Tuesday, April 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየቀድሞ የጋምቤላ ፕሬዚዳንት የአገሪቱን የፖለቲካና የግዛት አንድነት በመንካት ወንጀል ጥፋተኛ ተባሉ

የቀድሞ የጋምቤላ ፕሬዚዳንት የአገሪቱን የፖለቲካና የግዛት አንድነት በመንካት ወንጀል ጥፋተኛ ተባሉ

ቀን:

– ተጠርጥረው የተከሰሱበት የሽብር ድርጊት ወንጀል ውድቅ ተደረገ

የጋምቤላን ክልል እስከ 1996 ዓ.ም. ድረስ በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ የነበሩትና የሽብርተኝነትን ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ሰኔ 4 ቀን 2006 ዓ.ም. ክስ ተመሥርቶባቸው ሲከራከሩ የከረሙት አቶ ኦኬሎ አኳይ፣ የተከሰሱበት የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 ወደ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 214 ተቀይሮ፣ የአገሪቱን የፖለቲካና የግዛት አንድነት በመንካት ወንጀል መጋቢት 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ጥፋተኛ ተባሉ፡፡ አቶ ኦኬሎ የኖርዌይ ዜግነት አላቸው፡፡

የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋሕነን) እና የጋምቤላ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋዴን) በመባል የሚጠሩ ድርጅቶች አመራርና ታጣቂ በመሆን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በሽብር ጥቃት በማፍረስ የጋምቤላን ክልል ከፌዴሬሽን የመገንጠል ፖለቲካዊ ግብ በማስቀመጥ መንቀሳቀሳቸውን በመጥቀስ፣ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ሲመረምረው ከርሟል፡፡ ተከሳሾቹ አቶ ኦኬሎ አካይ፣ ዴቪድ ኡጁሉ፣ ኡቻን ኦፒዬ፣ ኡማን ኝክየው፣ ኡጁሉ ቻም፣ አታካ ኡዋርና ኡባንግ ኡመድ ናቸው፡፡ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተባቸውን የሽብርተኝነት ክስ እንዳልፈጸሙና ጥፋተኛ እንዳልሆኑ ክደው በመከራከራቸው፣ ዓቃቤ ሕግ ክሱን የሚያስረዱለት ምስክሮች አቅርቧል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የዓቃቤ ሕግን ምስክሮች ቃልና የሰነድ ማስረጃ ከሕጉ ጋር በማገናዘብ የመረመረው ፍርድ ቤቱ፣ ሁሉም ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን በመስጠት መጀመሪያ የተከሳሽነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

አቶ ኦኬሎ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዱት፣ የሰው ምስክር የላቸውም፡፡ የተከሰሱበት ጉዳይ አይመለከታቸውም፡፡ ከግንቦት ሰባት አባላት ጋር መገናኘትም ወንጀል ሊሆን እንደማይችል አስረድተዋል፡፡ ሌሎቹም ተከሳሾች ክሱ እንደማይመለከታቸውና ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን በወ/መ/ሥ/ሥ/ቁ/142(3) መሠረት የተከሳሽነት ቃላቸውን ሰጥተው፣ አብረዋቸው ታስረው የነበሩ በምርመራ ወቅት መደብደባቸውንና ለፖሊስ የሰጡት ቃል በግዳጅ መሆኑን የሚያስረዱላቸው የመከላከያ ምስክሮችን ቆጥረው አስመስክረዋል፡፡

ተከሳሾቹ ፈጽመውታል ተብሎ በዓቃቤ ሕግ በኩል በክስ አቤቱታ ዝርዝር ውስጥ የተጠቀሱት ክሶችና ከተሰማው የሰው ምስክርነትና የሰነድ ማስረጃ ጋር ተደምሮ፣ አግባብነት ካላቸው የአገሪቱ ሕጐች ጋር በመመርመር፣ የተፈጸመው የወንጀል ተግባር በፀረ ሽብር የሕግ ማዕቀፍ ሥር ሊወድቅ ይችላል ወይስ በመደበኛው የወንጀል ሕግ ማዕቀፍ ሥር የሚወድቅ ነው? የሚለው መታየት እንዳለበት ፍርድ ቤቱ ማመኑን ገልጾ፣ መዝገቡን መመርመሩን አስታውቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ የተቋቋመበትን ዓላማና ዝርዝር ድንጋጌዎቹን ተከሳሾቹ ፈጽመዋቸዋል ከተባለው የወንጀል ተግባር ድርጊትና በተጠቀሰባቸው አንቀጽ ሲመረምረው፣ ፈጽመውታል የተባለው የወንጀል ድርጊት ግራ ቀኙ ካቀረቧቸው ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች አንፃር የሽብር ወንጀል ድርጊትን የሚያቋቁም ሆኖ እንዳላገኘው ገልጿል፡፡

ተከሳሾቹ የጋምቤላ ሕዝብ ጭቆና ደርሶበታል በሚል መነሻ በአቶ ኦኬሎና ዴቪድ ኡጁሉ አመራር የጋምቤላን ክልል በትጥቅ ትግል ከፌዴሬሽኑ ለመገንጠል ተደራጅተውና አደራጅተው፣ ወታደር መልምለውና አሠልጥነው በማስታጠቅ፣ መንግሥትን ለመውጋት የተዘጋጁ መሆኑን የዓቃቤ ሕግ ክስ እንሚያስረዳ ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ተከሳሾች ፈጸሙት የተባለው የወንጀል ድርጊት ግን ሽብርን የሚያቋቁም ሳይሆን፣ የአገሪቱን የፖለቲካና የግዛት አንድነት በኃይልና በጦርነት፣ ሕገ መንግሥቱን በሚፃረር መንገድ በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር፣ ከፌዴሬሽኑ አንዱን ክፍል መገንጠልን መሠረት ያደረገ የወንጀል ድርጊትን ለመፈጸም መንቀሳቀሳቸውን የሚያሳይ መሆኑንም ፍርድ ቤቱ አብራርቷል፡፡

በመሆኑም ድርጊታቸው ከጥርጣሬ ውጪ የሚያሳይ ነገር ስለሌለው የሽብር ወንጀል ድርጊቱን የማያሟላና በጅምር የቀረ በመሆኑ፣ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 241 ሥር የሚወድቅ መሆኑን በመግለጽ በወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 149(1) መሠረት ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡ የቅጣት አስተያየት ለመቀበል ለሚያዝያ 17 ቀን 2008 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የወንጀል ሕግ አንቀጽ 241 ማለትም ማንም ሰው በኃይል ወይም በማናቸውም ሕገ መንግሥትን በሚፃረር መንገድ በቀጥታ ወይም በእጅ አዙር የአገሪቱ ሕዝቦች አንድነት እንዲፈርስ ወይም ፌዴሬሽኑ እንዲገነጠል ያደረገ ከሆነ፣ ከ10 እስከ 25 ዓመታት በሚደርስ ጽኑ እስራት ወይም ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜ እስከ ዕድሜ ልክ እስራት ወይም በሞት ሊያስቀጣ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...