Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊአደገኞቹ የአደጋ ማምለጫዎች

አደገኞቹ የአደጋ ማምለጫዎች

ቀን:

ከአራት ዓመታት በፊት ኮልፌ አካባቢ በአንድ ሌሊት ነው፡፡ በእፎይታ የንግድ ማዕከል ከታችኛው የሕንፃው ክፍል ድንገት እሣት ተነሣ፡፡ እሳቱ በቀላሉ ሊጠፋ አልቻለም፡፡ በሁኔታው የተደናገጡትና በሕንፃው ውስጥ የነበሩት ሁለት ወጣቶች ነፍሳቸውን ለማትረፍ ወደ ደረጃው ሄዱ፡፡ ነበልባሉን ሲመለከቱ መውረድ የማይታሰብ ሆኖ ታያቸው፡፡ ሌላ አማራጭ መውጫም አልነበረም፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ የእሣትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ኤጀንሲ ሠራተኞች እስኪደርሱ እሣቱን ለማጥፋት ይጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን አልተሳካላቸውም፡፡ ቃጠሎውም በፍጥነት ተስፋፋ፡፡ የሠጉት ወጣቶቹም የእሣት አደጋ መከላከያ ሠራተኞች እስኪደርሱላቸው እንዲሁ ባሉበት መቆየት አልቻሉም፡፡ ከሕንፃው ለመዝለልም ወሰኑ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎችም በሐሳባቸው ተስማሙ፡፡ መሬቱ እንዳይጐዳቸውም ፍራሽ አነጠፉላቸው፡፡ ወጣቶቹም ከአምስተኛ ፎቅ ወደታች ተወረወሩ፡፡ ያረፉት ግን የተዘረጋው ፍራሽ ላይ አልነበረም፡፡ የፈሩት መሬት ተቀበላቸው፡፡ ወዲያውም ሕይወታቸው አለፈ፡፡

በሕንፃዎች ላይ በሚፈጠሩ የተለያዩ አደጋዎች በውስጡ የሚገኙ ሰዎች የአደጋው ሰለባ እንዳይሆኑ ሕንፃዎች የአደጋ ጊዜ መውጫ በር ሊኖራቸው የግድ ይላል፡፡ ቢሆንም ግን በተለያየ ምክንያት የአደጋ ጊዜ መውጫ በር አልባ ሆነው ይስተዋላል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ በሩ ቢኖርም ከአደጋ ለማምለጥ የሚረዳ ሳይሆን ለሌላ አደጋ የሚሰጡ ሆነው ይታያሉ፡፡ የሕንፃ ባለቤቶች ተጨማሪ ወጪን በመሸሽ በዲዛይኑ ሳያካትቱት ይቀራሉ፡፡ ይህም እንደ እፎይታ የገበያ ማዕከል ለበርካቶች ህልፈት ምክንንያት ሆኗል፡፡ የተመሳሳይ ገጠመኞች ሕንፃዎች የአደጋ ጊዜ መውጫ በር እንዲኖራቸው የሚያስገድድ ሕግ እንዲወጣም አድርጓል፡፡ በሌላው ዓለም የአደጋ ጊዜ መውጫዎችን በተመለከተ አስገዳጅ ሕግ ወጥቶ አገልግሎት ላይ ከዋለ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በእንግሊዝ የአደጋ ጊዜ መውጫ በር አንዱ የሕንፃ መሥፈርት እንዲሆን የሚያደርግ ሕግ እንዲወጣ ግፊት ማድረግ የተጀመረው እ.ኤ.አ. ከ1883 ጀምሮ ነው፡፡ በእንግሊዝ አገር ሠንደርላንድ ግዛት ውስጥ በሚገኘው ቪክቶሪያ ሞል ላይ የደረሰው የእሣት አደጋ ለእንቅስቃሴው መነሻ እንደሆነም ይነገራል፡፡ በወቅቱ በቪክቶሪያ የንግድ ማዕከል ውስጥ ድንገት በተነሳ እሣት በሕንፃው ውስጥ የነበሩ 180 ሕፃናት አልቀዋል፡፡ በሕንፃው የአደጋ ጊዜ መውጫ አለመኖር ለሕፃናቱ ህልፈት ምክንያት ነበር፡፡ እንግሊዛውያንም የአደጋ ጊዜ መውጫ በር በሕንፃ ሕግ እንዲካተት ግፊት ያደርጉ ጀመር፡፡ ግን ጆሮ የሰጣቸው አልነበረም፡፡

- Advertisement -

እ.ኤ.አ. 1911 ደግሞ በአሜሪካ ውስጥ በሚገኝ አንድ ፋብሪካ በተፈጠረ ቃጠሎ 146 ሠራተኞች ሞቱ፡፡ እንዲሁም እ.ኤ.አ. በ1942 ቦስተን በሚገኝ የምሽት ጭፈራ ቤት በተፈጠረው አደጋ 492 ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡ ይህም እንግሊዛዊያኑ ከዓመታት በፊት የጀመሩትን እንቅስቃሴ እንዲቀጥል አደረገ፡፡ እንቅስቃሴውም ቀና ምላሽ አግኝቶ በአገራቱ የአደጋ ጊዜ መውጫ በር በሕንፃ ሕግ እንዲካተት ተደረገ፡፡

ይህ ዘግይቶም ቢሆን በኢትዮጵያም እውን ሆኗል፡፡ ከዓመታት በፊት በወጣው የሕንፃ ሕግ የአደጋ ጊዜ መውጫ በር አስገዳጅ ሆኖ ቀርቧል፡፡ በድንጋጌው አዋጅ 243/2011 መሠረትም ሕንፃዎች የአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያ እና በራሱ ሰዓት የሚሠራ የእሣት ማጥፊያ ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ የአደጋ ማምለጫ እና የመውጫ አመላካቾች በግልጽ ቦታ እንዲታዩ ሆነው እንዲዘጋጁ፣ ከተወሠነ ወለል በላይ ያላቸው ሕንፃዎች ከዋናው መወጣጫ ደረጃ በተጨማሪ ከአደጋ ነፃ ወደሆነ መሬት የሚያደርስ የአደጋ ጊዜ ማምለጫ ደረጃ ሊኖራቸው እንደሚገባ፣ የአደጋ ጊዜ ማምለጫ መስመሮችም በቀላሉ ሊለይ የሚችልና ዓለም አቀፍ ምልክቶችን እንዲጠቀሙ፣ የኃይል አቅርቦት ቢቋረጥም መሥራት የሚችሉ የብርሃን አቅጣጫ ጠቋሚ አመልካቾች የተገጠሙለትና ከመሰናክል ነፃ የሆኑ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሮች እንዲኖሩ ያስገድዳል፡፡

ይህ ከድንጋጌ ባለፈ ምን ያህል ተፈጻሚ እንደሆነ በከተማዋ እንደ ቦሌ፣ ሜክሲኮና ሌሎችም አካባቢ ያሉ በርካታ የአደጋ ጊዜ መውጫ አልባ ሕንፃዎች ምስክር ናቸው፡፡ መሥፈርቱን ሳያሟሉ የተገነቡት እንደ እፎይታ የመሳሰሉ ሕንፃዎች ላይ በሚከሰቱ አደጋዎች የሚሞቱ ሰዎችም ማሳያ ናቸው፡፡ አንዳንድ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሮችን አካትተው የሚገነቡ ሕንፃዎች ቢኖሩም እነዚህም ከችግር የማያመልጡበት ሁኔታ አለ፡፡

የኪነ ሕንፃ ንድፍ ሥራና ክትትል ባለሙያ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ብርሃኑ ሙሣ እንደሚሉት፣ በአንድ ሕንፃ ውስጥ አደጋ ሲፈጠር ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ አላርም ሊኖር ግድ ይላል፡፡ ከዚህ ጐን ለጐንም የአደጋ ጊዜ መውጫዎች ሊኖሩ ይገባል፡፡ አንድ ሕንፃ ከአንድ በላይ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሮች ሊኖሩት ይችላል፡፡ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሮች በመካከላቸው የሚኖረው ርቀትም የተመጠነ መሆን አለበት፡፡ ሕንፃው ወደ ጐን 15 ሜትር የሚሰፋ ከሆነ 2 የአደጋ ጊዜ መውጫ በሮች ያስፈልጉታል፡፡ እንደ ሆስፒታል ባሉ ተቋማት ደግሞ ከሌላው እኩል ራሳቸውን ለማትረፍ የማይችሉ ስለሚኖሩ ርቀቱ አጠር ቢል ይመከራል፡፡ ካልሆነ ግን በሕንፃዎች በርካታ ሰዎች ስለሚገኙ ድንገት አንድ አደጋ ቢደርስ በአንዴ በርካቶች እንዲያልቁ ምክንያት ይሆናል፡፡

ይህንን ሙሉ በሙሉ አሟልተው የተገነቡ ሕንፃዎችን ማግኘት ግን ከባድ ነው፡፡ ‹‹መሥፈርቱን ተከትለው የሚገነቡ ሕንፃዎች ዓለም አቀፍ ሆቴሎች፣ መሰብሰቢያ አዳራሾች ናቸው፡፡ የተቀሩት የዲዛይን ፈቃድ ለማግኘት ሲሉ እንደነገሩ የሚሠሩ ናቸው፤›› ሲሉ አርኪቴክቱ ይናገራሉ፡፡

የአደጋ ጊዜ መውጫ በሮች እሣት መቋቋም የሚችሉ፣ ግልጽ በሆነ ቦታ ላይ መገኘት ሲገባቸው በተቃራኒው ሆነው ይስተዋላል፡፡ ‹‹ለአደጋ ጊዜ የሚዘጋጀው በር ራሱን የቻለ ክፍል እንዲኖረው ይጠበቃል፤›› የምትለው ደግሞ በቴልዳ ኮንሰልት ድርጅት የዲዛይን ዲፓርትመንት ኃላፊ ሐረገወይን በቀለ ነች፡፡ እሷ እንደምትለው፣ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሮች ቃጠሎ መቋቋም የሚችሉ በራሳቸው መዘጋት እንዲሁም ነፃ ወደ ሆነ ቦታ የሚያደርሱ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገር ግን ግዴታዎቹን ሳያሟሉ ለተሠሩበት ዓላማ የማይውሉ ጥቂት አይደሉም፡፡ ብዙዎቹ ሕንፃዎች ደረጃውን ባልጠበቀ ግብዓት ከመገንባታቸው ባለፈም ሌሎች ችግሮችም ይስተዋሉባቸዋል፡፡

ደረጃውን የጠበቀ የአደጋ ጊዜ መውጫ በር ወደ ከውስጥ ውጭ የሚከፈትና በፍጥነት በራሱ የሚዘጋ መሆን አለበት፡፡ ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ ከደረጃ በታች በሆኑ ግብዓቶች ስለሚገነቡ የተገለጸው ዓይነት ባህሪ የላቸውም፡፡ በመሆኑም ሰርክ ክፍት መሆን አለበት የሚለውን ድንጋጌ በሚፃረር መልኩ ሌባ ሊገባ ይችላል በሚል ተዘግተው የሚውሉ መውጫዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ በሮቹ ከአደጋ ነፃ ወደሆነ ቦታ ማውጣት ሲገባቸው በተቃራኒው የሚሆኑበት አጋጣሚም ብዙ ነው፡፡ ይህንን እውነታ የሚመሰክሩ ሕንፃዎችን በከተማዋ ብቻም ሳይሆን አንድ አካባቢ ላይ እንኳ ማግኘት ከባድ አይሆንም፡፡

አምባሳደር አካባቢ የሚገኘው አንድ ታዋቂ ሆቴል የዚህ ማሳያ ነው፡፡ ሆቴሉ መንገድ ዳር የተገነባ ሲሆን፣ ምንም ዓይነት ክፍት ቦታ የለውም፡፡ የአደጋ ጊዜ መውረጃው የተገነባውም አደገኛ በሆነ ጥግ ላይ ነው፡፡ የአደጋ ጊዜ መውጪያው ከሆቴሉ ጐን ካለው ነዳጅ ማደያ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በእጅጉ ለእሣት አደጋ ተጋላጭ የሆነው ነዳጅ ማደያ  ለአደጋ ጊዜ መውጫ በር አቅጣጫ ሆኖ መመረጡ ግር ያሰኛል፡፡

ይሁን እንጂ የሆቴሉ አስተዳዳሪ ‹‹ይህንን ያህል የሚያሰጋ አይደለም፡፡ በሌላ አገር ሕንፃዎች ከሥር ነዳጅ ማደያ ከላይ ደግሞ ሆቴል ይሆናሉ›› በማለት ማደያው አደጋ ቢደርስበት እንኳ መደበኛውን ደረጃ መጠቀም እንደሚቻል ይህንን ያህል ሥጋት እንዳልሆነም በልበ ሙሉነት ይገልጻሉ፡፡

‹‹የአደጋ ጊዜ መውጫዎች መኖሩን አሉ፡፡ ነገር ግን ከአደጋ አያስመልጡም›› የምትለው ሀረገወይን በከተማው ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሕንፃዎች ላይ ችግሮች ተመልክታለች፡፡ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች አገልግላለች፡፡ ይህም በተለያዩ ሕንፃዎች እንድትሠራ ዕድሉን ሰጥቷታል፡፡ በየሕንፃዎቹም ከአደጋ መውጫ በሮች ጋር በተያያዘ  ችግሮችን አስተውላለች፡፡

ቦሌ አካባቢ የሚገኝ አንድ ግዙፍ ሕንፃ ነው፡፡ ሕንፃው ደረጃውን የጠበቀ ቢመስልም ውስጡ በተቃራኒው ነው፡፡ በመስታወት የተሠሩ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሮች ቢኖሩትም ዋና ነገር አልተሟላም፡፡ ደረጃ የለውም፡፡ ሁኔታው ከአደጋ ራሳቸውን ለማትረፍ በሩን የሚጠቀሙ ሰዎችን ከአደጋ ወደ አደጋ እንጂ ነፍሳቸውን ለማትረፍ የሚረዳ አይደለም፡፡

በአሁኑ ወቅት ከብረት የተሠሩ የአደጋ ጊዜ መውጫ ደረጃዎች በስፋት ሥራ ላይ እየዋሉ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ የብረት ደረጃዎች ምን ያህል አስተማማኝ ናቸው? የሚለው ጉዳይ አከራካሪ ነው፡፡ ከችግሮች የፀዱ ባይሆኑም ከምንም ይሻላሉ በሚለው ግን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ 

በከተማው ከሚገኙት ተመሳሳይ የአደጋ ጊዜ መውጫ ካላቸው ሕንፃዎች መካከል ነው፡፡ ከሕንፃው በስተጀርባ ከብረት የተሠራ የአደጋ ጊዜ መውጫ አለ፡፡ ነገር ግን ከተለመደው ወጣ ያለ ነገር ይታይበታል፡፡ ነገሩ ግርምትም ያጭራል፡፡ ደረጃው መሬት አያደርስም፡፡ አንደኛው ፎቅ ላይ ደርሶ ተንጠልጥሎ ቀርቷል፡፡ የአደጋ ጊዜ መውጫዎች ነፃ ወደሆነ ቦታ ማውጣት አለባቸው የሚለውን ሐሳብ በተፃረረ መልኩ የሚሠሩ መውጫዎችም ያጋጥማሉ፡፡ በዚህ መልኩ በግዴለሽነት የሚገነቡ ሕንፃዎች ከተማዋን ሞልተዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ሐረገወይን ከዚህ ቀደም ተቀጥራ ትሠራበት የነበረው ሕንፃ ተመሳሳይ ችግር አለበት፡፡ ሕንፃው ከብረት የተሠራ የአደጋ ጊዜ መውጫ አለው፡፡ ነገር ግን ደረጃው ነፃ ቦታ በማድረስ ፋንታ ወደ ቤዝመንት (ምድር ቤት) ያደርሳል፡፡ የሚገርመው ነገር ግን ወደ ላይኛው የሕንፃ ክፍል ይመልሳል እንጂ ቤዝመንቱ ሌላ መውጫ አልተዘጋጀለትም፡፡

