Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክያለፈው እንዳይደገም የኢትዮጵያና ኤርትራን ግንኙነት በሕግ መደገፍ

ያለፈው እንዳይደገም የኢትዮጵያና ኤርትራን ግንኙነት በሕግ መደገፍ

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ኤርትራ በግንቦት 1983 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ተነጥላ ነፃ መንግሥት ከመሠረተችበት ጀምሮ ለተወሰኑ ዓመታት ሕግ፣ መንግሥታዊ ተቋም፣ ግልጽና የታወቁ መርሆች ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ሳይኖራቸው በመቅረቱ የተነሳ ውሎ አድሮ በቀላሉ ሊፈቱት ያልቻሉት ግጭት ውስጥ ከቷቸዋል፡፡

ኤርትራ ሕዝበ ውሳኔ ያከናወነችው በገሃድ ከኢትዮጵያ ከተነጠለች በኋላ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እስከዚያው ድረስ ግን ሁለት መንግሥታት ያሏቸው ነገር ግን እንደ ሁለት ሉዓላዊ አገሮች መሆን ያቃታቸው አገሮች ነበሩ፡፡ ይህ የሆነው በዋናነት ኤርትራ ከኢትዮጵያ በጦርነት ከተገነጠለችበት ጊዜ ጀምሮ ዓለም አቀፍ ሕግን መሠረት ያደረገ የሁለት አገሮች ግንኙነት ከመመሥረት ይልቅ በትግል ዘመን በነበረ ድርጅታዊና ግለሰባዊ ቀረቤታ ላይ የተንጠለጠለ መሆኑ ነው፡፡ የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የሁለቱም አገሮች መሪዎች መንግሥታዊና አገራዊ ግንኙነቶች ዲፕሎማሲያዊና ዓለም አቀፋዊ ሥነ ሥርዓቶችን በመዝለል በግል ግንኙነት ይጨርሱ ነበር፡፡  

እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ የግለሰቦቹ ግንኙነት ሲሻክር የአገሮቹም ግንኙነት መሻከርን የማስከተሉ መዘዝ ነው፡፡ እንደ ሁለት ሉዓላዊ አገሮች የድንበርና የንግድ ልውውጥ ጉዳዮችን በፍጥነት ሕጋዊ አለማድረግ ውለው ሲያድሩ በተለይም የመሪዎች ግንኙነት ሲቀዛቀዝ በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ዕድሎች ጠባብ ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራም በሰላሙ ወቅት በፍጥነት የድንበር ጉዳይን እልባት አለማበጀት፣ የገንዘብ አጠቃቀምን አለማስተካከልና ሌሎችም ጉዳዮች ጦሳቸው የሕዝቦች ዕልቂት ሆነ፡፡ ቀድመው አንድ አገር በነበሩበት ወቅት ኋላ ድንበር በሆነው አካባቢ የሚኖሩ ሁለት ግለሰቦች ቢጣሉ/ቢጋጩ ጉዳዩ የሁለት አገሮች ጉዳይ ይሆናል፡፡ ጦርነት ይቀሰቅሳል፡፡  የሆነው ሆኖ ኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ውስጥ ገብተው እጅግ የከፋ ደም አፋሳሽ ጦርነት አድርገው በአደራዳሪዎችና በሸምጋዮች አማካይነት ዕርቅ መፍጠር ሳይቻል ቀረ፡፡ በአልጀርሱ ስምምነት መሠረትም በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ውሳኔ ቢሰጥም፣ ሁለቱን አገሮች ወደ ሰለማዊ ጎረቤቶች ማድረግ አልተቻለም፡፡ ውሳኔውም ሳይፈጸም ቆይቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአልጀርሱ ስምምነት መሠረት በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የተሰጠውን ውሳኔ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚቀበልና ከኤርትራ ጋር አዲስ ግንኙነት ለመጀመር በመወሰኑ በአደራዳሪ፣ በሽማግሌና በፍርድ ቤት ውሳኔ ሰላም ማስፈን ተስኗቸው የነበሩ አገሮች በራሳቸው ሰላም በማስፈን ላይ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሚና ከፍ ያለ እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የሚዳሰሰው ነጥብ የሚሽከረከረው ሁለቱ አገሮች የጀመሯቸውን ግንኙነቶች በ1983 ዓ.ም. ጀምሮ ጦርነቱ እስከተቀሰቀሰበት ወቅት ድረስ እንደነበሩት ጊዜያት ያለ አካሄድ እንዳይደገም በሕግ የመቃኘት አስፈላጊነትን ማሳየት ነው፡፡

የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የበለጠ ለማደራጀት የሁለትዮሽ ስምምነት ማድረግ የአገሮቹን ግንኙነት የበለጠ ያጠነክረዋል፡፡ ስምምነት (ውል) ያዋድዳል ያፋቅራል እንጂ አያጣላም፡፡ እርግጥ በፍቅር ዘመንና ወቅት ሕግ ጥቅም የለውም፡፡ በመዋደድ ዘመን ገዥው ሕግ ሳይሆን ፍቅር ነውና፡፡ ፍቅር ሲጠፋ ግን ማጣፊያው ሕግ ነው፡፡ ሁለቱ አገሮች ድንበር ሳይኖራቸው በፍቅር ድልድይ መገናኘታቸው እጅግ በጣም ጥሩ ነው፡፡ የፍቅር ድልድዩን ለማጠንከር አለበለዚያም በአጋጣሚ ከተሰበረም የመጨረሻ መግባቢያ የሚሆን ሕግ ማበጀት ደግሞ የአባት ነው፡፡

የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ሕጋዊ ያለማድረግ ያስከተለው ጦስ

አዲስ አገርነት ብዙ ጣጣ አለበት፡፡ እንኳንስ አዲስ አገር ቀርቶ አዲስ ጎጆ ወጪም  የጎጆው ሽንቁር ስለሚበዛበት በአንድ ጊዜ መርጎና ደፍኖ አይጨርሳቸውም፡፡ አዲስ አገሮችም ገንዘብ ማሳተም አለባቸው፣ ለዜጎቻቸው ቀድሞ የነበራቸውን ገንዘብ መለወጥ ይኖርባቸዋል፣ የባንክና የንግድ ሁኔታዎችን ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል፣ የፀጥታ ተቋማትን፣ ዳኝነቱን፣ ፓርላማውን ማዋቀር ግድ ይላል፡፡ የውጭ ግንኙነትን ለማጠናከር ኤምባሲዎችን መክፈት፣ የትምህርት ሥርዓት መቅረፅ ሌላም ሌላም፡፡

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል የቀድሞ እናቷ ጥሩ ጎጆ አውጭዋ ስለነበረች ብዙ አልተቸገረችም፡፡ ‹‹የወንድ በር›› ሰጥታት ነበር፡፡ በአንድ ገንዘብ (በብር) ብቻ በመጠቀም፣ ግብይቱም እንደ አንድ አገር ብቻ ሆኖ ቀጠለ፡፡ የተለያዩ የጦር መርከቦች ሁሉ ሳይቀር በነፃ አገኘች፡፡ ሽሮውን በርበሬውን ከባሏ ደበቅ እያደረገች ለልጇ እንደምትሰጥ እናት ሆናት ነበር፡፡ ‹ራስሽን ቻይ! ብሩን፣ ቡናውንና ጤፉን ወዘተ. በቀጥታ ማግኘት ይቅርና እንደሌሎቹ ሉዓላዊ አገሮች ግብይቱ በዶላር ይሁን› ማለት ሲመጣ የድንበርና የመሳሰሉት ጣጣዎች መጡ፡፡

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል ወይንም በራሷ ነፃነቷን ካወጀችበት ከግንቦት 1983 ዓ.ም. ጀምሮ ራሷን መቻል ሲገባት፣ ሁሉ ነገር እንደሌላው ሉዓላዊ አገር መሆን እያለበትና የድንበርና ሌሎች ጉዳዮች መስመር መያዝ ሲገባቸው እንዲሁም ኢትዮጵያ የነበረባትን ዕዳ ኤርትራም በድርሻዋ መካፈል ሲኖርባት፣ በጦርነት የተገነጠለችን አገር እንደገና ሁለት ዓመት ጠብቆ ሕዝበ ውሳኔ ማካሄድ የይስሙላ የሕግ ሽፋን ለማግኘትና በሌሎች በሌሎች ጉዳዮች ሆን ብሎ ለመጥቀም የተደረገ ዕቅድ ካልሆነ በስተቀር ምንም የሚጠቅመው ነገር ወይም እንዲዋሃዱ ሊያደርግ ያስችላል የሚያስብል ጭላንጭል አልነበረም፡፡ በተለይ ይህ ሕዝበ ውሳኔ እስኪፈጸም ድረስ ያው የኢትዮጵያ አንዷ ክልል ነበረች ማለት ይቻላል፡፡ በእርግጥ ይህ ሁኔታ ከዚህም በኋላ ቀጥሎ ነበር፡፡ ጎጆ አውጭ ሆና ከርማለች ማለት ይቻላል፡፡ በሁለቱም በኩል ያለው ሕዝብም በመለያየቱ ብዙም ሳይከፋ ኖረ፡፡ ከዚያም የሁለቱም አገሮች መሪዎች የነበራቸው ‹‹የጫጉላ ሽርሽር›› ጊዜያት ሲያልቅ ጦርነት ተጀመረ፡፡ ይህ እንዳይሆን ወይም ለመቀነስ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ሕጋዊ መስመር ማስያዝ ያስፈልግ ነበር፡፡

የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ከፍቅርም ባለፈ በሕግ የማጠናከር ፋይዳ

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል መግለጫ (Declaration) እንዳደረጉ በመገናኛ ብዙኃን ሰምተናል፡፡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መዋዋያና ማጽደቂያ ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1024/2009 አንቀጽ 2 (2)  ላይ እንደተገለጸው፣ መግለጫ ማለት ‹‹ዓለም አቀፍ ስምምነት በሚፈረምበት ወይም በሚፀድቅበት ወቅት የስምምነቱ የተወሰኑ ድንጋጌዎች በኢትዮጵያ ላይ ተፈጻሚ የሚሆንበት የተለየ አካሄድ የሚመለከትበት ነው፤›› የሚል ትርጓሜ አለው፡፡ ከዚህ ብያኔ መረዳት እንደሚቻለው መግለጫ ዓለም አቀፍ ስምምነትን ታሳቢ ያደርጋል፡፡

ይሁን እንጂ በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረገ አዲስ ስምምነት የለም፡፡ ስምምነት ከሌለ ደግሞ በአዋጁ መሠረት የሚጸና መግለጫ አለ ማለት አይቻልም፡፡ ካልሆነ መግለጫው በአዋጁ ላይ የተሰጠውን ብያኔ ትርጉም አይኖረውም፡፡ በሌላ አገላለጽ መግለጫው የሁለቱ አገሮች መንግሥታት ወደፊት ስለሚያደርጓቸው ጉዳዮች ፍላጎታቸውን የገለጹበት እንጂ በአዋጁ እንደተመለከተው ዓይነት ትርጓሜ የለውም፡፡ ስለሆነም ሁለቱ አገሮች በአዲስ መልክ ግንኙነት ከጀመሩ ጀምሮ የተደረጉ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሉም፡፡ ይህ ከሆነ ዓለም አቀፍ ስምምነት ምን እንደሆነና እንዴት እንደሚደረግ በአጭሩ እንመልከት፡፡

ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በአገሮች የዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ  ወሳኝ ድርሻ አላቸው፡፡ የዓለም አቀፍ ሕግ አካል ስለሚሆኑም በችግር ጊዜ መፍትሔ ለመሻት በሕግነት ያገለግላሉ፡፡ አገሮች ያጋጠሟቸውንም ይሁን ወደፊት እንዳያጋጥማቸው የሚፈልጉትን ወይም እንዲሆን የሚሹትን በሁለትዮሽ ወይም ባለብዙ ወገን ውል ላይ ማስፈር የተለመደ ነው፡፡ ተዋዋይ ወገኖች ደግሞ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ አገሮችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ስምምነቶቹን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ሕግ የተለመደው አጠራር ‹ውል› (Treaty) የሚለው ነው፡፡ ውል (Treaty) የሚደረግበትን  (የሚቋቋምበትን) ሁኔታና ውጤታቸው ምን መሆን እንዳለባቸው የሚገዙ  ሌሎች  ዓለም አቀፍ ውሎች አሉ፡፡ የመጀመርያው በአገሮች መካከል ብቻ የሚፈጸሙትን የሚመለከት ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. የ1969 የቬና የውሎች ስምምነት ነው፡፡ ከ1980 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ ላይ ውሎ ተፈጻሚ እየሆነ ይገኛል፡፡ ከአንድ መቶ አሥር የሚበልጡ አገሮች ያፀደቁት ቢሆንም ኢትዮጵያ፣ እ.ኤ.አ. በ1970 ብትፈርምም እስካሁን ድረስ ተቀብላ አላፀደቀችውም፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በአገሮችና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወይም የዓለም አቀፍ ድርጅቶች እርስ በርሳቸው የሚዋዋሉበትን ሁኔታ ሥርዓት ለማስያዝ በ1986 ዓ.ም. የወጣው ሌላው የቬና  የውሎች ስምምነት ነው፡፡ ይኼን ስምምነት ሥራ ላይ ለማዋል ቢያንስ 35 አገሮች ተቀብለው ማፅደቅን ስለሚጠይቅና አሁን ላይ አንድ አገር ስለሚጎድል ገና ሥራ ላይ አልዋለም፡፡ ኢትዮጵያ የዚህ ስምምነት ፈራሚም አይደለችም፡፡ 

ኢትዮጵያ እነዚህን ስምምነቶች ቢኖሩም ባይኖሩም ውል የምትዋዋልበትን ሥርዓት የሚገዙ ተጨማሪ ሕጎች ሊኖሯት ግድ ነው፡፡ እዚህ ላይ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መዋዋል ሲባል የስምምነቶቹን ረቂቅ ማዘጋጀት፣ መደራደር፣ መፈራረም፣ ውሉን መቀበል፣ ውሉ የፀደቀበትን ሰነድ መለዋወጥ፣ የየአገሮቹ ሕግ አውጭ ምክር ቤት (ቤቶች) ስምምነቱን ያፀደቁበትን አሳትሞ ማውጣት ከመንግሥታት ወይም እንደ ሁኔታው ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የተደረገውን ውል በየአገሩ ሕግ መሠረት የተፈጸመና በሕግ የተደገፈ መሆኑን፣ ፈራሚው ባለሥልጣንም ውሉን ለመዋዋል ተገቢው ሥልጣን (በሕግ ወይም በውክልና ሙሉ ሥልጣን የተሰጠው) መሆኑን ማረጋገጥን ያካትታል፡፡ በዋናነት ዓለም አቀፍ ሕግ ተፈጻሚ የሚሆነው በአገሮች ላይ ነው፡፡ አገሮችም ከዚሁ ሕግ የሚመነጩ መብትና ግዴታ አላቸው፡፡ ለዓለም አቀፍ ሕግ ምንጭ በመሆን ከሚያገለግሉት ውስጥ ደግሞ በአገሮች መካከል የሚፈጸሙ ስምምነቶች ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እነዚህ ስምምነቶች በተለያየ ስያሜ ይጠራሉ፡፡ ስምምነት (Agreement)፣ ውል (Treaty)፣ መግለጫ (Declaration)፣ ፕሮቶኮል፣ ቻርተርና ኮንቬንሽን ወዘተ. እየተባሉ ሊጠሩ ይችላሉ፡፡ በእርግጥ ሁሉም አንድ ዓይነት ናቸው ማለት አይቻልም፡፡ አንዱ ሌላውን ተክቶ ጥቅም ላይ ይውላል ማለትም አይደለም፡፡

እነዚህ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እንደማንኛውም ውል፣ በነፃ ፈቃድና በቅን ልቦና ከተፈጸሙ ተስማሚዎቹ ላይ የአስገዳጅነት ፀባይ ይኖራቸዋል፡፡ አገሮች በነፃ ፈቃድ የሚዋዋሏቸው ከሆኑና የሕግነት ጠባይ ካላቸው የሚዋዋሉበት ሥርዓት መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ በመሆኑም ረቂቅ ውል ማዘጋጀት ወይም ሲዘጋጁ ተሳታፊ በመሆን መደራደርና ከድርድር በኋላ በሚኒስትሮችና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች የሚፀድቁበት፣ የሚሻሻሉበትና ቀሪ የሚሆኑበትን ሥርዓት መዘርጋት ተገቢ ነው፡፡

እንግዲህ ይህ ከላይ የተገለጸው አዋጅ፣ ኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስምምነት የምትፈርም መሆኗን በመግለጽ እነዚህ ስምምነቶች በሚደረጉበት ጊዜ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ መሆን ስላለባቸው ይኼን ለማድረግ እንዲቻል ከሕገ መንግሥቱና ከሌሎች ሕጎች ጋር የሚጣጣም ስምምነቶችን መደራደሪያ፣ መዋዋያ፣ መፅደቂያና ቀሪ ማድረጊያ ሥርዓቱን በማሻሻል አዋጅ ስለወጣ በዚያው መሠረት መፈጸሙ ሕጋዊነትን ማስፈን ነው፡፡ ማንኛውም የመንግሥት አካል ድርድር እንዲደረግ ሐሳብ ሲያቀርብ የሚመለከታቸው አካላትንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን አማክሮ ስለስምምነቱ ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያን ምን እንደሚጠቅማትና ምን ግዴታ እንደሚጥልባት የሚገልጽ ሰነድ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ማቅረብ አለበት፡፡ ድርድር የሚደረግበት ስምምነት የሌሎች ሕጎችን መሻሻል የሚጠይቅ ከሆነ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን  ማማከር አስፈላጊ ነው፡፡ ፀድቀው ሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ የክልሎችን አስተዳደራዊ ድጋፍ የሚጠይቅ ከሆነ ከፊርማ በፊት አስተያየት መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በስተቀር ወይንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኘበት ካልሆነ በስተቀር ድርድር ለማድረግ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ  የሙሉ ሥልጣን ውክልና ሰነድ ሊኖረው ግድ ነው፡፡ ድርድራቸው ያለቁ ስምምነቶች የኢትዮጵያን ጥቅም ያስከበሩ መሆናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው፡፡ ስምምነት የሚደረግባቸው ጉዳዮች ብድር፣ ዕርዳታና ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት የሚደረጉ ከሆነ ሒደቱን በሙሉ የሚከታተለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳይሆን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ነው፡፡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመፅደቅ የሚቀርብ ማናቸውም ስምምነት ከነአማርኛ ቅጂው፣ በጥቅል የስምምነቱና የድንጋጌዎቹ ማብራሪያና ረቂቅ ማፅደቂያ አዋጅ እንዲሁም ከተለያዩ አካላትና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጡ አስተያየቶችን ጨምሮ የተደራደረው አካል ማቅረብ አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ላይ የሚጥለው ግዴታና የሚገኘውን ጥቅም ማካተት አለበት፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ካፀደቀው ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይላካል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማፅደቂያ አዋጁ ላይ ስምምነቱ እንዲካተት ሊያደርግ ይችላል፡፡ ተከታትሎ የሚስፈጽመውንም አካል ይሰይማል፡፡ ከስምምነቱ ውስጥ ኢትዮጵያ ተዓቅቦ ያደረገችባቸውንና (ያልተቀበለቻቸው ድንጋጌዎች) መግለጫ (Declaration) ማለትም ስምምነቱን የተረዳችበትና የምትተረጉምበት ሁኔታ ካለም የማፅደቂያ አዋጁ ላይ መካተት አለባቸው፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቁ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተፈረመ  የማስፀደቂያ ሰነዱን አገሪቱ ተቀብላ ያፀደቀቻቸው መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመላክ ያስመዘግባል ወይም ለሚመለከተው አገር በመላክ ይለዋወጣል፡፡ የፀቀደቁ ስምምነቶችን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር  የማስፈጸም ኃላፊነት የተጣለበት አካልና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ማስፈጸም አለበት፡፡ የአፈጻጸም ሁኔታውንም በዓመት ሁለት ጊዜ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴርም ብድር፣ ዕርዳታና ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት ስለተፈረሙ ስምምነቶች እንዲሁ ሪፖርት ያቀርባል፡፡

እንግዲህ ዓለም አቀፍ ስምምነት የሚደረገው በአጭሩ ከእዚህ በላይ እንደቀረበው ነው፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነቶች ከላይ በቀረበው አኳኋን ሕጋዊ መሠረት ሊይዙ ይገባል፡፡ ለአብነት የኢትዮጵያና የጂቡቲን ግንኙነቶች ብንመለከት ብዙ ጉዳዮች ላይ የሁለትዮሽ ስምምነት በማድረግ የተደገፉ ናቸው፡፡ ከላይ ከተገለጸው ባለፈም ሁለቱ አገሮች የሚያደርጓቸው ስምምነቶች አፈጻጻማቸው ክልሎችን የሚመለከት ከሆነ የክልሎችን አስተያየት መጠየቅ እንደሚያስፈልግ አዋጁ ላይ ተገልጿል፡፡ የፌዴራል ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች ዓለም አቀፍ ስምምነትን በሚዋዋሉበት ጊዜ የክልሎች ሚና ግልጽ ነው፡፡ የፌዴራል ሥርዓትን የሚከተሉ አገሮች ሁለት የፌዴራል ሕግ አውጭ ምክር ቤት ያላቸው መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ውሎች ሲደረጉም ከክልሎቹ በኩል በመሆን የሚሳተፈው የላይኛው ምክር ቤት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ግን የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲህ ዓይነት ሚና ስለሌለው ስምምነቶች ሲደረጉ ክልሎችን የሚወክል አካል የለም፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ይመስላል አዋጁ አፈጻጸሙ የክልሎችን ድጋፍ የሚፈልግ ከሆነ ከሚመለከታቸው የክልል መንግሥታት አስተያየት መጠየቅ እንደሚያስፈልግ ተደንግጓል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ይኼ አንቀጽ በፌዴራሉ መንግሥት አተያይ የሚፀድቀው አዋጅ ክልል ላይ የሚፈጸም ሲሆን እንጂ ማንኛውንም ውል አይመለከትም፡፡ ለነገሩ፣ አስተያየቱን የሚሰጠው የክልሉ ሕግ አውጭ ምክር ቤት ይሁን አስፈጻሚው ግልጽ አይደለም፡፡ የተሰጠው አስተያየት  ውሉን ለማጽደቅ በሚወጣው አዋጅ ውስጥ ስለማይካተት ሕጋዊ ውጤት ሊኖረው አይችልም፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረው ጦርነትን ያስከተለው ግጭት በፍርድ ያለቀ ነገር ግን ገና ያልተፈጸመ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እንደ ውሳኔው ገና ያልተፈጸመው ዋናው ድንበር ማካለል ነው፡፡ ድንበር የማካለሉን ጉዳይ በሚመለከት ስምምነት የሚደረግ ከሆነ ስምምነቱ ሲፈጸም የአፋርና የትግራይ ክልልን ድጋፍ ሊጠይቅ ስለሚችል አዋጁ ላይ እንደተቀመጠው የሁለቱን ክልሎች አስተያየት አስቀድሞ መጠየቅ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡

በጥቅሉ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ጽኑ መሠረት ላይ ለማስቀመጥ የግንኙነት አለቶቹ በመሪዎች ብቻ ሳይወሰኑ ሕጋዊ ማድረጉ ግንኙነታቸውን ዘላቂ ለማድረግ ያግዛል፡፡ ከሁለትዮሽ ስምምነት ይልቅ በመሪዎች ስምምነት የሁለቱን ከቀድሞ ስህተትም መማር ነው፡፡

‹‹ፊርማና ወረቀት ቀሪ ነው ተቀዳጅ፤

መተማመን ብቻ ይበቃል ለወዳጅ›› ቢባልም

እውነታውና የበለጠ የሚጠቅመው ግን

‹‹ፊርማና ወረቀት ቢሆንም ተቀዳጅ

መተማመን ብቻ አይበቃም ለወዳጅ፤›› በሚል መተካት ነው፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...