ቀረጥ ሳይከፈልባቸው ወደ አገር ውስጥ የገቡ ሞባይልን ጨምሮ ተንቀሳቃሽ የቴሌኮም መገልገያ መሣሪያዎችን ከአገልግሎት ለማስወጣት የሚያስችለውን የመገልገያ ቁሶች ምዝገባ፣ ኢትዮ ቴሌኮም በሚቀጥለው ሳምንት ሊጀምር መሆኑ ተሰማ፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መመርያ መሠረት ምዝገባውን ሊያካሂድ መሆኑን ሪፖርተር ያገኛቸው መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት የሚጀመረው ምዝገባ የሙከራ ሲሆን፣ ቅድሚያ የሚያደርገውም በራሱ ሠራተኞች ላይ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ደንበኞች ወደ ኢትዮ ቴሌኮም ሳይሄዱ ምዝገባውን ባሉበት በማንኛውም ቦታ ሆነው ማካሄድ የሚያስችለው ቴክኖሎጂ ባለቤት መሆኑ ታውቋል፡፡
ይህ ቴክኖሎጂ “Equipment Identity Registration (EIR)” የሚል መጠሪያ ያለው ሲሆን፣ ደንበኞች ሲም ካርድ በሚቀበሉ የመገልገያ ቁሶቻቸው ውስጥ የኢትዮ ቴሌኮምን ሲም ካርድ በከተቱበት ፍጥነት፣ የመገልገያ ቁሱን ዓይነትና መለያ ቁጥር ወደ ኢትዮ ቴሌኮም የመረጃ ቋት የሚያስገባ ቴክኖሎጂ ነው፡፡
በመሆኑም መረጃውን ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን መረጃ ጋር በማገናዘብ ቀረጥ ተከፍሎበት ወደ አገር ውስጥ የገባ ስለመሆኑ ማጣሪያ ከተደረገ በኋላ፣ ቀረጥ ያልከፈለ ሆኖ ከተገኘ ሲም ካርዱን መቆለፍና የመገልገያ ቁሱ የኢትዮ ቴሌኮምን ኔትወርክ እንዳይጠቀም ማድረግ የሚያስችለው ነው፡፡
በዚሁ መሠረት ኢትዮ ቴሌኮም ምዝገባውን በደንበኞቹ ላይ ከመጀመሩ አስቀድሞ፣ የራሱ ሠራተኞች የቴሌኮም አገልግሎት መቀበያ ቁሶችን ለመመዝገብ አቅዷል፡፡
በዚህ መሠረትም ሠራተኞቹ እስከ መጪው ሚያዝያ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ሞባይል፣ አይፓድ፣ ገመድ አልባ ዋይፋይ ራውተር፣ ታብሌቶችና ሌሎች ሲም ካርድ በሚቀበሉ መገልገያ መሣሪያዎቻቸው ውስጥ ሲም ካርድ ማኖር እንደሚጠበቅባቸው አሳስቧል፡፡
ይህንን ተግባር ወደ የኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች የማስፋፋት ሥራ በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት ይከናወናል ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዱዓለም አድማሴ ለሪፖርተር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ታክስ ሳይከፍሉ አገር ውስጥ የገቡ መገልገያዎችን ከመቆጣጠር በተጨማሪ፣ ተመሳስለው የተሠሩ ቀፎዎችን ከአገልግሎት ውጪ ለማድረግና የተሰረቁ ቀፎዎችን ለመዝጋት ቴክኖሎጂው ጥቅም ይኖረዋል፡፡
ዓርብ መጋቢት 30 ቀን 2008 ዓ.ም. የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮ ቴሌኮምና ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በዝግ ውይይት ሲያደርግ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
የዚህ ውይይት ዓላማ የቴሌኮም መገልገያ ቁሶቹን የመመዝገብ ሥራ በኢትዮ ቴሌኮም የሚከናወን ቢሆንም፣ የቁጥጥር ሥራው በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሥር ይሁን ወይስ በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሥር ይሁን የሚለውን ለመለየት መሆኑን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በቅርቡ በጉዳዩ ላይ መግለጫ እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