ይህንን ገጠመኝ እንድጽፍ መነሻ የሆነኝ ሰሞኑን ከአንድ ወዳጄ ጋር የነበረኝ ቆይታ ቢሆንም፣ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሙኝ አስገራሚ ጉዳዮችም አሉ፡፡ ከዓመታት በኋላ በአጋጣሚ ያገኘሁት ጓደኛዬ ድሮ በአዲስ አበባ ኮሜርስ ትምህርት ቤት አብረን ተምረናል፡፡ በኋላም ዩኒቨርሲቲ ድረስ ዘልቀናል፡፡ በቀድሞው ኢትሜክስ መሥሪያ ቤትም ሠርተናል፡፡ ለረጅም ዓመታት ተገናኝተን ባናውቅም፣ እስካሁን በሕይወት መኖራችንን ግን በተዘዋዋሪም ቢሆን እናውቃለን፡፡ በአካል ስንገናኝ ደግሞ አረፍ ብለን ማውጋት ነበረብን፡፡ ምሣ እየበላን ከጥንቱ እስከ ዛሬ ያለውን አወጋነው፡፡
ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ በአንዱ ታዋቂ ምግብ ቤት ምሣ እየበላን ብዙ ነገሮችን ካወጋን በኋላ፣ ይኼ የጥንት ወዳጄ የቦሌ አካባቢን በአጭር ጊዜ በሕንፃዎች መሞላት፣ በብዙዎቹ የንግድ መደብሮች ከአሜሪካና ከአውሮፓ ያልተናነሰ ዘመናዊነት እያጣቀሰ በቅርቡ የደረሰበትን ነገረኝ፡፡ አንድ እሑድ በማለዳ አንዲት ሴት ልጁን በአዲሱ የከተማ ባቡር ለማንሸራሸር ይዟት ይሄዳል፡፡ ከመገናኛ እስከ ጦር ኃይሎች፣ ከዚያም እስከ መገናኛ በባቡሩ የደርሶ መልስ ጉዞ አድርገው ይመለሳሉ፡፡ አንድ ካፌ ይገቡና ቁርሳቸውን እየበሉ ሻይ ቡና ሲሉ፣ ‹‹አባቢዬ ባቡር ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ የገባው በዳግማዊ ሚንሊክ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ እሱም አርጅቶ ቆሞ እንደ አዲስ እየተሠራ ያለው አሁን ነው፡፡ የከተማ ባቡር ደግሞ የጀመረው ገና አሁን ነው፡፡ ከአንድ መቶ ዓመት በፊት የተጀመረ ቴክኖሎጂ ዛሬ ለምን ብርቅ ሆነብን? እስካሁን ምን ሲደረግ ነበር? ከብዙ አገሮች በፊት ጀምሮ ኋላ መቅረት ምን የሚሉት ነው…?›› እያለች ያላሰበውን ዱብ ዕዳ ስታከታትልበት ራሱን በትዝብት ከማነቃነቅ ይልቅ ምንም መልስ እንዳልነበረው ነገረኝ፡፡
በእርግጥም ትምህርት፣ ባቡር፣ አውሮፕላን፣ መኪና፣ ስልክ፣ ፖስታና ቴሌግራፍ፣ ወፍጮ፣ ወዘተ ከአገር በፊት መጠቀም የጀመረች አገር የድህነትና የኋላቀርነት መጫወቻ ሆና መኖሯ ከማስገረም በላይ ምን ይባላል? በአንድ ወቅት በአፍሪካ አኅጉር ቅኝ ያልተገዛች አገር፣ የቅኝ ገዥዎችን ወረራ መክታና አሳፍራ የመለሰች አገር፣ በጥንታዊ የሥልጣኔ ዘመናት የአክሱም ሐውልቶችን፣ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን፣ የጎንደር ቤተ መንግሥትንና የተለያዩ አስደማሚ ኪነ ሕንፃዎችን ያነፀች አገር ኢትዮጵያ የረሃብና የልመና ተምሳሌት መሆኗ ከማስገረምም አልፎ እሪ ያሰኛል፡፡ ከሥልጣኔ ቁንጮዎች ተርታ ስሟ ይጠራ የነበረች አገር የአፍሪካ የውኃ ማማ ባለቤት፣ የሰፋፊ ለም መሬቶች ምድር፣ የቆላ፣ የደጋና የወይና ደጋ አየር ንብረቶች መናኸሪያ፣ የክንደ ብርቱዎችና የልባሞች አገር እንዴት በድህነት አረንቋ ውስጥ ለዘመናት ኖረች? ይገርማል፡፡
የጓደኛዬ ልጅ ባቡር እንዴት ብርቅ ይሆንብናል እንዳለችው ሁሉ፣ በአንድ ወቅት መርካቶ አውቶቡስ ተራ ያገኘሁት ሊስትሮ የጠየቀኝን አስገራሚ ነገር አልረሳውም፡፡ ጫማዬን የማስጠርገው በግምት የ14 ዓመት ታዳጊ ሊስትሮ ማታ ማታ ይማር እንደሆን እንደ ዘበት ጠየቅኩት፡፡ ‹‹አይ ጋሼ ትምህርት ማን ይጠላል? እስቲ መጀመሪያ የራበውን ሆዴን ላስታግስ፡፡ ከዚያ በኋላ ሌላው ነገር ይታሰብበታል፤›› አለኝ፡፡ አነጋገሩ ልቤን በጣም ስለነካው፣ ‹‹አይዞህ ጠንክረህ ሥራ እንጂ የማይታለፍ ነገር የለም፡፡ ብዙዎቹ የመርካቶ ሀብታም ነጋዴዎች እኮ እንዳንተ ተርበውና ተጠምተው ጠንክረው ስለሠሩ ነው ያለፈላቸው…›› ብዬ የተወሰኑትን ስሞቻቸውን ጠቃቀስኩለት፡፡ ልጁ ግን የዋዛ አልነበረም፡፡ ‹‹ይሁን ግዴለም፡፡ ግን እዚህ አገር እስከ መቼ ነው የሚሠራ ሰው እየተራበ የሚኖረው? ከድሮ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ሰው እየተራበ ነው መከራ የሚያየው፡፡ የጠራሃቸው ሰዎች በሙሉ ይርባቸው ነበር፡፡ ዛሬም እኔና ቢጤዎቼ ይርበናል፡፡ ግን እስከ መቼ?›› ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ ‹‹አይዞህ ሁሉም ያልፋል፤›› ከማለት ሌላ መልስ አልነበረኝም፡፡ መልስ ቢፈለግስ ከየት ይመጣል? አይጣል እኮ ነው፡፡
አንድ ቀን ፒያሳ መኮንን ባር ቡና እየጠጣሁ ወንድሜን ስጠብቅ ሦስት ወጣቶች ከእኔ ፈንጠር ያለውን ጠረጴዛ ከበው ቫቅላባ እየበሉ ያወራሉ፡፡ የወሬያቸው መነሻና መድረሻ በእዚህ አገር ፖለቲከኞች መካከል ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው መቋሰል ነው፡፡ አንደኛው፣ ‹‹ለ40 እና ለ50 ዓመታት የቋጠሩትን ቂም መፍታት አቅቷቸው ወጣቱን ትውልድ ወራሽ ማድረጋቸው ያናድዳል…›› እያለ በደም ፍላት ሲናገር ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹የሚያናድደው ደግሞ በመካከላቸው ያለው ልዩነት ፍርጥ ብሎ ሳይታወቅ ወጣቱን መጠቀሚያ ለማድረግ መሯሯጣቸው ነው፤›› ይላል፡፡ የሁለቱን ንግግር በፅሞና የሚያዳምጥ የሚመስለው ከእነሱ በዕድሜ ትንሽ የሚመስለው፣ ‹‹በአረጀና በአፈጀ አስተሳሰብ አዲሱን ዘመን መቆጣጠር ባይችሉም፣ አሁንም ሕይወታችንን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እያበላሹት ነው፡፡ እኔ ግን ያ ትውልድ የሚባለው ለራሱም ሆነ ለአገር ፋይዳ የሌለው ከሚጫወትብኝ ባልወለድ እመርጥ ነበር…›› እያለ ሲንገሸገሽ ደነገጥኩ፡፡ ወይ ጉድ?
ወገኖቼ ልብ በሉ፡፡ አሁን ያለው ትውልድ ብዙ ነገሮችን እያነሳ እየታዘበን ነው፡፡ ጀምረን መጨረስ ሳይሆን ለመቀጠል እንኳ ወኔ ያልነበረን ዓይነት አድርጎ ይስለናል፡፡ የአክሱም፣ የላሊበላንና የጎንደር ኪነ ሕንፃዎችን የሠራች አገር በሳርና በጭቃ ቤቶች መሞላቷ ይገርመዋል፡፡ ከብዙ ሺሕ ዓመታት በኋላ ኮንዲሚኒየም፣ ሪል ስቴት እየተባለ ላይ ታች ሲባል ይታዘባል፡፡ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም የመጀመሪያ የነበረች አገር እንደ አዲስ ስትፈነድቅ ግራ ይገባዋል፡፡ ልዩነቶቻችንን እያከበርን በሥልጣኔ መነጋገር ባለመቻላችን መፈጠሩም ያስጠላዋል፡፡ የዛሬው እንዲህ የተመረረብንና የተገረመብን የነገው ደግሞ ምን ይለን ይሆን? ሁልጊዜ ለነገሮች ብርቅ መሆን፣ መራብ፣ መጨቃጨቅና ኋላ ቀርነት እስከ መቼ መገለጫዎቻችን ይሆናሉ? የሚለን አሁን ያለው ታዳጊ ትውልድ ነው፡፡ የነገው ሲመጣ ደግሞ ቢያወግዘን እንዳይገርማችሁ፡፡ እኔ ይኼንን ታዝቤያለሁ፡፡ እናንተስ? (ዳንኤል ያሬድ፣ ከመሳለሚያ)