Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

እዚህ አገር ከርዕሶቻችን መካከል አንዱና ዋነኛው መሬት አይደል? እኔም ይኼንን መሠረታዊ ጉዳይ በተመለከተ ያጋጠሙኝን በቅደም ተከተል ልንገራችሁ፡፡ በአንድ ወቅት በሥራ ላይ ያለውን የሊዝ አዋጅ አስመልክቶ የተፈጠረው ግራ መጋባትና የተሰጡት ማብራሪያዎች መቼም አይዘነጉም፡፡ የሊዝ አዋጁ የይዞታ ባለቤትነት መብትን ከመጋፋቱም በላይ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን ሀብት የማፍራት እንቅስቃሴ ይገታል የሚሉ ክርክሮች ነበሩ፡፡ ‹‹መሬትን በሊዝ ሥርዓት በማስተዳደር የኪራይ ሰብሳቢነት እንቅስቃሴን በመገደብ ዜጎች እኩል ተጠቃሚ የሚሆኑበት ምኅዳር ይፈጠራል፤›› የሚሉ ግራ አጋቢ አመለካከቶችም ተሰምተዋል፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ውስጥ አዋጁ እንዴት በዘለቄታዊነት እንደሚፈጸም ግራ ያጋባል፡፡ የነባር ይዞታ ባለመብቶች ጥቅማቸውን በሚያሰሉበት መንገድ መንግሥትም የራሱን ድርሻ እያሰበ ስለነበር፣ የከተማ መሬት ገና ብዙ ጣጣ አለበት፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ከቢጤዎቼ ጋር ስንወያይ አንደኛው ጓደኛችን አንድ ሐሳብ አቀረበ፡፡ የመሬት ጉዳይን በተመለከተ መንግሥት የሚከተለው ፖሊሲ የሶሻሊስት ፍልስፍናን መሠረት ያደረገ በመሆኑና በሕገ መንግሥቱም መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው ተብሎ ስለተደመደመ፣ የሊዝ አዋጅ ቢኖር ባይኖር በነፃ ገበያ የኢኮኖሚ አስተሳሰብ ለመሞገት መነሳት ፋይዳ የለውም አለን፡፡ ‹‹መሬት የመንግሥት ነው በተባለበት አገር ውስጥ ስለግል ይዞታ በማሰብ ጊዜን ማጥፋት ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ነባርም በሉት አዲስ ዞሮ ዞሮ ለመንግሥት ግብር እስከተከፈለበት ድረስ፣ በማንኛውም ጊዜ የሆነ ሕግ ወይም መመርያ ቢወጣ ሊገርመን አይገባም፤›› አለ፡፡ ሰው የመሰለውን የመናገር መብት ስላለው በአንክሮ ሰማነው፡፡

ሌላው ጓደኛችን ግን የቀረበውን ሐሳብ በፅኑ ተቃወመው፡፡ በነፃ ገበያ ሕግ ኢኮኖሚውን እመራለሁ የሚል መንግሥት ከቶውንም የዜጎችን ነፃነት የሚጋፋ ተግባር ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ ነባር ይዞታ ያለው ሰው የሊዝ ሥሪት ውስጥ ሲገባ ንብረቱን መሸጥ ሲፈልግ እንኳ በወቅቱ የገበያ ዋጋ ጠቀም ያለ ጥቅም አያገኝም፡፡ ገዥው ለመሬቱ ተጨማሪ የሊዝ ክፍያ ስለሚጠየቅ ዋጋውን ያራክስበታል፡፡ መንግሥት በፈለገው ጊዜ ቦታውን እፈልገዋለሁ ካለ ወይም በወጣው የሊዝ ዘመን መሠረት ውሉ ከተጠናቀቀ ንብረቱን አፍርሶ እንዲነሳ ይገደዳል፡፡ ደረጃቸውን ያልጠበቁ በሚል በነባር ይዞታ ላይ የሚገኙ ቤቶች ሲፈርሱ በወቅቱ ዋጋ ካሳ አይከፈላቸውም፡፡ በእነዚህና በሌሎች ተዛማጅ ምክንያቶች ጉዳቶች ያጋጥማሉ አለን፡፡ የእዚህኛው ሐሳብም በሚገባ ተደመጠ፡፡ የማያባራው ክርክር ግን ቀጥሏል፡፡

የእኔና የሌሎቹ ጓደኞቼ ወግ ድንገት ሳናስበው ከከተማ መሬት ወጥቶ ወደ ገጠር መሬት ጉዳይ ገባ፡፡ አንዱ ጓደኛችን ኢትዮጵያ በዓለም የመገናኛ ብዙኅን በመሬት ወረራና ሽሚያ ስሟ ተነስቷል፡፡ ይህ ደግሞ አፍሪካን በልማት ስም ሊቀራመቱ ለመጡ ወራሪዎች እጅ እንደ መስጠት ይቆጠራል አለ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጥብቅ ደኖች፣ ፓርኮችና የአርሶ አደር መሬቶች ሳይቀሩ የእነዚህ አዳዲስ ወራሪዎች ሰለባ እየሆኑ ነው አለን፡፡ መሬት በገፍ የሚወስዱት ባዕዳን መሬቱን የሚያገኙት በሳንቲም ቤት እንደሆነ በኩራት መናገራቸው ያናድዳል ብሎን፣ ‹‹እነሱ ከማያመርቱት ምርት እሸቱን እንኳን የመቅመስ ነፃነት ስለሌለን ስለምግብ ዋስትና አፋችንን ሞልተን መናገር አንችልም ብሎ፤›› አሳረገ፡፡ በሚገባ አዳመጥነው፡፡ ተመሳሳይ ሐሳቦች ተዘረዘሩ፡፡

ሌላው ጓደኛችን ሌላ ሐሳብ አመጣ፡፡ አገሪቱ እጅግ በጣም ሰፊ ያልታረሰ መሬት እንዳላት፣ በመላ አገሪቱ በተለያዩ አቅጣጫዎች ብንጓዝ እንኳን ለውጭ አልሚዎች አይደለም ከእኛ ተርፎ ጦሙን የሚያድር በርካታ መሬት በመኖሩ መጨነቅ አይገባንም አለን፡፡ እኛ አቅም ከሌለን ካፒታልና ቴክኖሎጂ ያላቸው የውጭ ባለሀብቶች ሲመጡ በጣም ሰፊ መሬት ከመልማቱም በላይ የዕውቀት ሽግግር ይገኛል፡፡ ለአርሶ አደሩም ሆነ ለሌላው ሕዝብ የሥራ ዕድል ይፈጠራል፡፡ ከኤክስፖርት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይገኛል፣ ወዘተ አለ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰፊ ኢንቨስትመንት ሲፈጠር የአገር ውስጥ አልሚው ስለሚነቃቃ የምግብ ችግርን ለማስወገድ ይረዳል ብሎ አጠናቀቀ፡፡ እኛም በሚገባ ሰማነው፡፡ ሌሎች ተመሳሳይ ነገሮች ተባሉ፡፡ ክርክሩ መቋጫ ስለሌለው ሌላ ቀጠሮ ያዝን፡፡ ዕድሜ ለመከባበርና ለዴሞክራሲ በሰላም ተለያየን፡፡ በመሬት የተነሳ ስንት ተግባር በሚፈጸምበት አገር በሰላም መለያየት በራሱ ጥሩ ነው፡፡

ምሽት ላይ ቤቴ ገብቼ ለቤተሰቦቼ ስለውሎዬ ስነግራቸው ትልቋ ልጄ በጣም ሳቀች፡፡ ሳቋ ገርሞኝ ስለነበር፣ ‹‹ምን ያስቃል?››  አልኳት፡፡ አሁንም እየሳቀች፣ ‹‹በቃ እዚህ አገር ከጥንት ጀምሮ የያዘን የመሬት አባዜ አይለቀንም እንዴ?›› በማለት ጠየቀችኝ፡፡ ‹‹መሬት እኮ የምንኖርበትና ለኑሮአችን የምንጠቀምበት ስለሆነ ብንነጋገርበት ምን ይደንቃል?›› በማለት ቆጣ አልኩ፡፡ ‹‹አይ ዳዲ ለምን ትቆጣለህ? ኖረን ኖረን ተመልሰን የምንገባውም መሬት ውስጥ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ከመሬት በላይ ስለሌሎች ነገሮች ማሰብ ብንጀምር እኮ ባህሪያችንም ይቀየር ነበር፡፡ በመሬት የተነሳ ስንገዳደል መኖራችንን አትርሳ፡፡ አሁንም በመሬት በለው በብሔር የተነሳ ስንቶቻችን ሰላም አለን? መሬትን፣ ብሔርን ወይም ሌላ አጨቃጫቂ ነገሮች ትተን እስቲ ስለጠቃሚ ነገሮች ደግሞ እናስብ፤›› አለችኝ፡፡ አሁንም እየገረመኝ፣ ‹‹ለምሳሌ ስለምን?›› ማለት፡፡ ቆጣ እያለች፣ ‹‹ስለሰብዓዊነት፣ ስለመከባበር፣ ስለመፈቃቀር፣ ስለዴሞክራሲ፣ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ስለነገሩን ፍቅርና ይቅር ባይነት . . .›› እያለችኝ ስታፈጥብኝ ደነገጥኩ፡፡ ይኼም አለ ለካ?

በልጄ ማሳሰቢያ መሠረት እኔም ይኼንን ለማለት ፈለግኩ፡፡ ወገኖቼ በዚህ የመደመር ዘመን ከመሬት፣ ከድንበርና ከሌሎች ቁሳዊ ነገሮች በበለጠ የእኛ መተሳሰብ አይበልጥም? እኛ በብሔር ወይም በማንነት ምክንያት ስንጋጭ፣ መደማመጥ አቅቶን በነገር ስንቋሰልና ዓይንህን ለአፈር ስንባባል ዓለም ጥሎን ጭልጥ እያለ እኮ ነው? ሰብዓዊነት ከውስጣችን ነጥፎ በመሬትና በአስተዳደራዊ ወሰን አለመካለል ምክንያት ዓይናችን ደም ለብሶ ስንጋደል ያሳዝናል፡፡ ለሰላም በቀረበ ጥሪ ምክንያት ለሃያ ዓመታት የተለያዩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ቤተሰቦች እየተላቀሱ ሲገናኙ እያየን አብረን እያነባን፣ እኛ በተቃራኒው እርስ በርስ ካልተከባበርንና ካልተዋደድን ሰው የመሆናችን ትርጉሙ ምን ይሆን? እስቲ መጀመርያ እኛ ጥላቻና ቂምን እናስወግድ፡፡ ልባችንን ለፍቅርና ለይቅርታ ሳንከፍት ‹ተደምረናል› ማለት ቀልድ ነው፡፡ የገዛ ወገኖቻችንን ሳንወድ ኤርትራውያንን እንወዳለን ማለትም ከንቱ ነው፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግሮች እያጨበጨብን ከእሳቸው መልዕክቶች በተቃራኒ የገዛ ወገኖቻችንን መሳደብ፣ ማዋረድ፣ ማፈናቀል፣ አልፎ ተርፎም ማሰቃየትና መግደል ያሳፍራል፡፡ ‹ተደምረናል› እየተባለ ፀረ መደመር ተግባር መፈጸም ኩነኔ ነው፡፡ ኧረ እንታረም፡፡ 

(አቤል ሰፎንያስ፣ ከሲኤምሲ)   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...