Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ባንኮች ሆይ የመጣውን የዶላር ሲሳይ እንዳታሳጡን

የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለዓመታት የዘለቀ ችግር ነው፡፡ በዓለም ላይ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያስመዘገበች እንደሆነ በተደጋጋሚ የተነገረላት ኢትዮጵያ፣ የውጭ ምንዛሪ ካዝናዋ ሁሌም ረሃብተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡ ዛሬም ድረስ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ፋብሪካዎቻቸውን የዘጉ፣ ሠራተኞቻቸውን የቀነሱ፣ ከአቅማቸው በታች ለማምረት የተገደዱ በርካቶች እንደሆኑ እየታየ ነው፡፡

 የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሥራቸውን ያስተጓጎለባቸው እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ለምርት ሥራ የሚፈልጉትን ጥሬ ዕቃ መግዣ ያጡ፣ ነገም ስለማግኘታቸው ግራ የገባቸውና የመፍትሔ ያለህ የሚሉ ቁጥራቸው ብዙ ነው፡፡ ሌሎችም የጎንዮሽ ችግሮች ታክለውበት፣ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የሚጠባበቁ ነጋዴዎችም ሆኑ የፋብሪካ ባለቤቶች የባንኮችን ደጅ በመጥናት ባጅተዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ እየባሰበት በመምጣቱ ብቻም ሳይሆን የገንዘብ ለማሸሽ ሲደረጉ በነበሩ እንቅስቃሴዎች ሳቢያ፣ የጥቁር ገበያ የምንዛሪ ዋጋን ጣራ ያስነኩ ምክንያቶች ተበራክተዋል፡፡ በውጭ ምንዛሪ እቶት የተነሳ ጥሬ ዕቃ መግዛት ያቃተው ነጋዴ፣ ፋብሪካ መዝጋቱን በምሬት በሚናገርበት ከተማ ውስጥ ለውስኪ፣ ለኮስሞቲክስና ለቄንጠኛና ውድ መኪኖችና ዕቃዎች መግዣ የሚውለው ረብጣ ዶላር ከየት ይሆን የሚመጣው? ያሰኛል፡፡

በባንክ ዋጋና በጥቁር ገበያ መካከል ያለው የምንዛሪ ልዩነት ተምቦርቆ በቆየበቻው ጊዜያት፣ የአንድ ዶላር ዋጋ ከመደበኛው የምንዛሪ ዋጋ እስከ እስከ አሥር ብር የሚዘልቅ ብልጫ በማሳየቱ አጀብ ተብሏል፡፡ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዶላር ስንት ገባ? የሚለው የሰርክ ጥያቄያቸውም እየተበራከተ መጥቶ ነበር፡፡

ከጥቅምት 2010 ዓ.ም. የብር የመግዛት አቅም በ15 በመቶ እንዲቀንስ ከተደረገ በኋላ፣ የባንኮች የምንዛሪ ዋጋ ወደ 27.26 ብር ከፍ ሲል፣ በጥቁር ገበያም በአንድ ዶላር የምንዛሪ ዋጋ እስከ 37 ብር ድረስ አሻቅቦ ነበር፡፡ ብዙዎች ከባንኮች የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ዕድል ሲያጡ፣ ወደ ጥቁር ገበያው ጎራ እያሉ መመንዘራቸው ብቻም ሳይሆን፣ ዘመድ አዝማድ ከውጭ የሚልክላቸውን ገንዘብ ወደ ጥቁር ገበያው አጋፋሪዎች በመሔድ መዘርዘር የተለመደ ነበር፡፡ ይህም የጥቁር ገበያው ጡንቻ አፈርጥሞት ቆይቷል፡፡ በባንክና በጥቁር ገበያ መካከል የነበረው የምንዛሪ ልዩነት ከፍተኛ ስለነበር፣ በተለያየ መንገድ የሚገኙ የውጭ ገንዘቦችን በባንክ ከመመንዘር ይልቅ ወደ ጥቁር ገበያ በመሔድ መመንዘር መደበኛ ሆኖ ሲሠራበት ቆይቷል፡፡ እንዲህ ያለው ተግባር በብዛት ሲፈጸም የሚታየውም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አቅራቢያ በሚገኙ  ትናንሽ መደብሮች ጭምር መሆኑ እየታወቀ እንኳ አድራጎቱ ከልካል አልነበረውም፡፡

ይሁንና ባልታሰበና ባልተጠበቀ መንገድ ከጥቂት ቀናት ወዲህ በጥቁር ገበያውና በባንኮች መካከል የነበረው ሰፊ የምንዛሪ ዋጋ ልዩነት እየጠበበ መጠቷል፡፡ ይህ በአሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ አስገራሚ ሊባል የሚችል ክስተት ሆኖ ሊመዘገብ የሚችል ለውጥ ነው፡፡ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይ በጥቁር ገበያ አንድ ዶላር ከ28 ብር በታች እስከ 27.70 ብር ዝቅ ብሎ ነበር፡፡ በዚህም ሳቢያ ‹‹ባንኮችን በዘበዙን›› የሚለው ስሞታ ‹‹ዶላር ረከሰ›› በሚለው መተካት ጀምሯል፡፡ ‹‹ባንኮችን በዘበዙን›› የሚለው ነባር ስሞታ፣ ‹‹ምን ዋጋ አለው ዶላር ረከሰ፤ እኛን አከሰረ፤›› በሚለው መተካት ጀምሯል፡፡

በሳምቲም ደረጃ የወረደው የጥቁር ገበያ የምንዛሪ ልዩነት ዘላቂ እንደሆን ምኞታችን ሲሆን፣ በዚህ ረገድ የታየው፣ መመስገንና መወደስ ያለበት ተግባር የውጭ ገንዘብ ለመመንዘር ወደ ባንክ ሄደው የማያውቁ ዜጎችም፣ ከሰሞኑ ወደ ባንክ በሄደው በተመደበላቸው የምንዛሪ ዋጋ ሲመነዝሩ መታየታቸው ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማሳሰቢያ ሰምተው ወደ ባንኮች የሄዱ ብቻም ሳይሆኑ፣ ያላቸውን ዶላር በሕጋዊ መንገድ መመንዘር ኃላፊነታቸውን የመወጣት ግዴታ ስለመሆኑ የገለጹልኝም ነበሩ፡፡ በእጁ የነበረችውን ሽርፍራፊ ዶላር ወደ ባንክ በመሔድ የመንዘረ አንድ ወዳጄ፣ ‹‹ለመጀመሪያ ጊዜ ዶላር በባንክ መመንዘሬ አስደስቶኛል፤ አገሬንም እንደረዳሁ ተሰምቶኛል፤›› ብሎኛል፡፡ እንዲህ የለውጥና የመነሳሳት መንፈስ መፈጠሩ ቀላል ነገር አይደለም፡፡

ለነገሩ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቆንጠጥ ያለ ማስጠንቀቂያ ግምት ውስጥ አስገብተው ወደ ባንክ የሄዱትም ቢሆኑ ሊመሠገኑ ይገባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ጥቅሙ አነስተኛ ቢሆንም በጥቁር ገበያ መመንዘር እየቻሉ ወደ ባንክ መሔዳቸው ትልቅ ለውጥ ነውና፡፡ ነገም መቀጠል ያለበት ብርቱ ጉዳይ ነው፡፡ ዶላር በባንክ መንዝሬ መጣሁ ብለው ደረታቸውን ነፍተው በኩራት መናገር የሚችሉ ዜጎችን እያየን ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን ምሳሌ የሆኑ ዜጎች ዶላር ሊመነዝሩ ወደ ባንኮች ያቀኑ ሰዎች የገጠማቸው ጉዳይ መጠቀስ ይኖርበታል፡፡ ዜጎች በፍላጎታቸውም በስጋትም ወደ ባንክ ሄደው ዶላር ሊመነዝሩ ሲሞክሩ በአንዳንድ ባንኮች ቅርንጫፎች የጠበቃቸው መስተንግዶ የሚያበረታታ አይደለም፡፡ ባንኮቹ ይኼንን ወርቃማ ዕድል በአግባቡ እየተጠቀሙበት አለመሆኑ እያስተቻቸው ነው፡፡ የውጭ ገንዘብ ይዘው የመጡ ደንበኞቻቸውን በቅልፍጥና አያስተናግዱም፡፡ ለብቻው መስኮት ማዘጋጀት ሲገባቸው፣ ይኼንን ባለማድረጋቸው ወረፋ በዝቶ መታየቱ አግባብ አይደለም፡፡ እንደውም ብዙዎቹ ቅርንጫፎች ሕጋዊ ገንዘብ መሆኑን የሚለዩትበት ዘመናዊ መሣሪያ እንደሌላቸውም ታይቷል፡፡ በእርግጥ ወደ ባንኮቹ ሔዶ የውጭ ገንዘብ መመንዘር ጉዳት እንደሆነ ሲታሰብ በተኖረበት አገር ውስጥ አስቦና ፈልጎ ለመመንዘር የሚመጣውን በርካታ ተገልጋይ ይመጣል ብሎ ካለማሰብ የተነሳ የመፈተሻ መሣሪያኛ የመቁጠሪያ ማሽን አዘጋጅቶ መጠበቅ ላይታሰብ ይችላል፡፡  ቢሆንም የኅብረተሰቡ ተነሳሽነትና ፍላጎት እንዲጨምር ወደ ባንክ የሚሔደው ገንዘብ ለመመንዘር ብቻ ሳይሆን ጥሩ አገልግሎትና መስተንግዶ አግኝቶ ተሰደስቶ ለመመለስም እንዲሆን የሚያደርግ መስተንግዶ ቢሰጡ ባንኮቹን ይረዳቸዋል፡፡ ዶላር እንደ ሰማይ በራቀበት በዚህ ወቅት፣ የውጭ ምንዛሪ ባልተለመደ ሁኔታ ታቅፎ እየመጣ ያለውን ደንበኛ በእንክብካቤ ማስተናገድ ሲገባ የተንቀራፈፈ አገልግሎት እየሰጡ ማጉላላቱ ጋሬጣ እንዳይሆን ያሰጋል፡፡

በእርግጥም በአንዳንድ ባንኮች ዘንድ ይህንን መመልከት ይቻላል፡፡ የውጭ ገንዘቦች ትክክለኛነትን ለማጣራት የሚፈጅባቸውን ጊዜ ታዝቤያለሁ፡፡ ይህ ከሆነም ደንበኛውን በተለየ መስኮት መስተናድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንደውም ባንኮችቹ ይኼንን አጋጣሚ ተጠቅመው ሽልማት ጭምር እያዘጋጁ ቢሠሩ፣ ተፎካካሪ የሚሆኑበትን ዕድል ይፈጥራሉ፡፡ ዜጎች ተገደውም ሆነ ፈቅደው ወደ ባንክ በማቅናት መመንዘራቸው በጎ ጅምር ነውና ምሥጋና ይቸራቸዋል፡፡ ዳያስፖራውም በባንክ በኩል ገንዘብ መላኩን ማስፋፋቱ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት