Sunday, October 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልጥበብ በጎዳና

ጥበብ በጎዳና

ቀን:

‹‹ልጁ አስማተኛ ነው፤ አየር ላይ ጠርሙስ ደራርቦ ማቆም የሚችለው አስማተኛ ብቻ ነው፡፡››፣ ‹‹አስማተኛ ሳይሆን ስፖርተኛ ነው፤ ብዙ ጊዜ ተለማምዶ ነው፡፡››፣ ‹‹ልጁን አውቀዋለሁ፤ በየሠፈሩ እየተዘዋወረ ኳስ ያንጠባጥባል፤ በጣም አስደናቂ ሥራ ነው የሚሠራው፡፡››፣ ‹‹የሚያሳየው ነገር ያን ያህል ከባድ አይደለም፤ እኔም የምችለው ይመስለኛል፡፡››

እነዚህና ሌሎችም አስተያየቶችን የሚሰነዝሩ ሰዎች ያስተዋልነው ባለፈው ረቡዕ መጋቢት 28 ቀን 2008 ዓ.ም.  አራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ ነበር፡፡ ወደ 11 ሰዓት ገደማ እሳት አደጋ መካላከያ ጀርባ ባለ ክፍት ቦታ ላይ አንድ ወጣት ገመድ መዝለል ጀመረ፡፡ ሰዓቱ ከሥራ መውጫ እንደመሆኑና አካባቢው የባቡር ማቆሚያ በመሆኑም ብዙ ሰዎች በአካባቢው ይተላለፋሉ፡፡ አንዳንዶች ወጣቱን ቆም ብለው አይተው መንገዳቸውን ሲቀጥሉ፣ ሌሎች  ጠጋ ብለው ይመለከታሉ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ኳስ ማንጠባጠብ ጀመረ፡፡ ኳሱ መሬት ሳይነካ ሰውነቱ ላይ ሲያነጥረው ሌሎች መንገደኞችም እየተገረሙ ከበቡት፡፡ የሚስቁ፣ የሚያጨበጭቡ፣ በሞባይላቸው ቪዲዮ የሚቀርጹና ፎቶ የሚያነሱም ተመልክተናል፡፡ ቀስ በቀስ ተማሪዎችና ፐብሊክ ባስ የሚጠብቁ ሠራተኞች፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችም ተሰባሰቡ፡፡

ኳሱን መሬት ሳያስነካ በግንባሩ፣ በአገጩ፣ በትከሻው፣ በወገቡና በእግሩ ያለማቋረጥ ሲያንጠባጥብ አንድ፣ አምስት፣ አሥር ብርም የሰጡት ነበሩ፡፡ ኳሱን እያንጠባጠበ ይተኛል፣ ይነሳል፣ ይተጣጠፋል፣ ልብሱን እያወለቀ ይለብሳል፡፡ ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል ፈቃደኛ የሆኑትን በመጋበዝ እሱ ከሚያሳየው እንቅስቃሴ የቻሉትን እንዲሠሩ ይጠይቃል፡፡ ሁለት ወንዶች ወገባቸው ላይ በክር እስኪርቢቶ አስሮላቸው በጠርሙስ አፍ ውስጥ እንዲያስገቡ ተጠየቁ፡፡ የእስኪርቢቶውን ንቅናቄ ለመቆጣጠር እየሞከሩ በጠርሙስ ለመክተት ያደረጉት ጥረት ታዳሚውን ያዝናና ነበር፡፡ ከታዳሚዎቹ እስኪርቢቶ ወይም ኮፍያ ተቀብሎ እፍንጫቸው ላይ እንዲያቆሙት ይጠይቃቸዋል፡፡ ሞክረው ሲያቅታቸው ተቀብሏቸው አፍንጫው ላይ ያቆማል፡፡ ሰውም ሞቅ ያለ ጭብጨባውንና ፉጨቱን ይቀጥላል፡፡

ወጣቱ አረጋ ታደሰ ይባላል፡፡ ተመሳሳይ ትርኢቶችን ለስምንት ዓመታት ያሳየ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ውስጥ ያልደረሰበት ሠፈር አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሳይክል ወይም ወንበር አፍንጫው ላይ የማቆም ትርኢት ጀምሯል፡፡ አረጋ ያደገው በሕፃናት ማሳደጊያ ሲሆን፣ ከልጅነቱ ጀምሮ በኳስ የተለያዩ ትርኢቶችን ማሳየት ይወድ ነበር፡፡ በታዳጊነቱ በሕፃናት ማሳደጊያዎች በሚዘጋጁ መርሐ ግብሮች ትርኢቱን በማሳየት ታዋቂነት አገኘ፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ጎዳና ላይ ትርኢት የማሳየት ፍላጎት አደረበት፡፡ ከስምንት ዓመት በፊት መስቀል አደባባይ ጎዳና ላይ ኳስ ማንጠባጠብ ጀመረ፡፡ ያኔ ያንጠባጠበውን ኳስ እስከዛሬ ድረስ ትርኢት ያሳይበታል፡፡ በየቀኑ አመሻሽ ላይ በየሰፈሩ እየተዘዋወረም ትርኢቱን ያቀርባል፡፡

ትርኢቱን ሲያሳይ የሚያደንቁት እንዳሉ ሁሉ ‹‹መተተኛ ነው›› እያሉ የሚነቅፉትም አሉ፡፡ ከባዱ መሰናክል የሚገጥመው ግን ከፖሊሶች ነው፡፡ ብዙ ሰዎችን በመሰብሰብ፣ የትራፊክ ፍሰትን በማስተጓጎልና በመሰል ጉዳዮች በተደጋጋሚ ታስሯል፡፡ አንዳንድ ፖሊሶች ግን ስለ ሥራው ካወቁ በኋላ ሕዝቡ ሥነ ሥርዓት ይዞ እንዲያይ ከመቆጣጠር ባለፈ አያስቆሙትም፡፡ አንዳንድ ተመልካቾች ገንዘብ ሲሰጡት አጨብጭበው የሚሄዱም አሉ፡፡ 1,000 ብር የሸለመውን ሰው ሁሌ ያስታውሰዋል፡፡ ትርኢቱ እሱና ሴት ልጁን የሚያስተዳድርበት ብቸኛ ገቢው ሲሆን፣ ብዙዎች ለጎዳና ትርኢት ገንዘብ የመስጠት ልማድ ስለሌላቸው ገቢው እምብዛም እንዳልሆነ ይናገራል፡፡

የአረጋ የጎዳና ክዋኔ (ስትሪት ፐርፎርማንስ) በሌሎች አገሮች የተለመደ ነው፡፡ የጎዳና ትርኢቶች ለባለሙያዎቹ እንደ ገቢ ምንጭ ከመሆናቸው ባሻገር ተመልካችንም ያዝናናሉ፡፡ የሰርከስ ባለሙያዎች፣ ሙዚቀኞች፣ ፕርፎርማንስ አርቲስቶችና ተወዛዋዦች ጎዳና ላይ ጥበባዊ ሥራዎች ከሚያሳዩ መካከል ናቸው፡፡ በኛ አገርም ገንዘብ ለማግኛም ይሁን ጥበብን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የማድረግ ዓላማን በማንገብ ትርኢት የሚያሳዩ ባለሙያዎች አሉ፡፡ በእርግጥ ከሌሎች አገሮች አንፃር ባለሙያዎቹ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡

አረጋ እንደሚለው፣ የጎዳና ትርኢት እንዲለመድ እንደሱ ጥረት የሚያደርጉ ባለሙያዎች መበረታት አለባቸው፡፡ ተመልካቾች ባለሙያዎቹን ሊያከብሩና መንግሥትም በቀላሉ ፈቃድ ሊሰጣቸው ይገባል ይላል፡፡ መለማመጃ ቦታ ስለሌለው እንጦጦ ጫካ ውስጥ ይለማመዳል፡፡ ረዥም ጊዜ ተለማምዶ የሚያቀርበው ትርኢት ግን የልፋቱን ያህል ገንዘብ አያስገኝለትም፡፡ ‹‹ወደ ሁለት ሰዓት ኳስ ሳንጠባጥብ፣ በግንባሬ ወደ 3,000 ጊዜ ኳስ ስመታ ሰው ከማድነቅ ይልቅ በጥርጣሬ ተሞልቶ ኳሱን ይቀይር ይላል፡፡ ኳሱ ላይ አስደግሞበታል የሚሉም አሉ፤›› ይላል፡፡

ትርኢት ለማሳየት ከሕዝብ የሚዋሳቸውን ኮፍያዎችና እስኪርቢቶዎች  ተጠቅሞ ሲመልስላቸው ‹‹አንዳች ነገር ደግሞበታል›› ብለው የማይቀበሉት አሉ፡፡ የኅብረተሰቡ አመለካከት ካልተለወጠ ለውጥ ለማምጣት ያስቸግራል የሚለውም ከዚህ ተሞክሮው በመነሳት ነው፡፡ የሕዝቡን ጊዜ አቃጠለ፣ ሰዎችን በመተት አፍዝዞ አቆመ በማለት ትርኢት የሚያሳይበትን ጠርሙስ እስከመሰባበር የደረሱም ገጥመውታል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስለ ጎዳና ትርኢት ያለው አመለካከት ቢለወጥም ብዙ እንደሚቀረው ይናገራል፡፡ ፖሊሶች ሲያስሩት እንዲለቀቅ የሚጠይቅ ማኅበረሰብ ሲገጥመው ለጥብበ ተቆርቋሪ እንዳለ ያመላክተዋል፡፡ አንዴ ናዝሬት ሄዶ ትርኢት አሳይቶ ነበር፡፡ መጀመሪያ ሕዝቡ ግራ ቢጋባም ቀስ በቀስ ትርኢቱን የሚመለከቱ ሰዎች ተበራከቱ፡፡ ፖሊሶች ፀጥታ አደፍርሷል ብለው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ሲወስዱት፣ ትርኢቱን ይመለከቱ የነበሩ ሰዎች ይለቀቅልን ብለው ፖሊስ ጣቢያውን አጨናንቀውት ተፈቷል፡፡

ጥበባዊ ሥራዎችን ለመታደም ዕድሉን የማያገኙ ሰዎችን በጎዳና ትርኢት መድረስ እንደሚቻል ይገልጻል፡፡ ሐሳቡን የሚጋራው ተወዛዋዥ መላኩ በላይ ነው፡፡ መላኩ በባህላዊ ውዝዋዜ ዓለም አቀፍ እውቅና ካላቸው ተወዛዋዦች አንዱ ሲሆን፣ መርካቶ ምን አለሽ ተራ በብረት ቀጥቃጮች ታጅቦ ያሳየውን ውዝዋዜ ብዙዎች ያስታውሱታል፡፡ ብረት ቀጥቃጮቹ ሌላ ጊዜ እንደሚሠሩት ያለማቋረጥ ሲቀጠቅጡ፣ መላኩ መላ ሰውነቱን እያንቀጠቀጠ ይጨፍራል፡፡ የተለያዩ ብሔረሰቦችን ውዝዋዜ እየለዋወጠ ያሳያል፡፡ ትርኢቱ ‹‹አሁን›› ወደተሰኘ አጭር ዘጋቢ ፊልምም ተለውጧል፡፡

እሱ እንደሚለው፣ በፌስቲቫሎችና በኮንሰርቶች ወይም እንደ ምሽት ክለብ ባሉ ቦታዎች ተገኝተው ጥበባዊ ሥራዎችን መመልከት የሚችሉ ሰዎች ጥቂት ናቸው፡፡ የጎዳና ትርኢት  ሲቀርብ ግን በተለያየ ዕድሜ፣ ፆታና ሙያ ያሉ ሰዎች የመመልከት ዕድል ያገኛሉ፡፡ የጎዳና ትርኢቶች ለኢትዮጵያ አዲስ እንዳልሆኑ ይናገራል፡፡ እንደ ደመራና ጥምቀት ያሉ በዓሎችን ምክንያት በማድረግ ልዩ ልዩ ባህላዊ ትርኢቶች ይታያሉ፡፡ አዝማሪዎች በገጠር በተከተማም ጎዳና ላይ ይዘፍናሉ፡፡ እሱም ከዚህ በመነሳት በየዓመቱ ለጥምቀት ጃንሜዳ ውዝዋዜ ያሳያል፡፡ አንድ ወቅት ለገሀር አካባቢ አውቶብስ ውስጥ ገብቶ በአውቶብሱ ክላክስ እየታጀበ ተወዛውዟል፡፡ አውቶብሱ ውስጥ የነበሩ አንድ አዛውንት ‹‹አውቶብሱን ልታስገለብጠው ነው እንዴ? አርፈህ ተቀመጥ›› ብለው ገስጸውት ነበር፡፡

በእሱ እምነት፣ አማተርም ይሁን አንጋፋ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን ያለቅድመ ዝግጅት ጎዳና ላይ ማቅረብን መልመድ አለባቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ በጎዳና፣ በመገበያያ ቦታዎችና ሌሎችም ሕዝብ የሚበዛባቸው አካባቢዎች ትርኢት የሚያቀርቡ ታዋቂ ባለሙያዎች ማየት የተለመደ ነው፡፡ ለዓመታት የጎዳና ትርኢት ሲያሳዩ ቆይተው ታዋቂነት ያገኙ ብዙዎች ናቸው፡፡ ዝነኛዋ ድምፃዊት ትሬሲ ቻፕማን የጎዳና ዘፋኝ ነበረች፡፡ ፖለቲከኛ፣ ደራሲ፣ ፈጣሪና የብዙ ሙያዎች ባለቤት ቤንጃሚን ፍራንክሊን ጎዳና ላይ ግጥም ከማንበብ ነው የተነሳው፡፡ 

የጎዳና ትርኢት ሳካዩ ታዋቂ ሙዚቀኞች ሳሙኤል ይርጋ ይጠቀሳል፡፡ ፒያሳ ጎዳና ላይ ያለ ቅድመ ዝግጅት ፒያኖውን ይዞ ወጥቶ ተጫውቷል፡፡ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችና በአጋጣሚ በአካባቢው ያልፉ የነበሩ ተመልክተዋል፡፡ ከወራት በፊት ከሪፖርተር ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስም፣ ሙዚቃ በሚቀርብበት ቦታ የመገኘት ዕድሉን ማግኘት ለማይችሉ የማኅበረሰቡ ክፍሎች ሁነኛ መንገድ የጎዳና ትርኢት እንደሆነ ተናግሯል፡፡ መላኩ ‹‹ሕዝቡ የጎዳና ትርኢትን ያለ ምንም ልዩነት እኩል ሆኖ ይመለከታል፡፡ በቀላሉ መልክት የሚተላለፍበት መንገድ ከመሆኑ ባሻገር የባለሙያዎች ኦሪጅናል ሥራ ለሕዝቡ ይደርሳል፡፡ ሁሉም ባለሙያ በየፊናው ትልልቅ በሚባሉ መድረኮች ላይ ብቻ ሳይሆን አልፎ ሂያጁ ሰውም ቢያዝናና ያስደስታል፤›› ይላል፡፡

በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ሥራዎቻቸውን አቅርበው ተወዳጅነት ያገኙት ኢትዮከለሮች የጎዳና ትርኢት የማቅረብ እቅድ እንዳላቸውም ይናገራል፡፡ ፈቃድ ለማግኘት እየሞከሩ ሲሆን፣ ከተፈቀደላቸው መላኩን ጨምሮ ሌሎችም የኢትዮከለር የባህል ሙዚቀኞችና ተወዛዋዦች በየጊዜው ድንገቴ የጎዳና ትርኢት የሚያሳዩ ይሆናል፡፡

ስለጎዳና ትርኢት ሲነሳ በፐሮፎርማንስ አርት (ክውን ጥበባት) ረገድ በጥቂቱም ቢሆን ጭላንጭል እየታየ እንደሆነ ከሚያምኑ ባለሙያዎች አንዱ ነው፡፡ ብዙ ባይሆኑም ፐርፎርማንስ የሚያሳዩ የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች አሉ፡፡ ሠዓሊ ታምራት ገዛኸኝ መርካቶ ውስጥ ክዋኔ ካሳዩ አንዱ ሲሆን፣ ሠዓሊው ልብሱ ላይ አረንጓዴ ቀለም ቀብቶ ስለ ተፈጥሮ ጥበቃ መልዕክት ለማስተላለፍ ክዋኔውን አቅርቦ ነበር፡፡

ዘመን አየለ በጎዳና ትርኢት ከሚደሰቱ ሰዎች አንዷ ናት፡፡ አራት ኪሎ አካባቢ ሰርከስ፣ ቦሌ ደግሞ ሙዚቃ እንዳየች ታስታውሳለች፡፡ ቦሌ ያየቻቸው ሙዚቀኞች ሁለት ፈረንጆች ሲሆኑ፣ ጊታር እየተጫወቱ ሰዉ ገንዘብ እየሠጣቸው ሲያልፍ ማየቷ እንዳስገረማትም ትናገራለች፡፡ በቅርቡ ቦሌ መንገድ ላይ ያየችው ሥዕል ጥሩ ጅማሮ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ‹‹ሰዎች ተሰጥኦዋቸውን ሲያወጡ ሊበረታቱ ይገባል፤›› ትላለች፡፡

ካየቻቸው አንዳንዶች ጥበቡን ገንዘብ ለማግኘትም ያውሉታል፡፡ ቦሌ ያየችውን ሥዕል ሻጭና አራት ኪሎ ያየችውን በእግሩ የእንጨት ቁሳቁስ የሚሠራ ሰው ትጠቅሳለች፡፡ እንደ መላኩ በአደባባይ የሚወዛወዙና እንደ ልጅ ያሬድ ጎዳና ላይ የሚሥሉ ታዋቂ ባለሙያዎች ጥበቡን ለሕዝቡ ለማድረስ ይሠራሉ፡፡ ቢሆንም በቂ የጎዳና ትርኢት አለመኖሩን ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር ትስማማለች፡፡

ጥበብን የመመልከትና የማድነቅ ልማድ በጥቂቶች የተወሰነ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ ስለዚህም ጥበባዊ ሥራዎች ወደ ጎዳና ሲወጡ ኅብረተሰቡ ስለ ጥበብ የተሻለ ግንዛቤ እንደሚያገኝ ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡ የኢትዮጵያ ሠዓሊያንና ቀራፂያን ማኅበር ሥነ ጥበብን ወደ ጎዳና የመውሰድ ጅማሮ አሳይቷል፡፡ ከሦስት ሳምንታት በፊት ለወትሮው ልሙጥ የነበረው የቦሌ ጎዳና በቀለማት ማሸብረቅ ጀመረ፡፡ የኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች፣ የግዕዝ ቁጥሮች፣ የኢትዮጵያ ፊደላትና ሌሎችም ምስሎች በመንገዱ ይታያሉ፡፡ ሐሳቡ የአዲስ አበባ ከተማ ፅዳት፣ ውበትና መናፈሻ ዘላቂ ማረፊያ ኤጀንሲ ሲሆን፣ የሠዓሊያንና የቀራፂያን ማኅበር ከአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት፣ ከአቢሲኒያ የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤትና ከተፈሪ መኰንን የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት የተውጣጡ ተማሪዎች እንዲሥሉ አደረገ፡፡

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ሠዓሊ ሥዩም አያሌው እንደሚናገረው፣ የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ሐሳብ ከሸራ ባለፈ ኅብረተሰቡ ከሚደርስበት መንገድ አንዱ የጎዳና ሥዕል (ስትሪት አርት) ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንድ ቦታዎች ካሉ ትልልቅ የሞዛይክ ሥራዎች ባለፈ የጎዳና ሥዕል አልተለመደም፡፡ ቦሌ ሰፊ የትራፊክ ፍሰት ስላለ በአካባቢው መሣል ቢጀምሩም፣ ጥበቡን የማስፋፋት እቅድ አላቸው፡፡ ከኅብረተሰቡ የሚገኘው ምላሽ እየታየ ኢትዮጵያን እንዲሁም አፍሪካን የሚገልጹ ሥዕሎችንና ሞዛይኰች ማቆም እንደሚቀጥሉ ይናገራል፡፡

የጎዳና ሥዕሎች ባሉባቸው መንገዶች የሚተላለፉ ሰዎች ለጥቂት ደቂቃዎችም ቢሆን መልካም ነገር እንዲመለከቱ ማድረግ እንዳቀዱ ሠዓሊው ይናገራል፡፡ ‹‹ሥዕሎቹ ማኅበረሰቡ ስለ ሥነ ጥበብ ያለውን አመለካከት እንዲያስተካልና የጥበብ ሥራዎች ባለቤትነት እንዲሰማው ያደርጋሉ፤›› ይላል፡፡ በሌሎች አገሮች የጎዳና ላይ ሥዕሎች የኅብረተሰቡን ስሜት አንዳንዴም ተቃውሞ መግለጫ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ በተለይም ግራፊቲ አርትን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሁነቶችን ለመተቸት የሚያውሉ ጥበበኞች ብዙ ናቸው፡፡ በቅርቡ ግብፅ ካይሮ ውስጥ በተከታታይ የሚገኙ አምሳ ሕንፃዎች ላይ ግራፊቲ የሠራው ባለሙያ የመገናኛ ብዙኃን ተቀዳሚ ዜና ሆኖ ሰንብቷል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ስኬት››፣ በዋነኛነት በአዲስ አበባና በጥቂት የክልል ከተሞች ስኬት (ጎማ ባለው የእንጨት ቦርድ መንቀሳቀስ) የሚያደርጉ ወጣቶች የተሰባሰቡበት ድርጅት ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት የጎዳና ተዳዳሪዎችን ጨምሮ ብዙ ታዳጊዎችን ስኬቲንግ ከማሠልጠናቸው በተጨማሪ በፌስቲቫሎች ላይ ትርኢት ያሳያሉ፡፡ አብዛኞቹ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ስኬት ለማድረግ ባይመቹም፣ ባገኙት አጋጣሚ ስኬት ያደርጋሉ፡፡ በአንድ ወቅት ቦሌ ድልድይ ሥር ስኬት ሲያደርጉ የብዙ ተጓዦችን ቀልብ ስበው ነበር፡፡ በተመሳሳይ ሳር ቤት፣ ካሳንችስና አብዮት አደባባይ አካባቢም በስኬቲንግ ይታወቃሉ፡፡

ዶ/ር ሚካኤል ባህሩ የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያና የአባላቱም ሐኪም ነው፡፡ ታዳጊዎችና ወጣቶችን ስኬቲንግ እያስተማሩ ስኬት ቦርድ ከውጪ በዕርዳታ እያስመጡ እንደሚሰጧቸው ይናገራል፡፡ ‹‹ወጣቶች ስኬት በማድረግም ይሁን በስኬት ቦርድ ላይ በመሣል ራሳቸውን ይገልጻሉ፤ ኅብረተሰቡ ስለ ስኬቲንግ ግንዛቤው እንዲኖረውም በየጎዳናው ትርኢት እናሳያለን፤›› ይላል፡፡ ከቦታ ቦታ የሚያደርጉትን ጉዞ ‹‹ስኬት ቱር›› ይሉታል፡፡

ስኬቲንግ የወጣቶችን በራስ መተማመንና ተነሳሽነት እንደሚያጎለብት ዶ/ር ሚካኤል ይናገራል፡፡ ስኬት ሲያደርጉ ተሰብስበው ከሚመለከቷቸው ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በሰውነታቸው ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ፈርተው እንዲያቆሙ ይጠይቋቸዋል፡፡ የትራፊክ ጭንቅንቁም ሌላ ፈተና ነው፡፡ የቦታ ችግራቸውን ለመቅርፍ ላፍቶ ሞል ጀርባ አዲስ ፓርክ የተሰኘ የስኬቲንግ ፓርክ እያስገነቡ ነው፡፡

ቀድሞ ስኬት ሲያደርጉ በፀጥታ ኃይሎች የሚባረሩበትና ስኬት ቦርዳቸውን የሚነጠቁበትም አጋጣሚ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሕዝቡ ምላሽ እየተለወጠ ቢመጣም፣ አሁንም ለጎዳና ትርኢት ምቹ ቦታዎች በቀላሉ እንደማይገኙ ይናገራል፡፡ ብዙ ትርኢት የማቅረብ አቅም ያላቸው ባለሙያዎች ቢኖሩም የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተዋህደው ሲንቀሳቀሱ እንደማይታይም ያክላል፡፡ ‹‹ልዩ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ባለሙያዎች በኅብረት ቢሠሩ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፤›› ይላል፡፡

የጎዳና ትርኢቶች ሲገጥሙት ቆሞ ከማየት ወደኋላ የማይለው ካሳሁን ሀብቴ፣ የሙያ ማኅበራትና መንግሥት ባለሙያዎቹን መደገፍ እንዳለባቸው ይናገራል፡፡ ከዚህ ቀደም ልኳንዳ ተራ፣ ቦሌና ስቴዲየም አካባቢ የጎዳና ትርኢቶች አይቷል፡፡ ‹‹የጎዳና ትርኢት በሌሎች አገሮች በጣም ይዘወተራል፤ በእኛ አገርም ባለሙያዎቹን የሚደግፍ ቢኖር ጥበቡ ይስፋፋል፤›› ይላል፡፡ የጎዳና ትርኢት በከተማ ቀመስ አካባቢዎች ብቻ መወሰን እንደሌለበትም ያክላል፡፡ ተመልካቾችም ሙያውን በቁም ነገር ቢያዩት መልካም ነው ይላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...