የግንባታ ፈቃድ የሚሰጠው አካል ግንባታው በዲዛይኑ መሠረት መገንባቱን፣ ደረጃቸውን በጠበቁ ግብአቶች መዋቀሩን ቁጥጥር ባለመደረጉ ችግሮቹ መፈጠራቸውን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

‹‹በብረት የሚሠሩ የአደጋ ጊዜ መውጫዎች ብዙም አስተማማኝ አይደሉም፡፡›› የሚለው የቴልዳ ኮንሠልት ድርጅት ማኔጀርና ስትራክቸራል ኢንጂነር አቶ ዳዊት ታምራት በሕንፃ አዋጁ መሠረት የአደጋ ጊዜ መውጫ በሮች ከመሰናክል የፀዱ እንደሆኑ ይጠበቃል ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ጥቂት የማይባሉት ሕንፃዎች ይህንን አያከብሩም፡፡ መውጫ በሮቹን ዕቃ ማስቀመጫ የሚያደርጉ አልፎ አልፎ እንደ መጋዘን የሚጠቀሙባቸው የሕንፃ ባለቤቶችም አሉ፡፡ ይህም በተገቢው መንገድ አገልግሎት እንዳይሰጥ እያደረገ ይገኛሉ፡፡  የሚቆለፉ የአደጋ ጊዜ መውጫ በሮችም ብዙ ናቸው፡፡

ከ12 ሜትር ከፍታ በላይ ወይም አራትና ከዚያ በላይ ፎቅ ያላቸው ሕንፃዎች የአደጋ ጊዜ መውጫ ሊኖራቸው ግድ ይላል፡፡ ከዚያ በታች የሚገኙ ሕንፃዎች ደግሞ እሣት መቋቋም የሚችል ግድግዳ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የአደጋ ጊዜ መውጫ ደረዳዎችም በቂ ስፋት ቢኖራቸው ይመረጣል፡፡

‹‹የአደጋ ጊዜ መውጫ ደረጃዎችን ስፋት በተመለከተ ዝርዝር መረጃ አልወጣም፡፡ ነገር ግን መደበኛው የደረጃ ስፋት 1 ሜትር ከ20 ሴንቲ ሜትር ነው፡፡ ይህም በአደጋ ጊዜ መውረጃ ደረጃዎች ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋል›› የሚሉት በአራዳ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ጽሕፈት ቤት የግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ባለሙያው አቶ ዙሪያወርቅ ወዳጆ ናቸው፡፡

እሳቸው ይህንን ቢሉም የአብዛኞቹ ሕንፃዎች የአደጋ ጊዜ መውጫዎች ጠባብ እንደሆኑ፣ አንድ ሰው ለማሳለፍ እንኳ አስቸጋሪ እንደሆኑ የቴልዳው አቶ ዳዊት ይናገራሉ፡፡

ማኅበረሰቡ ስለ አደጋ ጊዜ መውጫ በሮች ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆንም ሌላው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ የአብዛኞቹ በሮች ግልጽ በሆነ ቦታ ላይ አለመገጠም ሌላው ችግር ነው፡፡ በመሆኑም በዙሪያው ያለውን ብዥታ የሚያጠራ የየሕንፃዎቹ የአደጋ ጊዜ ባለሙያ እንደሚያስፈልግ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ የተለያዩ ሕንፃዎች በሚገኙ ቢሮዎች ሠራተኞችን የሕንፃው የአደጋ ጊዜ መውጫ በሮችን ያውቁ እንደሆነ ለመጠየቅ ተሞክሯል፡፡ አንዳንዶቹ ስለመውጫው ራሱ ግንዛቤ የላቸውም፡፡ ሌሎች ደግሞ መውጫው የት ጋር እንዳለ ለመገመት ወይም ለማስታወስ ደቂቃዎች ወስዶባቸዋል፡፡ አዘውትረው የሚሄዱባቸውን ሆቴሎች፣ ሲኒማ ወይም ቴአትር ቤቶች የአደጋ ጊዜ መውጫ የት እንደሚገኝ የማያውቁ በርካቶች ናቸው፡፡

በሌላ በኩል በአደጋ ጊዜ መውጫ በሮች ላይ የሚስተዋሉት ተደራራቢ ችግሮች የእሣት አደጋ ሠራተኞች ሕይወት የማትረፍ ሩጫ በፈተና እንዲሞላ አድርጐታል፡፡ ‹‹በከተማው የሚገኙ 90 በመቶ የሚሆኑት ሕንፃዎች የአደጋ ጊዜ መውጫ በር የላቸውም፡፡ ያሉትም ቢሆኑ ይቆለፋሉ ተገቢው ምልክትም አይደረግባቸውም፡፡›› ያሉት በእሣትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከል መቆጣጠር ኤጀንሲ የኮሚኒኬሽን ኦፊሰር አቶ ንጋቱ ማሞ ናቸው፡፡

ከአደጋ ጊዜ መውጫ በሮች በተጨማሪ መሟላት ያለበት ነገርም አለ፡፡ እንደ እሳቸው አባባል፣ በሕንፃው ላይ ከነበሩት ሰዎች ምን ያህሉ ከአደጋ ተርፈው እንደወጡ ምን ያህሉ ሕንፃው ውስጥ እንደቀሩ ለመለየት የሚያስችል የአደጋ ጊዜ መሰብሰቢያ ሥፍራም ያስፈልጋል፡፡ ይሁንና ዋናውን የአደጋ ጊዜ መውጫ በሮች ማሟላት ያልቻሉ በርካታ ሕንፃዎች ባሉበት ሁኔታ ይህንን መጠየቅ ፅድቁ ቀርቶብኝ ያሰኛል፡፡  

‹‹የበሮቹ ዓላማ ሰዎችን ከአደጋ ማስመለጥ ነው›› የሚሉት አቶ ንጋቱ ተገቢው የአደጋ ጊዜ መወጫ በሮች ባለመሠራታቸው የኤጀንሲው ሠራተኞች አደጋ የደረሰበት ቦታ እስኪደርሱ የብዙዎች ሕይወት እንደሚያልፍ ይናገራሉ፡፡ ኤጀንሲው በቅርቡ ሰዎች ካሉበት ፎቅ ላይ ማንሳት የሚችል ማሽን አስመጥቷል፡፡ በዚህም የአደጋ መውጫ በሌላቸው ሕንፃዎች ለአደጋ ተጋላጭ የሚሆኑ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ ይቻላል፡፡ ይሁን እንጂ የማሽኑ ሰው የመያዝ አቅም ውስን ነው፡፡ በአንዴ ከ4 የሚበልጡ ሰዎችን መያዝ የሚችል አይመስልም፡፡ ኤጀንሲው ከሚያደርገው ጥረት ጐን ለጐን የአደጋ ጊዜ መውጫዎች በተገቢው መንገድ ቢገነቡ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀረፍ አቶ ንጋቱ ያምናሉ፡፡

በሕንፃ ደንቡ አንቀጽ 15 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት በግንባታ ጥራት ምክንያት ለሚደርስ ማንኛውም አደጋ ባለቤቱ ኃላፊነት ይወስዳል፡፡ እዚህ ከመደረስ አስቀድሞ ተገቢው ቁጥጥር ቢደረግ፣ በሕጉ መሠረት ካልተገነባም ዕርምጃ ቢወሰድ ባለሀብቱም ኃላፊነቱን በተገቢው መንገድ እንዲወጣ ማድረግ ትክክለኛው መፍትሔ ይሆናል፡፡

በከተማዋ በተለይም እንደ መርካቶ በተደጋጋሚ ለእሳት አደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ እንኳ የአደጋ ጊዜ መውጫ የሌላቸው ሕንፃዎች መኖር፣ ያሉት መውጫዎችም ባንድም ይሁን በሌላ ምክንያት አገልግሎት መስጠት የማይችሉ መሆን ችግሩ በምን ያህል ደረጃ ትኩረት እንደሚሻ ይናገራል፡፡  

   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...