Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሐዋሳ ኤርፖርት በከፊል ሥራ ሊጀምር ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የደቡብ ክልል መናገሻ በሆነችው ሐዋሳ ከተማ በ457 ሚሊዮን ብር የሚያስገነባው ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በከፊል አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው፡፡

የኤርፖርት ግንባታው ከ14 ወራት በፊት የተጀመረ ሲሆን፣ ግንባታውን የሚያካሂደው አገር በቀል ኩባንያ የሆነው ዮቴክ ኮንስትራክሽን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ወንድም ተክሉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ፕሮጀክቱ ሦስት ኪሎ ሜትር የአውሮፕላን መንደርደሪያ፣ የአውሮፕላን መዞሪያ (Taxi way)፣ የአውሮፕላን ማቆሚያና የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ያካትታል፡፡ ከዚህ ውስጥ ዮቴክ የአውሮፕላን ማኮብኮቢያ፣ ማዞሪያና ማቆሚያ ግንባታውን በማካሄድ ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ወንድም፣ የፕሮጀክቱ 85 በመቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ ሦስት ኪሎ ሜትር ርዝመት ካለው መንደርደሪያ ግንባታ ውስጥ ሁለት ኪሎ ሜትር መጠናቀቁን የተቀረው አንድ ኪሎ ሜትር በሁለት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል፡፡

የአውሮፕላን ማረፊያው እንደ ቦይንግ 777 ያሉ ግዙፍ አውሮፕላኖች ማሳረፍ የሚችል ሲሆን፣ ሁለት ኪሎ ሜትር የአስፋልት ኮንክሪት በሁለት ዙር ለብሷል፡፡ የሁለት ኪሎ ሜትር ግንባታ ሙሉ በሙሉ የተጠናቀቀ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ በረራ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቦምባርደየር ኪው 400 አውሮፕላኖች በተገቢው ሁኔታ መነሳትና ማረፍ እንደሚችሉ ተረጋግጧል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሃና አጥናፉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አየር መንገዱ ወደ ሐዋሳ በሳምንት አራት ቀናት በኪው 400 አውሮፕላኖች የበረራ አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ ነው፡፡ ዝግጅቱ ከተጠናቀቀ አየር መንገዱ ሚያዝያ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በረራውን ለመጀመር ማቀዱን ወይዘሮ ሃና ተናግረዋል፡፡

ከአዲስ አበባ በስተደቡብ 273 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የሐዋሳ ከተማ ዘመናዊ ሆቴሎች ያሏትና በመዝናኛነት የምትታወቅ ሲሆን የቱሪስት መናኸሪያ ናት፡፡ የኤርፖርቱ ግንባታ ያልተጠናቀቀ ቢሆንም ከፍተኛ የሆነ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ፍላጎት ያለ በመሆኑ፣ ኤርፖርቱ በቅርቡ በከፊል አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ከአቶ ወንድም ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የመንገደኞች ተርሚናል ሕንፃ ዲዛይን ሥራ መጠናቀቁን የገለጹት አቶ ወንድም፣ የግንባታ ሥራውን የሚያካሂድ ኮንትራክተር ለመቅጠር ጨረታ እንደሚወጣ ጠቁመዋል፡፡

የሐዋሳ ኤርፖርት ከመንገደኞች በረራ አገልግሎት በተጨማሪ የጭነት (Cargo) በረራዎችን እንዲያስተናግድ ታስቦ መገንባቱን አቶ ወንድም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሐዋሳ ለአግሮ ኢንዱስትሪ ዞን ከተመረጡ ከተሞች አንዷ እንደመሆኗና የኢንዱስትሪ ፓርክም የተገነባ በመሆኑ፣ የኤርፖርቱ ግንባታ እነዚህን የኢኮኖሚ አውታሮች ልማት ታሳቢ ያደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት መጠነ ሰፊ የኤርፖርቶች ማስፋፊያና ግንባታ ፕሮጀክቶች በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት የመንገደኞች ተርሚናልን በ350 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማስፋፋት ላይ ነው፡፡ በጂንካ፣ በሮቤ፣ በሰመራና በሽሬ የአውሮፕላን ማረፊያ ሜዳዎች በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ነቀምት ከተማ ዘመናዊ ኤርፖርት ለመገንባት ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ የቦታ መረጣ ሥራ ተጠናቆ ግንባታውን የሚያካሂደው የመከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅት የክሬሸር ማሽኖች በመትከል ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት 20 ኤርፖርቶች ያስተዳድራል፡፡ 14 ያህሉ የአስፋልት አውሮፕላን ማረፊያ ያላቸው ናቸው፡፡ አራቱ ደግሞ ዓለም አቀፍ ኤርፖርቶች ናቸው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች