Wednesday, October 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በርካታ ነጋዴዎች ገቢያቸውን እያሳወቁ አይደሉም አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን 52 በመቶ ነጋዴዎች ገቢያቸውን እያሳወቁ ባለመሆኑ ምርመራ እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡ ገቢያቸውን አሳውቀው ግብር የማይከፍሉ ነጋዴዎች ከመበራከታቸውም በላይ ያለደረሰኝ ሽያጭ የሚያከናወኑ፣ ሕጋዊ ደረሰኝ የማይጠቀሙና ‹‹ጉዳይ አስፈጻሚ›› ደላሎች ችግር እንደሆኑበት ባለሥልጣኑ ገልጿል፡፡

ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መጋቢት 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ባካሄደው ውይይት ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ ደስታ በዛብህ እንደገለጹት፣ 52 በመቶ የሚሆኑ ነጋዴዎች ገቢያቸውን አሳውቀው ግብር እየከፈሉ አይደሉም፡፡

‹‹ከተቀሩት 48 በመቶ ነጋዴዎች ውስጥም ቢሆን ገቢያቸውን በትክክል እያሳወቁ አይደሉም፤›› በማለት አቶ ደስታ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ሕጋዊ ያልሆኑ ‹‹ጉዳይ አስፈጻሚዎች›› ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ በመምጣታቸው፣ ከዚህ በኋላ ሕጋዊ ውክልና የማያቀርቡ ‹‹ጉዳይ አስፈጻሚዎች››ን እንደማያስተናግዱ ገልጸዋል፡፡

ሕጋዊ ባልሆነ ደረሰኝ የሚፈጸም ግብይት ለማስቀረት ባለሥልጣኑ ሚስጥራዊ ኮድ ያለው ደረሰኝ እንደሚያሳትም፣ ኅትመቱንም ሕጋዊ ማተሚያ ቤቶች እንዲሠራ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ያለደረሰኝ የሚፈጸም ግብይት መኖሩን አብነት ጠቅሰው አብራርተዋል፡፡

አቶ ደስታ እንደገለጹት፣ በመጋቢት ወር 2008 ዓ.ም. ብቻ ባለሥልጣኑ በአዲስ አበባ ከተማ ባካሄደው ድንገተኛ ዘመቻ ያለደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ የተገኙ 120 ነጋዴዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

ዘመቻው 85 የንግድ ተቋማት ላይ ያነጣጠረ መሆኑን፣ ከ85 ንግድ ተቋማት 77 የሚሆኑት ያለደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ መገኘታቸውን፣ በዚህ ምክንያት 120 ነጋዴዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አቶ ደስታ ተናግረዋል፡፡

አቶ ደስታ ዘመቻው የተካሄደው በትልልቅ ጅምላ ነጋዴዎች፣ አስመጪዎችና አምራች ኩባንያዎች ላይ መሆኑን ገልጸው፣ በትልልቅ ተቋማት ችግሩ በስፋት መኖሩ አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡ አቶ ደስታ ሕገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል የተባሉትን አካላት ለጊዜው ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

አቶ ደስታ እንደሚሉት፣ ከእነዚህ ጉዳዮች በተጨማሪ ባለሥልጣኑ ተመላሽ ሒሳብና የገንዘብ መቀበያ ማሽን አሠራሮች ላይ ማሻሻያ አድርጓል፡፡ የገቢ ግብር አዋጅና የታክስ አስተዳደር አዋጅ በዚህ ዓመት ለመንግሥት ቀርበው እንደሚፀድቁ ተገልጿል፡፡

የገቢ ግብር አዋጅ በየጊዜው የሚሻሻል ባለመሆኑ በደንብ ተጠንቶ መዘጋጀት እንዳለበት፣ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና በውጭ አማካሪ ኩባንያ አማካይነት ጥናት ተደርጎ አዋጅ መዘጋጀቱን አቶ ደስታ ጨምረው ተናግረዋል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች