Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉ በአግባቡ መጠበቅ ያለበት የመደመር ፍልስፍና

 በአግባቡ መጠበቅ ያለበት የመደመር ፍልስፍና

ቀን:

በሒሩት ደበበ

አንድ ችግኝ ተተክሎ ውኃ እየጠጣ አረሙ እየተነቀለለት፣ እየተኮተኮተ፣ በእንስሳት እንዳይበላም ሆነ በሰው እንዳይነቀልና እንዳይቀጠፍ ሲጠበቅ፣ ነገ ዛፍ ሆኖ ዘርፈ ብዙ ጥቅም መስጠት ይችላል፡፡ ለውጥና አዲስ አስተሳሰብም እንዲሁ ነው፡፡ ዘወትር እየተጠበቀ፣ እያደገ፣ እንክብካቤ እያገኘና ከአረም እየፀዳ ከሄደ ከራስና ከአገር አልፎ ለሌሎችም መትረፍ የሚችል ፍልስፍና ይሆናል፡፡ እኛም አሁን የተጀመረውን የይቅርታ፣ የፍቅርና፣ የመደመር መንፈስ በመደማመጥና ከስሜት በራቀ አግባብ፣ ብሎም ርካሹን የዜሮ ድምር ፖለቲካ ለመሰብሰብ ከመዳከር ወጥተን መጠበቅ ግድ የሚለን ጊዜ ላይ የመገኘታችን እውነት ፈጦ እየታየ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዋነኛ መተዳደሪያ ሰነድ የሆነው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ፀድቆ በሥራ ላይ ከዋለ ወዲህ አገራችን የተሻለ የዕድገት አቅጣጫ ብትከተልም፣ በሕዝባዊ አንድነትና በዴሞክራሲ ግንባታ ረገድ የተፈጠረው ክፍተት ቀላል እንዳልነበር በጥልቀት መገንዘብ እየተቻለ ነው፡፡ በቀድሞዎቹ ሥርዓቶች ምክንያት የብሔሮችና ብሔረሰቦች እስር ቤት እስከመባል ደርሳ የነበረችው አገራችን የሕዝቦቿ መብት የተረጋገጠባት፣ የዕድገትና የልማት ብሩህ ተስፋን የሰነቀች፣ የእኩልነትና የፍትሕ ምባ ለመሆን ትችል ዘንድም በተለያዩ ትውልዶች የተከፈለው መስዋትነት ቀላል አልነበረም፡፡ ነገር ግን የተጀመረው አዲስ መንግሥታዊ ሥርዓት የጥቂቶችና የአንድ ወገን (አንዱን አቅፎ ሌላውን አስኮርፎ) ከመምሰል ወጥቶ የብዙኃኑን ጥቅም በማስከበር ረገድ የታዩት ጉድለቶች፣ በትውልዱ አዲስ ለውጥ እንዲቀነቀን ከማነሳሳት የታደጉ አልሆነም ነበር፡፡ አሁን የተጀመረው ለውጥም ጥንስሱ የተነሳው ከዚሁ ነባራዊ ሀቅ ነው፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት በአገራችን የብሔር ብሔረሰቦች ባህል፣ ታሪክና ቋንቋ፣ የሕዝቦች መኩሪያና መከበሪያ፣ ብሎም መድመቂያ ጌጥና የመልካም ገጽታዋ መገለጫ እየሆነ መምጣቱ ባይካድም፣ ‹ልዩነት ጌጥ ነው› በሚል ብሒል ብቻ አብሮነታችን ክፉኛ ተጎድቶ አንዱ ሌላውን ‹‹የእኔ አይደለህም ዘወር በልልኝ!›› ብሎ እስከማሳደድ ደርሷል፡፡ ይህን አደጋ ለመመከት ደግሞ የተረሳውን አንድነት ማንሳት እጅ አስፈላጊ ነበር፡፡ ዕድሜ ለዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ይሁንና የመደመርና የአንድነት መንፈስን ማቀንቀን ባይጀመር ኖሮ በዚህ ረገድ የገጠመው ፈተና በቀላሉ የሚታለፍ አልነበረም፡፡ እነሆ ታሪክ ተቀየረና በፍቅርና በይቅር መባባል አይደለም፣ በአንድ አገር ያለነው ሕዝቦች ትናንት ከተለያየናቸው ከኤርትራውያን ወገኖቻችን ጋር በጋራ ለመድመቅና ለመሰባሰብ የቻልነውም፣ በዚሁ ከፍ ያለ ሥፍራ በሚሰጠው አመራር መሆኑ ደምቆ ሊጻፍ የሚችል ነው፡፡  

