Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበስኳር የሚያዙ ቁጥር በሦስት እጥፍ እየጨመረ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አሳሰበ

በስኳር የሚያዙ ቁጥር በሦስት እጥፍ እየጨመረ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አሳሰበ

ቀን:

ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ላይ የዓለም የስኳር ሕመም ቀንን ታሳቢ በማድረግ ይፋ ባደረገው የስኳር ሕመም የመጀመሪያ ሪፖርቱ የዓለም ጤና ድርጅት በዓለም አቀፍ ደረጃ 422 ሚሊዮን በስኳር የተያዙ ሰዎች እንዳሉ እነዚህም በአብዛኞቹ በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የሚገኙ መሆናቸውን አሳወቀ፡፡

እ.ኤ.አ. ከ1980 ወዲህ በስኳር ሕመም የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በሦስት እጥፍ እየጨመረ 422 ሚሊዮን ላይ ደርሷል፡፡ ለዚህ የሦስት እጥፍ ጭማሪ ደግሞ ከመጠን ያለፈ ውፍረት ዋነኛው ምክንያት መሆኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ በተጠቀሰውና በሌሎችም ምክንያቶች እየጨመረ ያለውን የስኳር ሕመም በመከላከልም ሆነ በማከም ረገድ እርምጃዎች ከፍ ብለው መቀጠል እንዳለባቸው የዓለም ጤና ድርጅት አሳስቧል፡፡

አካላዊ እንቅስቃሴ የሚገድቡ ሁኔታዎችን መቀነስ፣ ጤናማ ያልሆኑ የአመጋገብ ሥርዓቶችን ማስወገድ፣ በስኳር የተያዙ አስፈላጊውን ሕክምናና እንክብካቤ ያገኙ ዘንድ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ሪፖርቱ ካስቀመጣቸው የመከላከል እርምጃዎች መካከል ናቸው፡፡

‹‹የስኳር ሕመምን በአስተማማኝ ሁኔታ መቀነስ ከፈለግን አዋዋላችንን ደግመን ማጤን አለብን፡፡ ጤናማ አመጋገብ ለመከተል፣ አካላዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ አላስፈላጊ የክብደት መጨመርን ስለማስወገድ ማሰብ ይኖርብናል፤›› ብለዋል የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ዶ/ር ማርጋሬት ቻን፡፡

እሳቸው እንደገለጹት የዓለም ደሃ አገሮች ጭምር ሰዎች እነዚህን ጤናማ ምርጫዎች ማድረግ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይኖርባቸዋል፡፡ ያም ብቻ ሳይሆን በበሽታው የተያዙም አስፈላጊውን ሕክምናና እንክብካቤ ማግኘት የሚያስችላቸውን የጤና አገልግሎት ሥርዓት መዘርጋቱንም ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡

በአገራችን ምን ያህል የስኳር ሕመምተኞች ይገኛሉ የሚለውን ለማወቅ ራሱን የቻለ ጥናት እንደሚያስፈልግ የሚገልጹት ዶ/ር አህመድ ረጃ ለረዥም ዓመታት በስኳር ሕመም ሕክምና ላይ ቆይተዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት በሕመሙ የሚያዙት በአብዛኛው ከ45-65 ዓመት የሆኑ ናቸው፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርትም በዓለም ላይ በበሽታው እየተያዙ ያሉት አዋቂዎች መሆናቸውን ያስቀምጣል፡፡ በአገራችን ከአዋቂዎች ከ4-5 በመቶ የሚሆኑት በስኳር ሕመም የተያዙ ናቸው፡፡

የሪፖርቱ ግኝት እንደሚያሳየው በስኳር ሕመም የተያዙ ሰዎች ቁጥር እንዲሁም ሥርጭቱ የጨመረው በሁሉም የዓለም ክፍሎች ነው፡፡ በንጽጽር እ.ኤ.አ. 1980 የስኳር ሕመም የነበረባቸው ሰዎች 108 ሚሊዮን (4.7%) የነበረ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ2014 422 ሚሊዮን አዋቂዎች (8.5%) ሆነዋል፡፡ በ2014 ከ18 ዓመት በላይ ከሆኑ ከሦስት አዋቂዎች አንዱ ወይም ከዚያ በላይ ከመጠን ያለፈ ክብደት አላቸው፡፡ በሌላ በኩል የስኳር ሕመም በሚገባ ካልታከመ የልብ ችግር፣ ስትሮክ፣ እይታ ማጣትን እንዲሁም የኩላሊትና እግር ችግርን ያስከትላል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2012 የስኳር ሕመም ለ1.5 ሚሊዮን ሰዎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት ሲሆን 2.2 ሚሊዮን ሰዎችን ደግሞ ለልብና ለሌሎች የጤና ችግሮች በማጋለጥ ሕይወታቸው እንዲያልፍ አድርጓል፡፡

ስኳር ተላላፊ ያልሆነ በደም ውስጥ በሚገኝ የስኳር መጠን ከፍተኛ መሆን የሚከሰት በሽታ ነው፡፡ ሕመሙ በሁለት መንገድ ሊከሰት ይችላል፡፡ ጣፊያ የደም ውስጥ የስኳር መጠንን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን የኢንሱሊን ሆርሞን በበቂ ሁኔታ ማምረት ሳይችል ሲቀር አልያም ሰውነት የተመረተውን ኢንሱሊን በትክክል መጠቀም ሳይችል ሲቀር ነው፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...