Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኬንያ ትልልቅ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ዝግጅት ጀምረዋል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኬንያው ሳፋሪኮምና ኬሲቢ ባንክ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር በኢትዮጵያ እንደሚተገብሩ ይፋ ካደረጋቸው ለውጦች መካከል የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉና በከፊል ወደ ግል እንደሚዛወሩ የሚለው፣ ከአገር ውስጥም ከውጭም ትልቅ ፍላጎት ፈጥሯል፡፡

የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት፣ በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ወደ ግል እንደሚዛወሩ አለያም የአክሲዮን ድርሻቸው ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች በከፊል እንደሚሸጥ ይፋ የተደረጉ ትልልቅ የልማት ድርጅቶች ትኩረታቸውን ከሳቡት መካከል የኬንያ ኩባንያዎች፣ በዚህ ሳምንት ያወጡት መግለጫ ትኩረትን ስቧል፡፡

በኬንያ ሰፊ የገበያ ሽፋን እንዳለው የሚነገርለት ሳፋሪኮም የተሰኘው የቴሌኮም ኩባንያ፣ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ጫፍ መድረሱ ከሰሞኑ ተዘግቧል፡፡ መረጃዎች እንዳመለከቱት፣ ኢትዮ ቴሌኮም በከፊል ወደ ግል እንደሚዛወር በመወሰኑ ምክንያት በኢትዮጵያ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት መስክ የመግባት ፍላጎት እንዳለው ያስታወቀው ሳፋሪኮም፣ በኬንያ ሰፊ የገበያ ድርሻና ዕውቅና ያለውን ‹‹ኤም-ፔሳ›› የተሰኘውን የሞባይል የክፍያ ሥርዓት ለማምጣት ከመንግሥት ጋር በመነጋገር ላይ እንደሚገኝ ዘገባዎች አመላክተዋል፡፡ 

ማርሳቢት ከተሰኘው የኬንያ አካባቢ እስከ ሞያሌ ድረስ የተዘረጋውን የ260 ኪሎ ሜትር የፋይበር ኬብል ከዘረጋው የሞውሪሸየስ ኩባንያ የገዛው ሳፋሪኮም፣ ወደ ኢትዮጵያ የቴሌኮም ገበያ ዘልቆ የመግባት ዝግጀቱ ምን ያህል ጫፍ እንደደረሰ አሳይቷል፡፡ በኢትዮጵያ ከ16 ሚሊዮን በላይ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች መኖራቸውና ኢትዮ ቴሌኮም በቅርቡ ለሌሎች ኩባንያዎች የሰጠው የቨርቹዋል ኢንተርኔት አቅርቦት አገልግሎት ስምምነትም በገበያው ውስጥ እንደልብ ተወዳድሮ ለመሥራት የሚያስችልና የውጭ ኩባንያዎችንም የሚጋብዝ ለውጥ ሆኖ እንዳገኘው ሳፋሪኮም ማስታወቁን የኬንያ ድረ ገጾች ዘግበዋል፡፡ ከ30 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች በኬንያ በአጎራባች አገሮች ያፈራው ሳፋሪኮም፣ በለንደን ከሚገኘው እህት ኩባንያው ቮዳፎን በኩል በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀስበትን የንግድ ስያሜና ምልክት ማግኘቱና ከመንግሥት ጋር ድርድር መጀመሩንም ሮይተርስ ስለመዘገቡ ተሰምቷል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1896 በዛንዚባር የናሽናል ባንክ ኦፍ ኢንዲያ ቅርንጫፍ ባንክ በመሆን የተመሠረተው፣ ኬሲቢ ባንክ ከካቻምና ወዲህ ወደ ግሩፕ ኩባንያዎች ደረጃ ራሱን በማሳደግ በምሥራቅ አፍሪካ እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከኬንያ ባሻገር በታንዛንያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኡጋንዳ፣ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ እንዲሁም በኢትዮጵያ ጭምር በመደበኛ ባንክነት የማይንቀሳቀሱ ነገር ግን ወኪል ጽሕፈት ቤቶቹን እንደከፈተ አስታውቋል፡፡

ኬሲቢ ግሩፕ፣ ከወኪል ባንኮቹ በተጨማሪም ኬሲቢ ኢንሹራንስ ኤጀንሲ፣ ኬሲቢ ካፒታል፣ ኬሲቢ ፋውንዴሽን የተባሉትን ኩባንያዎችና ሌሎችም ኩባንያዎቹን በአንድ ጥላ ሥር ማስተዳደር ጀምሯል፡፡ በኢትዮጵያ የታየውን ለውጥ በመከተል በአገሪቱ የፋይንስ ኢንዱስትሪ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ያለውን ተስፋ ከመግለጽ ባሻገር፣ በቅርበት በመሆን የመንግሥትን ውሳኔ እየተከታተለ እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል፡፡ በኢትዮጵያ የሚታየው የባንኮች ተደራሽነት ዝቅተኛነት፣ የፋይናንስ አገልግሎት ደካማ መሆንና አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል የባንክ ሒሳብ እንደሌለው መገንዘባቸውን የኬሲቢ ባንክ ኃላፊዎች በመግለጽ ልዩ ልዩ የባንክ አገልግሎቶችን ለኢትዮጵያውያን ማቅረብ የሚችሉበትን የገበያ ዕድል የኢትዮጵያ መንግሥት ይፈጥራል የሚል ተስፋ እንዳላቸው እየተገለጸ ይገኛል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች