገናኘት ላይቀር እንነጋገረው እንጂ፡፡

ማነህ የእኔ ዘር ልዩ ነው፣ የእኔ ዘር ይበልጣል እያልክ በተለያዩ ሚዲያዎች የምታደነቁረን፣ ማነህ ወንድሜ ከእኔ ይሻላል ከሚል የበሰለ የሰው አስተሳሰብ ይልቅ እኔ ከወንድሜ እበልጣለሁ እያልክ የምትመጣ፣ ዛሬ ከመላው ቤተሰቤ ይህንን መልዕክት ተቀበል፡፡ የዘረኝነትህን ካባ አውልቀህ፣ እትብትህን የቀበርክበት ቦታ ፈልገህ ቅበረው፡፡ እኛ የተመሳሰልንበት ሰንሰለት እንዲህ በቀላሉ የሚበጠስ አይደለም፡፡ ድንበሩን አፍርሱ፣ መንገዱን ቀይሱና ፍቅርን፣ ሰላምንና መዋደድን ስበኩ የሚል ቤተሰባዊ ምክራችን በያላችሁበት ይድረስልን! ከሚለያየን የሚያመሳስለን አይበልጥም? መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት