Monday, March 4, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በምሕረት አዋጁ አሳዛኙ የታሪክ ምዕራፍ ይዘጋ!

ዓርብ ሐምሌ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ የምሕረት አዋጁን አፅድቋል፡፡ አዋጁ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ለተሳተፉ፣ የፖለቲካ መብታቸውን ለመጠቀም እንቅስቃሴ በማድረጋቸው መንግሥት ሲፈልጋቸው ከአገር ሸሽተው በተለያዩ አገሮች በስደት ለሚኖሩ ምሕረት ለመስጠት፣ በተጨማሪም የእርስ በርስ ጥላቻንና ጥርጣሬን በማስወገድ በብሔራዊ መግባባት አብሮ ለመሥራት ሲባል መውጣቱ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት ከግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በፊት የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ፈጽመዋል ተብለው በመጠርጠር በሕግ የሚፈለጉም ሆኑ፣ ጉዳያቸው በምርመራ ላይ ሆኖ ክስ የተመሠረተባቸው ወይም ጥፋተኛ ተብለው የተፈረደባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ምሕረት ያገኛሉ፡፡ ምሕረት የተደረገላቸው ወገኖች ፓርላማው ካፀደቀበት ቀን ጀምሮ በስድስት ወራት ውስጥ ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸው ተደንግጓል፡፡ ይህ አዋጅ ከመከላከያ ሠራዊቱ ኮብልለው የወንጀል ክስ የተመሠረተባቸውን ጭምር በማካተት የምሕረት ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡ ይህ የምሕረት አዋጅ ለአገሪቱ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ አስተማማኝ ይሆን ዘንድ ኢትዮጵያውያን አሳዛኙ የታሪክ ምዕራፍ እንዲዘጋ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል፡፡

ኢትዮጵያ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል ችግር ከፈጠሩባት መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የጥላቻና የቂም ዓረም የወረረው ፖለቲካ ነው፡፡ ሥልጣን ላይ የወጣ ኃይል የተፎካካሪዎቹን መብት አክብሮ በሕጋዊ መንገድ አገር ከማስተዳደር ይልቅ፣ ያገኘውን ሁሉ እየጨፈላለቀ የፖለቲካ ምኅዳሩን ማዳፈን የተለመደ ተግባር ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዚህም ሳቢያ መፈናፈኛ ያጡ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ተቃውሞዋቸውን ሲያሰሙ ማፈን፣ መሰወር፣ ማሰር፣ መግደል ወይም እንዲሰደዱ ማድረግም የተለመደ የአገር ሕመም ነበር፡፡ ሥልጣንን ሕጋዊ ለማስመሰል የይስሙላ ምርጫ እየተካሄደ የፖለቲካ ምኅዳሩ የበለጠ እንዲዳፈን ሲደረግ፣ ተቃዋሚን ወይም ተፎካካሪን የአሸባሪነት ወይም የከሃዲነት ስም እየለጠፉ መወንጀልና ማሳደድ የቅርብ ጊዜ ትዕይንት እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህ ምክንያት ፖለቲከኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ወዘተ. የጥቃት ዒላማ ተደርገው በርካታ በደሎች ተፈጽመዋል፡፡ ብዙዎች ለእስር ሲዳረጉ ለደኅንነታቸው በመሥጋት የተሰደዱም በርካቶች ናቸው፡፡ ይህ የምሕረት አዋጅ መፅደቁ ይህንን አሳዛኝ የታሪክ ምዕራፍ እንደሚዘጋ ተስፋ ይደረጋል፡፡

አገር ሰላምና መረጋጋት የሚሰፍንባት አንዱ አሳዳጅ ሌላው ተሰዳጅ መሆኑ በሕግ ማዕቀፍ ሲገታ ብቻ ነው፡፡ ሥልጣን ከጠመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን ከነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መገኘት የሚችለው ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት የሚፎካከሩበት የፖለቲካ ምኅዳር ሲፈጠር ነው፡፡ ይህ በተግባር ይረጋገጥ ዘንድ የሲቪክ ማኅበራት በነፃነት መደራጀት አለባቸው፡፡ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሕጋዊ ዋስትና አግኝተው በተግባር መረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ በአስተሳሰቡ ወይም በፖለቲካ አቋሙ ምክንያት ጉዳት እንደማይደርስበት ማረጋገጫ ማግኘት አለበት፡፡ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትና የሙያ ማኅበራት ከፖለቲካ ፓርቲ ተፅዕኖ ፍፁም ገለልተኛና ነፃ ሆነው ሊደራጁ ይገባል፡፡ በማናቸውም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች የሕግ የበላይነት መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ሕግ አውጭው፣ አስፈጻሚውና ተርጓሚው እርስ በርስ ቁጥጥር የሚያደርጉበትና የሚናበቡበት ሕጋዊ ማዕቀፍ ኖሮ በተግባር መታየት አለበት፡፡ ከሕግ በላይ መሆን የሚያምራቸው ፖለቲከኞችም ሆኑ የመንግሥት ሹማምንት በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ ሊገዙ ይገባል፡፡ ሌሎች በርካታ ለብሔራዊ መግባባት የሚጠቅሙ ጉዳዮች ጭምር ሊታሰብባቸው የግድ ይላል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በይፋ ሥልጣናቸውን ከተረከቡ ከመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ወዲህ የተከናወኑ በርካታ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች፣ ለአገሪቱ መፃኢ ዕድል ተስፋ የሚሰጡ መሆናቸው በግልጽ እየታየ ነው፡፡ የምሕረት አዋጁ በፍጥነት ተዘጋጅቶ አስፈላጊ የሚባሉ ምልከታዎች ከተደረጉበት በኋላ በመፅደቁ፣ የተጀመረው ለውጥ የበለጠ እንዲቀላጠፍና ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አያጠራጥርም፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የተከሰሱ፣ የተቀጡ፣ ከአገራቸው በግድ ተሰደው በባዕድ አገር የሚኖሩ ለአገር የሚጠቅሙ ወገኖችን እንደሚታደግ ተስፋ ይደረጋል፡፡ ኢትዮጵያ ከገባችበት ቀውስ ውስጥ ወጥታ ወደ ታላቅነት መገስገስ የምትችለው፣ በተለያዩ የሙያ መስኮች አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ ልጆቿ በዙሪያዋ ሲሰባሰቡ ነው፡፡ ለበርካታ ዓመታት በስደስት ሆነው ስለአገራቸው ሲጮሁ የነበሩም ሆኑ በስቃይ ውስጥ የቆዩ ወገኖች፣ በምሕረት አዋጁ አማካይነት ከጥላቻና ከቂም በቀል ተላቀው የፍቅርና የይቅርታ አካል ሲሆኑ ለአገር ትልቅ ስኬት ነው፡፡ የተበላሸው ገጽታ ተቀይሮ ኢትዮጵያውያን ሲሰባሰቡ ለአገር ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ይህ ዕድል የበለጠ መጠናከር አለበት፡፡

የምሕረት አዋጁ ተጠያቂነትን በማንሳት ኢትዮጵያውያን ከስደት ወደ አገራችው ሲመለሱ የበለጠ ኃይል ይገኛል፡፡ ገንዘብ፣ ዕውቀት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የመሳሰሉት በብዛት ይገኛሉ፡፡ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በዲፕሎማሲው፣ በማኅበራዊ ጉዳዮችና በመሳሰሉት አገር የባከነባት ዕምቅ ሀብት እንደገና ይሰባሰባል፡፡ ከዚህ ቀደም የምናውቃቸው ልፍስፍስ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ይጠናከራሉ፡፡ በፖለቲካ ምኅዳሩ ውስጥ የሚሳተፉ ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይገኛሉ፡፡ የተሻለ ሐሳብና ራዕይ ያላቸው ልሂቃን የሐሳብ ገበያውን ይቀላቀላሉ፡፡ በፍራቻ ምክንያት ከፖለቲካው አደባባይ የራቁ ሰዎች ይደፋፈራሉ፡፡ በሕዝብ ዘንድ የተከበሩና መልካም ሰብዕና ያላቸው አንጋፋዎች ምክራቸውን ያለ ስስት ያቀርባሉ፡፡ ለውጡ ሕዝብ በሚፈልገው መንገድ ብቻ መከናወን የሚችለው፣ ኢትዮጵያ የሁሉም ኢትዮጵያውያን አገር መሆኗ በተግባር ሲረጋገጥ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን ደግሞ ከምንም ነገር በላይ ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሰላም የሚፀናው ይቅር መባባል የአገር ወግና ባህል ሲሆን ነው፡፡

ይህች ታሪካዊት አገርና ይህ እጅግ የተከበረ ሕዝብ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ናቸው፡፡ ይህ የታሪክ ምዕራፍ ጭቆናን፣ አፈናን፣ አምባገነንነትንና አገር አፍራሽነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማሰናበት ይጠበቅበታል፡፡ ለውጡ ኢትዮጵያውያን የመሰላቸውን ሐሳብ በነፃነት እያንሸራሸሩ ለብሔራዊ መግባባት መሠረት ከመጣል በተጨማሪ፣ የሚወዷት አገራቸው ተመልሳ ወደ ቀውስ እንዳትገባ ተግቶ ለመሥራት ማስቻል አለበት፡፡ ኢትዮጵያውያን ለማንነታቸው፣ ለባህላቸው፣ ለቋንቋቸው፣ ለፖለቲካ አቋማቸውና ለመሳሰሉት ዕውቅና በመሰጣጠት ለአገራቸው ዕድገት፣ ብልፅግና፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ከልብ መትጋት አለባቸው፡፡ ለጥፋት የባከኑ ዓመታት ያስቆጫሉ፡፡ እነዚያን የሚያስቆጩ ዓመታት ለማካከስ ግን ዕውቀት፣ ብልኃትና ጥበብ ያስፈልጋሉ፡፡ የተፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በማስተዋል መራመድ የሚጠቅመው ለሕዝብና ለአገር ዘለቄታዊ ህልውና ነው፡፡ ካሁን በኋላ ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ ማለት መልካም አጋጣሚዎችን ማበላሸት ነው፡፡ ስለዚህ በምሕረት አዋጁ አሳዛኙ የታሪክ ምዕራፍ ይዘጋ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...

ምርጫ ቦርድ ፓርላማው ያፀደቀለትን 304 ሚሊዮን ብር አለማግኘቱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ሰኔ 2016 ዓ.ም. በአራት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰብዓዊ ቀውስና በውድመት የታጀቡ ግጭቶች በአስቸኳይ ይቁሙ!

በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ተጀምሮ አማራና አፋር ክልሎችን ያዳረሰው የሁለት ዓመቱ አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢገታም፣ ከነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል የተጀመረው...

ታላቁ የዓድዋ ድል ሲዘከር የጀግኖቹ የሞራል ልዕልና አይዘንጋ!

የታላቁ ዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሲዘከር፣ ለአገርና ለሕዝብ ክብር የሚመጥኑ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ በዓድዋ ከወራሪው ኮሎኒያሊስት ኃይል ጋር ተፋልመው ከትውልድ ወደ...

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...