Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበጌዴኦና በምዕራብ ጉጂ በግጭት ሳቢያ የተፈናቀሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን እስከ ሐምሌ...

በጌዴኦና በምዕራብ ጉጂ በግጭት ሳቢያ የተፈናቀሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎችን እስከ ሐምሌ መጨረሻ ወደ ቀዬአቸው ለመመለስ ታቅዷል

ቀን:

ተመድ ተፈናቃዎች ለምግብ እጥረትና ለበሽታ ሥጋት መጋለጣቸውን አስታውቋል  

በደቡብ ክልል በጌዴኦ ዞንና በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ጉጂ ዞን ነዋሪዎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢዎች የሠፈሩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች፣ እስከ ሐምሌ ወር መጨረሻ ወደ ቀዬአቸው ሊመለሱ እንደሚችሉ ተገለጸ፡፡

የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ለሪፖርተር  እንደገለጸው፣ በሁለቱም ዞኖች የሚገኙ ተፈናቃዎችን ወደ የመኖሪያ አካባቢያቸው ለመመለስ ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው፡፡

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደበበ ዘውዴ ከጌዴኦ ዞን 860,056፣ ከምዕራብ ጉጂ ዞን 188,747 ዜጎች በእርስ በርስ ግጭት ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያዎች ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ እንደ አቶ ደበበ ማብራሪያ ከሆነ፣ ከጌዴኦ ዞን የተፈናቀሉ ዜጎች በ77 ጣቢዎች የተጠለሉ ሲሆን፣ የምዕራብ ጉጂ ዞን ተፈናቃዮችም በስድስት መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ተጠልለዋል፡፡ ከ110 ሺሕ በላይ ሕፃናትም ከሁለቱ ዞኖች መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሪፖርት አመላክቷል፡፡

ተፈናቃዎቹን በአስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ አቅርቦትና ምግብ ነክ ባልሆኑ ቁሳቁሶች ለመደገፍ ብሎም ደኅንነታቸውን ለማስጠበቅ፣ አዳዲስ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ መስጫና ማስተባበሪያ ማዕከላት በሁለቱም ዞኖች መቋቋማቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡ የተቀናጀ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ለማቅረብ እንዲያግዙ የተቋቋሙት አዳዲሶቹ ማዕከላት፣ ከምግብና ከቁሳቁስ ድጋፎች በተጨማሪ የጤና ክብካቤ ሥራዎችንም በማስተባበር እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ አቶ ደበበ አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት ከለጋሽ አጋሮቹ ጋር በመሆን 35 በመቶ አልሚ ምግቦችና 90 በመቶ የምግብ አቅርቦት እየሸፈነ እንደሚገኝ ያስታወቁት አቶ ደበበ፣ በሁለቱም ዞኖች የሚገኙ ነዋሪዎችም የቁሳቁስና የአልባሳት ድጋፎችንም እያቀረቡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ ብርድ ልብስ፣ የምግብ ማብሰያና አልሚ ምግቦችን ጨምሮ የጤና ክብካቤ ድጋፍና የመፀዳጃ ቤት አቅርቦቶችን የሚያከናውኑ 12 ያህል የተመድና ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች በሁለቱም ዞኖች እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

የዓለም የፍልሰት ድርጅት (አይኦኤም)፣ የተመድ ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን፣ በተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ የተመድ የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ)፣ እንዲሁም ኤንኤስኤፍ የተባለና በጤና ላይ የሚንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ ተቋም ለተጎጂዎቹ የጤና ክብካቤ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም ተመልክቷል፡፡

ይህ ዘገባ እስከ ዓርብ ሐምሌ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት እስከተጠናቀረበት ወቅት፣ አቶ ደበበ በምዕራብ ጉጂ ዞን ውስጥ ሥራ ላይ ነበሩ፡፡ በስልክ ከሥፍራው ለሪፖርተር በገለጹት መሠረት ተጎጂዎችን በሦስት አቅጣጫዎች ማለትም የሰላምና የፀጥታ ድጋፍ፣ የአስቸኳይ ድጋፍና ምላሽ፣ እንዲሁም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ክፍሎች፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ የብሔራዊ አደጋ መከላከልና ማስተባበሪያ ኮሚቴ የሚታገዝ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው፡፡  

አቶ ደበበ በአሁኑ ወቅት አሳሳቢ የጤናም ሆነ የፀጥታ ችግር በመጠለያ ጣቢዎቹ አካባቢ የለም ቢሉም፣ ተቀማጭነቱ አዲስ አበባ የሆነው የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስባበሪያ ጽሕፈት ቤት አዲስ ሪፖርት ግን የበሽታና የምግብ አቅርቦት እጥረት ሥጋቶች እንደተጋረጡ አመላክቷል፡፡

በሰኔ ወር ለተፈናቀሉ 822,187 ተጎጂዎች ያስፈልጋል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው የዕርዳታ ገንዘብ 117.7 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ያስታወሰው ጽሕፈት ቤቱ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ከፍተኛ የቁሳቁስና የሌሎች አቅርቦቶች ክፍተት መከሰቱን አስታውቋል፡፡ ተፈናቃዮች በተጨናነቀ የመጠለያ ጣቢዎችና በየመንደሩ በሚያስጠልሉ በጎ ፈቃደኛ ነዋሪዎች ጭምር ድጋፍ እየተሰጣቸው ቢሆንም፣ አብዛኞቹ በተለይም ነፍሰ ጡሮች፣ ሴቶች፣ ተጎጂዎችና ሕፃናት ለአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) እና ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች፣ ሕፃናቱም ለሳንባ ምችና ለመሳሰሉት ተጋላጭ መሆናቸውን የተመድ ሪፖርት ይጠቁማል፡፡

በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማና በምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ ከተማ የተመሠረቱ ሁለቱ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ መስጫ ማዕከላትን ጨምሮ በይርጋ ጨፌ፣ በወናጎ፣ በቆጨሬ፣ በሀምቤላ፣ በዓባያ፣ በገላና እንዲሁም በቢርቢርሳ ቆጆዋ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የመጠለያ ጣቢዎች የሚገኙ ተጎጂዎች እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ወደ ተፈናቀሉባቸው አካባቢዎች እንደሚመለሱ ሲጠበቅ፣ የመልሶ ማቋቋም ድጋፎች እንደሚደረጉላቸውም የኮሚሽኑ መረጃ ይጠቁማል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...