በደቡብ ክልል በካፋ ዞን ገዋታና ዴቻ ወረዳዎች በተከሰቱ ግጭቶች በአካባቢው ባሉ ስምንት የእርሻ ኢንቨስትመንቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ በግጭቶቹም የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተጎጂ ሆነዋል፡፡
በአካባቢው ባሉ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ አለመሆናቸውን፣ ቦታቸው በኢንቨስትመንት ስም ተወስዶ ምንም ሳይጠቀሙበት ከሚቀሩ እነሱ አርሰው ቢጠቀሙበት የተሻለ ነው ባሉ የአካባቢው ወጣቶች በተፈጸመ ጥቃት የእርሻዎች መጋዘኖች፣ ቢሮዎች፣ ማደሪያዎችና የቢሮ መገልገያዎች እንደተዘረፉና እንደወደሙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የዞኑ የኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘመዴ አንዳርጌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢንቨስተሮች ለቢሮው በመደወል በልማታቸው ላይ ጥቃት እንደደረሰ ለጽሕፈት ቤቱ እንዳስታወቁ ገልጸው፣ በኢንቨስትመንቶቹ ላይ በብዛት የማፈራረስ ጥቃት እንደደረሰባ አስታውቀዋል፡፡
በጥቃቱ ምክንያት የቢሮ መገልገያ ቁሳቁሶችና ሌሎች የእርሻ ንብረቶች መውደማቸው ተነግሯል፡፡ ይሁን እንጂ በእርሻዎቹ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልደረሰ አቶ ዘመዴ ጠቁመዋል፡፡
ችግሩ የተከሰተባቸው አካባቢዎች የዞንና የክልል የፀጥታ አካላት በጋራ የማረጋጋት ሥራ እያከናወኑ እንደሆነ፣ ችግር ባልተከሰተባቸው አካባቢዎች ቅራኔዎች ካሉ በውይይት አስቀድሞ ለመፍታት የውይይት መድረኮችን ለማዘጋጀት ዕቅድ መያዙንም የኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
ከዞኑ የፀጥታ አካላት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የዞኑ ወጣቶች በርካታ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡ ጥያቄዎቻቸው ሳይመለሱ በመቆየታቸው ይህ ችግር መከሰቱን ተናግረዋል፡፡ ኢንቨስተሮችም ሀብት በሚያካብቱበት አካባቢ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚጠበቅባቸው ቢሆንም፣ ይኼንን ለማድረግ እጅግ መጓተቶች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ ኢንቨስተሮች ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጥቅም ብለው የሚያከናውኑት ሥራ እንዲኖር ለማድረግ ውይይት እየተደረገ እንዳለም ተገልጿል፡፡
የአካባቢው ትንንሽ አርሶ አደሮችን ለመደገፍ ትምህርት ቤት የማስፋፋትና የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ የጀመሩ ኢንቨስተሮች እንዳሉ ታውቋል፡፡
በዞኑ 118 የግብርና ኢንቨስትመንቶች የሚገኙ ሲሆን፣ በርካታዎቹ በእርሻና በአግሮ ፕሮሰሲንግ የተሰማሩ መሆናቸው አቶ ዘመዴ አስረድተዋል፡፡
በካፋ ዞን ቦንጋ ከተማና አካባቢው ከአንድ ወር በላይ የዘለቀ ተቃውሞ እንደነበረ፣ ወጣቶች በአስተዳደሩ ላይ ያላቸውን ምሬትና የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን በስፋት ሲያነሱ መቆየታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