Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አነጋጋሪ ሆኖ የዘለቀው የንግድ ምዝገባና ረቂቅ አዋጅ ገጽታዎች

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በንግድ ኅብረተሰቡ ዘንድ ለአሠራር አመቺ አይደሉም ተብለው አስተያየት ሲሰጥባቸው ከነበሩ አዋጆች ውስጥ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ማሻሻያ አዋጅ አንዱ ነው፡፡ አዋጁ ከዚህም ቀደም ተሻሽሎ በሥራ ላይ የዋለ ቢሆንም፣ አሁንም ሊስተካከሉ የሚገባቸው የአዋጁ አንቀጾች አሉ በሚል በተደጋጋሚ ውይይት የተደረገበትና የማሻሻያ ሐሳቦች ሲቀርቡበት የቆየ ነው፡፡ ይህንኑ ሐሳብ ተንተርሶ መንግሥት በንግድ ሚኒስቴር በኩል አዋጁን ለማሻሻል አዲስ ረቂቅ አዋጅ በማዘጋጀት አዋጁ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ለውይይት ቀርቦ በንግድ ምክር ቤቶች በኩል ሐሳብ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በአንድ አገር የንግድ ሥርዓት ውስጥ ወሳኝ ከሚባሉ ማስፈጸሚያ አዋጆች ውስጥ አንዱ መሆኑ የሚጠቀሰው የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ የንግዱ ኅብረተሰብ ሐሳብ እንዲሰጥበት ባለፈው ዓርብ በተዘጋጀ የምክክር መድረክ ላይ አሁንም ረቂቅ አዋጁ ሊመለከታቸው የሚገቡ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ በንግድ ምክር ቤቱ ባለሙያዎች በኩል የቀረበው ጽሑፍ ረቂቅ አዋጁ ሊያስተካክላቸው ይገባሉ የተባሉ አንቀጾችን ያመለከተ ነው፡፡ ሊሻሻሉ ይገባቸዋል የተባሉ የረቂቅ አዋጁን አንቀጾችም እንዲህ ባለው ቢተካ የሚል ሐሳብም የተቀመጠበት ነበር፡፡  ተወካዮችም በረቂቁ ላይ ሐሳብ ሰጥተዋል፡፡

አዲሱ ረቂቅ አዋጅ አምስት ክፍሎችና 47 አንቀጾችን የያዘ ነው፡፡ የአገሪቱ የንግድ ሥርዓት ዋንኛ ዓላማ ለማንኛቸውም የንግድ ሥራ መስክ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ስለሆነና የንግድ ምዝገባና የንግድ ሥራ ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን ፍትኃዊ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ የረቂቅ አዋጁ መግባቢያ ያትታል፡፡ ዘመናዊ፣ የተቀላጠፈና ተደራሽ በማድረግ የንግዱን ማኅበረሰብና ኅብረተሰቡ ከንግዱ ሥርዓት የሚጠብቀውን አገልግሎት እንዲያገኝ የሕግና የአሠራር ክፍተቶችን በመድፈንና እርካታውን በማሳደግ በአገሪቱ ሁለንተናዊ ኢኮኖሚ ውስጥ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት በማድረግ አገራዊ ራዕይን በማሳካት የኢኮኖሚ ዕድገትን ማስገኘት በማስፈለጉ የሚወጣ አዋጅ መሆኑንም ያመለክታል፡፡ የንግድ ምዝገባና የንግድ ፈቃድ አሰጣጥን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲደገፍ በማድረግ፣ ለመረጃ አያያዝ አመቺ እንዲሆንና ሕገወጥ እንቅስቃሴ ለመግታት እንዲቻል የንግድ ሥርዓቱ ዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂን በመጠቀም መረጃዎችን ለማደራጀት እንዲያስችልም ነው፡፡ የንግድ ሥርዓቱ ግልፅነት፣ ተጠያቂነትና መልካም አስተዳደር የሰፈነበት በማድረግ የአገሪቱን ራዕይ ለማሳካት እንዲቻል አገሪቱ ዘመናዊ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ሕግ እንዲኖራት ሥራ ላይ ባለው አዋጅ ያልተካተቱ አዲስ አንቀጾች የተቀመጠበት ነው፡፡ በቀድሞ አዋጅ ያልነበሩ አዳዲስ አንቀጾችን ያስቀመጠም እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

አንዳንድ ወገኖች ይህ ረቂቁ አሁንም ሊሻሻል የሚገባቸው አንቀጾች አሉት ሲሉ፤ የሚታዩ መሻሻሎች የታየባቸው አንቀጾችም የተካተቱበት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በንግድ ምክር ቤቱ በኩል የቀረበውም ጽሑፍ ይህንኑ ሁለት ሐሳብ የሚያንፀባርቅ ነበር፡፡

አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በጨረፍታ

የንግድ ምዝገባ ስለማከናወን በረቂቅ አዋጁ እንደተቀመጠው፣ የሚሻሻለው አዋጅ ውስጥ ለንግድ ምዝገባ የሚቀርብ ማመልከቻ ለዚሁ የተዘጋጀውን ቅጽ በመሙላትና  አዋጁን ለማስፈጸም በሚወጡ ደንብና መመርያዎች መሠረት የሚጠየቁትን ሰነዶችን በማያያዝ የንግድ ሥራው ይጀምራል ተብሎ ከሚታሰብበት ቀን ቀድሞ መቅረብ ይኖርበታል፡፡ ማናቸውም ለመዝጋቢው አካል በንግድ መዝገብ ለመመዝገብ የቀረበ  ማመልከቻ ተቀባይነት ያለው ሆኖ ከተገኘ መዝገቢው አካል የአገልግሎት ክፍያ በማስከፈል መዝግቦ የንግድ ምዝገባ ምስክር ወረቀት ለአመልካቹ ይሰጠዋል፡፡ ሆኖም የምዝገባው ጥያቄ ውድቅ ከተደረገ መዝጋቢው አካል ምክንያቱን ገልጾ ለአመልካቹ በጽሑፍ ወዲያውኑ ማሳወቅ እንዳለበት ያመለክታል፡፡ በማዕድን ዘርፍ የሚሰማሩ የውጭ ነጋዴዎች፣ የፌደራል የመንግሥት ልማት ድርጅቶች፣ የንግድ እንደራሴዎች፣ የውጭ አገር ነጋዴዎች፣ በዓለም አቀፍ ጨረታ አሸናፊ ሆነው የሚገቡ የውጭ አገር ነጋዴዎች፣ ተቋቁሞ የሚገኝ የንግድ ድርጅቶችን ገዝቶ ባለበት ሁኔታ ንግድ ለማካሄድ የሚፈልግ የውጭ አገር ነጋዴ በዚህ አዋጅ መመዝገብ ይኖርባቸዋል፡፡ በሌሎች ሕጎች የንግድ ሥራ እንዲሠሩ የተፈቀደላቸው ማኅበራት፣ በፌደራል የሚቋቋሙ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት እንዲሁም በሚኒስቴሩ የተፈቀደላቸው የውጭ አገር ንግድ ምክር ቤቶች  በሚኒስቴሩ መመዝገብ እንዳለባቸው የሚያመለክት አንቀጽም አካትቷል፡፡

አንድ ሰው ወይም የንግድ ማኅበር በንግድ መዝገብ እንዳይመዘገብ በሕግ መሠረት የሚቀርብ መቃወሚያ በንግድ መዝገብ ከመመዝገብ ሊያግደው እንደሚችልም ረቂቅ አዋጁ ያስረዳል፡፡

የንግድ ምዝገባ ለውጥ ወይም ማሻሻያ ሲያስፈልግ ደግሞ ማንኛውንም የንግድ ምዝገባ ለውጥ ወይም ማሻሻያ በሚመለከተው የሰነድ አረጋጋጭ አካል እንደተረጋገጠ ለመዝጋቢው አካል ወዲያውኑ ማስመዝገብ እንደሚኖርበት፣ ወዲያውኑ ካላስመዘገበ የተረጋገጠው ሰነድ እስከ ሁለት ወር ጊዜ ብቻ የፀና መሆኑን የሚያመለክትበት አንቀጽ አለው፡፡

የንግድ ምዝገባ ለውጥ ወይም ማሻሻያ የቀረበው ተቀባይነት ለማግኘቱ መዝጋቢው አካል ማረጋገጫ በመስጠት ተቀባይነት ያገኘበትን ቀንና በንግድ መዝገብ ስለገባው ለውጥ ወይም ማሻሻያ በዝርዝር በመግለጽ ለአመልካቹና ለሚመለከታቸው  አካላት በጽሑፍ ማሳወቅ ይኖርበታል ይላል፡፡ በዚህ አዋጅ ለንግድ ምዝገባ የተቀመጡ መሥፈርቶች እንዳስፈላጊነቱ በንግድ ምዝገባ ለውጥ ወይም ማሻሻያ ተፈጻሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ፤ በዚህ አዋጅ መሠረት የሚቀርቡ የንግድ ማኅበራት መመሥረቻ ጽሑፎችና መተዳደሪያ ደንቦች ለውጦችና ማሻሻያዎች ዋና ቅጅዎች የተረጋገጡ መሆን እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡

የንግድ ምዝገባን ስለመሰረዝ ከተቀመጡ አንቀጾች ውስጥ በንግድ ሕጉ ምዝገባን ስለመሰረዝ የተደነገጉት እንደተጠበቁ ሆነው፤ ነጋዴው  የንግድ ሥራውን በማናቸውም ምክንያት የተወ እንደሆነ፣ ነጋዴው ንግዱን ለመነገድ እንደማይችል በአስተዳደራዊ ዕርምጃ ወይም በሕግ ሲወሰን፣ ሊሰረዝ የሚችል መሆኑን ያስቀምጣል፡፡ ነጋዴው ሐሰተኛ መረጃ ወይም ሰነድ አቅርቦ የተመዘገበ እንደሆነ፣ ነጋዴው ይህንን አዋጅ ወይም አዋጁን ለማስፈጸም የሚወጡ ደንቦችንና መመርያዎችን የጣሰ እንደሆነ፣ አንድ ነጋዴ በንግድ መዝገብ ተመዝግቦ የንግድ ፈቃድ ሳያወጣ ለአንድ ዓመት የቆየ ከሆነ መዝጋቢው አካል ያለምንም ተጨማሪ ቅድመ ሁኔታ ምዝገባው እንደሚሰረዝበት ረቂቅ አዋጁ ያመለክታል፡፡ ሌሎች ለስረዛ የሚደረጉ ምክንያቶችም በዝርዝር ቀምጠዋል፡፡  

የንግድ ምዝገባው የተሰረዘበት ነጋዴ በማንኛውም ጊዜ ያንኑ የንግድ ምዝገባ መልሶ መውሰድ የሚችልበት አንቀጾችም ተካትተውበታል፡፡ በሌላ በኩል ግን የንግድ ፈቃዱ የተሰረዘበት እንደገና እንዳይመዘገብ የሚከለክል የሕግ ወይንም አስተዳደራዊ ምክንያት ከሌለ በስተቀር የተሰረዘውን የንግድ ምዝገባ  እንደገና ሊመዘገብ የሚችለው ከተሰረዘበት ቀን ጀምሮ ከአንድ ዓመት በኋላ ስለመሆኑም ተመልክቷል፡፡

የንግድ ማኅበራት ምዝገባ ስረዛ የሚፀናው የስረዛው ማስታወቂያ በአመልካቹ ወጪ በጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት በኋላ መዝጋቢው አካል ከንግድ መዝገብ ከሰረዘበት ቀን ጀምሮ እንደተሰረዘ ይቆጠራል፡፡ ሆኖም ግለሰብ ነጋዴ በሆነ ጊዜ በማስታወቂያ ማስነገር ሳስፈልግ፣ ስረዛው በመዝገብ ከሰፈረበት ጊዜ ጀምሮ የፀና እንደሚሆን የሚጠቅስ አንቀጽ አለው፡፡

በረቂቅ አዋጁ ከተካተቱ ዓበይት ድንጋጌዎች መካከል ስለንግድ ስያሜዎች የተቀመጡት አንቀጾች ይጠቀሳሉ፡፡ የግለሰብ ነጋዴ የሕግ ስም የግለሰቡን ስም የአባቱንና የአያቱን ስም ያካትታል፡፡ ስሙ ቀደም ብሎ የተመዘገበ  ሲሆን፣ የቅድመ አያትን ስም በመጨመር፣ የቅድመ አያት ስም ድረስ የተያዘ ሲሆን፣ የእናት ስም ተጨምሮ ይመዘገባል፣ የእናት ስም ከተያዘ ሌላ መለያ በመጨመር እንዲመዘገብ ይደረጋል፡፡ የኅብረት የሽርክና ማኅበር ስም ቢያንስ የሁለት ማኅበርተኞችን ሕጋዊ ስሞች ያካተተ ሆኖ፣ የንግድ ሥራ  ዘርፉን በማመልከት የኅብረት የሽርክና ማኅበር የሚል መጨመር ይኖርበታል፡፡ የማኅበሩ ስም ከማኅበርተኞች ስሞች ሌላ ስም መጠቀም አይችልም፡፡ ከማኅበርተኞቹ አንዱ ከማኅበሩ ሲወጣ የማኅበሩ ስም መለወጥ እንዳለበት ይጠቀሳል፡፡

የአክሲዮን ማኅበር ስም ስያሜ ደግሞ በአባላቱ የሚወሰን ሆኖ የንግድ ሥራ ዘርፉን በማመልከት፣ የአክሲዮን ማኅበር የሚል ማካተት ይኖርበታል፡፡ የኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስም በአባላቱ የሚወሰን ሆኖ የንግድ ሥራ ዘርፉን በማመልከት፣ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የሚል ማካተት እንደሚጠናቀቅ ይደነግጋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ማንኛውም ነጋዴ የንግድ ምዝገባ በሚያደርግበት ቦታ የድርጅት ስሙን ማስመዝገብ አለበት፤ ማንኛውም ነጋዴ የንግድ ሥራ ፈቃድ በሚያወጣበት ቦታ የንግድ ስሙን ማስመዝገብ አለበት፤ የድርጅት ስም በዚህ አዋጅ ለንግድ ስም የተደነገጉትን መሥፈርቶች እስካሟላ ድረስ በንግድ ስምነት ሊመዘገብ እንደሚችል ያሳያል፡፡

የንግድ ስም እንዳይመዘገብ የሚያደርጉ ምክንያቶች የትኞቹ እንደሆኑም በረቂቅ አዋጁ በዝርዝር ቀርቧል፡፡ ሕጉ በጥቂቱ ሲታይ መዝጋቢው አካል ከዚህ በታች በተገለጹት ምክንያቶች ምዝገባውን ላይቀበል ይችላል፡፡ እንዲመዘገብ የተጠየቀው የንግድ ስም ቀደም ብሎ ከተመዘገበ ሌላ የንግድ ስም ወይም የድርጅት ስም ጋር አንድ ዓይነት ወይም በሚያሳስት ደረጃ ተመሳሳይ ከሆነ የንግድ ኅብረተሰቡ አይመዘገብም፡፡ እንዲመዘገብ የተጠየቀው የንግድ ስም ከመንግሥት ተቋማት፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከፖለቲካ ፓርቲ፣ ከብሔር ብሔረሰቦች ነገዶችና ጎሳዎች መጠሪያ፣ ከሌላ ማንኛውም ዓይነት ማኅበር፣ ከመንግሥታት ኅብረት ድርጅቶች ተቋማት ወይም ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ስሞች ጋር አንድ ዓይነት ወይንም በሚያሳስት ሁኔታ ተመሳሳይ ከሆነም ምዝገባው እንደሚካሄድለት አዲሱ ረቂቅ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ ሌሎች ምክንያቶችም አሉት፡፡ ይህ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት ነጋዴው በንግድ ስምነት ለረዥም ጊዜ ሲታወቅበት የኖረ ሆኖ በዚህ አዋጅ ድንጋጌ የንግድ ስሙ የተከለከለ በሆነ ጊዜና ያልተመዘገበ ከሆነ፣ የመዝጋቢው አካል የበላይ ኃላፊ በሚወስነው መሠረት ሊመዘገቡ እንደሚችሉ ረቂቁ ያመለክታል፡፡ ከተመዘገበ የንግድ ስም ጋር ተመሳሳይ የአነባበብ ድምፅ አለመሆኑ ሲረጋገጥ፤ የዚህ አንቀጽ ድንጋጌዎች አፈጻጸም ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መመርያ መሠረት ይሆናል የሚሉትና ሌሎች አንቀጾችም የተካተቱበት ነው፡፡

በረቂቁና በቀድሞ አዋጅ መሐል የሚነሱ ጥያቄዎች

አንዳንድ ንግድ ምክር ቤቶች በዕለቱ ከቀረበው ጽሑፍ መረዳት እንደተቻለው አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ውስጥ የነበሩ በረቂቁ ላይ ቢሻሻሉና በበጎ የሚታዩ አንቀጾች መኖራቸውን ነው፡፡

በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ ለማሻሻል በተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ውስጥ አንዳንድ አንቀጾች ላይ የተደረገው መሻሻል በበጎ ጎናቸው ሊታዩ የሚችሉ ስለመሆናቸው የንግድ ምክር ቤቱ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡ ለምሳሌ ከንግድ ምዝገባ ጋር በተያያዘ ቀደም ብሎ የንግድ ምዝገባ በየዓመቱ መታደስ አለበት የሚል ግዴታ አንዱ ነበር፡፡ ከዚያም የንግድ ምዝገባው በአምስት ዓመት አንድ ጊዜ መደረግ ይችላል የሚል ማሻሻያ ተደርጎ ሲሠራበት ከቆየ በኋላ፣ አሁን በተዘጋጀው ረቂቅ ላይ ደግሞ ስለንግድ ምዝገባ ምንም የተጠቀሰ ነገር ያለመኖሩ ጥሩ መሻሻል ነው ብለውታል፡፡

ስለ ንግድ ምዝገባ ዕድሳት በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ምንም አለመባሉ የንግድ ምዝገባ አንድ ጊዜ ብቻ መደረግ አለበት የሚል እምነት ያሳድራል፡፡  ነገር ግን ይህ አንቀጽ ግልጽ ብሎ መቀመጥ እንደሚኖርበት አመልክተዋል፡፡ ስለዚህ እንዲህ የተደረገ ምዝገባ ፀንቶ የሚቆይ መሆኑን የሚያሳይ በመሆኑ ጥሩ ማሻሻያ ነው ተብሏል፡፡

ከዚህ ቀደም ብዙ ያካራከሩና ሊቀየሩ ይገባል ተብሎ ሲተቹ ከነበሩ የአዋጁ አንቀጾች ውስጥ አንዱ የንግድ ስያሜን የሚመለከተው ነው፡፡

በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ የንግድ ስያሜን የሚመለከቱ አንቀጾች እንደሚያሳዩት መሻሻሎች የተደረገባቸው መሆኑን የጥራት አቅራቢዎች ገልጸዋል፡፡  ከንግድ ስም ስያሜ ጋር ተያይዞ በጣም አስቸጋሪ የነበሩ ቅድመ ሁኔታዎች እንደነበሩ በጣም ዝርዝርና የግል ዘርፉን ያስጨንቁ የነበሩ ለምሳሌ ስያሜው ገላጭ መሆን የለበትም የሚሉ ጉዳዮች በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ላይ ያለመኖራቸው በመልካምነት የሚታይ ነው፡፡

ነጋዴው ምዝገባ ሳያደርግ ፈቃድ ሲወስድ ዝቅተኛ ካፒታሉ በዝግ ሒሳብ የመቀመጥ የሚለው ድንጋጌ በአዲሱ አዋጅ እንደሚቀር መታሰቡም መልካም ነገር ነው ብሏል፡፡  የንግድ ምዝገባ ከተደረ በኋላ ወደ ሥራ እንዲገባ ቀነ ገደብ የንግድ ረዳት የሚለው ከዋናው የንግድ ሕግ ጋር የሚናበብ እንዲሆን ጥረት መደረጉ በዚህ ረቂቅ ውስጥ ከተካተቱ የንግድ ፍቃድ ማሳደሻ ጊዜ መራዘሙ ሁሉ በመልካምነት ተነስቷል፡፡ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ የንግድ ፈቃድ ማሳደስ ጊዜ በስድስት ወር ተራዝሟል፡፡

አዋጅ የወጣበት ድንጋጌዎች  በዚህ ረቂቅ አዋጅ በሌላ ሕጎች የተደነገጉት የቅጣት ድንጋጌዎችና በዚህ አዋጅ መሠረት አግባብ ያለው ባለሥልጣን የሚወሰዳቸው አስተዳደራዊ ዕርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው ሊያስቀጡ የሚችሉና የቅጣት መጠን የያዙ አንቀጾች አሉት፡፡ ለምሳሌ ሐሰተኛ የንግድ ምዝገባ የምስክር ወረቀት ወይም የንግድ ሥራ ፈቃድ ወይም የእንደራሴ ልዩ የምስክር ወረቀት በማዘጋጀት ሲጠቀም  የተገኘ ማንኛውም ሰው  ከ50,000 እስከ 100,000 ብር   የሚደርስ የገንዘብ መቀጫና ከአምስት ዓመት እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ እሥራት ሊቀጣ ይቀጣል ይላል፡፡ የንግድ ሥራ ሲካሄድባቸው የነበሩ የንግድ ዕቃዎችና የአገልግሎት መስጫና የማምረቻ መሳሪያዎች ይወረሳሉ፡፡ የፀና የንግድ ፈቃድ ሳይኖረው በንግድ ሥራ ተሰማርቶ የተገኘ ሰው ደግሞ ከ20,000 እስከ 60,000 ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጫና ከሁለት ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ  እሥራት የሚቀጣ ሲሆን፣ በተጨማሪም የንግድ ሥራ ሲካሄድባቸው የነበሩ የንግድ ዕቃዎችና የአገልግሎት መስጫና የማምረቻ መሣሪያዎች እንደሚወረሱ ያመለክታል፡፡

ማንኛውም ነጋዴ በንግድ ሥራ ፈቃዱ እንዲሠራ ከተፈቀደለት ሥራ ውጭ  ሲሠራ ከተገኘም ከ15,000 እስከ 40,000 ብር የገንዘብ ቅጣትና ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት የሚደርስ እሥራት ይቀጣል፡፡ የነበሩ የንግድ ዕቃዎችና የአገልግሎት መስጫና የማምረቻ መሳሪያዎች ይወረሳሉ፡፡

ማንኛውም ሰው የአድራሻውን ለውጥ በደንቡ በተመለከተው የጊዜ ወሰን  ውሰጥ ለመዝጋቢው መሥሪያ ቤት ያላስታወቀ እንደሆነም ከ5,000 እስከ 10,000 ብር በሚደርስና እስከ ሦስት ወር በሚደርስ ቀላል እሥራት ይቀጣል፡፡

ይህንን አዋጅ ወይም አዋጁን ለማስፈጸም የሚወጡ ደንብና መመርያዎችን ለማስተግበር በሚሠራ ሥራ አግባብ ያለው አካል የሚልካቸው ሠራተኞች የሚጠይቁትን መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ የማይሆን ወይም በማናቸውም ዓይነት ሁኔታ ተግባሮቻቸውን የሚያስተጓጉል ማንኛውም ነጋዴ የቅጣት መጠን ተቀምጧል፡፡ በረቂቅ አዋጁ ከአዋጁ በተፃራሪ ለተቀመጡ ጥፋቶች እንደየጥፋቱ መጠን የቅጣት መጠን አስቀምጧል፡፡  በአዲሱና በሥራ ላይ ባለው አዋጅ መካከል ቅጣት የተመለከቱት ድንጋጌዎች የተወሰነ ልዩነት አላቸው ብሏል፡፡ በተለይ የቅጣቱ ጣሪያ ከ15 ዓመት ወደ አሥር ዓመት የወረደባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ አምርሮ የተቃወመው አንቀጽ

‹‹በማዕድን ዘርፍ የሚሰማሩ የውጭ ነጋዴዎች፣ የፌደራል የመንግሥት ልማት   ድርጅቶች፣ የንግድ እንደራሴዎች፣ የውጭ አገር ነጋዴዎች፣ በዓለም አቀፍ ጨረታ አሸናፊ ሆነው የሚገቡ የውጭ አገር ነጋዴዎች፣ ተቋቁሞ የሚገኝ የንግድ ድርጅቶችን ገዝቶ ባለበት ሁኔታ ንግድ ለማካሄድ የሚፈልግ የውጭ አገር ነጋዴ፣ በሌሎች ሕጎች የንግድ ሥራ እንዲሠሩ የተፈቀደላቸው ማኅበራት፣ በፌደራል የሚቋቋሙ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት እንዲሁም በሚኒስቴሩ የተፈቀደላቸው የውጭ አገር ንግድ ምክር ቤቶች በሚኒስቴሩ ይመዘገባሉ፤›› የሚል ረቂቅ አዋጅ አንቀጽ አለ፡፡ አንቀጹ በተለይ የንግድ ምክር ቤቶች ምደባ በዚህ አዋጅ ይሁን መባሉ አግባብ አይደለም ተብሏል፡፡  

የንግድ ምክር ቤቱ ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ለአንዳንድ የንግድ ሥራ ፈቃድ መስጫ መደቦች እንደቅድመ ሁኔታ ባይጠየቅም፣ ብቃትን ለማረጋገጥ ሥልጣን የተሰጣቸው የመንግሥት አካላት ለንግድ ሥራ ፈቃዱ የሚፈለገውን የብቃት ማረጋገጫ መሥፈርት መሟላቱን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ‹‹የንግድ ምክር ቤት›› ማለት ነጋዴዎች ሆነው የጋራ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በየደረጃው በአገሪቱ ሕግ መሠረት የሚያቋቁሙት ማኅበር ነው፤ ‹‹የዘርፍ ማኅበራት›› ማለት ነጋዴዎችን የያዘ ሆኖ በአምራችነት ወይም በአገልግሎት ሰጪነት በአንድ ዓይነት የንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ወይም የንግድ ሥርዓቱን ለመደገፍ በፆታ ወይም በማንኛውም ሁኔታ የተደራጁ ማኅበራት ናቸው፡፡

አግባብ ያለው ባለሥልጣን ተግባርና ኃላፊነቶች ሚኒስቴሩ በፌደራል ለሚቋቋሙ የንግድ ዘርፍ ማኅበራት መዝግቦ የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የሚሰጥ ሲሆን፣ የክልል ንግዱን የሚያስተዳድሩ አካላት በክልል ለሚቋቋሙት ለንግድ ዘርፍ ማኅበራት በመመዝገብ የሕጋዊ ሰውነት የምስክር ወረቀት ይሰጣል ይላል፡፡ ይህ አገላለጽ ግን የንግድ ምክር ቤትና የዘርፍ ማኅበራት ትርጓሜ ከ341/95 ድንጋጌዎች ጋር የሚቃረንና የሌለ አደረጃጀት የሚፈጥር በመሆኑ፣ ለምን አዋጅ ውስጥ እንዲገባ እንደተደረገ ግራ እንደሚያጋባ ተገልጿል፡፡

እንደባለሙያዎቹ ማብራሪያ የንግድ ምክር ቤቱ ምዝገባ እዚህ ውስጥ ያላግባብ የገባ ነው፡፡ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በራሱ አዋጅ የተቋቋመ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ አንድ የንግድ ተቋም በዚህ ረቂቅ አዋጅ መሠረት ይመዝገብ መባሉ በዚህ አዋጅ ይመዝገብ ከተባለ በዚህ አዋጅ ይሰረዛል ማለት ነውና፣ ንግድ ምክር ቤቱ በዚህ አዋጅ ይመዝገብ መባሉ አግባብ አለመሆኑን አስታውቀው ይህ አንቀጽ መሻሻል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

በዓርብ ዕለቱ የምክክር መድረክ ሊሻሻሉ ይገባል ከተባሉ የረቂቅ አዋጁ አንቀጾች ውስጥ በማመልከቻው ላይ ከሚሰጥ ውሳኔ ጋር በተያያዘ የተዘረዘሩት አንቀጾች ናቸው፡፡ የምዝገባ ጥያቄ ውድቅ በመደረጉ የሚቀርብ ቅሬታ ስለሚስተናገድበት ሁኔታ የሚገልጸው ምንም ነገር ባለመኖሩ፣ የቅሬታ አቅራቢዎችን መብት ሊያጣብብ የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጥርና ተፅዕኖም ሊያሳድር ይችላል ተብሏል፡፡

የንግድ ምዝገባ ማመልከቻ ላይ የሚሰጡ ውሳኔዎችን በሚመለከተው አንቀጽ ውስጥ ሊሻሻል ይገባል የሚል ሐሳብ ተሰንዝሯል፡፡ ይህም የንግድ ምዝገባ ማመልከቻ ላይ የሚሰጥበት ውሳኔ ላይ ቅሬታ የሚስተናገድበት ሥርዓት ያለመቀመጡ አግባብ በመሆኑ ይህ ሊሻሻል ይገባል ተብሏል፡፡

እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ በረቂቅ አዋጁ የንግድ ምዝገባ ማመልከቻው ውድቅ የሚሆንበት ሁኔታ መኖሩን ስለሚገልጽ፣ ጥያቄው ያላግባብ ውድቅ ከተደረገ ይህ ሊስተናገድ የሚችልበት አንቀጽ ያስፈልገዋል ተብሏል፡፡ መሻሻል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የንግድ ሥራ ፈቃድ ስለማውጣት ‹‹በተደነገገው ውስጥም የማምረት ወይም የማስመጣት የንግድ ሥራ ፈቃድ ያላቸው ያመረቷቸውን ወይም ያስመጧቸውን ምርቶችንና ዕቃዎችን ብቻ ቀደም ብለው ባስመዘገቡት የንግድ ሥራ አድራሻ በጅምላና በችርቻሮ ለመሸጥ ተጨማሪ የንግድ ፈቃድ እንዲያወጡ አይገደዱም፤›› የሚል አንቀጽ ተቀምጧል፡፡ የሌላው አንቀጽ ላይ ደግሞ የአምራች ወይም የአስመጪ የንግድ ሥራ ፈቃድ ያላቸው ነጋዴዎች ላመረቷቸው ወይም ላስመጧቸው ምርቶችና ዕቃዎች የችርቻሮ ንግድ ፈቃድ መውሰድ አይችሉም፡፡ ሆኖም በጅምላ መሸጥ የማይቻሉ ምርቶችንና ዕቃዎችን በችርቻሮ እንዲሸጡ ሚኒስቴሩ ዝርዝር መመርያ ያወጣል ይላል፡፡ ስለዚህ ይህ በግልጽ መቀመጥ እንዳለበት ባለቤቶቹ ገልጸዋል፡፡

ይህ አዋጅ በሚሸፍናቸው የንግድ ሥራዎች ለሚሰጡ ፈቃዶች ሊሟሉ የሚገባቸውን የብቃት ማረጋገጫ መሥፈርቶች አግባብነት ያለቸው የሴክተር መሥሪያ ቤቶች በመመርያ ይወስናሉ፡፡

በዚህ አዋጅ ድንጋጌዎች፣ ደንቦችና ንግድ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመርያ መሠረት የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ለመስጠት ሥልጣን የተሰጣቸው የመንግሥት አካላት የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ይሰጣሉ፡፡ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ለአንዳንድ የንግድ ሥራ ፈቃድ መስጫ መደቦች እንደቅድመ ሁኔታ ባይጠየቅም፣ ብቃትን ለማረጋገጥ ሥልጣን የተሰጣቸው የመንግሥት አካላት ለንግድ ሥራ ፈቃዱ የሚፈለገውን የብቃት ማረጋገጫ መስፈርት መሟላቱን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡

ከንግድ ምክር ቤቱ ባለሙያዎች ረቂቅ አዋጅ ማስተካከያ ሊያደርግበት ይገባል ያሉት ሌላው አንቀጽ ደግሞ፣ አንድ የንግድ ምዝገባ ሲደረግ አገር አቀፍ በሆነ ጋዜጣ ላይ ማሳወቅ አለበት የሚለው ነው፡፡ በተለይ የንግድ ማኅብራት ምዝገባቸውን ለማጽናት የግድ በጋዜጣ ማሳወቅ እንዳለባቸው፣ ሲሰረዝም በራሳቸው ወጪ ምዝገባው መሰረዙን የሚገልጽ ማስታወቂያ ማስነገር እንዳለባቸው የተቀመጠው አዲስ ድንጋጌ ፈጽሞ መሆን የሌለበት ነው ተብሏል፡፡

እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ ይህ አንቀጽ አስፈላጊ አይደለም ብለው ያስቀመጡት ምክንያት፣ ከዚህ ቀደም ተሞክረው ያልጠቀሙና ነጋዴውን ለወጪ የሚዳርጉ በመሆናቸው ነው፡፡

በአንድ በኩል መንግሥት የንግድ ምዝገባውን ዘመናዊ እያደረገ በመሆኑ የተመዘገቡና የተሰረዙ ድርጅቶችን ማወቅ የሚቻል በመሆኑም አንቀጹ መውጣት አለበት የሚል አቋማቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ በጋዜጣ አሳውጁ መባሉም ጊዜ ያለፈበት ነው ተብሏል፡፡

የብቃት ማረጋገጫ የሚመለከተው አንቀጽ አሁንም መሻሻል ይኖርበታል ተብሏል፡፡ በብቃት ማረጋገጫ ዙሪያ የተወሰኑ ዘርፎች ማረጋገጫ ያስፈልጋቸዋል የሚል በመሆኑ የትኞቹ ማረጋገጫ እንደሚያስቸልጋቸው የትኞቹ እንደማያስፈልጋቸው መለየት አለበት፡፡ ከዚህ በላይ ግን መሆን የሚገባው የብቃት ማረጋገጫ ሳያስፈልግ ፈቃዱ ተወስዶ የማረጋገጡ ሥራ ነጋዴው ሥራ ከጀመረ በኋላ መሆን አለበት የሚል ሐሳብ ተሰንዝሯል፡፡ ከተወያዮቹም ሐሳብ የተሰነዘረ ሲሆን፣ በውይይቱ የተገኘው ነጥብ ለንግድ ሚኒስቴር ይሰጣል ተብሏል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች