Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየተጠለፈው ሚኒስቴር

የተጠለፈው ሚኒስቴር

ቀን:

የዳበረ የፖለቲካ ሥርዓት ባላቸው አገሮች ውስጥ፣ ፖሊሲዎችንና ሕግጋትን ማስቀየር የሚችሉ የዕውቀትም ሆነ የገንዘብ አቅም ያላቸው ተቋማት በመንግሥት የአሠራር ሥርዓት ላይ ተፅዕኖ በማሳደር በሚፈልጉት መንገድ የመንግሥትን አቅጣጫ እንዲቀየስ የሚያደርጉበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተዘርግቶላቸዋል።

የግል ጥቅማቸውን መሠረት በማድረግ የተደራጁ አካላት፣ መንግሥት ፍላጎታቸውን በሚያሟላ አኳኋን በአስፈጻሚውም ሆነ በሕግ አውጪው በኩል ተገቢውን ማዕቀፍ እንዲያዘጋጅ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በማፍሰስ ፍላጎታቸው የሚሳካበትን አግባብ በውትወታ (Lobby) ተፅዕኖ የሚያሳድሩ መሆናቸው ይታወቃል።

መንግሥት ባለበት ሕዝባዊ ኃላፊነት ምክንያት በአገሪቱ የበላይ ሕግ ማለትም በሕገ መንግሥት በተጣለበት ግዴታ ምክንያት የተለያዩ አካላት ተፅዕኖ ቢያበዙበትም፣ የሁሉንም ፍላጎት በሚያጣጥም መልኩ ለማስተዳደር ሲጥር ይታያል። ይህም ሲባል በእነዚህ አገሮች ውስጥ ጠንካራና ተናባቢ ተቋማዊ አደረጃጀትና አሠራር የተገነባ በመሆኑ ዕውቀትና ገንዘባቸውን በማፍሰስ ተጽዕኖ ለማሳደር ከሚተጉ ወትዋቾች ቡድኖች የሚመጣውን ግፊት የማኅበረሰቡን ጥቅም ባማከለ መልኩ፣ በተገቢው መጠን ማስተናገድ ያለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት ይወጣሉ።

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በዓለም ላይ ከተፈጠሩ የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክስተቶች በመነሳት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አገሮች በተለያዩ መስኮች የአሠላለፍና የአቋን ለውጥ አድርገዋል።

በተለይም የኅብረተሰባዊነትና የነፃ ኢኮኖሚ አስተሳሰቦች ጎልብተው በመውጣታቸው በርካታ ያላደጉ አገሮችን በኢኮኖሚና በፖለቲካ ያለመዳበራቸውን ሰበብ በማድረግ በአስተዳደር ሥርዓታቸው እንዲሁም በምጣኔ ሀብታቸው ላይ ጣልቃ በመግባት ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድረዋል።

ለአብነትም በአፍሪካ ውስጥ ባሉ ፈርጀ ብዙ እንቅስቃሴዎች ሉዓላዊ አገሮች በውስጣቸው ከሚከናወኑ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራት መካከል የድንበር ተሻጋሪ የንግድ ማኅበሮች ተፅዕኖ እጅግ የጎላ ነው። በዚህ የተነሳ አንዳንድ የንግድ ማኅበራት ከፖለቲካ አመራሩ ጋር በመቆራኘት የአገራቸውን ሀብት ከመበዝበዝ ባለፈ፣ ጥቅማቸው እንደሚነካ ሲገምቱ ፖለቲካዊ አሻጥር በማቀናበር እስከ መፈንቅለ መንግሥት የሚያደርስ ቀውስ ማስከተላቸው የሚታወቅ የታሪክ ክስተት ነው።     

ይህ ማለት ባላደጉት አገሮች ውስጥ ለማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት የሚሆኑት ድንበር ተሻጋሪ የንግድ ማኅበራት በአገራቸው በተዘረጋው ሥልጡንና ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት የፖሊሲ አቅጣጫዎች እንዲቀየሱለት በሰላማዊ መንገድ የሚጠይቅ ወትዋች አካል ሆኖ ይሠራል።

ኢትዮጵያ በዘውዳዊው አገዛዝ ሥርዓት ሥር በነበረችበት ወቅት፣ መንግሥት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች፣ ሕጎችና የሚተላለፉ ውሳኔዎች ከላይ ያለውን የገዥ መደብ ማለትም የከበርቴውን ፍላጎት የሚያስጠብቁ እንደነበሩ ይታወቃል። በመቀጠልም ወታደራዊው የመንግሥት ሥርዓቱት በተከተለው የኅብረተሰባዊነት ርዕዮተ ዓለም ምክንያት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች፣ ሕጎችና የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች በአብዛኛው የላብአደሩን ጥቅም ያማከሉ ናቸው በማለት ሲምል ሲገዘት መቆየቱ ዕሙን ነው። ከወታደራዊው መንግሥት ውድቀት በኋላ፣ ሥልጣን የያዘው የኢሕአዴግ መንግሥት፣ የአገሪቱን ማንነትን መሠረት ያደረገ ፌዴራላዊ አደረጃጀት አዋቅሮ የተለያዩ የሥልጣን ዕርከኖችን በማደራጀት ሕዝቦች እንዲተዳደሩ አድርጓል። በዚህም የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ሦስቱን የመንግሥት አካላት ተገቢውን ተቋማዊ ኃላፊነት በመደልደል አደራጅቷቸዋል።

በአሁኑ ወቅት የፌዴራል መንግሥቱ ከአቋቋማቸው አስፈጻሚ አካላት መካከል የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አንዱ ነው። ሚኒስቴሩም በማቋቋሚያው በባህልና በቱሪዝም ዘርፍ ያሉ የተለያዩ ተልዕኮዎች የተሰጡት ሲሆን ለእነኝህ ተግባራት አፈጻጸም የተለያዩ ፖሊሲዎችን በማዘጋጀት አፅድቋል። ፖሊሲዎቹም በሚኒስቴሩና በሥሩ በሚገኙ ሰባት ተጠሪ ተቋማት አማካኝነት እንደ ሚመለከታቸው መጠን እንዲፈጽሙ ይሠራሉ።

የባህል ፖሊሲው

      የአገሪቱ የባህል ፖሊሲ በ1990 ዓ.ም. ተዘጋጅቶ ፀድቆ የነበረ ሲሆን በይዘት ደረጃ በበቂ መልኩ ስትራቴጂዎችንና የፖሊሲ ማስፈጸሚያ ሥልቱን ያልዘረጋ በመሆኑ ሰነዱ ተሻሽሎ በ2008 ዓ.ም. እንደ አዲስ ተዘጋጅቶ ፀድቋል።

 ፖሊሲውም ባህል በምጣኔ ሀብትና ባህል በቴክኖሎጂ ሽግግር የሚኖረውን አስተዋፅኦ በማካተት (አሥራ ሦስት) ዋና ዋና የፖሊሲ ጉዳዮችንና ዝርዝር ማስፈጸሚያ ስትራቴጂዎች በመንደፍ ተዘጋጅቷል።

ከፖሊሲ ጉዳዮች አንዱ የባህል ተቋማት አወቃቀር የሚመለከት ሲሆን፣ የሚመለከታቸውን ባለድርሻና አጋር አካላትን ተሳትፎ በማጎልበት ዘርፉን ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ በማሰብ የኪነ ጥበባትና የባህል ምክር ቤቶች እንደሚቋቋሙ በፖሊሲው ተቀምጧል።

እነኝህ ምክር ቤቶች የተቋማትን አወቃቀር ሥርዓት ተከትለው ሲደራጁ በሚቀመጥላቸው ኃላፊነት መሠረት ዘርፉን በሚመለከት ለመንግሥት ተገቢውን ሙያዊ ምክር መስጠት፣ ዘርፉ ያጋጠመውን ተግዳሮቶች የሚፈቱበትን አግባብ ማሳየት፣ እንዲሁም ዘርፉ ከተለያዩ አካላት ጋር የሚኖረውን ቅንጅታዊ አሠራሮች የሚዘረጉበትን አግባብ እንዲመቻች የመፍትሔ አቅጣጫ እንደሚሰጡ በፖሊሲው ግምት ተወስዷል። እነኝህንም የባህል ተቋማት በባለድርሻዎች ተሳትፎ ለማቋቋም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሒደት ላይ ይገኛል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአገሪቱ የተፈጠረውን የለውጥ ጥያቄ ተከትሎ ገዥው ፓርቲ በመጋቢት 2010 ዓ.ም. አንዳንድ የመዋቅርና የሥልጣን ማስተካከያዎችን ማድረጉ ይታወሳል። በዚህም መሠረት አዲስ የተሾሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ካቢኒያቸውን ሲያዋቅሩ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቀድሞ ኃላፊዎችን በማንሳት በአዲስ እንዲተኩ አድርገዋል። አዲሶቹ ሚኒስትሮች በተለያዩ አስፈጻሚ አካላት ኃላፊነት የሠሩ በመሆኑ ዘርፉን በመረዳት በተገቢው ፍጥነት እንደሚያሻሸሉት ተስፋ ተጥሎባቸው ነበር።

ሆኖም ዘርፉ ከሚመራባቸው ፖሊሲዎች በተፃራሪ በመሥሪያ ቤቱ አዲስ ተሿሚዎች ላይ የባለ ድርሻ አካላት ውክልና በሌላቸውና የግል ዝናን ተገን ባደረጉ ውስን ሰዎች በሚደረግ ግፊት የተለያዩ አደረጃጀቶች እንዲዋቀሩ በመደረግ ላይ ይገኛል። ከእነኝህም መሀል በሚያዚያ 2010 ዓ. ም. እነኝህ ጥቂት የጥበብ ባለሙያ ነን የሚሉ አካላት ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አመራር ጋር በመሆን በባህል ዘርፍ አገራዊ አሰላሳይ ኮሚቴ (Think thank committee) አዋቅረዋል። ኮሚቴውም 11 አባላት ያሉት ሲሆን፣ ከባህል ዘርፍ ውስጥ የስነ ጽሑፍ፣ የሙዚቃና የሥነ ሥዕል ባለሙያዎች የሆኑ የከፍተኛ ትምህርት መምህራንና በግል ሥራ ከተሰማሩ ባለሙያዎች የተውጣጣ ነው። ከእነኝህ የኮሚቴው አባላት መካከል በአሁኑ ወቅት አራቱ ለሚኒስቴሩ ተጠሪ በሆኑ ተቋማት ኃላፊነት ላይ እንዲሾሙ ተደርጓል። በዚህም ምክንያት በሹመት ኃላፊነቱን የያዘው ውክልና አልባው ኮሚቴ በተቋሙ የፖሊሲ አቅጣጫዎችና የአሠራር ሥርዓቶች ውስጥ ጣልቃ በመግባት የሚኒስቴሩን ትላልቅ አገራዊ ፕሮጀክቶች በመጥለፍ እንዲሠራ በሚኒስቴሩ የበላይ አመራር ተወስኗል። ከዚህም ባለፈ ለሚኒስቴሩ ተጠሪ የሆኑት ተቋማት ኃላፊዎችና የመሥሪያ ቤቱ የተወሰኑ የሥራ ክፍሎች በሚሳተፉበት የፖሊሲ ኮሚቴ ውስጥ የአድራጊ ፈጣሪነት ሚና እንዲኖራቸው በማድረግ በዘርፉ የሚኖሩትን አቅጣጫዎች ላይ ተፅዕኖ በማሳደር የባህል ዘርፉን ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠሩት አስችሏቸዋል።

      መንግሥት አስፈጻሚ አካላትን በአዲስ መንገድ ሲያዋቅርና አዳዲስ የበላይ ኃላፊዎችን ሲሾም፣ በቀደሙት ኃላፊዎች ተገልለናል ወይም በቂ ትኩረት አልተሰጠንም የሚሉ የዘርፉ አቀንቃኞች በተቻላቸው አቅም አዲሶቹን ኃላፊዎች በመጥለፍ፣ ራሳቸውን እንደተበዳይ እንዲቆጥሩ በማድረግ የግል ፍላጎታቸውንና ሐሳባቸውን በመጫን ተቋሙን ለመዘወር እንደሚጥሩ ይታወቃል።

በዚህ መንገድ የቀረበው የባህል ዘርፍ አሰላሳይ ቡድን በኃላፊዎቹ ላይ በሠራው የውትወታ ተግባር ተሳክቶለት ያለምንም ልምድና የአገልግሎት ታሪክ የመንግሥትን ሥልጣን ለመቆጣጠር አስችሏቸዋል። በተለይ አንዱ ተሿሚ ከዚህ ቀደም በሌላ ተቋም በኃላፊነት ሲሠሩ የነበሩ ሲሆን፣ ከሕዝብና ከኪነ ጥበቡ ማኅበረሰብ በቀረበ ከፍተኛ እሮሮና የተቋሙን ሀብትና ንብረት ላይ ባስከተሉት ከፍተኛ ውድመት ከሥልጣናቸው በ2009 መጨረሻ ከኃላፊነት የተነሱ ሆኖ ሳለ በአሰላሳይ ኮሚቴ ውስጥ በመካተታቸው በሌላ ተቋም ዳግም በኃላፊነት እንዲሾሙ ተደርጓል።

ከላይ የተጠቀሱትን ግለሰብ ያካተተው ኮሚቴ ከምስረታው፣ ከውክልናውና ከስብጥር አኳያ በሚኒስቴሩ አዲስ ተሿሚዎች ይሁንታ ብቻ ተዋቅሮ ወደ ሥራ እንዲገባ የተደረገ ሲሆን በተቋሙ አሠራር ውስጥ በመግባት በባለድርሻ አካላት ነጥረው የተዘጋጁትን ፖሊሲዎች የሚቃረን እንዲሁም ይህን ፖሊሲ ለማስፈጸም ዕውቀትና ሀብት ፈሶበት የተዘረጋውን ሥርዓት የሚያፋልስና ዋጋ የሚያሳጣ ተግባራት እንዲፈጸሙ ተደርጓል።

በዚህም ምክንያት የባህል ዘርፍ ተግባራት በእነኝሁ አካላት ቁጥጥር ሥር እንዲገቡ ከመደረጉ በላይ በሚያቀርቧቸው የተለያዩ ጽሑፎች ምክንያት ፖሊሲዎቹ እንዳይተገበሩ እንቅፋት በመፍጠር ላይ ይገኛሉ። ስለዚህም የሚኒስቴሩ የባህል ዘርፍ ተቋማት ሹመትና አሠራር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በአሰላሳይ ኮሚቴው ፈቃድ ላይ አንዲያርፍ በመደረጉ ሚኒስቴሩ በእነኝሁ አካላት መጠለፉን በግላጭ የሚያሳይ ክስተት ሆኗል።

ከላይ በተብራራው እውነታ በአገራችን የተለመደ የአሰላሳይ ኮሚቴ አወቃቀርና ተግባር ያልተለመደ ቢሆንም መዋቅሩ ካለው ጠቀሜታ አንፃር በመንግሥት ፖሊሲዎችና አሠራር ላይ የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያሳይ አካል እንዲኖር ማድረግ ተገቢ ይሆናል። አሁን ባለን ልምድ እነኝህን ሙያዊ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን የሚያሳይ አካል በምክር ቤት በመዋቀር የባለድርሻና የአጋር አካላትን ተሳትፎ ለማረጋገጥ ተችሏል።

ስለዚህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ አገር በሚዘጋጁ ፖሊሲዎች የተለያዩ ምክር ቤቶች እንዲዋቀሩ የሚደረግ በመሆኑ፣ በፖሊሲ ይዘትነት እንደ አንድ መስፈርት እንዲቆጠር አስችሏል። በዚህ ምክንያት የባህልና የፊልም ፖሊሲዎችን በአግባቡ ተረድቶ ምክር ቤቶችን በማዋቀር ፈንታ፣ አሰላሳይ ቡድን ማቋቋም ከፖሊሲው መፃረር ከተጠያቂነት መርህ ያፈነገጠ ተግባር ነው። በመሆኑም የሚኒስቴሩ የበላይ አመራር ፖለሲዎችን ባለመገንዘብ ያዋቀሩትን አሰላሳይ ኮሚቴ በመበተን የፖሊሲዎቹን ይዘትና ማስፈጸሚያ ሥልቶቹን በተገቢው ደረጃ ተረድተው እንዲያስፈጽሙ ቢደገረግ የተጣለባቸውን መንግሥታዊ ኃላፊነት ለመወጣት እንደሚያስችላቸው ይታመናል።

(ሊቀመኳስ፣ ከባልደራስ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...