Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየትኛዋ ኢትዮጵያ በየትኛው ሰንደቅ ዓላማ ትገለጽ?!

የትኛዋ ኢትዮጵያ በየትኛው ሰንደቅ ዓላማ ትገለጽ?!

ቀን:

በሪያድ አብዱል ወኪል

እንደ መንደርደሪያ ይህ ጽሑፍ በሐሳብ ደረጃ ከተፀነሰ ቢሰነብትም፣ ሁኔታዎች ሰከን እስኪሉና ለመግባባት የመነጋገሩ ድባብ እስኪመለስ መጠበቁ አስፈላጊ ስለነበር ዘግየት እንዲል ተደርጓል፡፡ በአንድ በኩል በአገራችን የፖለቲካ ትርክቶች ውስጥ ለረዥም ጊዜ የቆየው፣ ከሞላ ጎደል እንደማያዛልቀን የተስማማንበት፣ ከፊሉን የኅብረተሰብ ክፍል በመሥራችና ቀዳሚ ተቆርቋሪነት አቅፎ ቀሪውን ኢትዮጵያዊ ከእነ ብሔርና ሃይማኖታዊ ማንነቱ የሚገፋው የ‹‹ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት›› ትርክት ዳግም በከፍተኛ ጉልበት እያንሰራራ መጥቷል፡፡ በሌላኛው ጫፍ ከኢትዮጵያዊነቴ በፊት የብሔር ማንነቴ ይቀድምብኛል የሚለውና በተቃራኒው ጎራ ባሉ ብሔርተኞች ‹‹ጠባብ ብሔርተኛ›› ተብሎ የተሰየመው አካልም፣ ምንም እንኳ አሁን ባለው የፖለቲካ ድባብ ውስጥ ሐሳቡን የመግለጽ መብቱን በሕግ ሳይሆን በጊዜያዊ ኅብረተሰባዊ ጫና ሳቢያ የተነጠቀ ቢመስልም ቁጥረ ብዙ ስለመሆኑ አያጠያይቅም፡፡

በእነዚህ ሁለት ጫፎች መካከል ሽብልቅ ሆኖ ኢትዮጵያዊነትን ‹‹በአሰባሳቢ ማንነት›› የሚመለከተውና ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው የኅብረተሰብ ክፍል የግራና ቀኙ ሆይ ሆይታዎች (Mobs) ሰከን ብለው የውይይትና መነጋገሪያው ‹‹መድረክ›› እስኪገኝ ድረስ፣ በዝምታዊ ትዝብት ውስጥ ተሸብቦ እንዲቆይ ያደረገው ይመስለኛል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አሰናጅም ከዚሁ ጎራ ውስጥ ራሴን ስለመደብኩት ይኼንኑ ለመነጋገር፣ በእኔ ምልከታ ተሳስቷል የምለውንና ግለሰቦች ኢትዮጵያን የተረዱበትን የተሳሳተ አዝማሚያ ለማረም ጊዜው የደረሰ ይመስለኛል በሚል ሐሳቤን ‹ይድረስ ለሪፖርተር› ብያለሁ፡፡

ብሔርተኝነት የትኛውንም ዓይነት መልክና ስያሜ ብንሰጠውም ያው ከብሔርተኝነት እንደማይዘል አምናለሁ፡፡ ለእኔ ኢትዮጵያዊው ብሔርተኝነትም ሆነ አሁን ስሙን ቀይሮ በ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት›› መለዮ ከኢትዮጵያዊነት በመለስ የሚቀነቀነው የዘውጌ ብሔርተኝነት፣ ግባቸው ተመሳሳይ ነውና ትርፋቸው አይታየኝም፡፡ ሁለቱም አጓጉል ትምክህቶችና የዛሬም፣ የነገም ችግሮቻችን ናቸውና ለኢትዮጵያችን አያስፈልጓትም ብዬ እሟገታለሁ፡፡

አሮጌው የኢሕአዴግ አመራር እንደ ድርጅትም እንደ መንግሥትም የብዝኃነታቻችንን ያህል አንድ በሚያደርጉንና የጋራ በሆኑ እሴቶቻችን ላይ መሥራት ባለመፈለጉና መሥራትም ባለመቻሉ የታሪክ ፈተናውን ወድቋል፡፡ በ‹‹ትምክህተኝነት›› እና በ‹‹ጠባብነት›› ሲፈርጃቸው የነበሩና አሁንም ህያው ሆነው ያሉ አመለካከቶች ግን ለዛሬይቱም፣ ለወደፊቷም ኢትዮጵያ ችግር ሆነው መቀጠላቸው እንደማይቀር አምናለሁ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ለደፋር ውይይትና ለዘላቂ መፍትሔ መነሾ እንዲሆነን የፈለግኩት፣ አሁን ኢትዮጵያ ብለን እየገለጽናት ያለችው ኢትዮጵያ ላይ የጋራ መግባባት እንዲኖረን አመለካከቴን በማስቀመጥ ነው የምጀምረው፡፡

በዚህ ረገድ ተሸነፈ ያልነውና በእርግጥም በብዙዎች መስዋዕትነት የተሸነፈው የፀረ ዴሞክራሲ አካሄድና የሕገ መንግሥታችን ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ትርጉም ያልገባን ግለሰቦችና የሁሉም ዘርፍ የመገናኛ ብዙኃን አባላት፣ ‹‹እኔ የምዘምረውን ካልዘመርክ አልሰማህም!›› ይሉትን የተለየ አመለካከት ያለማስተናገድ ‹‹ሐሳብ›› ወጥተን፣ መድረኩን ለሁሉም ሐሳቦች ክፍት ለማድረግ ልባችንን እንድንከፍት እመክራለሁ፡፡ በተለይ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የተለየ ሐሳብ የያዘውን በሙሉ ለመስማት ያለመፈለግና የመፈረጅ አደገኛ አካሄድ እንደከዚህ በፊቱ ሁሉ አምባገነንነትን እንዳያዋልድ እሠጋለሁ፡፡ የሐሳብ ገበያው መርህ ሐሳቦች ሁሉ ይገለጹ፡፡ ለምርጫም ይቅረቡና የተሻለው ሐሳብ ያሸንፋል (The best ideas will win.) የሚል ነው፡፡

የትኛዋ ኢትዮጵያ?!

አገራችን ኢትዮጵያ በየወቅቱ በተለያዩ ስያሜዎች የምትጠራና የምትታወቅ ብትሆንም፣ በዓለም ላይ ቀዳሚ ሥልጣኔ ከነበራቸውና ገናና ከነበሩ መንግሥታት ጎራ የምትደመር ናት፡፡ የሩቁን አፋዊና ትውፊታዊ ትርክት ለጊዜው አቆይተነው የቅርብ ጊዜውን ስንመለከት፣ ዘመናዊ መንግሥታዊ ሥርዓት ያላትን ኢትዮጵያ የመፍጠሩ ቴዎድሮሳዊ ሕልም በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዕውን ሆኖ ይታየናል፡፡ ይህች ኢትዮጵያ በዳግማዊ ምኒልክ አሁናዊውን ቅርፅ እንድትይዝ ሲደረግም ከዲፕሎማሲው ጀምሮ እስከ የማስገበሩ ጦርነት ድረስ ያሉ መንገዶች ሁሉ ተተግብረዋል፡፡

አንዳንድ ምሁራን ይህንን የማስገበርና የማዋሀድ (Unification) ጦርነት ‹‹ወረራ›› የሚሉበት ምክንያትም የማማከሉና ዘመናዊ ሥርዓተ መንግሥትን የመፍጠሩ ጥንስስ እንዲሰምር፣ የየራሳቸው አስተዳደራዊና መሰል ሥርዓቶች ውስጥ የነበሩ ሕዝቦችን ያመሳሰሉ በመሆናቸው ሲሆን፣ ይህም በኋላ ላይ በደቡብ ኢትዮጵያና በመላው ኦሮሚያ ላይ ችግር የፈጠረ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የዚህ ተማስሎ መፍጠሩ የመጨረሻ ግብ በቋንቋ፣ በባህልም ሆነ በእምነት ምን ዓይነት ዜጋ መፍጠር እንደነበር መካድ አይቻልም፡፡ እዚህ ላይ አንድ ማሳያ ብጠቅስ እወዳለሁ፡፡ በመጨረሻው ንጉሥ ዘመን የአማርኛና ትግርኛ መዝገበ ቃላትን ያሰናዱት አባ ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር የተባሉ ሰው በቃላት መፍቻው ‹‹የሰላምታ መቅድም›› ላይ፣ በቋንቋ መለያየት ምክንያት ባቢሎን እንዴት እንደፈራረሰች በመጥቀስ ‹‹ለአገራችን አይጠቅማትም የቋንቋ ብልፅግና፣ አንድ ንጉሣዊ አፍ ብቻ ይበቃታልና!›› ብለው በድፍረት ጽፈዋል፡፡

በኢትዮጵያችን ብዝኃነታችንን አጥንቶ እርግጠኛውን ቁጥር የነገረን ባይኖርም ከሰማንያ እንደምንልቅ፣ እንዲሁም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ተወካይ ያላቸው ከስልሳ በላይ ስለመሆናቸው ሰምተናል፡፡ ኢትዮጵያውያን የአንዲት እናት አገር ዜጎችና ሕዝቦች ብንሆንም አንድነት ማለት ‹‹አንድ ዓይነትነት›› ማለት አይደለምና ከዚያ በመለስ የተለያዩ ማንነቶች ያሉን ሕዝቦችም ነን፡፡ ይህ ዓይነተ ብዙነት ወደ ውህደት ሲመጣ ያምራልና ነው፡፡ በብዝኃነታችን ውስጥ የሚገለጸውን ልዩነታችንን እንደ የአንድነታችን ሥጋት ሳይሆን እንደ ተፈጥሯዊ ውበታችን የምንቀበለው፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ‹‹ይህች ኢትዮጵያ . . . የሰማንያ ውብ ውብ ማንነቶች የጋራ ቤት ናት፤›› አንድነታችንም በብዝኃነት ልዩነት (Diversity) ውስጥ ለጋራ ዓላማና ጥቅም በጋራ መቆም መቻል ማለት ነው፡፡ በቅርቡ በሞት የተለየን ዕውቁ ጸሐፊና የሕግ ምሁር አቶ አሰፋ ጫቦ፣ ‹‹ጋሞነቴ ከኢትዮጵያዊነቴ ጋር ተጋጭተውብኝ ላስታርቃቸው ቁጭ ብዬ አላውቅም!›› እንዳለው፣ የማንነትና የባህል ልዩነቶች እንዳሉን መካድም ሆነ እስከ ቅርብ ጊዜ ሲደረግ እንደቆው እነዚህን ልዩነቶች ከኢትዮጵያዊ ማንነታችን በላይ ማግነን ሳይሆን፣ ጤነኝነቱ ሁለቱንም የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎችና የማይጋጩ የእኛ ማንነቶች አድርጎ መቀበሉ ይመስለኛል፡፡

የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የብሔር፣ የማኅበራዊ መስተጋብርና የባህልን ጨምሮ በርካታ ብዝኃነቶች አሉን፡፡ የብዝኃነት ልዩነት የለንም ብለን በደፈናው ማለባበሱና የሌለንን ወጥነት መናፈቁ ይጠቅመናል ብዬ አላምንም፡፡ ቋንቋዎቻችን ውበቶቻችን ናቸውና ነው፡፡ ለዚህም ነው ጠቅላያችን አስመራ ድረስ ዘልቀው በትግርኛቸውና በትግርኛችን ያስደመሙን፡፡ እነዚህን የቋንቋ ልዩነቶቻችንን ከወታደራዊው አስተዳደር ውጪ ያሉት የከዚህ በፊቶቹ ሥርዓቶችም ሆኑ የኢሕአዴግ አመራር እንዳደረገው መናከሻችን ሳይሆን፣ እንዴት አድርገን ውበትና የጋራ መገለጫዎቻችን እናድርጋቸው የሚለው ላይ ነው መሥራት የሚጠበቅብን፡፡

መሬት ሲወረድ የሌለውን አንድነት እንዲሁ አየር ላይ ማስጮህ ጋሪውን ከፈረሱ ማስቀደም ነውና ትርጉም ያለው መፍትሔ ያመጣልናል ብዬ አላምንም፡፡ እነዚህን ውብ ብዝኃ ማንነቶች አጥፍቶ አንድ ዓይነትነትን ብቻ ለማንገሥና ለአገዛዝ ምቹ ለማድረግ በግዴታ፣ በዘዴ፣ በውዴታና በብልኃት፣ . . . ለማጥፋት በምኒልክም፣ በኃይለ ሥላሴም፣ በዮሐንስና ሌሎችም ተሞክሮ ከሽፏል፡፡ ለእኔ በዚህ የፍቅርና የይቅርታ ዘመን ትግርኛ ቋንቋ ሲነገር ሲሰማ ደስ የማይለው ኢትዮጵያዊ ካለ፣ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የ‹‹መደመር›› ጽንሰ ሐሳብ ገና አልዘለቀውምና ራሱን ሊፈትሽ ይገባ ይመስለኛል፡፡ ጽንሰ ሐሳቡ የራስ ማንነትን በሌላ ማንነት ሥር አቅልጦ የሚያስቀር አይደለምና፡፡

የብሔር ብሔረሰብ፣ የቋንቋና የሃይማኖታዊ ማንነትን በሕግ ዕውቅና በመንፈግም ሆነ ‹‹ኑ እኛን ምሰሉ!›› በማለት የምትፈጠር ኢትዮጵያ አትዘልቅም ብዬ በፅኑ አምናለሁ፡፡ የጋራ ቤታችንን ማፅናት ከፈለግን አሁን የተገኘውን ዕድል ተጠቅመን አሸዋ ላይ ሳይሆን በፅኑ አለት ላይ ልንገነባትም ይገባል እላለሁ፡፡ ከአማራውና ከትግራዩ ወንድም ሕዝብና ከወጡት የያኔዎቹ ጥቂት አፄዎች ሳቢያ መላውን የአማራና የትግራይ ሕዝባችንን እንደማንጠላው ሁሉ፣ ከትግራይ ወገናችን ከተገኙት መሰሪ የሕወሓት መዝባሪዎች ምክንያት የትግሬን ዓይን አያሳየን የምንልና ይህንኑ የምንሰብክ በተለይ ስመኞቹ ‹‹አክቲቪስቶች›› ነገን ልናስብና ልናድብ ይገባል፡፡ ስትቃወሙትና ስንቃወመው የነበረው ዘረኝነት ዛሬ መልኩን ቀይሮና ቦታ ለውጦ እናንተና እኛ ላይ ሲገን ማየቱ ምንኛ ነውር እንደሆነ ማስታወሱም አይከፋም፡፡

የኢሕአዴግ ሰዎች ብዝኃነትን ዕውቅና የሰጡበት መንገድ የዘመናትን ጥያቄ የመለሰ ነው፡፡ አሁን ድረስ ያልተመለሱ፣ እንዲሁም ከዚህ በኋላም የሚቀርቡ የማንነት ጥያቄዎች መኖራቸው የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ኢሕአዴጋውያን ይህንን እውነታ ያስረዱበት መንገድና ለአደገኛው የከፋፍሎ መግዛት ፖለቲካዊ ግብ ማዋላቸው ትክክል ስላልነበር የኢትዮጵያዊነትን መንፈስ አዳክመውታል፡፡ በኢትዮጵያ የማንነት ጥያቄ (የጽንሰ ሐሳቡ ሰፊነት እንዳለ ሆኖ) እና የአስተዳደራዊ ወሰን ጥያቄዎችን በተመለከተ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በኩል እየተንከባለሉ የቆዩ ጥያቄዎችን ስናስተውል ብዙ ያልተፈቱ ችግሮች መኖራቸውን እንረዳለን፡፡ በተለይ ለረዥም ዘመን የክልልነት ጥያቄን ሲያነሱ የቆዩትን የሲዳማ ወገኖቻችንን ጥያቄ ጨምሮ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ የደኢሕዴን አመራር ሸፋፍኖ ያቆያቸው ጥያቄዎች በቅርቡ ምላሽ መሻታቸውና አደባባይ መሰጣታቸው አይቀሬ ነው፡፡

ከሁሉም በላይ ከብሔር ማንነት የተፋታ የኢትዮጵያዊ ማንነት ደረጃ ላይ የደረሰውን የመሀል አገር (Metropolitan) ሰውም ሆነ፣ የተለያየ ብሔር ካላቸው ወገኖች ጋብቻ የተፈጠሩ ዕድለኛ ኢትዮጵያውያንን የዜግነት ማንነት ዕውቅና አለመስጠቱም የኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ሌላው ስህተት ነበር፡፡ ምንም እንኳ ሕገ መንግሥታችን ከብሔር ማንነቱ እኩል ለግለሰቦች መብትም ዕውቅና የሰጠ ቢሆንም፣ ይህ ድንጋጌ በተግባር ባለመገለጹ ዜጎች የባይተዋርነት ስሜት እንዲሰማቸው ሆኗል፡፡ በቅርቡ ይሻሻላል ብለን ተስፋ ብናደርግም በአዲስ አበባ ከተማ አሁንም የብሔር ማንነቱን ከእናት ወይም ከአባቱ ወገን ያልደመረ ሰው የነዋሪነት መታወቂያ ለማግኘትም ሆነ ለማሳደስ መቸገሩ አይቀርም፡፡

በሰው ተወዳጁና ሰውን ወዳጁ ጠቅላያችን ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ኃላፊነት መጥተው ነገሮች መስተካከል እስኪጀምሩ ድረስ በቃልም በተግባርም ከምንለያይባቸው ጉዳዮች አንዱና የችግራችን ሁሉ መጠቅለያ ነጥብ፣ የኢትዮጵያዊነት መረዳትና የዚሁ መረዳታችን መገለጫ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማችንን የሚመለከተው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ላይም ከስሜትና የእኔ ብቻ ይደመጥልኝ ከሚለው አስተሳሰብ ወጥተን የሠለጠነ ንግግር ማድረግ እንዳለብን ይሰማኛል፡፡ ነገና በኋላ ሳይሆን ዛሬና አሁን፡፡

ኢትዮጵያ የምንላት የትኛዋ ኢትዮጵያ ናት?! ገጣሚው ከዓመታት በፊት እንዳጣየቀው ኢትዮጵያዊ የምንለው ኢትዮጵያዊስ የትኛው ኢትዮጵያዊ ነው?! ይህች ኢትዮጵያስ መገለጽ ያለባት በየትኛው ሰንደቅ ዓላማ ነው?! ስንታገለው የኖርነው አምባገነንነት ዳግም ከመንግሥታዊ መዋቅሮች ወጥቶ ኅብረተሰባችን ውስጥ እየታየና ስለምንም ነገር ተቃውሞ ማሰማት አደገኛ እየሆነ የመጣ ቢመስልም፣ በእኔ በኩል ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን የተረዳሁበትንና ይህንንም ኢትዮጵያዊነት በየትኛው ሰንደቅ ዓላማ ብንገልጸው ያዛልቀናል የምልበትን መንገድ ገልጫለሁ፡፡

ጥቂት ስለሰንደቅ ዓላማችን

ሰኔ 16 ቀን 2010 ‹‹ዴሞክራሲን እናወድስ›› በሚል ፍካሬ በመስቀል አደባባይ በተካሄደው ሠልፍ ላይ ተጠብቆ የነበረ አንድ ክስተት ዕውን ሆኗል፡፡ ይኼውም ከመዲናችን አዋሳኝ የኦሮሚያ አካባቢዎች የተገኙ ወጣቶች (ቄሮ) በብዛት እንደ ክልል የኦሮሚያን፣ እንደ ድርጅት የኦነግና የኦሕዴድን፣ እንዲሁም እንደ አገር ደግሞ የኢትዮጵያን ሕጋዊ ሰንደቅ ዓላማ ይዘው የታዩ ሲሆን፣ ‹‹አንዲት አገር፣ አንድ ሕዝብ፣ አንድ ሰንደቅ ዓላማ!” የሚለውን ሐሳብ ያቀነቀኑ ወገኖችም በእነሱ አገላለጽ ‹‹ንፁሁን/ልሙጡን የኢትዮጵያ ባንዲራ›› አንግበው ታይተዋል፡፡

ከዚህ ታሪካዊ የዴሞክራሲ ድጋፍ ሠልፍ በኋላ ከኦሮሚያና ከአንዳንድ የደቡብ ክልል ከተሞች በስተቀር፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተካሄዱት ሠልፎች ላይ በተለይም በባህር ዳሩ ሠልፍ ላይ ይኼው ክስተት ተስተውሏል፡፡ አስገራሚው ነገር በመስቀል አደባባዩ የመወድሰ ዴሞክራሲ ሠልፍ ላይ የመደመርም ሆነ የዴሞክራሲ ትርጉም ያልዘለቃቸው ወገኖቻችን፣ አንዱ የአንዱን ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ ዓርማ ለማስጣል ግብግብ እስከ መፍጠር ደርሰውም ነበር፡፡ በተለይ ‹የንፁሁ ባንዲራ› ወዳጆች ያንን በሰንደቅ ዓላማነት የማይቀበለውንና ብሔራዊው ዓርማ ይገልጸኛል ብሎ ያመነውን ወገን የማሸማቀቅና የማጥላላት ሥራ ውስጥ ገብተው የተስተዋሉ ሲሆን፣ አሁንም ይህ እንደቀጠለ ነው፡፡

ባንዲራ (Bandiera) የሚለውን ቃል ባለማስተዋል ብንጠቀምበትም አባቶቻችን እንደነገሩን ጣሊያኖች ሰንደቅ ዓላማን ለመግለጽ የሚጠቀሙበት ቃል በመሆኑ፣ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የምንግባባው ሰንደቅ ዓላማ በሚለው ቃል ይሆናል፡፡ ሰንደቅ ዓላማ የሚለው መጠሪያ ‹‹ሰንደቅ›› እና ‹‹ዓላማ›› ከሚሉት የሁለት ቃላት ጥምረት የተመሠረተ ነው፡፡ ሰንደቅ ማለት ምሰሶ ወይም ቋሚ ዘንግ፣ ዓላማ ማለት ደግሞ ምልክት፣ መለዮ እንደ ማለት ነው፡፡ የሁለቱ ቃላት ጥምረት ነው እንግዲህ ‹‹ሰንደቅ ዓላማ›› የሚለውን ቃል በአንድ ላይ አስሮ ‹‹በአብዛኛው የተወሰኑና የተለያዩ ቀለማት ካሏቸው ጨርቆች የሚዘጋጅ የአንድ አገር የነፃነት ምልክትና መለያ››፣ የአንድ አገርና ሕዝብ የሉዓላዊነቱ ምልክት ወይም ትዕምርት ተደርጎ የሚወሰደው ይለናል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል ከመጠነኛ ማሻሻያዎች ጋር በ2001 ዓ.ም. የታተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት፡፡ ሰንደቅ ዓላማ የሕዝቦች ማንነት ማሳያ፣ የታሪካቸውና የሉዓላዊነታቸው መገለጫ ሲሆን፣ ዘርዘር ስናደርገው ከዚህ ጠለቅ ያለ ትርጉም ይይዛልና ከዘንጉም ሆነ ከባለኅብረ ቀለማቱ ጨርቅ በስተጀርባ ያለው መልዕክት ሰፊ ነው፡፡

አገሮችና ሕዝቦች ለሰንደቃቸው ያላቸውን ፍቅር በተለያየ መንገድ የሚገልጹት ሲሆን፣ በዚሁ ዙሪያ በርካታ ታሪኮች ተጽፈዋል፣ ፊልሞችም ተሠርተው ተመልክተናል፡፡ በሰላሙም ሆነ በጦርነቱ ወቅት ኢትዮጵያውያን ለሰንደቅ ዓላማችን ጥልቅ ፍቅርና ልባዊ ክብር ያለን ሕዝቦች ነን፡፡ ኢትዮጵያችን እንደ ቀዳሚና ገናና ሥልጣኔዋ ሁሉ የረዥም ዘመን የሰንደቅ ዓላማ ታሪክ ያላት አገር ስትሆን፣ እስከ 1890ዎቹ ድረስም አንድ ወጥ የሆነ ሰንደቅ ዓላማ አልነበራትም፡፡ የታሪክ ገጽ ሲገለጽ በዚህች አገር ከአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ውጪ ያሉ ቀለማት ተውለብልበውም ያውቃሉ፡፡

ከበደ ሚካኤል ‹‹ታሪክና ምሳሌ አንደኛ መጽሐፍ›› ላይ መግቢያውን ሲጽፉ፣ ‹‹ሰንደቅ ዓላማ የነፃነት ምልክት፣ የአንድ ሕዝብ ማኅተብ፣ የኅብረት ማሠሪያ ጥብቅ ሐረግ ነው….. ሰንደቅ ዓላማ ትዕምርተ ኃይል ትዕምርተ መዊዕ ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማችን አረንጓዴ፣ ብጫና ቀይ ሦስት ቀለማት ናቸው፡፡ ምሳሌያቸውም አረንጓዴው ተስፋ፣ ልምላሜና ሀብት፣ ቢጫው ሃይማኖት፣ አበባና ፍሬ፣ ቀዩ ፍቅር መስዋዕትነትና ጀግንነት ነው፤›› ይላሉ፡፡ እነዚህኑ ቀለማት ከሃይማኖት አንፃር የሚመለከቱ ግለሰቦች ደግሞ የኖኅን ታሪክና ‹‹ቀስተ ደመና››ን የኢትዮጵያ የቃል ኪዳን ምድርነት መነሻ በማድረግ አረንጓዴው የአብ፣ ቢጫው የመንፈስ ቅዱስ፣ ቀዩ ደግሞ የወልድ ምልክቶች ናቸው ሲሉም አድምጫለሁ፡፡

በታሪክ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ ብቻ ሆኖ ያውቃል፡፡ ኢትዮጵያ ሕገ ኦሪትን ስትቀበል ቢጫ ተጨምሮበት ሰንደቁ አረንጓዴና ቢጫ ሆኗል፡፡ የክርስትና ሃይማኖትን እስክትቀበልና ቀዩ እስኪጨመር ድረስም ይኼው ሰንደቅ ዓላማ ፀንቶ ለረዥም ጊዜ ቆይቷል፡፡ የተገላቢጦሽ ሆኖና ሦስቱ ቀለማት ቦታ ተቀያይረውም ያውቃሉ፡፡ አሁን ያለውን የቀለማት አደራደር ያገኘው በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን፣ ይህ ጊዜም የአውሮፓውያኑ ተስፋፊዎች ጊዜ ስለነበር ሰንደቅ ዓላማችን የነፃነትና የኩራት ምልክት በመሆን ለብዙ የአፍሪካና ሌሎች አገሮች እንደ መነሻ ሆኖ ቆይቷል፡፡

በየትኛው ሰንደቅ ዓላማ የምትገለጽ ኢትዮጵያ?!

የሕገ መንግሥታችንን መግቢያ አራተኛውን ፓራግራፍ ያነበበ ማንኛውም ሰው ‹‹መጪው የጋራ ዕድላችን መመሥረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል…›› የሚለውን የታሪክና የፖለቲካ እውነታ ያስታረቀና የዛሬ መሠረታችንን በመጣል፣ የነገ ብሩኅ መድረሻችንን የተለመውን አገላለጽ አይስተውም፡፡ በታሪክ አሁን ‹‹ንፁሁ›› እየተባለ የሚገለጸው የድሮው ሰንደቃችን ከውጭ ለነፃነት ምልክት እንደሆነው ሁሉ፣ ከውስጥ የጭቆናና ከፊሉን ኢትዮጵያዊ የማግለል ምልክት እንደነበርም መዘንጋት የለበትም፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እንደ አንድ ሙስሊም ‹‹ባለመስቀሉ የይሁዳ አንበሳ›› ያረፈበትም ሆነ አሁናዊው ብሔራዊው ዓርማ የሌለበት ‹‹ልሙጡ›› ሰንደቅ ዓላማ ያለምንም መሸማቀቅ እንድዘምርላቸው አያደርጉኝም፡፡

መሠረታዊ ቀለማቱን በተመለከተ አባታችን ሡልጣን ዓሊ ሚራህ ሐንፈሬ በአንድ ወቅት እንደገለጹት፣ ‹‹እንኳን እኛ ግመሎቻችንም ያውቁታል›› እና ማንም የፈለገውን ትርጓሜ ቢሰጣቸውም፣ በዚሁ መቀጠሉ አይቀርም የሚሻለውም ይኼው ነው በሚል እሳቤ ይነስም ይብዛ ወቅታዊ የሕዝብ ውክልና የነበራቸው የሕገ መንግሥቱ አርቃቂዎች የአገራችንን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ ይሆናል ብለው ያመኑበትን ብሔራዊ ዓርማ (ትዕምርት) አኑረውበታል፡፡ በወቅቱ ሰንደቅ ዓላማችን መሀል ያረፈውን ዓርማ የሠራው ዕውቁ ገጣሚና ሰዓሊ መስፍን ሀብተ ማርያም ነው፡፡ ስለትዕምርቱ ዝርዝር የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2009 ከስድስተኛው አንቀጽ ጀምሮ ያሉትን ድንጋጌዎች ማየት የሚቻል ቢሆንም፣ ለእኔ ደስ ያለኝን አገላለጽ ከሸገር አፍኤም ጋዜጠኛ ዘከሪያ ሙሐመድ የፌስቡክ ገጽ በመዋስ እንዲህ ላስቀምጠው፣  

‹‹በዓርማው ላይ ለእኔ የሚታየኝ ዓርማው ከአንድ ወጥ ሪባን የተገመደ ኮከብ ነው። ሪባኑ አንዱ በሌላው ላይና ሥር፣ ሌላውም በአንዱ ላይና ሥር ያልፋሉ። የትኛውም የበላይ ብቻ አይደለም። የትኛውምም የበታች ብቻ አይደለም። የተጋመደ ህልውና ነው ያላቸው። የተሳሰረ። የተሰናሰለ። መስፍኔ ይህን ኮከብ የሚያስገርም የእኩልነት ተምሳሌት አድርጎ ነው የሳለው። ከዚህ በእኩልነት የታነፀ ኮከብ ውስጥ ብርሃን ሲፈነጥቅ ነው የሚያሳየው። ይህ እኔ ተራው ሰው ዓርማውን በጥሞና ከማየት የተረዳሁት ትርጓሜ ነው። የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ከዚህም የጠለቀ ትርጉም ይሰጡታል፤›› ይለናል ዘከሪያ፡፡

ሰንደቅ ዓላማ ከነፃነት ምልክትነት የዘለለ መንፈሳዊ ይዘት የለውም፡፡ ሰንደቅ ዓላማው መስቀል ከተሸከመ አንበሳ ጋር ለዘመናት ሲቆይ ‹‹እንደ ሕዝብ›› ያን ያህል ሆድ ያልባሰንና ያልመረረን ለምን ነበር?! ዳሩ ‹‹ቀስተ ዳመናው ላይ አንበሳው ከሌለ፣ የኢትዮጵያ ባንዲራ ትርጉሙ የታለ!›› ተብሎ ተዘፍኖም የሕዝበ ኢትዮጵያ ግማሽ የሆነውን ሕዝበ ሙስሊም ያገለለ ሰንደቅ ዓላማ ሲናፈቅ ሰምተናልና በየራሳችን ህሊና ዳኝነት መስጠት እንችላለን፡፡ አሁን ምን አዲስ ዕውቀት ተገኘ? ምንስ እውነት ተገለጠልን?! የአንባሻ ምልክት ስለሆነ ከተባለም ስንበላው ያደግነው የትግራይ አንባሻ ለትዕምርትነት ከጠቀመንና በአንድነት ክር ካጋመደን ችግሩ ምንድን ነው?! አሁን አሁን ደግሞ የሰይጣናውያን እምነት ምልክት ነው የሚለውም በዝቷል፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ምን እንደሚባል ባናውቅም፡፡

ይኼው አሁንም በሥራ ላይ ያለውና መንግሥታችን እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ አላከብረውምም አላስከብረውምም ያለው ሕገ መንግሥት በአንቀጽ ሦስት፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ›› በሚለው ርዕስ ሥር ተከታዩን ደንግጎ እናገኛለን፡፡

  1. የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሀል ቢጫ፣ ከታች ቀይ ሆኖ በመሀሉ ብሔራዊ ዓርማ ይኖረዋል፡፡ ሦስቱም ቀለማት እኩል ሆነው በአግድም ይቀመጣሉ፡፡
  2. ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦችና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንፀባርቅ ይሆናል፡፡
  3. የፌዴራሉ አባላት የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማና ዓርማ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ዝርዝሩን በየራሳቸው ምክር ቤት ይወስናሉ፡፡

ያለንበት የብዝኃነት እውነታ፣ የሥርዓተ (የቅርፀ) መንግሥቱ ጥቅምና ይኼው ሥርዓተ መንግሥት ከዚህ በፊት በጥቂት ጥቅመኞች ለሁለት ዓላማ የዋለ ቢሆንም፣ ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያችን ችግር ፍቱን መድኃኒት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ደግሞ የፌዴራል መንግሥቱ አባላት የሆኑ ክልሎች (ክፍላተ ሀገሮች) በየምክር ቤቶቻቸው ውሳኔ ከፌዴራላዊው ሰንደቅ ዓላማና ዓርማ ጎን ለጎን የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማና ዓርማ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ አስገዳጅ ስላይደለ ላይኖራቸውም ይችላል፡፡ ለምን ኖራችሁ? ለምንስ የላችሁም? ማለቱም ተገቢ አይደለም፡፡ ዕድሜ ለፌዴራሊዝም፡፡

ለእኔ የሚታየኝ ችግር በሕገ መንግሥቱ የፌዴራሉ አባላት ተብለው የተገለጹትና ክፍለ ሀገሮች ወይም ክልሎች የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ በአግባቡ ማጤን ሲኖርባቸው በቀጥታ የየራሳቸውን ሰንደቅ ዓላማና ዓርማ ማዘጋጀታቸው ሲሆን፣ አንድም ክልል የፌዴራሉ ዓርማ ዓርማዬ ይሆናል አለማለቱንም መታዘብ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ድንጋጌው በክልሎቹ ላይ ግዴታን ሳይሆን ያስቀመጠው ምርጫ ነው የሰጣቸው፡፡ የሕገ ቃል አገባቡም ሊኖራቸው ይገባል (Shall) ላይሆን ይችላል (May) በሚል ነው ያስቀመጠው፡፡ ነገር ግን ክልሎቹ በየሕገ መንግሥቶቻቸው ከፊሉ የሰንደቃቸውን ዝርዝር በዓይነት ሲወስኑ ከፊሉ ደግሞ ክልሉ የራሱ ሰንደቅ ዓላማና ዓርማ ሊኖረው እንደሚችል በመግለጽ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል ብለዋል፡፡

ሕግና የሕግ የበላይነት ይከበር!

ሕግ በሌላ ሕግ እስካልተሻረ ድረስ የፀና ነውና መከበር አለበት፡፡ ይህ ሕግ ለምድራዊ ጉዳዮቻችን የሕጎች ሁሉ የበላይ የሚሆነው ሕገ መንግሥት ሲሆን ደግሞ፣ ይበልጥ እንድናከብረውና እንድናስከብረው እንገደዳለን፡፡ የሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 9 ሕጉን የማክበርና የማስከበርን ኃላፊነትን ለሁላችንም ቢሰጥም፣ በዋነኝነት የሕግ አስከባሪና የፍትሕ አካላት ሊያከብሩትና ሊያስከብሩት ቃል የገቡለትን ይህንን ሕገ መንግሥትና ይህንኑ ሕገ መንግሥት ተከትለው የወጡ ሕግጋትን ሁሉ አክብሮ የማስከበር ግዴታ አለባቸው፡፡ ፍቅርና ይቅርታ ጥሩ ነገር ቢሆኑም፣ ሕግና የሕግ የበላይነት ደግሞ ከፍቅርም፣ ከይቅርታም በላይ የሕዝብ ሰላምና የአገር አንድነት መጠበቂያ (ላልቶም ጠብቆም ቢነበብ) ዋስትና ናቸው፡፡

በደፈናው ኢሕአዴግ የነካውን ሁሉ ከመቃወም ይልቅ የትዕምርቱን ጠሊቅ ትርጉም በማስተንተን በዚሁ ላይ ብንደመር የሚሻል ይሆናል፡፡ ግለሰቦች በስታዲዮሞች፣ በመስቀል አደባባይ፣ በኤምባሲዎች በመግባትና የአሁኒቱን ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በማውረድ፣ ክብሩንም በማዋረድ የድሮውን ለመስቀል ስለመሞከራቸው በተደጋጋሚ ሰምተንና ተመልክተን የሰለቸን ጉዳይ ነው፡፡ አሁናዊው አዲስ ነገር ይህ በሕገ መንግሥትና በሌሎች ሕጎች ጥበቃ የተሰጠው ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ ዓርማ እኔን ይገልጸኛል ብሎ የሚቀበለው ወገን የሌለ ይመስል፣ ወይም ደግሞ ቢኖርም የዚህ ወገን የኢትዮጵያዊነት መረዳት ላይ ሌላ ለመጫን ሕጎቹ ተፈጻሚነታቸው ሳይሻር በየአደባባዩ መዘበቻ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡

በአንድ ወቅት ሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ መንግሥታቸው የሕግ የበላይነት ላይ በአግባቡ አለመሥራቱን ሲገልጹ፣ ‹‹ራሱን ለሕግ የበላይነት ያስገዛ መንግሥት ብቻ ነው ዜጎቹ ለሕግ የበላይነት እንዲገዙ ለመጠየቅ ሞራላዊ መብት የሚኖረው!›› ብለው እንደነበረው ሁሉ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ የመንግሥቱ የሕግ አስከባሪና የፍትሕ አካላት በቅድሚያ ለሕግ የበላይነት መከበር ንቁ መሆን የሚኖርባቸው ጊዜ ላይ ነው ያለነው ብዬ ብጽፍ ስህተት አይሆንም፡፡ መንግሥታችን የሕግ የበላይነት መኖሩን ማሳየት የሚገባው ደግሞ ለውጡ ላንገሸገሻቸው የቀድሞ አምባገነኖች ብቻ ሳይሆን፣ በለውጡ ጥላ ሥር ሆነውና የለውጡ አካል ሆነውም ከሕግ ውጪ የሆነ ተግባር ውስጥ ያሉትን ሁሉ ነው፡፡

የመንግሥት ሥልጣንና ተግባር ምንድነው? ይህንን ሥልጣንና ኃላፊነትስ በምን አኳኋን ነው ወደ ተግባር የሚቀይረው? የሚለውን መሠረት የሚያስቀምጠው ሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ ሕገ መንግሥት በልማዳዊ አሠራሮች የሚጣስ ከሆነ የዜጎች መብት ዋስትና ያጣል፣ ለአምባገነንነትም በር ይከፍታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሁሉም የመንግሥት ኃላፊዎች ላይ ቢበረታም ዜጎችም ሕገ መንግሥቱን የማክበርና የማስከበር የሕግ መብት እንደተሰጠንና የሕግ ግዴታ እንዳለብንም መዘንጋት የለብንም፡፡ መብትን ለመጠየቅ ግዴታን መወጣት ይቀድማል፡፡ አምባገነኑን የኢሕአዴግ አመራር የተቃወምነው የሕግ የበላይነት አልተከበረም ብለን ከነበረ፣ አሁን ያለውንም አመራር ለምን የሕግ የበላይነትን አክብሮ እንደማያስከብር ካልጠየቅን ከግለሰቦቹ እንጂ ከሥርዓቱ ጋ ችግር አልነበረብንም ማለት ይሆናል፡፡ የሕግ የበላይነት ይከበር ስንል ኖረን ዛሬ በተራችን ‹‹የምን ሕግ ነው?›› ማለት ከጀመርንም ችግር አለ ማለት ይሆናል፡፡

የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2009 ሰንደቅ ዓላማውንና ብሔራዊ ዓርማውን በተመለከተ የተከለከሉና የሚያስቀጡ ወይም ቅጣት የሚያስከትሉ ተግባራት ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ፣ ሰንደቅ ዓላማውን ለብቻው ማለትም ብሔራዊ ዓርማውን ሳያካትቱ መጠቀም፣ የማዋረድና መሰል ድርጊቶችን መፈጸም በገንዘብ መቀጮ እንደሚያስቀጣና እንደየሁኔታውም እስከ አንድ ዓመት ከስድስት ወራት ሊደርስ በሚችል ፅኑ እስራት ሊያስቀጣ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡

አሁን በሰንደቅ ዓላማው ላይ ያለው ብሔራዊ ዓርማ ‹‹የሕወሓት ኢሕአዴግ ዓርማ›› ከመሆን እንደማይዘል የሚያምኑትና ዓርማው በሕግ ሳይሆን በግለሰቦች በመነሳቱም ደስተኛ የሚመስሉት ዶ/ር ዘላለም እሸቴ የተባሉ ግለሰብ፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፈጣሪ ስለመሰጠቱና የተስፋው ቃል ሕዝቦች ስለመሆናችን በመጽሐፍ ቅዱስ የዳዊት መዝሙር ምዕራፍ 75 ቁጥር 4 ላይ (?) የተጠቀሰውንና ‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› የሚለውን በመያዝ ‹‹ኢትዮጵያ ከጥሪዋ ጋር የሚሄድ ዓርማ (የተዘረጉ እጆች) በባንዲራችን ላይ የሚያርፍበት ዘመን ይምጣልን የሚል ምኞት አለኝ፤›› ብለው የጻፉትን አንብቤያለሁ፡፡ ምኞት እንደማይከለከል ባውቅም ጥቂት መስመሮችን ገፋ አድርጌ ሳነብ፣ ‹‹ይህ ዓርማ ከማናቸውም ሃይማኖት ምልክቶች ስለማይያያዝ፣ ሃይማኖት እንደማይከፋፍለን ምልክት ይሆንልናል፤›› በማለት ነገሩን እንዳይሆን እንዳይሆን ሲያደርጉትም አስተውያለሁ፡፡

በእርግጥ ዛሬም ድረስ ራስ ተፈራውያን በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማነት የሚያውቁትና ‹‹የራስ ተፈራውያን ሰንደቅ›› እየተባለ የሚታወቀው የይሁዳ አንበሳን ከእነ መስቀሉ ያነገበውንና ዘውድ የጫነውን፣ ለሙስሊም ኢትዮጵያውያንም ፈፅሞ ቦታ ያልነበረውን ስለመሆኑ ማስታወስ ይኖርብኝ ይሆን? አንድ ወሳኙ ነገር አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩ ሰንደቅ ዓላማ ያለ ብሔራዊ ዓርማው ሃይማኖታዊ ትርጉም (Sentiment) ይሰጠናል የሚሉ ወገኖቻችን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ካሉ፣ ለሃይማኖታዊ ክብረ በዓላቱ ሲባል ሕጉ በልዩነት (Exceptionally) ፈቃድ የሚሰጥበትን ሁኔታ ማሰብ እንደሚገባ፣ መብትም ትክክልም እንደሚሆን አምናለሁና ሕግ አርቃቂዎቹ ልዩ ሁኔታውን ቢያጤኑት መልካም ይሆናል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትራችን ክቡር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ‹‹ይህች ኢትዮጵያ….›› ብለው የገለጿት ኢትዮጵያ ከትናንት ከፍታዋ በጎ በጎውን እንጂ ክፉውን የምትወርስ አይደለችምና በዶ/ር መረራ ጉዲና አገላለጽ፣ ‹‹በሁለቱም ጫፍ ሆናችሁ ገመድ የምትጓተቱ›› ወገኖቻችን ሆይ እባካችሁ ወደ መታረቂያው መንገድ ኑልንና ለሁላችንም የምትበቃንን፣ ሁላችንንም ያለምንም ቅሬታ የምታቅፈውንና ሁላችንንም በእኩል የምትገልጸውን ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን እናዋልዳት፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትን መነሻ ድንጋጌዎች ተከትሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 654/2009 በአንቀጽ አራት ሥር ስለብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን ክብረ በዓል ሲያትት፣ ‹‹በየዓመቱ የመስከረም ወር ሁለተኛ ሳምንት ላይ በሚውለው ሰኞ ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ይከበራል›› ይላል፡፡ በመጪው መስከረም የምናከብረው ይህ የአዲሱ ዓመት አዲስ ቀን የመደመራችን ማሳያና የዚሁ መደመራችን ውጤት የሆነችው ሁሉን አቃፊዋ ኢትዮጵያ የማይናወጥ ፅኑ መሠረታችን እንድትሆን፣ የየበኩላችንን ጥረት እንድናደርግ የዜግነት ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡ ሰላም ለእናንተ ይሁን!፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በጉራጌ ዞን የወለኔ ወረዳ ዓቃቤ ሕግ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...