Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበቦምብ ፍንዳታው ተጠርጥረው የታሰሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመብን ነው አሉ

በቦምብ ፍንዳታው ተጠርጥረው የታሰሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመብን ነው አሉ

ቀን:

ለሦስተኛ ጊዜ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደባቸው

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የድጋፍና የምሥጋና ሥነ ሥርዓት ሲከናወን በመስቀል አደባባይ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ተወርውሮ በፈነዳው ቦምብ ምክንያት በእስር ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች፣ ሰብዓዊ መብታቸው መጣሱን ለፍርድ ቤት ተናገሩ፡፡

ለሦስተኛ ጊዜ በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ዓርብ ሐምሌ 13 ቀን 2010 ዓ.ም. የቀረቡት ተጠርጣሪዎች እንዳስረዱት፣ የታሰሩት ጨለማ ቤት ውስጥ ነው፡፡ ወቅቱ ክረምት በመሆኑ በጣም እንደሚቀዘቅዝ፣ የፀሐይ ብርሃን እንደማያገኙና መልካቸውም እየተቀየረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይ ተጠርጣሪ ጌቱ ግርማና ደሳለኝ ተስፋዬ ከጉድጓድ የወጣ አይጥ እንጂ ሰው እንደማይመስሉ ተናግረው፣ ከአንገታቸው በላይ ያለውን አካላቸውን ለፍርድ ቤቱ እያሳዩ አቤቱታቸውን አሰምተዋል፡፡

ለፍርድ ቤቱ ሐምሌ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ተመሳሳይ ችግር እንዳለባቸው አቤቱታ አቅርበው ፍርድ ቤቱ እንዲስተካከልላቸው ትዕዛዝ መስጠቱን አስታውሰው፣ የፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ቡድን ግን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ አለማክበሩን አስረድተዋል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው መሆኑን ደጋግመው በመናገር፣ ኢትየጵያዊ ዜጋ በመሆናቸው፣ አንድ እስረኛ ማግኘት ያለበትን መብት እንዲያገኙ እንዲደረግላቸውና የሕግ የበላይነት እንዲከበር ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸው የተናገሩት በተጠርጣሪ አብዲሳ ቀነኒ መዝገብ የተካተቱት ደሳለኝ ተስፋዬ፣ ጌቱ ግርማና ባህሩ ሎላ ናቸው፡፡ ሕይወት ገዳ የተባለችው ተጠርጣሪ የአዕምሮ ሕመምተኛ በመሆኗ አማኑኤል ሆስፒታል ተኝታ እየታከመች እንደሆነ፣ የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ መርማሪ ቡድን ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡

ሌላው መዝገብ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ግርማ ካሳን ጨምሮ ዘጠኝ የፌዴራል ፖሊስ አባላት የተካተቱበት ነው፡፡ በዚህ መዝገብ የፌዴራል ፖሊስ በተሰጠው አሥራ አንድ ተጨማሪ ቀናት የምርመራ ጊዜ የሠራውን ለፍርድ ቤት አስረድቷል፡፡ በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ ምን ያህል የምስክሮች ቃል እንደተቀበለ ባይናገርም፣ በተሰጠው ጊዜ የ30 ምስክሮችን ቃል መቀበሉን፣ ልዩ ልዩ የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰቡን፣ ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን መለየቱን፣ ሁለት የምርመራ ቡድን ወደ ተለያዩ ክልሎች መላኩን በማስረዳት የቀሩትን ሥራዎች ገልጿል፡፡ ተጨማሪ ምስክሮችን መስማት፣ ልዩ ልዩ የሰነድ ማስረጃዎችን መሰብሰብ፣ የተለዩ ተጠርጣሪዎችን መያዝና ተጠርጣሪዎችን በምስክሮች ማስለየት (በወቅቱ የአሠራር ክፍተት እንዳለ ምስክሮቹ ለተጠርጣሪዎቹ ሲነግሯቸው ሊቀበሏቸው እንዳልቻሉ የሚያስረዱ) እንደሚቀራቸው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን በተሰጠው ጊዜ ሠርቻቸዋለሁ ያላቸውን የምርመራ ሒደቶች ተጠርጣሪዎቹ ተቃውመውታል፡፡ መርማሪ ቡድኑ በተደጋጋሚ ለሦስት ጊዜያት፣ ቀሩኝ እያለ የሚያቀርባቸው ምርመራዎች ተመሳሳይና አንድ ዓይነት መሆናቸውን፣ ቀደም ብሎ የሠራውን እየገለበጠ እንጂ አዲስ የሠራው ሥራ አለ ብለው ስለማያምኑ ፍርድ ቤቱ የምርመራ መዝገቡን ወስዶ በመመልከት እንዲያረጋግጥላቸው አመልክተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱም የተጠርጣሪዎቹን አቤቱታ ተቀብሎ የምርመራ መዝገቡን በመውሰድ ተመልክቶታል፡፡ መርማሪ ቡድኑም በመሀል በሰጠው ምላሽ፣ ‹‹ምስክሮች የምንሰማው በእያንዳንዱ የተጠረጠሩበት ጭብጥ ላይ በመሆኑና ከክልልም የሚመጡ ምስክሮች በመሆናቸው ጊዜ ይወስዳል፤›› ብሏል፡፡

ፍርድ ቤቱም የተመለከተውን የምርመራ መዝገብ በሚመለከት ለተጠርጣሪዎቹ እንደነገራቸው፣ በተፈቀደለት ጊዜ መርማሪ ቡድኑ መሥራቱን መዝገቡ ያመለክታል፡፡ ተጨማሪ የምትሉት ነገር ካለ ግለጹ በማለቱ ተጠርጣሪዎች አቤቱታዎችን አሰምተዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ እንዳስረዱት፣ በእነሱ እምነት መርማሪ ቡድኑ በተደጋጋሚ ሠራሁ በሚለው ምርመራ ላይ ለውጥ የለም:: ሠራሁም ሆነ ይቀረኛል የሚላቸው የምርመራ ሥራዎች በተከበሩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው፣ ከእነሱ ጋር የሚያገናኛቸው ምንም ነገር የለም ብለዋል፡፡ በ11 ቀናት ውስጥ ለምን 30 ምስክሮችን ብቻ ሰሙ? አልተመቻቸውም? ጊዜ አጠራቸው? የታሰርነው እኮ ሰዎች ነን? ይኼ የሚያሳየው ሥራቸውን እየሠሩ አለመሆናቸውን እንደሆነ በማለት አቤቱታቸውን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ምስክር ከሌለው እንደሌለው መናገር እንጂ ምክንያቱ አሳማኝ አለመሆኑንም አክለዋል፡፡ ተጠርጣሪዎች የመጠየቅ፣ መርማሪዎች የመመርመርና እውነቱን የማውጣት ግዴታና ፍርድ ቤትም ፍትሕ የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው የጠቆሙት ተጠርጣሪዎቹ፣ በተደጋጋሚ 14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መፍቀድ እውነትን ሊያወጣ እንደማይችል አስረድተዋል፡፡

ለ20 እና ለ30 ዓመታት ሕዝብንና መንግሥትን ሲያገለግሉ መቆየታቸውንና ለማንኛውም ምርመራ አጋዥ መሆናቸውን ገልጸው፣ ከመርማሪዎቻቸው ይልቅ በወቅቱ ቦታው ላይ የነበሩት እነሱ በመሆናቸው ለምርመራው አጋዥ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውን፣ ከቤተሰቦቻቸውና ከልጆቻቸው ተለይተው ከፍተኛ ችግር ላይ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡ በመንግሥት ተቋም ለሚገኝ ሰነድና ላልተያዘ ሰው መያዣ ሆነው መታሰር እንደሌለባቸው አስረድተው፣ ፍርድ ቤቱ በነፃ ወይም በዋስ ሊለቃቸው እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የመርማሪ ቡድኑ አባላት የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ ተቃውሞ በዋስ ቢወጡ ሰነድ እንደሚያጠፉ፣ ምስክር እንደሚያባብሉና እንደሚያስጠፉ በመግለጽ፣ ጥያቄያቸው ውድቅ እንዲደረግለት ጠይቀዋል፡፡ ሰብዓዊ መብታቸው እንደተጣሰ የገለጹትን ተጠርጣሪዎች በሚመለከትም፣ መርማሪዎቹ ራሳቸው እየሄዱ እንደሚያዩዋቸውና እንደ ማንኛውም ተጠርጣሪ በአግባቡ መያዛቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጸው፣ ተጠርጣሪዎቹ የሚናገሩት ከእውነት የራቀ መሆኑን አስረድተው ለተጨማሪ የምርመራ ጊዜ 14 ቀናት እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ መርማሪ ቡድኑ የሠራውን የምርመራ መዝገብ ተመልክቶ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ግንዛቤ መውሰዱን በመግለጽ፣ የተጠርጣሪዎችን የዋስትና ጥያቄ በማለፍ ከተጠየቀው ቀናት ውስጥ ሰባት ቀናት በመፍቀድ ለሐምሌ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞብናል ስላሉ ተጠርጣሪዎች መርማሪ ቡድኑ ተከታትሎ ማንኛውም ተጠርጣሪ የሚያገኘውን መብት እንዲያገኙ እንዲያስደርግ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ምርመራውንም ቶሎ ቶሎ ሠርተው በማን ላይ ምን እንደተከናወነ ለይተው እንዲያቀርቡም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...