Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች ኤርትራን እየጎበኙ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኤርትራ አየር መንገድ ከአስመራና ከአሰብ ወደ አዲስ አበባ በረራ ሊጀምር ነው

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለ20 ዓመታት አቋርጦ የነበረውን የአስመራ በረራ ረቡዕ ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲጀምር፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች በኤርትራ ያሉ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዕድሎችን ለመመልከት በኤርትራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡

ዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን ባዘጋጀው የንግድ ጉዞ 54 የሚሆኑ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ አየር መንገድ ታሪካዊ በረራ ተሳፍረው ወደ አስመራ ተጉዘዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም ከኤርትራ ንግድ ምክር ቤት ጋር ግንኙነት ለመመሥረት ወኪሉን ልኳል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ገብረ ሥላሴ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ንግድ ምክር ቤቱ ከኤርትራ ንግድ ምክር ቤት ጋር የሥራ ግንኙነት ለመጀመር እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ ተቋርጦ የነበረውን የንግድ ትስስር ለመቀጠል የሁለቱ አገሮች ንግድ ምክር ቤቶች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ አቶ አሰፋ አስረድተዋል፡፡

በዋፋ ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን የተመራው የንግድ ልዑክ የኤርትራ ንግድ ምክር ቤትና ምፅዋ ከተማን ሐሙስ ሐምሌ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ጎብኝቷል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የንግዱን ማኅበረሰብ አባላት ያቀፈ ሌላ ጉዞ በማዘጋጀት ላይ ነው፡፡ ይህ የንግድ ልዑክ ሐምሌ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ አስመራ በማቅናት ከኤርትራ ንግድ ምክር ቤት ጋር የመግባቢያ ሰነድ እንደሚፈራረም አቶ አሰፋ ተናግረዋል፡፡ የኤርትራ የንግድ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

‹‹የተበጠሰውን የንግድ ትስስር ለመቀጠል ጥረት ጀምረናል፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ንግድ ምክር ቤቶች በጋራ ብዙ ሊሠሩ ይችላሉ፡፡ የድንበር ንግድ አለ፡፡ ኢትዮጵያ የአሰብን ወደብ እንድትጠቀም ዝግጅት ተጀምሯል፡፡ ስለዚህ በጋራ የምንሠራቸው ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፤›› ብለዋል፡፡

ለጉብኝት ከተጓዙት ኢትዮጵያውያን ባለሀብቶች መካከል የአዲካ ቱር ኤንድ ትራቭል ኩባንያ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አዋድ መሐመድ፣ በቱሪዝም ዘርፍ ሁለቱ አገሮች ተባብረው ሊሠሯቸው የሚችሉት ሥራዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ የኤርትራ የቱሪስት መዳረሻዎች ከሰሜን ኢትዮጵያ ታሪካዊ ሥፍራዎች ጋር በቅንጅት የማስተዋወቅ ሥራ ሊሠራ እንደሚችል አቶ አዋድ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ‹‹በቱሪዝም ዘርፍ በሁለቱ አገሮች ትብብር ሊሠራ የሚችል ሰፊ የሆነ ዕድል ይታየኛል፤›› ብለዋል፡፡

የጎመጁ ኦይል ኢትዮጵያ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ የሺዋስ በኤርትራ ያሉ የንግድና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለመመልከት ወደ አስመራ መምጣታቸውን ገልጸው፣ ኩባንያቸው በኤርትራ የነዳጅ ማደያዎችን የመገንባት ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን ለመጠቀም ዝግጅት የጀመረች በመሆኗ፣ ጎምጁ ኦይል በአሰብ የነዳጅ ማደያ የመገንባት ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም የአየር መንገዱ ዋና ዓላማ ተቆራርጦ የቆየውን የኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝብ ማገናኘት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ አፍሪካን ከመላው ዓለም ሲያገናኝ ወንድም የሆነው የኤርትራ ሕዝብ በዚህ ተጠቃሚ ሳይሆን ቆይቷል፡፡ አስመራን የምናገናኛት ከአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በአምስት አኅጉሮች ካሉን 114 ዓለም አቀፍ መዳረሻዎች ጋር ነው፡፡ አሁን ኤርትራ ከዓለም ጋር ተገናኝታለች፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ተወልደ በአስመራ ቆይታቸው ከኤርትራ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነርሰዲን ኢብራሂም ጋር ሁለቱ አየር መንገዶች በጋራ ተባብረው በሚሠሩባቸው ጉዳዮች ላይ ተነጋግረዋል፡፡ አቶ ነርሰዲን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኤርትራ አየር መንገድ የረዥም ጊዜ ልምድ ካለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመንገደኛ ልውውጥ፣ በቴክኒክ ሥልጠናና በመሳሰሉት ጉዳዮች ተባብሮ የመሥራት ፍላጎት አለው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኤርትራ አየር መንገድ የ20 በመቶ ድርሻ ይገዛ እንደሆን ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ የተጀመረው ንግግር ተባብሮ አብሮ ለመሥራት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ለጊዜው እየተነጋገርን ያለው በጋራ ልንሠራቸው ስለምንችላቸው ሥራዎች ነው፡፡ ድርሻ የመግዛት ጉዳይ ወደፊት በሒደት የምናየው  ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልዑክን በመምራት ወደ አስመራ የተጓዙት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ ያባከኑት ሃያ ዓመታትን ለማካካስ ጠንክረው መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ሁለቱም አገሮች ተጎድተዋል፡፡ ኩብ ኩባና አንበጣ የበላውን ጊዜ፣ የደረሰውን ኪሳራ ለማካካስ እንደምንችል በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ ይህ ወርቃማ ቀን እንደሚመጣ አምን ነበር፤›› ብለዋል፡፡

በአፍሪካ ኅብረት የኤርትራ አምባሳደር አርዓያ ደስታ የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግሥታት አስከፊ የሆነውን የኋላ ታሪካቸውን ረስተው አዲስ ወዳጅነት፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ትብብርና ልማት ለማስፈን መስማማታቸውን ተናግረዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የኤርትራ አየር መንገድ ከአስመራና ከአሰብ ወደ አዲስ አበባ በረራ ለመጀመር ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡ አቶ ነርሰዲን ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የኤርትራ አየር መንገድ ከሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሳምንት ሦስት ቀናት ከአስመራ አዲስ አበባ በረራ ይጀምራል፡፡ ከነሐሴ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሳምንት ሁለት ቀናት ከአሰብ አዲስ አበባ በረራ እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች