Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  በሕግ አምላክሕግን ያለማስፈጸም ጣጣ የትራፊክ ቁጥጥር ደንብ እንደማሳያ

  ሕግን ያለማስፈጸም ጣጣ የትራፊክ ቁጥጥር ደንብ እንደማሳያ

  ቀን:

  ባለፈው ሳምንት በዕለተ ሰንበት የወጣው የፎርቹን ጋዜጣ የመግቢያ ገጹ የትራፊክ አደጋ አስከፊነትን የአዲስ አበባ ከተማን መረጃ በመግለጽ ይተነትናል፡፡ ጸሐፊው ከስድስት ዓመት በፊት በኮልፌ 18 ማዞሪያ አካባቢ 26 ሰዎችን ገሎ ብዙዎችን ያቆሰለውን ታሪክ መነሻ አድርጎ የትራፊክ አደጋው በአቃቂ ቃሊቲ፣ በቦሌና በየካ ክፍለ ከተማ መብዛቱን ይተነትናል፡፡ ሰኞ ዕለት 18 ማዞሪያ አካባቢ ሦስት ሰዎችን የገደለው አደጋ ሲሰማ ጸሐፊውን በልቤ ሟርተኛ በሚል ከማማት ይልቅ የመኪና አደጋ አስከፊነቱ ተቀዳሚ የአገሪቱ ችግር ግን መንግሥት ተገቢ ትኩረት እንዳልሰጠው ታሰበኝ፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት እንደገለጸው የመኪና አደጋ በአገሪቱ ከተከሰተው ሞት ቢያንስ ለ2.5 በመቶ ምክንያት ሲሆን፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከሚገድለት ምክንያቶች ከ12ቱ ቀዳሚ ምክንያቶች ውስጥ ተመድቧል፡፡ የፎርቹኑ ጸሐፊ እንደገለጹት አደጋ የሚበዛባቸው ተብለው በተገለጹት የአዲስ አበባ ሦስት ክፍለ ከተሞች ከ100,000 ሰው ቢያንስ 14 ሰዎች በመኪና አደጋ ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ የአደጋው መጠን አምና ከነበረበት በ16 በመቶ የጨመረ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአዲስ አበባ ብቻ 5,280 አደጋዎች ተከስተዋል፡፡ ያልተመዘገቡትን አገር ይቁጠራቸው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ በየዕለቱ የምንሰማቸውን አደጋዎች ከጨመርን የአደጋው ቁጥር ብዙ፣ የአደጋው ዓይነትም የከፋ መሆኑን እንረዳለን፡፡

  ሕዝባችን በመኪና አደጋ እያለቀ ነው፡፡ ለድርቁና ለበሽታው የምንፀልየውን ያህል ለመኪና አደጋም የመፀለያው ጊዜ ረፍዷል፡፡ ወጥ የሆነ ጥናት ባይኖርም በየመገናኛ ብዙኃኑ እንደሚገለጸው ለመኪና አደጋው ምክንያቱ ብዙ ነው፡፡ አዲስ አበባን ማዕከል ያደረገው የፎርቹን ጸሐፊ ከገለጻቸው ውስጥ ከተማውን በአግባቡ ያላገናዘበው የቀለበት መንገድ አሠራር፣ የእግረኛ ማቋረጫ አለመኖር፣ የመንገድ አለመመቸት፣ የምልክቶች አለመኖር፣ የመኪናዎች የቴክኒክ ብቃት ማነስና የአሽከርካሪዎች የሥነ ምግባር ጉድለት ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ በየዕለቱ በሬዲዮ እንደሚነግሩን ደግሞ ‹‹በፍጥነት ማሽከርከር፣ ለእግረኛ ቅድሚያ አለመስጠት፣ ርቀት ጠብቆ አለማሽከርከርና ተገቢ ያልሆኑ አቀዳደም፤›› ፀሐይ የሞቃቸው አገር ያወቃቸው ምክንያቶች ናቸው፡፡

  አደጋው እንደዚህ ከፍቶ፣ ምክንያቶቹ እንደዚህ በርክተው ለተመለከተ ህሊናው ላይ የሚመጣው ጥያቄ አገሪቱ የትራፊክ ቁጥጥር ሕግ የላትምን? ሕግስ ካላት ለምን አይተገበርም? የሚል ነው፡፡ ከአንድ ወር በፊት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ባለሥልጣን መንጃ ፈቃድ እስከማገድ የሚያደርስ ዕርምጃ በታክሲ አሽከርካሪዎች ላይ እንደሚወስድ ሲገልጽ፣ ታክሲዎቹም በአድማ መንግሥትን ‹‹አንሰማህም!›› ሲሉ አዲስ ሕግ ወይም መመርያ እንደወጣ ያሰቡ ብዙኃን አይጠፉም፡፡ ሕጉ አለ፡፡ ከወጣ ቆይቷል፡፡ ሕጉ በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣ ደንብ ነው፡፡ የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 208/2003 የሚባል ሲሆን፣ ከወጣ አምስት ዓመት ሊሆነው ወራት ቀርተውታል፡፡ በኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1963 ዓ.ም. ከወጣው ደንብ በኋላ የወጣ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ከወጣ አምስት ዓመት ሊሞላው ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ሕጉ በተግባር ላይ አልዋለም፡፡ ሕጉ ያልወጣ ያህል በአብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል የማይታወቅ፣ ባለመፈጸሙ የሚታወቅ ደንብ ነው፡፡ የደንቡን ይዘት በአጭሩ በመቃኘት በዚህ ጽሑፍ ሕጉ ያልተፈጸመበትን ምክንያትና ውጤቱን ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡

  ሕዝቡን ከመኪና አደጋ የሚታደግ ደንብ

  የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ በ2003 ዓ.ም. ሲወጣ በጊዜው በስፋት ተወርቶበታል፡፡ ደንቡ ከላይ በመግቢያው የገለጽናቸውን የመኪና አደጋ ምክንያቶች በመለየት አሽከርካሪዎች፣ እግረኞች፣ ተቆጣጣሪዎች፣ ወዘተ. ሊፈጽሟቸው የሚገቡ ግዴታዎችንና ኃላፊነቶች ይደነግጋል፡፡ ሕጉ ሰፊና ዝርዝር ነው፡፡ በመጽሐፍ መልክ ከታተሙት ሕግጋት ቀጥሎ በደንብ ደረጃ ከወጡት ሕግጋት ሰፊው ሳይሆን አይቀርም፡፡ ደንቡ ከ67 ገጽ በላይ ሲሆን፣ 86 ድንጋጌዎችንና አባሪዎችን የያዘ ነው፡፡

  የደንቡ ዓላማ በመንገድ ላይ ደኅንነቱ የተጠበቀና ቀልጣፋ የትራፊክ እንቅስቃሴ መኖሩን ለማረጋገጥ የወጣ ነው፡፡ ደንቡ ማንኛውም ትራፊክ በኢትዮጵያ መንገዶች ላይ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡ በደንቡ ውስጥ የተካተቱት 14 ክፍሎች ስለጥንቃቄ መርሆች፣ ስለመንገድ አጠቃቀምና ፍጥነት፣ ስለትራፊክ ድንጋጌዎች፣ ስለእንስሳት፣ ስለመንገደኞች፣ ስለመንገድ ምልክቶችና መብራት ወዘተ. በዝርዝር ደንግገዋል፡፡ ሕጉ የተንቀሳቃሽ ስልክና ምስል እየተጠቀሙ ማሽከርከርን ከልክሏል እንዲሁም የደኅንነት ቀበቶን በአስገዳጅነት ማሰርን ለመጀመርያ ጊዜ በአሽከርካሪዎች ላይ ግዴታ ጥሏል፡፡ አሽከርካሪዎች ሊጠብቋቸው የሚገቡ የትራፊክ ደንቦችን ከመዘርዘር ጎን ለጎን እያንዳንዱን ጥፋት በስድስት ደረጃ በመክፈል ከገንዘብ ቅጣት መንጃ ፈቃድ እስከማገድ ያለውን ቅጣት ደንግጓል፡፡ የዛሬ ወር አከራካሪ የነበረውና የታክሲ አሽከርካሪዎችን ለአድማ የዳረገው መንጃ ፈቃድ የማገድ ቅጣትም በዚሁ ደንብ የተካተተው ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ነው፡፡ የደንቡን መተግበር ተከትሎ የአዲስ አበባ የታክሲ ማኅበራት ተቃውሟቸውን አሰምተው ደንቡ ሳይፈጸም ከቆየበት አራት ዓመት በተጨማሪ ለሦስት ወራት አፈጻጸሙ እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ የታክሲ ማኅበራቱ ካነሷቸው ቅሬታዎች ውስጥ ዋናው የታክሲ አሽከርካሪ በተለያዩ እርከኖች የተቀመጡትን ጥፋቶች ለሁለተኛ ጊዜና ከዚያ በላይ ጥፋት ሲፈጽም 14 ነጥቦች ያህል ከሞላ ለስድስት ወር የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ዕገዳና የተኃድሶ ሥልጠና እንደሚወስድ የተደነገገ ነው፡፡ ድንጋጌው ሁሉንም ተሽከርካሪዎች የሚመለከት ቢሆንም ሾፌርነት እንጀራቸው፣ የትራፊክ ቅጣትም ፀበላቸው የሆነላቸውን የታክሲ ሾፌሮች በተግባር በተለየ የሚመለከት አስመስሏል፡፡ የታክሲ ሾፌሮች እንደሚናገሩት በገንዘብ ብቻ መታለፍ ያለባቸው ጉዳቶች ለዕገዳ ምክንያት መሆናቸውን ይቃወማሉ፣ ደንቡም ከታክሲ አቅርቦትና ትርፍ ከአዲስ አበባ የመንገድ ሁኔታም ጋር እንደማይጣጣም ይገልጻሉ፡፡ በአድማ መፈጸሙ የተላለፈው ደንብ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን? መንግሥት ሕጉን ያለመፈጸሙን ሕጋዊነትና የማያመጣውን ጣጣ በቀጣዮቹ ክፍሎች እንመለስበታለን፡፡ ደንቡ አሽከርካሪዎችን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ ደንቡ መንገደኞችን በተመለከተ ሊፈጽሟቸው የሚገቡ ግዴታዎችን በመግለጽ ደንብ ተላልፈው ሲገኙም 40 ብር እንደሚቀጡ ደንግጓል፡፡  

  መንግሥት ለምን ሕግን አያስፈጽምም?

  ከመንግሥት ግዴታዎች አንዱ ኅብረተሰቡን የሚመለከቱ ፖሊሲዎችና ሕጎችን መቅረጽና ማስፈጸም ነው፡፡ ሕግ ማውጣት ብቻ ሳይሆን ሕጉን ማስፈጸም የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ ሕግ ወጥቶ የማይፈጸም ከሆነ ሕጉ የወረቀት ነበር ነው፡፡ መንግሥታት ሕግን ለምን አያስፈጽሙም በማለት ምክንያቶቹን የመረመረ ፊል ራቢኖዊዝ የተባለ ተመራማሪ፣ አንዳንድ መንግሥታት ሕግ ካወጡ በኋላ ለማስፈጸም ዳተኛ የሚሆኑት የሕጉን ጥሬ ይዘት ከማስፈጸም ይልቅ የሕጉን መንፈስ ማስፈጸም ጠቃሚ ነው ብለው ሲያምኑ፣ ከሕጉ መውጣት ጀርባ ያሉ መሠረታዊ ችግሮችን ለመቅረፍ በማሰብ ወይም የሕጉን አፈጻጸም ለብዙኃኑ የኅብረተሰብ ክፍል ጥቅም ለማዋል በማሰብ ኅብረተሰቡ ስለሕጉ መጥፎ ግንዛቤ እንዳይኖራቸው ለማድረግ በማሰብ ነው ይላል፡፡ የትራፊክ ቁጥጥር ደንቡን በዚህ መነሻ ካሰብነው መንግሥት ላለማስፈጸም አንዱንም ምክንያት አስቦ ስለመሆኑ መከራከር አሳማኝ አይሆንም፡፡ የትራፊክ አደጋው ችግር እንኳን የሕጉን መንፈስና ከጀርባ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ማሰብ፣ ሕጉንም በጠንካራ ተቋም ቢያስፈጽም ችግሩን ማቃለል በቶሎ የሚታሰብ አይደለም፡፡ የብዙኃኑን የኅብረተሰብ ክፍል ፍላጎትንም ካሰብን የሕጉ መፈጸም ከትራፊክ አደጋ ሥጋት ነፃ ስለሚያደርገው ሕጉን አለመፈጸም ምክንያታዊ አይሆንም፡፡ ተመራማሪው እነዚህ ታሳቢ ምክንያቶች (Considerations) ቢኖሩም መሠረታዊ ችግሩ ከሰፋ፣ ወይም ሕጉ ለመቅረፍ ያሰበው ችግርን የሚያጠናክሩ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ፣ ሕጉ ባለመከበሩ የተጎጂዎች ቁጥር ከበዛ፣ ወይም የኅብረተሰብ ግፊቱ ወይም ጫናው የሕጉን አለመተግበር የሚቃወም ከሆነ ሕጉ ሊፈጸም፣ መንግሥትም ሊያስፈጽመው እንደሚገባ ይተነትናል፡፡

  የትራፊክ ቁጥጥር ደንቡን ከመረመርነው ደንቡ የሚፈጸምበትን ጊዜ በግልጽ አመልክቷል፡፡ በደንቡ አንቀጽ 86 ደንቡ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ የፀና ይሆናል ሲል ይደነግጋል፡፡ ደንቡ ከወጣበት ከነሐሴ 20 ቀን 2003 ዓ.ም. አንፃር የአዋጁ መፈጸሚያ ወይም ማስፈጸሚያ ጊዜ ከጀመረ አራት ዓመት አልፎታል፡፡ አንዳንድ አዋጆች ወይም ሕግጋት እንደወጡ እንዳይፈጸሙ ወይም ከመፈጸም ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆዩ ለማድረግ ግልጽ ድንጋጌ በይዘታቸው ሊካተት ይገባል፡፡ ለምሳሌ ከልደት፣ ሞትና ጋብቻ ምዝገባ ጋር በተያያዘ የፍትሕ ብሔር ሕጉ መዝጋቢ አካል እስከሚቋቋም እንደማይፈጸም ደንግጓል፡፡ ተመሳሳይ ድንጋጌ በዚህ ደንብ ውስጥ አይገኝም፡፡ እንዲያውም ደንቡ በአንቀጽ 84 ደንቡን የሚቃረን ማንኛውም ደንብ፣ መመርያ ወይም የአሠራር ልምድ በዚህ ደንብ ውስጥ በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተፈጻሚነት አይኖረውም ሲል ደንግጓል፡፡ ይህ ማለት ደንቡን ሳይፈጽሙ ወይም ሳያስፈጽሙ ማቆየት ወይም ማዘግየት ሕጉ የከለከለውን የቀደመ የአሠራር ልማድ እንዲቀጥል መፍቀድ ነው፡፡

  ከላይ የጠቀስነው ተመራማሪ ሕግጋትና ደንብን እንዲፈጸሙ የማይደረግባቸውን ሰባት ተጨማሪ ተግባራዊ ምክንያቶች ያነሳል፡፡ የተመራማሪውን ሐሳብ ከተነሳንበት ነጥብ አንፃር እስኪ እንመርምረው፡፡ የመጀመርያው በሕግጋቱ የተደነገጉት ግዴታዎች ሲጣሱ የማያስታውቁ ወይም ሊታዩ የማይችሉ ወይም በሌላ ነገር በመሸፈናቸው የማናስተውላቸው ሲሆኑ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአደጋው መክፋት የአደባባይ ምስጢር በሆነበትና የትራፊክ ደንብ ጥሰቱ በተንሰራፋበት የእኛ አገር ይህ ምክንያት አያሳምንም፡፡

  ሁለተኛው ምክንያት ለማስፈጸም በሕግ ሥልጣን የተሰጠው ተቋም ወይም ኤጀንሲ ሕጉን ለማስፈጸም በቂ የሰው ኃይልና የበጀት ችግር ሲያጋጥመው ነው፡፡ ይህ ምክንያት ለትራፊክ ደንቡ የሚሠራ ይመስላል፤ ግን ከአደጋውና ከሕግ አወጣጥ አስተምህሮ አንፃር ለእኛ ጉዳይ አሳማኝ አይሆንም፡፡ አንድ መንግሥት ለማስፈጸም የሚያስችለው የሰው ኃይል፣ የተቋም አደረጃጀትና የበጀት ሁኔታ እንዲሟላ ባላቀደባት ሁኔታ አዲስ ሕግ ሊያወጣ አይገባም፡፡ ካወጣም በቅርቡ እንደሚሟላለትና አፈጻጸሙ እንደሚጀምር ወይም የተወሰኑትን የመፈጸሚያ ጊዜ የሚያራዝም ድንጋጌ ሊቀርጽ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ግን የአገራችን የመኪና አደጋ ችግር ከዓለም አንደኛ በደረሰበት ወቅት የወጣ ሕግ በቂ ተቋምና የሰው ኃይል የለኝም ብሎ አለማስፈጸም ለሕዝብ መሠረታዊ ችግር ቸልተኛ መሆን ነው፡፡

  ሦስተኛው የመብት ጥሰቱና ተጎጂዎቹ ይታወቃሉ፤ ግን የጥሰቱና የጉዳቱ መጠን ጠንካራ የሕግ መፈጸምን የሚያስገድድ ባልሆነ ጊዜ ነው፡፡ የመኪናው አደጋ ዓይነቱና ብዛቱ፣ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የሚደርሰው አደጋ ከህሊና በላይ ለሆነባት አገራችን ይህ የተመራማሪው ምክንያት ውኃ የሚቋጥር እንዳይሆን ያደርገዋል፡፡

  አራተኛው ምክንያት የመብት ጥሰቱ እየታወቀ ሕግን መፈጸም ከጥቅሙ ጉዳቱ ሲያመዝን ወይም የፖለቲካ ፋይዳው አደገኛ በሆነ ጊዜ ነው፡፡ ተመራማሪው ይህንን ሕግ የማይፈጸምበትን ምክንያት በምሳሌ ሲያስረዳ ብዙ ሠራተኛ ቀጥሮ የሚያስተዳድር ተቋም የአካባቢ ብክለት አድርሰሃል በሚል ጠንካራ የሕግ አፈጻጸም መከተል ያለውን ጉዳት ይገልጻል፡፡ ይህ አመክንዮ የሰዎችን በሕግ ፊት እኩል መሆኑን የሚፃረር ከመሆኑም በላይ በአገራችን የመኪና አደጋ ተጎጂ እንጂ ተጠቃሚ አካል ባለመኖሩ ሕግን ላለማስፈጸም ተገቢ አመክንዮ አይሆንም፡፡

  አምስተኛው የመብት ጥሰት በሚያደርሰውና በተቆጣጠሪው (ሕጉን በሚያስፈጽመው አካል) መካከል የጥቅም ግጭት (ሙስና፣ የፖለቲካ ጫና፣ ወይም የግል ታማኝነት) በኖረ ጊዜ ሲሆን፣ በትራፊክ ቁጥጥር ደንብ አለመፈጸም ጋር ምክንያቶቹ የሚያያዙ አይመስሉም፡፡

  ስድስተኛው ሕጉን የሚያስፈጽመው አካል ግዴለሽ ሲሆን ነው፡፡ ተመራማሪው እንዲህ ዓይነት ምክንያት የሚሰጠው ሕግ የሚያስፈጽሙትን በቀጥታ የማይመለከት ሲሆን፣ ወይም በሕጉ መውጣት የማያምን አስፈጻሚ ጥሰቶችን ቸል ስለሚል ነው በሚል ይገልጹታል፡፡ በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ የመኪና አደጋ አስፈጻሚውን ጨምሮ ያላንኳኳው ቤተሰብ የለምና ሁሉም በቀጥታ ተጎጅ ነው፡፡ የአደጋው ምክንያት የአሽከርካሪ ጥፋት፣ የትራፊክ ፍሰት መዛባት ወይም የመንገደኛ ጥንቃቄ ማነስ መሆኑ ገሃድ በሆነባት እነዚህን ችግሮች የሚቀርፍ ሕግን የማይደግፍ ዜጋ መኖሩ ያጠራጥራል፡፡ በሌላ በኩል ግን አስፈጻሚው ቸልተኛ አይደለም ለማለት አይቻልም፡፡ የፀረ ሽብር ሕጉን፣ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ሕጉን ያህል ተፈጻሚነት አለመኖሩ የአስፈጻሚውን ቸልተኝነት አስረጂ ነው፡፡ አሁንም ከአራት ዓመታት በላይ ሳይፈጸም የቆየውን ደንብ ለተጨማሪ ሦስት ወራት እንዳይፈጸም መስማማት የቸልተኝነቱ ጥግ ነው፡፡

  የመጨረሻው ምክንያት አስፈጻሚው ተቋም ሕጉን በአግባቡ እያስፈጸመ መብት የሚጥሰው አካል ሳይማርበት ሲቀር ነው፡፡ ይህ ምክንያት ለትራፊክ ደንቡ የቀረበ ምክንያት ቢሆንም፣ ሕጉ በምልዓት ተፈጻሚ ባልሆነበት ሁኔት በአሽከርካሪዎችና በእግረኞች ላይ ያመጣውን ለውጥ መገምገም ያስቸግራል፡፡

  ሕጉን ያለማስፈጸም ውጤትናሰ ያለው የሕግ አማራጭ

  አንድ ሕግ ተመክሮበት በሕግ አውጭ አካል ከወጣ በኋላ የማይፈጸም ከሆነ ዘርፈ ብዙ አሉታዊ ውጤቶች ይኖሩታል፡፡ የመጀመሪያው ሕጉ የወጣለት ዓላማ ወይም የኅብረተሰብ ችግር ሳይቀረፍ ይቀራል፡፡ የትራፊክ ቁጥጥሩ ጤናማ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖርና  ኅብረተሰቡን ከአደጋ እንዲታደግ ያለመ ቢሆንም፣ በተገቢው ጊዜ ካልተፈጸመ በጎ ዓላማው አይሳካም፡፡ ሁለተኛው በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚፈጥረው ትርጉም ነው፡፡ ሕግ አውጥቶ አለመፈጸም፣ ኅብረተሰቡ ለሕጉ ቦታ እንዳይሰጥ ያደርገዋል፡፡ ሕግ የሚጻፍ እንጂ መንግሥት የማያስፈጽመው፤ ወይም ሲፈልግ የሚጠቅሰው፣ ሲፈልግ የሚቀጣበት መሣሪያ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ ሌላው ሕግ የማስፈጸም ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ ያለበትና የመንግሥት አካል ብቃት ጥያቄ ውስጥ ይከታል፡፡ ሕጉ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ደንቡን ለማስፈጸም ሥልጣን የተሰጠው የትራንስፖርት ሚኒስቴር የወሰደው ዕርምጃ የለም ማለት ነው፡፡ ሕግ ማስፈጸም ዋና ግዴታው የሆነ አካል ሕግ እያስፈጸመ ካልሆነ ምን እየሠራ ነው? ለሚለው አሳማኝ መልስ መስጠት አይቻልም፡፡

  በሌላ በኩል ግን በአገራችን የሕግ ሥርዓት ሕጉ ያለውን ዕጣ ፈንታ ከመዘንን በምንም ምክንያት የሕጉን አለመፈጸም ልንቀበል አንችልም፡፡ ሕጉ በሕዝቡና በባለድርሻ አካላት በቂ ውይይት ካልተደረገበት፣ ሕጉን ለመፈጸም በቂ ተቋምና ባህል ካልተፈጠረ ሕጉን አለማውጣት አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነበር፡፡ ግን ሕጉ ወጥቷል፡፡ ስለዚህ ሕዝቡና ባለድርሻ አካላት መክረውበታል፤ መንግሥትም ለማስፈጸም የሚያስችል አቅም አለው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ማስፈጸም አማራጭ የለውም፡፡ ሕግ ሲፈጸም ሁሉንም አያስማማም፡፡ ስርቆትን የሚቀጣ ሕግ የንብረት ባለቤትን እንጂ በስርቆት የሚተዳደርን አያስደስትም፡፡ ስለዚህ ብዙኃኑን ካስማማ ሕጉ የታክሲ አሽከርካሪዎች ስላልተመቻቸው ብቻ ከመፈጸም ሊዘገይ አይገባም፡፡ የታክሲ አገልግሎት ላለመስጠት አድማ በመምታት ሕግ እንዳይፈጸም ማድረግ ከተቻለ የሚፈጥረው ባህል መጥፎ ነው፡፡ ነገም ሌላ ሕግ ሲወጣ እንዳይፈጸም በየሴክተሩ አድማ ማድረግን ያበረታታል፡፡ በሌላ በኩል ግን ሕጉ ሲፈጸም ችግር ከገጠመው ወይም ሕጉ እንዳይፈጸም የሚያደርገው መሠረታዊ የይዘት ችግር ካለው ሕጉን ማሻሻል አሁንም ሌላው አማራጭ ነው፡፡ ሕጉን የማሻሻል ሐሳብ በሌለበት ሁኔታ ሕጉን እንዳይፈጸም ለተጨማሪ ዓመታት መግፋት አሳማኝ አይደለም፡፡ መንግሥት የሚቀረው ብቸኛ አማራጭ ማስፈጸም ነው፡፡ ማስፈጸም ማለት የትራፊክ ሕግን የሚጥስ አሽከርካሪን መቅጣት፣ ከብዙ ቅጣት ካልተማረ መንጃ ፈቃዱን ማገድና ተኃድሶ መስጠት ነው፡፡ እግረኛውም ተገቢውን ጥንቃቄ ሳያደርግ መንገድ ሲያቋርጥ፣ ለተሽከርካሪ በተፈቀደለት መንገድ ላይ ያለ በቂ ምክንያት ሲቆም ወይም ሲጓዝ 40 ብር እየቀጡ መቀጠል ነው፡፡ እግረኛን ሁሉ መቅጣት ከመጀመር ትምህርት ይቅደም ከተባለም ደንቡን አሻሽሎ ቅጣቱን ማዘግየት ነው፡፡ በእኛ አገር የእግረኛ ባህል የትራፊክ ደንብን የሚጥስ እግረኛ ከቀጣን አገሩ በሙሉ 40 ብር እየያዘ ከቤቱ መውጣት ይኖርበታል፡፡ ዞሮ ዞሮ መንግሥት ያወጣውን ሕግ ራሱ ካላስፈጸመው ማን ያስፈጽምለታል? ሕጉ ይፈጸም፣ አለበለዚያ ሕጉ ይሻሻል፡፡ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ በአድማ የሕግን መፈጸም ማስተላለፍ የሕግ የበላይነት ባህልን ያበላሻል፡፡ እንኳን ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ እንዲል፡፡            

  አዘጋጁ፡– ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...