ባለፉት ጊዜያት የተለያየ እምነትና የአኗኗር ዘይቤን የሚከተሉ የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመግባባትና በመረዳዳት ምትክ የተናጠል ሥልጣንና ወሰን፣ አጀንዳ እንዲያቀነቅኑ የተፈቀደ መስሎ ቆይቷል፡፡ አንድነትና አብሮነት፣ እንዲሁም የጋራ እሴቶች የሌሉ ይመስል የአገራችን ሕዝቦች ለዘመናት አብሮ በመኖር በዓለም የሚታወቁበት የመቻቻል ባህልም፣ ከመቼውም በላቀ ሁኔታ እያሽቆለቆለ የመጣውም ለዚሁ ነበር፡፡ ታሪካዊ፣ ባህላዊና መንፈሳዊ ብሎም ሃይማኖታዊ የጋራ እሴቶቻችን ለአገራችን ተጨማሪ ክብርና ሞገስ ከማላበስ አልፈው ለፈጣን ልማትና ብልፅግና በማዋል ረገድ የነበሩብን ክፍተቶችም ግልጽ በመሆናቸው፣ ከመገፋፋትና ከጥላቻ ወጥተን በበጎና በቀና መንፈስ ለሕዝቦች ብልፅግናና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጠንክረን መሥራት ይገባናል፡

ለዚህም የተጀመረው የመደመርና የመተባበር መንፈስ በቋሚነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁላችንም የበኩላችንን ልናበረክት ግድ ይለናል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከአገራቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሕይወት ተገልለው ለመኖር የተገደዱበት አድሏዊና ፍትሕ አልባ አካሄድ እንዳይኖር በጋራ መታገሉ ብቸኛ አማራጭ ነው፡፡ አንዱ ገራፊና አሳዳጅ፣ ሌላው ተሳዳጅና ባዕድነት የሚሰማው፣ አንዱ የቤት ልጅና በየሁኔታው ያሻውን የሚፈተፍት፣ ሌላው አኩራፊና ካሰኘውም አደናቃፊ ሆኖ የሚቀጥልበት አገር ሊኖረን አይችልም፣ አይገባም (በእርግጥ አሁንም አንዳንድ ጦማርያንና አርቲስት ተብዬ የአስተሳሰብ ድንክዬዎች በዚህ ረገድ ሌላ ባለተራ እንዲፈጠር ሲዳክሩ መታየታቸው አደብ እንዲይዝ መደረግ ይኖርበታል)፡፡ በመሆኑም ባለፉት ጊዜያት እንደ አገር በጀመርነው አዲስ ሥርዓት ውስጥ የነበሩና ቀስ በቀስ እያቆጠቆጡ የመጡ ክፍተቶችን በማረም፣ ዜጎች በማንኛውም አገራዊ ጉዳይ ውስጥ እኩል ተሳታፊ የመሆን ዕድል ማግኘት አለባቸው፡፡ ጎን ለጎን የሕግ የበላይነትም ሳይዛነፍ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

ይህንኑ አጥብቆ የመሄድ ጉዳይም ለነገ ሊባል አይገባም፡፡ ይህን ዕድል በተጨባጭ ሥራ ላይ በማዋል የአገሪቱንና የሕዝቦችን የማደግና የመበልፀግ ተስፋ እጅግ እያለመለሙ መሄድ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም በሁከትና በትርምስ የከረመውን የዞረ ድምር ለመመለስም ሆነ ፖለቲካዊ ቁማር ለመጫወት መሞከር የሚያስከፍለው አገራዊ ዋጋ መክበዱ አይቀርም፡፡ መላው የአገሪቷ ሕዝቦች ለመብቶቻቸው በባለቤትነት እየታገሉና ዘላቂ ጥቅሞቻቸውን እያስከበሩ በፈጣን ልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቅጣጫ ላይ የተያያዙትን ፈጣን የዕድገት ጉዞ አጠናክሮ ለመቀጠልም ቢሆን፣ ብቸኛውና ጠቃሚው መንገድ ይቅር ባይነቱ፣ ፍቅርና አንድነት ብቻ ሳይሆኑ የአገር ፍቅር ስሜትንና መደማመጥን ማስፈን ሊሆን ይገባል ባይ ነኝ፡፡  

የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል› እንደሚባለው አሁን በአገሪቱ የሚታየው የለውጥ መዘውር ደግሞ በመንግሥት አካላት ብቻ ሳይሆን፣ በራሱ በሕዝቡና በአዲሱ ትውልድ መመራቱ የሚያኮራ ነው፡፡

ይኼ አካሄድም የበርካታ የአገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃንን ቀልብ ከመሳብ አልፎ፣ በአርዓያነት እየተጠቀሰና በሞዴልነትም እየተወሰደ መሆኑን ያለፉት የአዲሱ አመራር 100 የሥራ ቀናት ብቻ መመልከት በቂ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ አሁንም ፊት ለፊት ተጋፍጦ ማሸነፍ የሚያስፈልጋቸው መሰናክሎችን መዘንጋት ግን ተገቢ አይሆንም፡፡ ቀዳሚው ጉዳይ ነገሮችን አሁንም ወደ ጥላቻ ፖለቲካና የሕዝብ ለሕዝብ ግጭት የመውሰዱ ስንኩል አካሄድ ሲሆን፣ ሁለተኛው ወደ ተሻገርናቸው የጠባብነትም ይባሉ የትምክህተኝነት አስተሳሰብ አዙሪት በመመለስ ያልተገባ ጥቅምን ለማስከበር የሚደረገው መንፈራገጥ በሕዝብ ትግል እንዲቆም መደረግ ይኖርበታል፡፡      

በዚህም ላይ ለልማትና ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ አጥብቆ መረባረብ ግድ የሚል ይሆናል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለው ተስፋ መቀየር የጀመረው የዴሞክራሲ ገጽታችንን የሰብዓዊነት መብት አያያዝ ሁኔታችንን ወይም ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱን ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁንም ላለፉት ሦስት ዓመታት እንደ አገር የገጠሙንን ፈተናዎች በይቅርታና በፍቅር ከመፍታት ባሻገር፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በመሩት የሰላም ጥሪ የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች (እስካሁን ብዙ ተሞክሮ ያልተሳካውን) ሰላምና አንድነትን መላበስ መጀመራቸው ነው፡፡ በተለይ ከሰሞኑ በጉልህና በአደባባይ እንደታየው የኤርትራ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በሰላማዊ መንፈስ ሕዝቡን መገናኘታቸውና በድጋፉም መደነቃቸው ነው፡፡ ይህ አብነታዊ የፖለቲካ ሥልጡን ዕርምጃና መተሳሰብ ደግሞ ተመሳሳይ እምነት፣ ባህልና ቋንቋ ብሎም ትውፊቶች ያላቸው የሁለት አገር አንድ ሕዝቦችን ጥቅም በማስከበር የተሻለ ቀጣና ለመፍጠር የሚያስችል ነው።

ለወደፊቱም በአገራችን ዕውን የሆነው አዲስ ሥርዓት ለአገራችንና ለቀጣናችን አንድነት፣ ሰላምና ዕድገት መጠናከር ወሳኝ አስተዋፅኦ እያበረከተ ሊሄድ የሚችለው ወደኋላ በመመለስ ሳይሆን፣ ለወደፊቱ በመደመርና በአንድነት መንፈስ በመንጎድ ብቻ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ አዲስና በሕዝባዊ ድጋፍ የታጀበ የለውጥ ጉዞ የማይዋጥላቸውና የሚያሠጋቸው ኃይሎችና ወገኖች የተስፋውን ብርሃን እስከ ማጨለምና ጉዞውን እስከ ማደናቀፍ የሚደርስ መንፈራገጥ ማድረጋቸው የሚቀር አይደለም፡፡

ይኼ ደግሞ የማይለወጠው ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው፡፡ ይኼንንም የተዛባ አካሄድ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ታግሎ የሚጥለው ሕዝቡ እንደሆነ መዘንጋት ግን ከሞኝነትም በላይ አላዋቂነት ነው፡፡ ስለሆነም ፈተናውን ለይቶ አቅጣጫ ማሳየትና ነገሮችን በቅንነት ብቻ በማየት ውድቀት እንዳይከተል ዙሪያ ገባውን ሁሉም በጥንቃቄ እንዲመረምር ማድረግ ያስፈልጋል፣ ይገባልም፡፡

በመሠረቱ ላለፉት 27 ዓመታት ሕገ መንግሥቱ ፀድቆ በሥራ ላይ ከዋለ ጀምሮ አገራችንና ሕዝቦቿ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ መስኮች የተለያዩ ተግባራትን  አከናውነዋል፡፡ እነዚህን ውጤቶች ግን ምልዓተ ሕዝቡን በማርካትም ሆነ ወዳጅና ጎረቤት አገሮችን በማሰባሰብ ረገድ የራሳቸው ተግዳሮቶች አጋጥመዋቸዋል፡፡ አሁን ያለውን ወጣት ኃይል የልማት፣ የዴሞክራሲና የፍትሕ ጥያቄ በመመለስ ረገድም ቀላል የማይባሉ ችግሮችን ለመፍታት አላስቻሉም ነበር ማለት ስህተት አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም ሕዝብ በመራው ትግል እስካሁን የተገኙትን ተስፋ ሰጪ ዕርምጃዎች አቅቦ ለመጓዝና አዳዲስ ድሎችን እያስመዘገቡ ለመቀጠል፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥትና መላው ሕዝብ በላቀ ቁርጠኝነት እየተረባረቡ መገኘት ግድ ብሏቸዋል፡፡ ይኼው ጥረትም ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ሲባል ሁሉም በየደረጃው የድርሻውን እየተወጣ መሆን አለበት፡፡

በሌላ በኩል በሰላምና የፖለቲካ መረጋጋት ብቻ የማይፈታው የአገሪቱ ችግር አሁንም ፈጣን ልማትና ያልተቆረጠ ዕድገት የሚሻ የመሆኑ ጉዳይም ሊጤን ግድ ይላል፡፡ እስካሁን አገራችን በሁሉም የልማት ዘርፎች ዕድገት ብታስመዘግብም፣  የዕድገት መገለጫዎቹ ሕዝቡን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው ለማለት አያስደፍርም ነበር፡፡ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ተጠቃሚነት ነበር ማለትም እጅግ አዳጋች ነበር፡፡ የሕዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነት አለመኖር ወይም መጓደል ደግሞ የአገራችንን ዕድገት የሚያደናቅፍ ብቻ ሳይሆን፣ እርስ በርስ የሚያባላም መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ሀቅ ነው፡፡ ለዚህም ይመስለኛል አሁን በዶ/ር ዓብይ የተጀመረው የመደመር ፍልስፍና በፍቅር የእኔነት መንፈስን የመገንባት አካሄድ የሕዝቦችን  ያለፉ መጥፎ ዝንባሌዎችና አስተሳሰቦችን የሚሽር ከመሆኑም በላይ፣ መፃኢ ዕድላቸውን ብሩህ እያደረገ እንደሚሄድ በጉልህ ተስፋ ተጥሎበት የሚገኘው፡፡

አሁንም ግን አዲሱን የይቅርታና የመደመር አስተሳሰብ ሚናና ፋይዳ የሚያኮስሱና የሚያደናቅፉ፣ ብሎም ተጨማሪ ትግል የሚጋብዙ ፈታኝ የአስተሳሰብ ተግዳሮቶች መፈጠራቸው አይቀሬ ነው፡፡ አንዳንዱ ፍልስፍናው የሕግ የበላይነትን እንደሚጥስ፣ የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ላይ እንደሚጥል፣ አናሳውን ሕዝብ እንደሚጨፈልቅ ሊያቀነቅን ይዳዳዋል፡፡ ሌላው የአገሪቷ ሉዓላዊነት አደጋ ላይ እንደወደቀ፣ በመተባበር ስም ሌሎች ጥቅማችንን እንደሚሻሙት ወይም ለምዕራባዊያን ተፅዕኖ እንደተንበረከክን ሊወስዱት ያምራቸዋል፡፡ አለፍ ሲልም በድሮ በሬና ሕዝቡ ባልተደሰተበት አካሄድ ለመንገታገት የሚሻውም ቁጥሩ ትንሽ አይደለም፡፡ እነዚህን እጅግ የተራራቁ አስተሳሰቦችን ማቀራረብ ብሎም ማስተካከልና ወደ ቀናው መንገድ ማምጣት የሚቻለው ግን ፌዴራላዊ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መንፈስ ሁሉን አሳታፊ፣ የሠለጠነና ዴሞክራሲ ባህል እየገነቡ ሰላምን በመጠበቅ ብቻ መሆኑን በተግባር ማሳየትና የድርሻን ማበርከት፣ የሁሉም ዜጋና የመንግሥት ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል፡፡

መሰመር ያለበትም ይህ ለውጥ የአዲሲቷ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሕገ መንግሥቱ እየተመራ ወደ አዲስ ምዕራፍ በመሸጋገር ያመጣው ለውጥ የመሆኑ እውነታ ነው፡፡ የትናንትም ሆነ የዛሬ የታሪክና የጥቅም ቅራኔዎችን ወደ ኋላ በመተው፣ መደመርና ይቅር በመባባል መንፈስ ወደፊት እየገሰገሱ መሄድ የሚያስፈልገውም ለዚሁ ነው፡፡ ለዚህ ሕዝብ ትናንት ታሪክ ሲሆን፣ ነገ ደግሞ አዲስ ዕለት ነው፡፡ ወደ አዲስ ማንነት የሚሸጋገርበትና ባለፉት 27 ዓመታት ገደማ የተጓዘባቸውን መንገዶች እያስታወሰና ድክመት ጥንካሬያቸውን እየፈተሸ፣ ነገ የህዳሴውን ማማ ዕውን ለማድረግ ዛሬ ላይ የሚተጋ ትውልድ መሆን ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አሁን የተጀመረውን የይቅርታ፣ የፍቅርና፣ የመደመር ፍልስፍና በሁሉም ልብ ውስጥ እንዲሰርፅ ከማድረግ ባሻገር እንዳይደናቀፍ ማድረግ ወሳኝ ተግባራችን ሊሆን ይገባዋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...