Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትበ‹ብሔር የበላይነት› መጠመድን እንደምን እንርታው?

በ‹ብሔር የበላይነት› መጠመድን እንደምን እንርታው?

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

ለሩብ ምዕት ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ ሕዝቦች የኖሩበት ብሔርተኛ ፖለቲካና አገዛዝ ያደረሰው አዕምሯዊ መከታተፍና የመናቆር ሥነ ልቦና፣ ጭፍን ብሔረሰባዊ ጥቃትና መበቃቀል ውስጥ እስከ መግባት ድረስ ህሊና ነስቶ ቀይቷል፡፡ በቶሎ ለችግሮቻችን መፍትሔ እስካላመጣን ድረስም መመለሻ የሌለው መጨፋጨፍ መጨረሻችን እንደሆነ እያሳየ አስጠንቅቆናል፡፡ በዚህ የመጠፋፋት አፋፍ ላይ ሆነን ግን እውነታን ያለመቀበል ሽምጠጣና ምኞታዊ ፖለቲካ እየተናነቀን ይገኛል፡፡

በያዝነው 2010 ዓ.ም. ወረት የሞቀለት የ‹‹ሰጎን ፖለቲካ›› የሚባል ፈሊጥ ነው፡፡ ብዙ ጊዜም የሚነሳው ጎሰኛ ጥቃትንና አውዳሚነትን ዝም ብሎ ማሳለፍ፣ አሸዋ ውስጥ ጭንቅላቷን እንደቀበረችው ሰጎን መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ የአባባሉ አጠቃቀም ያስጨነቀንን እውነታ የሚናገር ቢሆንም፣ የጥላቻ ጥቃትንና ንብረት አጥፊነትን እንኮንን እናስቁም ከማለት ያላለፈና ችግሩን ሊነቅል የሚችል የፖለቲካ ማሻሻያ ላይ ያላተኮረ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር ዛሬ “የሰጎን ፖለቲከኛነት” ዋና መገለጫ ሆኖ ያለው ስለሰጎን እያወሩ ግን የዴሞክራሲ ለውጥ ማሻሻያዎችን የመውሰድ ዳተኝነት ነው፡፡

የዚህ ዳተኝነት ዋና ማዕዘን ደግሞ በዓይነ ደረቅነት ወይም በምኞታዊነት ውስጥ የመደበቅ ግትርነት ነው፡፡ በዓመቱ መጀመርያ ወራት የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አንድ ወር ያህል የፈጀ ጥልቅ ግምገማና ተሃድሶ አደረገ ከተባለ በኋላ መሪዎቹ ያንኑ ሲደጋገም የኖረውን የፓርቲም የብሔርም የበላይነት የለም. . . እኩልነት ተረጋግጣል. . . የተገነባው ሥርዓት ለበላይነት የሚመች አይደለም የሚል ግማሽ እውነት ግማሽ ውሽት ከመናገር አላመለጡም፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ከዚያ በኋላ 17 ቀናት የፈጀ ስብሰባ አድርጎ ሲመለስ ባወጣው የጽሑፍ መግለጫም፣ የአራቱ አባል ድርጅቶች መሪዎች በሰጡት መግለጫም ይኸው ተደግሟል፡፡

ከለውጡ ወዲህ ማለትም በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አመራርና አዲስ የለውጥ ጅምር ውስጥ ጉዳዩ ወይም ችግሩ በተለየ ሁኔታ (በተሻለ ሁኔታም ባይሆን) ተነስቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. በፓርላማ የቀረበላቸውን ጥያቄዎች ሲመልሱ፣ ‹‹ከጥያቄው ጋር ብዙም ባይቀራረብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ጥሪ ማቅረብ የምፈልገው ስለትግራይ ሕዝብ ነው?›› ብለው፣ ውስጥ ለውስጥ የሚብላላውን ይህንን ጉዳይ በአንፃራዊነት በአደባባይ ፍርጥ አድርገው አቅርበውታል፡፡ ጥቂቶች በስሙ ነግደው ይሆናል እንጂ የትግራይ ሕዝብ የተለየ ያገኘው ነገር የለም፡፡ የተለየ ነገርም እንዲደረግለት አይፈልግም ብለዋል፡፡

ሐምሌ 12 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢቲቪ ዜና የተጠቀሱት ሌተና ጄኔራል ፃድቃን ወልደ ትንሳዔ፣ ‹‹ከለውጡ ጋር ተያይዘው የሚነሱ አንዳንድ መፈክሮችና ንግግሮች›› እንዳሉ ገልጸው፣ ‹‹የትግራይ ሰው በመሆንህ ብቻ እዚህ አገር እየተፈጠረ ባለው ሙድና ጫጫታ እንድትፈራና ሳትወድ መሸሸጊያ እንድታገኝ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ይህም ለውጥ ለማይፈልጉ ኃይሎች ጠቃሚ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ኢቲቪ በዚያው ዝግጅት የጠቀሳቸው ሜጄር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖትም አብዛኛው ሰው ለውጥ ደጋፊ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹ይህን እንቅስቃሴ የሚፈሩና የሚጠሉ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ደግሞ የትግራይን ሕዝብ እንዲያደርጉት ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ አንዳንድ አካባቢ እንደሚታየው የመሀል አገር ሕዝብ ምሽግ ጥሩ ማቀጣጠያ ቤንዚን እየሰጣቸው ነው፤›› በማለት ችግሩን አሳይተዋል፡፡

ጉዳዩን እንዲህ አድርጎ ፊት ለፊት መጋፈጥና ጥያቄውን ከውይይትና ከንግግር በላይ አድርጎ የሚያየውን ባህል ሽሮ መፍትሔ መፈለግ ሲበዛ መበረታታት ያለበት የአገር ጉዳይ ነው፡፡ ጉዳዩ ግን እውነትን ያለመቀበል ድርቅናና ሽምጠጣ የተጠናወተው ሆኗል፡፡ ድርቅናን ወይም ከእውነታ ለመደበቅ የቆረጡትን ለማሳመን ሳይሆን፣ በፕሮፓጋንዳ የተወናበዱት መዘዙ የት ጋ እንዳለ እንዲታያቸውና በትግራዊነት ላይ ተፈጥሮ የከረመውን አደገኛ አሉታዊ ስሜት ለመንቀል እንድንችል የሚያግዙ ጥያቄዎች እናንሳ፡፡

ሕወሓታዊ የበላይነት ከሌለ በሕወሓትም ሆነ በትግራዊነት ላይ የተፈጠረው አሉታዊ ስሜት ተጨባጭ የእውነታ መሠረት የለውም ማለት ነው፡፡ የብሔረሰቦች እኩልነትና ነፃነት ከተረጋገጠ፣ እዚህ ላይ በልማት የታየው ማንሰራራት ሲታከል ሕወሓት/ኢሕአዴግ በመወደስ ፋንታ ስለምን መጠመዱ? ሐበሻ ምሥጋና ቢስ ስለሆነ? ወይስ በቁም ማመስገን ስለማይወድ? ይህንን ማመካኛ ከመረጥን ሳንከራከር መሸነፋችን ነው፡፡ ሲባል እንደኖረው ጥላቻውን ከደርግ ጀምሮ የተገነባና ይህን ሥርዓት ለመምታት የሚካሄድ የፀረ ሕዝቦች ሴራ ካደረግነውም፣ ሐሰተኛ የብሔርና የድርጅት የበላይነት ውንጀላ እንደምን ረዥም ዕድሜ ሊያገኝና በሰዎች ውስጥ ሊስፋፋ እንደቻለ፣ ልማቱ የሚታይና የማይካድ ለመሆን እንደበቃ ሁሉ ብሔረሰቦች እየኖሩት ያለው እኩልነትስ ለምን የማይካድ የመሆን አቅም እንዳላገኘ፣ አኅጉሮችን አቆራርጦ የሚናኘውን መንግሥታዊ ፕሮፓጋንዳ እንደምን ፀረ ሕዝቦች ሊበልጡ እንደቻሉ የሚያሳምን መርቻ ማቅረብ ያሻል፡፡

መርቻውን የመልካም አስተዳደር መጓደልና ግለሰባዊ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ፀረ ሕዝቦችን አገዛቸው የሚል ከሆነም፣ ይህ ችግር መላ አገሪቷን በየክልሉ በየዞኑና በየወረዳው ያሉትን የኦሮሞ፣ የአፋር፣ የሶማሌ፣ የደቡብና የጋምቤላ ወዘተ. ሁሉ ጎሰኛ ሌቦችን ሁሉ የሚያጠቃልል ሆኖ ሳለ ለምን ሕወሓትና ትግራዊነት ላይ የበላይነት የሚባል ነገር እንደተሰካ፣ በግለሰባዊ ማናለብኝነት ዘንድ ሕወሓታዊ-ትግራዊ እብሪት ለምን ጎልቶ እንደወጣ፣ የሌላ ብሔረሰብ ሹሞች ሳይቀሩ በሕወሓታዊ-ትግራዊ ድንፋታ ፊት ስለምን እንደሚብረከረኩ ማስረዳት ይጠይቃል፡፡ የሚሸፋፈነውን እውነት ከመገላለጣችን በፊት በሁለት ነገሮች ላይ እንግባባ፡፡

አንደኛ የፖለቲካ ልሂቃኖቻችን የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሰዎችን ጨምሮ ስላለፈው ስለሸዋ ወይም ስለአማራ የበላይነት (ገዥነት) ሲናገሩ ሞረቴ፣ መንዜ፣ ቡልጌና ተጉለቴ ወዘተ. እንዳለ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ የበላይ ሆነ ማለታቸው አልነበረም፡፡ ገዥዎቹ ውስጥ ስላለው የጥቂቶች ክምችት ማውራታቸው እንጂ፡፡ ብዙኃኑ ሕዝብ በድህነት እንደሌላው ሲማቅቅ ስለመኖሩ አገር ያውቃል፡፡ ዛሬም ስለብሔር የበላይነት ሲነሳ በገዥነት ውስጥ ስላለ የጥቂቶች ብልጫ ከማውራት በቀር፣ የአንድ ብሔር ሕዝብ በሌሎች ብሔረሰቦች ላይ ተሰማርቷል ማለት እንዳልሆነ ሆድ ያውቃል፡፡ ሆድ እያወቀ ሽምጠጣ ከሆነ ራስን ማታለል ነው፡፡ የበፊቱንም የአሁኑንም የጥቂቶች ገዥነት “የብሔር የበላይነት” እያሉ ስም መስጠት አሳቻ መልዕክት እየረጨ በዓይነተኛ ድፍን ሕዝብ ላይ ጠንቅ የሚያመጣ ጥፋት ነውና መቅረት አለበት ከሆነ እሰየው! የውሾን ነገር ላለማንሳት የዚህ ጽሑፍ ባለቤትም ፍላጎቱ ነው፡፡ ክፋቱ ግን ለሐሜቱ መነሻ የሆኑትን ችግሮችን ለይተን አውቀን እስካላረምናቸው ድረስ “እንተወው” ስለተባባልን መብጠልጠሉ አይላቀቀንም፡፡

ሁለተኛ ፌዴራላዊ አገዛዙ እውነት ነው ላዩ ሲታይ የፌዴራል አባል አካባቢ ገዥዎች ከዚያው ከየአካባቢው የወጡ ስለሆኑና ሌላ ውጫዊ ሿሚ ስለሌለባቸው፣ ጥፋትና ልማታቸው ከሞላ ጎደል በራሳቸው አያያዝ ስለሚወሰን ለብሔር የበላይነት የማይመች አወቃቀር የተፈጠረ ሊመስል ይችላል፡፡ ግን ይህ መልክ ብቻ ነው፡፡ እያንዳንዱ የፌዴራል ሥርዓቱ አካል የሆነ አካባቢ ከአንዳድ፣ ከአንድ ነጠላ ብሔረሰብ ብቻ የተሠራ አይደለምና ከብሔረሰብ ጋር የተያያዘ ቡድናዊ ጫና (ጭቆና) በየክክሎች ውስጥም ሊከሰት የሚችል መሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ ይህንን ለማጤን በየክልሉ ዋና የአካባቢው ባለቤት ነኝ እያለ የሚያንጓልል ገዥነት አለ ወይ? ብሎ መጠየቅ ብቻ በቂ ነው፡፡ ከክልል ውጪ ሁሉን በሚያስተሳስረው አገዛዝ፣ በአገር አቀፍ ደረጃም ሊዘረጋ የሚችልበት ቀዳዳ አለ፡፡ የእነዚህን ቀዳዳዎች መዘጋትና አለመዘጋት የሚወስነው በየአካባቢዎችና በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው አገዛዝ፣ በሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ልዕልና የሚመራ መሆን አለመሆኑ ነው፡፡ እዚህም ላይ በኢትዮጵያችን በየአምስት ዓመቱ የአካባቢዎችና የፌዴራል ሪፐብሊኩ ተወካዮች ምርጫ የሚካሄድበት፣ በተወካዮች ምክር ቤቶችም ውሳኔ የየአካባቢና የፌዴራል ሥልጣን መሪዎች የሚሾሙበት ሥርዓታዊ ቅርፅ ስላለ ቀዳዳዎቹ የተዘጉ ሊመስል ይችላል፡፡

የምክር ቤቶች በምርጫዎች መደራጀታቸውም ሆነ ሿሚነትና ተቆጣጣሪነታቸው ከመልክ ያለፈ እውነታ መሆን አለመሆኑ የመንግሥታዊ አውታራቱ፣ በተለይም የፀጥታ አውታራቱ፣ ከፖለቲካ ቡድን መዳፍ ነፃ በመሆንና ባለመሆናቸው ይወሰናል፡፡ በውድም በግድም መግዣ የሆኑት መንግሥታዊ አውታራት በአንድ ቡድን መዳፍ ወይም ወገንተኝነት ውስጥ እስከ ወደቁ ድረስ፣ ምርጫዎችና ምክር ቤቶች የዚያ ቡድን መጫወቻ ከመሆን አያመልጡም፡፡ የሕዝቦች እንደራሴያዊ ዋና ባለሥልጣንነት መረጋገጥና መዝለቅ የሚችለው የቆመባቸው መንግሥታዊ አውታራት፣ ከየትኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ ቡድን ታማኝነት ነፃ ሆነው እስከታነፁ ድረስ ብቻ ነው፡፡

ከዚህ ንድፈ ሐሳባዊ እውነት አኳያ የኢትዮጵያን እውነታ በትክክል ለማየት፣ የሚታየውንም ለመቀበል ለደፈረ ህሊና እውነቱ ፓውዛ መብራት ወይም አጉሊ መነጽር የማይሻ ነው፡፡ ሕወሓት፣ “ኢሕአዴግ” የሚል ካባ ደርቦ የኢትዮጵያ መንበረ ሥልጣን ላይ መጀመርያ ሲወጣ የፈጠነባቸውና የለፋባቸው ሁነኛ ሥራዎች ሁለት ነበሩ፡፡ አንደኛው ነባሮቹን የታጠቁ ኃይሎች (የጦር፣ የደኅንነትና የፖሊስ ኃይሎች) በትኖ በራሱ የተጋዳላይ አከርካሪ ላይ እንደገና መገንባት ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ከየብሔረሰቦች ለሕወሓት ፖለቲካ ተቀጥላ የሆኑ ብሔርተኛ ቡድኖች ማርባትና ተቀጥላነታቸውን በአስተማማኝ አዘላቂ የማድረግ ሥራ ነበር፡፡

ከቁጥጥር ያልወጣ ሕገ መንግሥት የማርቀቅና የማፅደቅ ክንዋኔ የተካሄደው በዚህ ውጤት ላይ ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ የመጀመርያ ምርጫ ከተካሄደበት 1987 ዓ.ም. እስከ ዛሬ ድረስ “ምርጫዎች”ን በማሸነፍ ስም ሥልጣንን በርስትነት የያዙት ሕወሓትና እርቢዎቹ ናቸው፡፡ ዋነኞቹ የሥልጣን ኃይል መሣሪያዎች (መከላከያ፣ ደኅንነት፣ ፖሊስ) የዝርዝር ጥንቅራቸው ኅብረ ብሔራዊነት እየጨመረ ቢሄድም፣ ዛሬም ድረስ ኢሕአዴጋዊ ባህርያቸው አልተቀየረም፡፡ የሕወሓት ተጋድሎ ታሪክን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ነፃነት ታሪክ፣ የ1983 ዓ.ም. ድልን የመላ ኢትዮጵያ ሕዝብ ድልና የአዲሷ ኢትዮጵያ ግንባታ መክፈቻ ያደረገ አመለካከት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋሮች አመለካከት ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቱ መከላከያ፣ ደኅንነትና ፖሊስ አውታራትም አመለካከት ነው፡፡

