– ምርመራው ከአትሌቶቹ ባለፈ ወደ ማናጀሮችና አመራሮች ሄዷል
– አሁንም ለመቆመር የሚሞክሩ አትሌቶች መኖራቸው ተጠቆመ
– መንግሥት የፅዕ መመርመሪያ ላቦራቶሪ ለማቋቋም ቢፈልግም ወጪው ከአቅም በላይ ሆኖበታል
የተከለከለ አበረታች ንጥረ ነገር ተገኝቶባቸዋል ተብለው ከተጠረጠሩት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መካከል የተወሰኑት፣ ዕቀባ ለተጣለባቸው ዕፆች ባወጡት ወጪ ምክንያት ለኪሳራ በመዳረጋቸውና ገንዘብ በማጣታቸው ለችግር መጋለጣቸውን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ሬድዋን ሁሴን መጋቢት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 21ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ወቅታዊ ጉዳዮችን በሚመለከት ከአባላቱ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ በተገኙበት ወቅት፣ መንግሥት ለአትሌቶቹ ሰለባ መሆን በዋና ተጠያቂነት የሚጠረጠሩትን የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ወኪሎች እንዴት ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ እንደቻሉ መረጃ እንዳልነበረው ገልጸዋል፡፡
ዋና ተጠርጣሪ የሆኑት የውጭ ዜግነት ያላቸው ወኪሎች ቢሆኑም፣ አትሌቶቹን ለጉዳት ዳርገዋል በተባሉ ተጠርጣሪ ኢትዮጵያውያን ላይም ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡ የምርመራው ሒደት አሠልጣኞችን፣ ማናጀሮችን፣ ኤጀንቶችንና የአመራር አባላትንም እንደሚጨምር ጠቁመዋል፡፡
ነገር ግን የአመራር አባላቱ ያሏቸው እነማን እንደሆኑ ዘርዝረው ባይገልጹም፣ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን አካባቢ ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡
የአነቃቂው ዕፅ ሰለባዎቹን ማንነትንም ሆነ አጠቃላይ ተጠርጣሪዎችን ብዛት ከመግለጽ ቢቆጠቡም፣ አብዛኞቹ አትሌቶች ‹‹የሚያስቆጩና ለአገር ብዙ ድሎች ማስመዝገብ የሚችሉ ተስፋ ያላቸው›› ወጣቶች እንደነበሩ ሚኒስትሩ በቁጭት ተናግረዋል፡፡
‹‹የዚህ ችግር ሰለባ ከሆኑት ተጠርጣሪ አትሌቶች የተወሰኑት ነፃ መሆናቸው ቢረጋገጥም፣ የቀሩት አትሌቶች ብዙ ድል ማስመዝገብ የሚችሉ እንደነበሩ፣ እንዲያውም ከዚህ በፊት በማራቶን 2 ሰዓት ከ04 ደቂቃ ጊዜ ማስመዝገብ የቻሉም ጭምር ነበሩበት፤›› ብለዋል፡፡
በዓለም አቀፍ የፀረ አበረታች ዕፅ ኤጀንሲ (ዋዳ) ለአትሌቶች ክልክል ተብለው የተቀመጡት ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገሮች በስፖርቱ ዓለም መጠቀም ከሚያስከትለው ከፍተኛ ቅጣትና ቀውስ ባሻገር፣ በአትሌቶች ላይ የሚያደርሰው የጤና ጉዳትን አስመልክቶ በመንግሥትም ሆነ በሌሎች አካላት አስፈላጊው ትምህርት ባለመሰጠቱ፣ አትሌቶቹ ለዚህ ችግር መጋለጣቸውን እንደ ዓብይ ምክንያት አውስተዋል፡፡
የሰሞኑ ችግር በጣም ሰፊና ከባድ የሚባል ዓይነት መሆኑን በመጥቀስ ለምክር ቤቱ አባላት ያስረዱት አቶ ሬድዋን፣ ‹‹አገራችን ዓለም አቀፉን የፀረ አበረታች ዕፅ ስምምነት ከፈረመች 11 ዓመታት ገደማ ቢሆናትም፣ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የሚፈለገውን የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ባለመሥራታችን ችግሩ ተከስቷል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
ለአትሌቶቹ የሚያስፈልገው ግንዛቤ ባለመድረሱ መንግሥት ‹‹በከፊል›› ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃንም ሆኑ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ያህል የግንዛቤ ማስጨበጫ አስተዋጽኦ አለማድረጋቸውን አክለዋል፡፡
ምንም እንኳ ኃይል ሰጪ ወይም አበረታች ንጥረ ነገር ያለባቸው የመድኃኒት ዓይነቶች ለሁሉም ሰዎች ክልክል መሆናቸውን የሚደነግግ ሕግ ባይኖርም፣ በስፖርቱ ዘርፍ ግን በጥብቅ የተከለከሉ ናቸው ብለዋል፡፡ ማንኛውም አትሌት እነዚህን ንጥረ ነገሮች ተጠቅሞ ተገኘ ማለት በሌላው ዘርፍ ልክ እንደተከለከለ ሕገወጥ አደንዛዥ ዕፅ ይዞ የተገኘ ያህል ይቆጠራል ሲሉ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያውያኑን አትሌቶች የተከለከለውን ዕፅ እንዲወስዱና ለአሁኑ ጉዳት ዳርገዋቸዋል ያሏቸውን የውጭ አገር ዜግነት ያላቸውን ኤጀንቶች ‹‹ሰው የመግደል ያህል›› ወንጀል አድርሰውባቸዋል ብለዋል፡፡ አትሌቶቹ ወስደዋቸዋል የተባሉት የዕፅ ዓይነቶች በስፖርቱ እንደ ወንጀል ከመቆጠራቸውም በላይ ለጤናም አደገኛ እንደነበሩ ያስረዱት አቶ ሬድዋን፣ ‹‹አንዳንዶቹ የዕፅ ዓይነቶች ሴትን ወደ ወንድነት የመቀየር ኃይል አላቸው፤›› ሲሉም ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡
ይህ የሰሞኑ ቀውስ በዚህ ደረጃ መነጋሪያ በሆነበት ወቅት አሁንም ‹‹ቁማር የሚቆምሩ›› አትሌቶች እንዳሉም ሚኒስትሩ ሳይናገሩ አላለፉም፡፡
እየቆመሩ ነው ያሏቸውን አትሌቶች በየትኞቹ ውድድሮች የሚሳተፉ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ባይገልጹም፣ መንግሥት ከፍተኛ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ከመሥራቱ ጎን ለጎን የአገሪቱ የፀረ አበረታች ዕፅ ተቋም የክትትልና የቁጥጥር ሥራውን እንደሚያጠናክር ግን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቶች ከተከለከሉ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገሮች ጋር መያያዝ የሰሞኑ ክስተት የመጀመሪያው አለመሆኑን ያስታወሱት አቶ ሬድዋን፣ ‹‹ከቀደምት አትሌቶች ተገቢውን ትምህርት ባለመውሰዳችን ነው እነዚህ አትሌቶች ሰለባ የሆኑት፤›› በማለት በመንግሥት በኩል የነበረውን ድክመት ገልጸዋል፡፡
አበረታች ዕፁ ተገኝቶባቸዋል የተባሉት አትሌቶች ለዕፁ ግዥ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያወጡ የጠቆሙት አቶ ሬድዋን፣ ‹‹አንድ አትሌት ለአንዴ መግዣ ብቻ በትንሹ ከ18 ሺሕ እስከ 30 ሺሕ ብር ያወጣል፡፡ አትሌቱ ዕፁን ቢያንስ እስከ ስድስት ጊዜ ያህል ለመዋጥ ይገደዳል፤›› በማለት አትሌቶቹ የሚያወጡት ወጪ ቀላል አለመሆኑን አመልክተዋል፡፡ ‹‹በዚህም የተነሳ የዕፁ ሰለባ የሆኑት አትሌቶች በአሁኑ ወቅት ምንም ስለሌላቸው ባዶ እጃቸውን ቀርተዋል፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ከግንዛቤ ማስጨበጫ ጎን ለጎን የዕፅ መመርያ ላቦራቶሪ በአገር ውስጥ በማቋቋም አትሌቶችን ሌላ አገር ወስዶ ለማስመርመር የሚወጣን ወጪ ማስቀረት እንደሚቻል አውስተዋል፡፡
ነገር ግን ላቦራቶሪውን ለማቋቋም እስከ 28 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠይቅ በመሆኑ ለአገሪቱ ፈታኝ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ በሒደት የሚቻል ከሆነ መንግሥት እንደሚገፋበት፣ በሌላ በኩልም ባለሀብቶች ማቋቋም የሚችሉም ከሆነ እንደ አማራጭ ይታያል ብለዋል፡፡
‹‹በተለይ በአፍሪካ ምንም ላቦራቶሪ የለም፡፡ ደቡብ አፍሪካ ቀድሞ የነበራት ቢሆንም በዓለም አቀፍ ተቋም ማዕቀብ ተጥሎበታል፡፡ ስለዚህ እኛ አገር ማቋቋም ብንችል ከራሳችን አትሌቶች አልፎ ለሌሎች የአፍሪካም ሆነ የሌሎች አኅጉሮች አትሌቶች አገልግሎት በመስጠት ለአገር ኢኮኖሚ ተጨማሪ ምንዛሪ ማስገኘት እንደሚቻል ከግምት በማስገባት ልንሠራ ይገባል፤›› ብለዋል አቶ ሬድዋን፡፡
በሌላ በኩል የመልካም አስተዳደርና የሙስና ችግር ከሚታዩባቸው የስፖርቱ ዘርፎች ውስጥ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዋናው መሆኑን፣ መጠኑ ይነስ እንጂ በእግር ኳሱም ያልተቀረፉ ችግሮች እንደነበሩ አቶ ሬድዋን ከምክር ቤት አባላት ለተነሳላቸው ጥያቄ በአዎንታ መልሰውታል፡፡
በአትሌቲክስ በኩል አሉ የተባሉ ችግሮችን ለመፍታት በተለይ በአመራር በኩል ያሉ የትምህርትና አግባብነት ጉዳይን ለማስተካከል ጥረት እንደተደረገ ቢገልጹም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ችግሩ እየተባባሰ የመጣው የቴኳንዶ ስፖርት እንደሆነ ሚኒስትሩ አመልክተዋል፡፡ እንደ አትሌቲክሱ ፌዴሬሽን ