Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከሥራ አስፈጻሚው ጋር አብሮ ቁጭ ብሎ ሕግ ያስከብራል ብዬ አላምንም›› አቶ ዮሐንስ ወልደገብርኤል፣ የሕግ ባለሙያ

አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል በአሁኑ ወቅት የአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የግልግል ዳኝነት ተቋም ኃላፊ ናቸው፡፡ አቶ ዮሐንስ የሕግ ምሩቅ ሲሆኑ፣ የደርግ ከፍተኛ አመራሮችን ለመክሰስ ተቋቁሞ በነበረው ልዩ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት፣ በኋላም በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በዓቃቤ ሕግነት አገልግለዋል፡፡ በቀድሞው የኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለሥልጣን የሕግ ክፍል ኃላፊ ሆነውም ሠርተዋል፡፡ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከዮሐንስ አንበርብር ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡ እንደሚከተለው ተሰናድቷል፡፡

ሪፖርተር፡- ሰሞኑን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን ለማቋቋም ረቂቅ ሕግ ለፓርላማ ቀርቦ በውይይት ላይ ይገኛል፡፡ የረቂቁ መግቢያ የዓቃቤ ሕግ ሥልጣን በመበታተኑ የሕግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ እክል እንደገጠመ ይገልጻል፡፡ የዓቃቤ ሕግን ሙያ በአንድ ነፃ የሆነ ተቋም ሥር እንዲመራ ማድረግ ቀደም ባሉት የኢትዮጵያ መንግሥታት ተግባራዊ ከመደረጉ አንፃር ያለዎትን ግምገማና ፋይዳውን ቢያስረዱን?

አቶ ዮሐንስ፡- በኢትዮጵያ ስለ ዓቃቢያነ ሕግ ሥራና ስለ ዓቃቤ ሕግ ተቋም አደረጃጀት ለመጀመሪያ ጊዜ በሕግ የተደነገገው በ1934 ዓ.ም. ነው፡፡ ይህ ሕግ ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ ዘመናዊ የዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት መቋቋሙን የሚያበስር ነው፡፡ በ1938 ዓ.ም. ናታን ማረን የሚባሉ እስራኤላዊ አይሁድ የመጀመሪያው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ነበሩ፡፡ እኚህ ግለሰብ በእስራኤል የሚገኙ የኢትዮጵያ ገዳማትንና የተለያዩ ሕንፃዎች በተመለከተ፣ ጣሊያን ኢትዮጵያን ከወረረ በኋላ እነዚህን ገዳማትና ሕንፃዎች የእኔ ናቸው በማለቱ ከፍተኛ የሆኑ የፍርድ ቤት ሙግቶችን በመቃወም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለጠበቃነት ክፍያ ሳይከፈላቸው የቆሙ ናቸው፡፡ እኚህ ሰው የኢትዮጵያን ጥቅምና ሀብት፣ እንዲሁም በእስራኤል የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን መብት በማስከበር ጉልህ ተሳትፎ ያደርጉ የነበሩ የሕግ ባለሙያ ነበሩ፡፡ ናታን ማረን ከ1938 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1954 ዓ.ም. ድረስ በዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግነት ከኢትዮጵያውያን ምክትል ዓቃቤያነ ሕጎች ጋር በመሆን የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አሠራር፣ ልማዶች፣ የተለያዩ የአሠራር ፎርሞችንና አወሳሰኖችን በመቅረፅ መሠረት የጣሉ እንደሆነ በታሪክ መዛግብት ላይ ሰፍሯል፡፡

በዚህም መሠረት አሁን የምንጠቀምባቸው አሠራሮችና ልምዶች እርሳቸው ያመጡዋቸው እንደሆኑ፣ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ያደረጉዋቸው የዓቃቤ ሕግ አሠራርና ልምዶች ከእንግሊዝና ከእስራኤል ልምዶች ናታን ማረን ቀድተው ያመጡት እንደሆነ ይነገራል፡፡ በቅርቡ በወጣ አንድ መጽሐፍ ላይ እንደተመለከትኩት ናታን ማረን በሥራቸው ታታሪ፣ በጣም ገለልተኛ ከመሆናቸው የተነሳ እስካሁን በዘመናዊ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሰነዶች በብዛት ያላየሁትን አንድ አስገራሚ አቤቱታ በአንድ ተከሳሽ ስም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዳመለከቱ ተመልክቻለሁ፡፡ ሕግ ከሚፈቅደው የቅጣት ውሳኔ በላይ በዚህ ተከሳሽ ላይ ፍርድ ቤት ወስኗል ብለው ነው ናታን ማረን ፍርድ ቤቱ ስህተቱን እንዲያርም አቤቱታቸውን ያቀረቡት፡፡ ይህ እንግዲህ የሚያስረዳው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለሚከሰውም ተከሳሽ ተቋርቋሪ ወይም ለተከሳሹም የሕግ ጠባቂ መሆን እንዳለበት በንድፈ ሐሳብ የተማርነውን ናታን ማረን በተጨባጭ ማድረጋቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ሕግ በአግባቡ መተግበሩን እንጂ ማስፈረድ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዓላማ አለመሆኑን በተግባር ያስገነዘቡበት ድርጊት ነው፡፡

ከእሳቸው ቀጥሎ በአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ወቅት የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን ይመሩ የነበሩ እጅግ በጣም የተማሩና ሰፊ ልምድ የነበራቸው ናቸው፡፡ ለመጥቀስ ያህልም አቶ መርአዮ ኢሳያስ በአሜሪካ የተማሩ የሕግ ምሩቅ የናታን ማረን ምክትል ነበሩ፡፡ አሁንም በሥራ ላይ ያለውን የፍትሐ ብሔር ሕግ በማርቀቅ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የነበሩት ለጥቂት ጊዜያት ቢሆንም አቶ ተሾመ ኃይለ ማርያም ይባላሉ፡፡ ከዚህ በመቀጠል ሁለተኛው አቶ ተሾመ ገብረ ማርያምና አቶ አማኑኤል አምደ ሚካኤል ይጠቀሳሉ፡፡ በአጠቃላይ በኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የነበረው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሙያዊ ነፃነት ኖሮት መንግሥትን ወክሎ የሚከስ ተቋም ነበር፡፡ በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ላይም ይሳተፍ ነበር፡፡ የደርግ መንግሥት ከተፈጠረ በኋላ ሥርዓቱን የሚገልጽ የዓቃቤ ሕግ አደረጃጀት ነበር፡፡ የልዩ ጦር ፍርድ ቤት ዓቃቤ ሕግ፣ የልዩ ፍርድ ቤት ዓቃቤ ሕግ የሚባሉ ነበሩ፡፡ የምርመራ አካላት ደግሞ የሠርቶ አደር ቁጥጥር ኮሚቴ፣ የደርግ ምርመራ፣ ልዩ ምርመራ፣ የማዕከላዊ ምርመራ የሚባሉ አደረጃጀቶች ነበሩ፡፡ ትኩረቱ በአጠቃላይ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ምርመራዎች ላይ ነበር፡፡ በመጨረሻ ላይ በ1980 ዓ.ም. የልዩ ፍርድ ቤት ዓቃቤ ሕግና ዋናው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋም አንድ ላይ ተዋህደው ግዙፍ የሆነ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፍት ቤት በኢሕዲሪ ሕገ መንግሥት መሠረት ተቋቁሟል፡፡

ኢሕአዴግ ወደ መንግሥት ሥልጣን ከመጣ በኋላ ደግሞ በ1985 ዓ.ም. የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት በአዋጁ ቁጥር 39 ተቋቋመ፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ተቋም እንደቀድሞው አልነበረም ሥልጣኑ፡፡ ምክንያቱም በክልልና በማዕከል ተብሎ የተከፈለ አደረጃጀት ስለነበር የዚህ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥልጣን ማዕከል ላይ ብቻ ነበር፡፡ ይህ ተቋም አንድ ዓመት ብቻ ከሠራ በኋላ ወደ ፍትሕ ሚኒስቴር እንዲካተት በመደረጉ፣ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አደረጃጀት ነፃ ህልውናውን አጥቶ በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር እንደ አንድ መምሪያ ሲሠራ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚህም መሠረት የፍትሕ ሚኒስትሩ ዋና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተደርገው ይቆጠራሉ ማለት ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን በኃይለ ሥላሴም ሆነ በደርግ ጊዜ ከነበረው ሁኔታ በተለይ ነፃ የሆነ ህልውናውን አጥቶ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- የዓቃቤ ሕግ ተቋም በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር መደበቁ አሉታዊ ተፅዕኖ በሕግ ማስከበር ሥራው ላይ አድርሷል ብሎ መገመት ይቻላል?

አቶ ዮሐንስ፡- በትክክል፡፡ ተቋማዊ ህልውናውን አሳጣው ማለት ተቋማዊ ትውስታን (Institutional Memory) ልምዶቹና አሠራሮቹ ላለፉት 20 ዓመታት ደብዛቸውን አጥተዋል ማለት ነው፡፡ ለዓቃቤ ሕግ ሙያ ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረግ አልቻለም ማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ ባለፈም በ1993 ዓ.ም. የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የፖሊስነትና የዓቃቤ ሕግነትን ሥልጣን ይዞ እስካሁን እየሠራ ይገኛል፡፡ በ2001 ዓ.ም. ደግሞ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንም ራሱን የቻለ የዓቃቤ ሕግና የምርመራ ሥልጣን እንዲኖረው ተደርጎ ተደራጅቷል፡፡ በቅርብ ደግሞ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣንም ተመሳሳይ የመመርመርና የዓቃቤያንነት ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰሞኑ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን ለማቋቋም ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀርቦ የመጀመሪያ ሕዝባዊ ውይይትም ተደርጓል፡፡ በዚህ ውይይት ላይ ከተሳተፉት መካከል አንዱ እርስዎ ነዎት፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ያዩትን ምልከታ ቢያካፍሉን?

አቶ ዮሐንስ፡- ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤትን በድጋሚ ለማደራጀት የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ተመልክቼዋለሁ፡፡ እንደ ቀድሞ የዓቃቤ ሕግ ባለሙያ እጅግ የዘገየ አዋጅ ብዬ ነው የማምነው፡፡ ምክንያቱም የተበጣጠሰ ፍትሕ የለም፡፡ ፍትሕ አንድ ነች፡፡ የወንጀል ሕግን ስናስፈጽም ወይም ስናስከብር በተለያዩ ተቋማት፣ የተለያዩ የአሠራር ልማዶች፣ የተለያየ ዓይነት ፍትሕ መሰጠት የለበትም፡፡ ፍትሕ ወጥና ተመሳሳይ ሆኖ መሰጠት መቻል አለበት፡፡ ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ነው፡፡ ስለዚህ በሕግ ፊት ሁሉም ሰው በእኩል የወንጀል ፍትሕ ማግኘት አለበት፡፡ ምክንያቱም ሕጎቹ አንድ ናቸው፡፡ ሁሉም ሰው ደግሞ በእኩልነት መዳኘት አለበት፡፡ ይኼንን ለማድረግ ደግሞ ራሱ ተቋሙ አንድ ሆኖ፣ አንድ ዓይነት አሠራር፣ አንድ ዓይነት ልማድ፣ ሕጉን የተከተለ አንድ ዓይነት አከሳሰስ፣ አንድ ዓይነት አወሳሰንና አንድ ዓይነት ተጠሪነት ያለው ተቋም እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ የዚህ ረቂቅ አዋጅ በማብራሪያ ሀተታ ውስጥ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋም በ1986 ዓ.ም. የፈረሰበትን ምክንያት በተመለከተ የተገለጸ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ያንን ተቋምም ማፍረሱ ትክክል እንዳልነበር፣ ያስከተለውንም ጉዳት በረቂቅ አዋጁ መቅድም ላይ ሰፍሯል፡፡ ለመጥቀስ ያህልም ወጥነት የሌለው፣ ቀልጣፋ አገልግሎት የማይሰጥ፣ ውጤትማ ያልሆነ፣ የሕዝብንና የመንግሥት ጥቅም የማይጠብቅ ሕግ አስከባሪ መፈጠሩን የሚጠቁም ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ትልቅ ተግዳሮት እንደተፈጠረ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚጠቁም ዓረፍተ ነገር በመቅድሙ ላይ ሰፍሯል፡፡ በዚህም ምክንያት የሕዝብ ተዓማኒነት ያለው፣ የተሟላ ተቋማዊና ሙያዊ ነፃነት ኖሮት አገልግሎት የሚሰጥ፣ ግልጽና አሳታፊ የሆነ የዓቃቤ ሕግ ተቋም ማደራጀት አስፈላጊ መሆኑን መንግሥት አምኖበት አሁን ከቀድሞ ስህተቶቹ ተምሮ ይኼንን ተቋም ለማደራጀት እንደወሰነ ነው የተረዳሁት፡፡

ምንም እንኳን የዘገየ ቢሆንም ይህንን ተቋም ለማቋቋም የወሰደው ዕርምጃ ራሱን በሚያከብር ዜጋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ተገቢ የሆነ ረቂቅ አዋጅ ነው ብዬ አምናለሁኝ፡፡ ነገር ግን ይህ አዋጅ ስለፀደቀ በመቅድሙ ላይ የሰፈረው ዓላማ ተሟላ ማለት አይደለም፡፡ ከረቂቁ ጋር አባሪ የተደረገው ማብራሪያ ሕጉን ለማርቀቅ ልምድ ተቀሰመባቸው ከተባሉት አገሮች ልምድም፣ በአገራችን ቀደም ሲል ከነበረው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋም ጋር ተጣጥሞ የወጣ ነው የሚል እምነት አላደረብኝም፡፡ እኔ ይህንን ሕግ ለማውጣት የተወሰደውን ተጨባጭ ዕርምጃ ነው አድንቄ ለመግለጽ የፈለግኩት፡፡ እንግዲህ ይህ ረቂቅ ሕግ በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ በገቢዎችና ጉምሩክ  ባለሥልጣንና በሌሎች ተቋማት ሥር ተበታትነው የነበሩ የዓቃቤ ሕግ ሥልጣኖችን በመሰብሰብ ለሚቋቋመው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ እንዲሁም የምርመራውን ሥራ ደግሞ ለፖሊስ የሚሰጥ በመሆኑ ፍጹም ተገቢነት ያለው ዕርምጃ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በተመሠረተ የመጀመሪያዎቹ ዓመታት በዓቃቤ ሕግነት ያገለገሉ እንደመሆንዎ መጠን የፀረ ሙስና ተቋሙ የዓቃቤ ሕግነት ሥልጣን እንዲይዝ የተደረገበትን ምክንያት ለማወቅ ቅርብ ነዎት ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን ደግሞ ይህንን ኃላፊነቱን እንዲያጣ እየተደረገ ነው፡፡ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

አቶ ዮሐንስ፡- የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሲጀመር ሁለቱም ሥልጣኖች እንዲኖሩት ታስቦ አልነበረም ጥናቱ የተደረገው፡፡ ወይ የምርመራ ወይ የዓቃቤ ሕግ ሥልጣንና ኃላፊነት እንዲሰጠው ተብሎ ነበር ጥናት የተደረገው፡፡ እንግዲህ የምርመራው ሥልጣን ምንም እንኳን የፖሊስ ቢሆንም፣ የፀረ ሙስና ተቋምን ባደራጁ አገሮች ተሞክሮ የምርመራውን ኃላፊነት ለፀረ ሙስና ተቋም ይሰጣሉ፡፡ በመደበኛ ፖሊስ ላይ ያለው የሙስና ክስተት ከፍተኛ ስለሆነ የፀረ ሙስና ትግሉን ያደናቅፈዋል በሚል አስተሳሰብ ነው፣ የምርመራ ሥልጣኑን ለፀረ ሙስና ተቋም የሚሰጡት፡፡ በሌላ በኩል የሙስና ክስተት በዓቃቤ ሕግ ተቋም አለ ብለው ያመኑ አገሮች የመክሰስ ሥልጣን ለፀረ ሙስና ተቋም ይሰጣሉ፡፡ ስለኢትዮጵያ ሁኔታ ጥናቱን ያከናወነው ባለሙያ ይኼንን ለይቶ ነው ያቀረበው፡፡ በጣም ጥቂት አገሮች ሁለቱንም ሥልጣን አደባልቀው የሰጡ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ግን በእኛ አገር የነበረውን የፀረ ሙስና ኮሚሽን አቋቋም በአብዛኛው በመከላከልና በማስተማር ላይ አተኩሮ የምርመራውንም ሥራ እንዲያከናውን ነበር የታሰበው፡፡ በተቋሙ ውስጥ በነበረኝ ጥቂት ቆይታና ጥናቱንም እንዳነበብኩት ተቋሙ ሊሰጠው ታስቦ የነበረው የማስተማርና የምርመራ ሥልጣን እንጂ፣ የመከሰስ ሥልጣን ታስቦ እንዳልነበር ጥናቱ ያመለክታል፡፡

በተቋሙ አደረጃጀት ውስጥም የዓቃቤ ሕግ አደረጃጀት ባለመኖሩ ምክንያት ጥናቱን ያከናወነው ኩባንያ ያልሠራውን የዓቃቢያነ ሕግ የሥራ መዘርዘር ራሴ ማዘጋጀቴን አስታውሳለሁ፡፡ የሌሎቹ የሥራ መዘርዝር በሙሉ የተዘጋጀ ሲሆን የዓቃቤ ሕግ ግን ባለመዘጋጀቱ ነው እኔ እንድሠራ የተደረገው፡፡ ምክንያቱም በኋላ የመጣ ኃላፊነት በመሆኑ ነው፡፡ በ1993 ዓ.ም. በወጣው የፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅም አንድ አንቀጽ ብቻ ናት ስለ ዓቃቤ ሕግ ተሰንቅራ የገባችው፡፡ በወቅቱ የዓቃቤ ሕግነት ሥልጣን ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ይሰጥ ብለው መግለጫ ሲሰጡ የነበሩት የፍትሕ ሚኒስቴር ሹማምንት መሆናቸው ለእኔ ያስገርመኝ ነበር፡፡ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን በተመለከተ ተቋሙ ለምርመራ ሥራ እንግዳ አልነበረም፡፡ ከዚህ ቀደም ብሎ ፊናንስ ፖሊስ የሚባል ነበር የጉምሩክ ወንጀሎችን የሚመረምር፡፡ ይህንን ስል ግን የገቢዎች ባለሥልጣን ፈጽሞ የዓቃቤ ሕግ ሥራ ሠርቶ አያውቅም ማለቴ አይደለም፡፡ ከፍትሕ ሚኒስቴር ውክልና እየተሰጠው በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር ሆኖ ይሠራ ነበር፡፡

በመሆኑም ከእነዚህ ተቋማት የዓቃቤ ሕግነት ሙያ ተነጥቆ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሊሰጥ መታሰቡና የምርመራው ሥራ ለፖሊስ መሰጠቱ ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት የዓቃቤ ሕግነትን ሙያ አዳብረዋል አሳድገዋል ብዬ አላምንም፡፡ ይልቁንም በእነዚህ ተቋማት የተለያዩ የዓቃቤ ሕግ ልምዶች፣ አሠራሮች፣ ሥርዓቶችና ደንቦች ኮስሰዋል፣ ደክመዋል፣ ከሕጉም አፈንግጠዋል ብዬ ነው የማምነው፡፡ ይህንን በቀላል ምሳሌ ማስረዳት እችላለሁ፡፡ በተለይ በገቢዎችና በፀረ ሙስና ተቋማት እንደ ትልቅ ተሞክሮ ተደርጎ እየተወራረሱት ያሉት ተገቢ ያልሆኑ የክስ አቀራረቦች አንደኛው ናቸው፡፡ ክስ ሲቀርብ ተከሳሽ የሠራው ወንጀል ንጥር ብሎ ተለይቶ እንዲያውቀው ተደርጎ እንዲከላከል በሚያስችለው መልኩ ነው የሚዘጋጀው፡፡ በእነዚህ በሁለቱ ተቋማት ዛሬ የምናያቸው ክሶች በሚያሳዝን ሁኔታ አንድ ክስ ለሁለትና ለአራት ተሰነጣጥቆ ተደራራቢ ክስ የሚቀርብበት አሠራር ተፈጥሯል፡፡ የሚቀርቡትም ክሶች ተከሳሹ የፈጸመውን ወንጀልና የተላለፈውን ሕግ በደንብ ለይቶ አውቆ ራሱን እንዲከላከል ሳይሆን በተቃራኒው የሚቀርቡ ክሶችን ነው የሚያየው፡፡ በኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ላይ አስገዳጅ የሆነውን የክስ ናሙና የማይከተሉ ክሶች ናቸው አሁን የሚቀርቡት፡፡ በመሆኑም ከዓቃቤ ሕግ ሥራ ያፈነገጠ የክስ አቀራረብ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ እርሾ ተደርጎ የሚወሰድ ልምድና ተሞክሮ በእነዚህ ተቋማት አለ ብዬ አላምንም፡፡ እንደዚህ ዓይነት አሠራር አሁን ባለው የፍትሕ ሚኒስቴር ዓቃቤ ሕግ ውስጥም አለ ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህ አሁን የሚፈጠረው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ትልቅ ተግዳሮቱ ሁሉንም ነገር ወደ ሕግና ወደ ሥርዓት ማምጣት መቻሉ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የረቂቅ ሕጉ ዝርዝር ይዘትን ከሙያ አንፃር እንዴት ገመገሙት?

አቶ ዮሐንስ፡- ወደ ዝርዝር ሕጉ ስንገባ አንዳንድ የሚያሰጉ አንቀጾች አሉ፡፡ ለምሳሌ የሚሾመው ዋና ዓቃቤ ሕግ ምን ዓይነት ሰብዕና፣ ምን ዓይነት ችሎታ፣ ምን ዓይነት ልምድ፣ ተሞክሮና ዕውቀት ሊኖረው እንደሚገባ አይገልጽም፡፡ ይህ ቢቀመጥ ኖሮ ለሚቋቋመው ተቋም ትልቅ ተቀባይነትን የሚፈጥር ይሆናል ብሎ አምናለሁ፡፡ በዓቃቤ ሕግነት የሠራ፣ ተገቢ የትምህርት ዝግጁነት ያለው፣ የዕድሜውና የጤናው የመሳሰሉት መሥፈርቶች መቀመጥ ነበረባቸው፡፡ ምክንያቱም ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ እንደምንገነዘበው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋም ጥንካሬ በዋና ዓቃቤ ሕጉ ብርታት፣ ጉብዝናና ጥንካሬ ላይ የሚመሠረት ነው፡፡ አመራሩ የዓቃቤ ሕግነት አቅም ከሌለው ተቋሙም የተሽመደመደ ነው፡፡ በዚህኛው ረቂቅ አዋጅ ግን ዋና ዓቃቤ ሕጉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፓርላማ ይሾማል ነው የሚለውና ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምን ዓይነት ዓቃቤ ሕግ ነው የሚሾመው የሚለውን፣ በምን መስፈርት የሚለውን የሚገልጽ ነገር የለም፡፡ እንዲሁም የቀደመ ልማድም የለም፡፡

ሪፖርተር፡- በተደጋጋሚ እንዳነሱት የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሥራ በአንድ ተቋም መመራቱ ወይም መደራጀቱ መልካም ቢሆንም፣ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ዝርዝር ይዘት መሠረት በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኘው የፍትሕ ሚኒስቴር ሥልጣንም ተደርቦ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እንዲሰጥ መደረጉን የሚተቹ አሉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ የሚቋቋመው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በዋና ሙያዊ ተግባሩ ላይ እንዳያተኩርና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ እንዲዘፈቅ ያደርገዋል የሚሉ አሉ፡፡ የእርስዎ አቋም ምንድነው?