ሕወሓታዊ ኢሕአዴጋዊው አመለካከት ከታጠቀው መንግሥታዊ አውታር አልፎ፣ የፓርቲ መታወቂያ በያዘና ባልያዘ መልክ የመንግሥታዊ ሲቪል ቢሮክራሲን፣ የፕሮፓጋንዳ አውታራትን፣ መንግሥታዊ የትምህርትና ሥልጠና ተቋማትን፣ ከዚያም አልፎ የብዙኃን ማኅበራትን ሁሉ እያጥለቀለቀ እንዲውጥ ነው የተደረገው፡፡ ለሕወሓት የበላይነት መዘዝ የሆነው ይኸው በፌዴራላዊ መዋቅሩ በተለይም በታጠቀው መንግሥታዊ ኃይል ውስጥ ያለው የባህሪ ቃኝነት ነው፡፡

ሌላው ገጽ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ነው፡፡ በትጥቅ ትግል ዓለም ውስጥ ከደጋፊዎች ዕርዳታ ሳያሰባስብ፣ በውጊያ የሚታገለውን መንግሥት ሳይዘርፍና ከየድሎቹ ምርኮ ሳያሰባስብ ወታደራዊ አቅሙን ማሳደግና ወደ አሸናፊነት መጓዝ የሚችል ቡድን አይገኝም፡፡ ሕወሓት ግን ከዚህም ያለፈ ነበር፡፡ ነባሩን የኢትዮጵያ መንግሥት ድል ከመታ በኋላ የኢትዮጵያ ገዥ ወደ መሆን እየሄደ ሳለ በእጁ እየገባ የነበረውን ትኩስ የምርኮ ንብረት እንኳ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተወሰደ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት ብሎ ልመልስ ያላለ ቡድን ነበር፡፡ ሕወሓታዊ/ኢሕአዴጋዊ የሥልጣን መረቡን ከመዘርጋቱ ሥራ ጎን ለጎን ይኸው በምርኮና በሌላ መንገዶች የተሰባሰበ ሀብት ፖለቲካዊ ንቃተ ህሊና ለመሆንና “ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኛነት” ለመባል በበቃ ጎሰኝነት እየታገዘ (እንዳይሳጣም እነ ኦሕዴድንና ብአዴንን ማኖ አነካክቶ)፣ መንግሥታዊ ይዞታዎችን ወደ ግል ባዘዋወረ ግዥና አዳዲስ ኩባንያዎች በመክፈት በኩል ከፈብራኪ እስከ አከፋፋይ ንግድ ድርጅቶች የሰፋ የኢኮኖሚ መረብን በእነ ‹ኤፈርት› መልክ ለመዘርጋት ችሏል፡፡

አንድ ግለሰብ ከቤተሰቡ ጋር ሆኖ ወይም ከተለያየ ብሔርና አካባቢ የበቀሉ ግለሰቦች አንድ ላይ ገጥመው አገር ያካለለም ሆነ ከአገር አልፎ የሄደ የግዙፍ ኩባንያዎች መረብ ሊዘረጉ እንደሚችሉ ዓለማችን አሳይቶናል፡፡ የአገዛዝ አውታራትን ታማኝ መጠቀሚያ የማድረግ ነገር በግለሰብ ሊካሄድ እንደሚችል ሁሉ፣ የመንግሥት ሥልጣንን የዘረፋ ጥቅማችን ባሉ ፓርቲያዊ በሆኑና ባልሆኑ ቡድኖች ሊከናወን እንደሚችልም ይታወቃል፡፡ ሕወሓታዊ ቀለም በፓርቲዎች ላይም ሆነ በአገዛዙ ላይ የማጋባትና የኩባንያዎች መረብ ፈጠራውም ቢሆን በመሠረቱ የቡድን ሥራ ነው፡፡

እነዚህ የቡድን ሥራዎች የትግራይ ሕዝብ መታሚያና መጠመጃ ሊሆኑ የቻሉት ትግራዊነትንና ቡድኑን ምን አገናኝቷቸው ነው? በያዝነው 2010 ዓ.ም. “ኢኤንኤን” በተባለ የቴሌቪዥን ሥርጭት ላይ በተደረገ አንድ ውይይት፣ “ለምንድነው ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ ተለያይተው የማይታዩት? ለምን በትግሬነት ጥቃት ይፈጸማል?” የሚል ጥያቄ ያነሳ ሰው ነበር፡፡ መውጫ የቸገረው ተገቢ ጥያቄ፡፡

እዚህ ላይ ብሔሩን ከሕወሓት ቡድን ለመለየት እክል የሆነው (ለብሔሩ መታማት መዘዝ የሆነው) ገጽታ ድቅን ይላል፡፡ ፖለቲካዊ ቡድኑና የኩባንያ መረቡ ባለቤትነት ከብሔረሰባዊ ውጥንቅጥነት የተገነባ ቢሆን ኖሮ ጣጣው የራሱ የቡድኑ ዕዳ ሆኖ ይቀር ነበር፡፡ በዚህ ፋንታ ትግራዊነትን መሠረት አድርጎ የተደራጀ መሆኑ የቡድኑ ጣጣ ለመላው ትግራዊነት እንዲተርፍ አደረገው፡፡ በብዙ ብሔረሰቦች አገር ውስጥ የሚፈጠር የዚህ ዓይነት ብሔረሰባዊ አምሳያነትን መሠረት ያደረገ ስብስብ ጣምራ አሳሳችነትን ያስከትላል፡፡ ቡድኑ የሚሠራውን ጥፋትንም ሆነ መልካም ነገር ለመላ ብሔረሰቡ ሰጥቶ የእከሌ ብሔረሰብ እያሉ ማውራት ይመጣል፡፡ የቡድኑን ብሔረሰባዊ መገኛ በሚጋሩ ሰዎች ዘንድም ቡድኑን የእኛ (ለእኛ የቆመ) ብሎ ማሰብ ይፈጠራል፡፡  ቡድን አንድ ግለሰብ ሥልጣን ላይ ሲወጣ እንኳ የእኛ ወገን (ለእኛ ሊያዳላ የሚችል) ወጣ የሚል ግምት አብሮ ብቅ ይላል፡፡

በብሔርተኛነት የተሟሹ ማኅበራዊ አዕምሮዎች በደሩበት (ኅብረ ብሔራዊ የጋራ ትግል በደከመበት) እና ዴሞክራሲ ከይስሙላ ባላለፈበት አገር ውስጥ ደግሞ እንኳን ሥልጣን ግለሰባዊ ፀቦች ሳይቀሩ በብሔረሰቦች ዓይን እየታዩ፣ የጅምላ አምባጓሮና የሰፋ ግጭት መክፈቻ እስከመሆን ድረስ ችግር ያባዛሉ፡፡ እነዚህን መሰል ችግሮችን ሁሉ የማስወገድ ሥራ በየብሔርተኛነት ከተጣበበ አዕምሮና ፖለቲካዊ አደራጃጀት መውጣትንና ከወገንተኛነት በፀዱ አውታራት ላይ ዴሞክራሲን መገንባት ይጠይቃል፡፡ ራስን ማታለል ካላማረን በቀር ደግሞ በኢትዮጵያ እስካሁን በብሔረተኛ ሩጫዎች ያገኘናቸው ልምዶች ይህንን እውነት ለመገንዘብ አያንሱንም፡፡ የእኛ ብሔርተኛ ልሂቃን ግን የኑሮ ልምድ ትምህርት እንዲህ በቀላሉ የሚዘልቃቸው መቼ ሆነው?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...