አቶ ዮሐንስ፡- እኔም በግሌ የማምነው እንደዚያ ነው፡፡ የዓቃቤ ሕግ ሥራ ሙሉ በሙሉ ከአስተዳደራዊና ከፖለቲካዊ ሥራ መነጠል አለበት፡፡ አሁን ይህ ረቂቅ አዋጅ የዛሬ 20 ዓመት የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን ለማፍረስ የወጣው አዋጅ እንዳፈረሰው ሁሉ፣ ይኼኛውም አዋጅ የፍትሕ ሚኒስቴርን የሚያፈርስ አዋጅ ነው የሚሆነው፡፡ ማፍረስ ብቻ ሳይሆን የፍትሕ ሚኒስቴርን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ ወደ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋም የሚያዘዋውር ነው፡፡ ይህ የሚያስከትለው ጉዳት የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋም ሕግ የማስከበሩ ዋነኛ ተልዕኮ ላይ እንዳያተኩርና የፖሊሲና የአስተዳደር ጉዳዮች ተጠቅጥቀው እንዲሰጡት ነው የሚያደርገው፡፡ እርግጥ የዚህ ዓይነት አደረጃጀት ያላቸው አገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ከእኛ ተሞክሮና ልምድ ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ አሁን የሚቋቋመው የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋም የወንጀል ፍትሕ ፖሊሲዎችን በመንደፍና በማውጣት እንደሚሠራ ይገልጻል፡፡ የካቢኔ አባልም ነው፡፡ የአስፈጻሚው አካል ጭምር ሕግን እንዲያከብር የማድረግ ኃላፊነት ያለበት ተቋም የካቢኔ አባል ሆኖ የፖሊሲ ውሳኔዎችን ይወስናል፡፡ እንደገና ደግሞ ሕግ ሲጣስ ሕግ የማስከበር ሥራ ተደባልቆ ነው የተሰጠው፡፡ ይህ አደረጃጀት የተቋሙን ሥራ የሚያሽመደምደው ነው የሚሆነው፡፡ ለጠበቆች ፈቃድ የመስጠትም ሥልጣን አለው፡፡

እንግዲህ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማለት የሕግ ማስከበር ሥራውን ሲሠራ ተከራካሪና ተሟጋች የሚሆነው ከጠበቆች ጋር ነው፡፡ ታዲያ የእነዚህን ጠበቆች ፈቃድ የሚሰጥና የዲሲፕሊን ጉዳይ የሚመለከት ሆኖ መደራጀቱ በጣም የሚያስገርም ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተቋም ለግሉ ዘርፍም የሕግ ትምህርት እንዲሰጥ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ይህ የሚመለከተው ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ እነዚህ ተግባራት አስፈላጊ ናቸው ተብሎ ከታመነባቸው መሰጠት ያለበት ለፍትሕ ሚኒስቴር ነው፡፡ ስለዚህ የፍትሕ ሚኒስቴርን እንዳለ አቆይቶ ከውስጡ የዓቃቤ ሕግ ሥራን ብቻ አውጥቶ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን ማደራጀት ነበር ተገቢው አማራጭ፡፡ ገና ዳዴ ማለት የሚጀምር ተቋምን ይህንን ሁሉ ሥልጣን አሸክሞ እንዲደራጅ መወጠን ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ከሁሉ ነገር በተለይ ሙያዊና ተቋማዊ ገለልተኝነት አይኖረውም፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በፓርላማ የሚሾም ዓቃቤ ሕግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያነሱበት የሕግ አቀራረፅም ሰምቼ አላውቅም፡፡ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የሥራ ዘመንም በጭራሽ አልተቀመጠም፡፡

ሪፖርተር፡- ሌሎች ሚኒስትሮችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ አሹመው በኋላ ላይ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ናቸው ከሹመት የማያነሱት የሚል መከራከሪያን በዚህ ረገድ ለማቅረብ ይሞከራል?

አቶ ዮሐንስ፡- እያወራን ያለነው ስለ ሕግ ማስከበር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ሕግን የሚጥሰው ሥራ አስፈጻሚው፡፡ አስፈጻሚው ሕግ የሚጥስ ሆኖ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ከአስፈጻሚው ጋር አብሮ ቁጭ ብሎ የፖሊሲና የአስተዳደራዊ ጉዳዮችን እየወሰነ ሕግ ለማስከበር ይችላል ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህ የካቢኔ አባል ሆኖ እንዲደራጅ መፈቀዱ ነፃነቱን በእጅጉ ነው የሚሸረሽረው፡፡ ስለዚህ የቀረበው መከራከሪያ በፍጹም ከዋና የዓቃቤ ሕግ ዓላማ ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡ ነፃነቱን የሚያረጋግጥ ወይም የሚያስከብሩ አንቀጾች በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ቢቀመጡ የተሻለ ነው፣ መሆንም ይገባዋል፡፡ ይህ ከሆነ ዋና ዓቃቤ ሕጉን የፈለገው አካል ሊሾመው ካስፈለገ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም ፓርላማው መሆኑ ችግር አይኖረውም፡፡ በዚህ ረቂቅ ላይ ሌላው ያልታየው ነገር ብዬ የማስበው ወታደራዊ የፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ዓቃቤ ሕጎችንም የሙያ ጉዳይ የሚያሳስበውና ብቃታቸውን ለማሳደግም ኃላፊነት መውሰድ ያለበት የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ነው፡፡ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ የሚያሳየውም ይህንኑ ነው፡፡ በረቂቅ አዋጁ ላይ እንደ ሞዴል የተወሰዱ አገሮች ጭምር ይህ አደረጃጀት አላቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በረቂቅ ሕጉ ላይ ሌላው የተካተተው የሚቋቋመው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመመካከር ክስ እንደሚያነሳና እንደሚቀጥል ይገልጻል፡፡ ይህም የዓቃቤ ሕግን ነፃነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥር እንዲወድቅ ያደርገዋል የሚል መከራከሪያ ይቀርባል፡፡

አቶ ዮሐንስ፡- ሌላው የረቂቅ ሕጉ ችግር ይህ አንቀጽ ነው፡፡ ክስ ማንሳት ተዓምር አይደለም፡፡ ሕግንና ሥርዓትን ተከትሎ ነው ክስ የሚነሳው፡፡ በቀድሞ አሠራሮችም ነበረ፡፡ ክስ የሚነሳው መንግሥት የማይፈልጋቸውን ክሶች ወይም ደግሞ በወንጀለኛ መቅጫ የሕግ ዓላማ የሆነውን ሰላምና መረጋጋትን መፍጠር የማያስችሉ ክሶችን እንዲነሱ መንግሥት ሲያዝና በዚህ ላይም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሲያምንበት መነሳት አለበት፡፡ በመንግሥት ትዕዛዝ ክስ እንዳሻው እንዲነሳ የሚደረግበት ሥርዓት መኖር የለበትም፡፡ ነገር ግን በማብራሪያዎቹ በትልልቅ ጉዳዮች ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመማከር ክስ ያነሳል ቢልም በረቂቅ ሕጉ ላይ ግን ይህንን የሚገልጽ ነገር የለም፡፡ በደፈናው ነው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመማከር ክስ እንደሚያነሳ የሚገልጸው፡፡

ሪፖርተር፡- በፀረ ሙስናና በገቢዎች የነበረው የዓቃቤ ሕግ ሥልጣን ቢወሰድም እንኳ፣ የመመርመር ሥልጣን በሙስናና በታክስ ወንጀሎች ለተቋማቱ መስጠት እንዳለበት፣ ምክንያቱም ልዩ ችሎታንና ቴክኒክን የሚጠይቅ ነው የሚል ክርክር የሚያቀርቡ አሉ፡፡ የእርስዎ አቋም ምንድነው?

አቶ ዮሐንስ፡- በገቢዎችና ጉምሩክ አካባቢ አንዳንድ ለየት ያሉ መርሆዎች ይኖራሉ፡፡ ምክንያቱም የገንዘብ አሰባሰብና የቀረጥ አጣጣልን የሚመለከቱ በመሆናቸው ማለቴ ነው፡፡ ይህ ግን በትንሽ ሥልጠና መስተካከል የሚችል በመሆኑ ከፖሊስ የምርመራ አቅም የበለጠ ሊሆን አይችልም፡፡ በሙስና በኩል ያለው ደረቅ ወንጀል ግን የተለየ የምርመራ ልምድና ተሞክሮ የሚጠይቅ አይደለም፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች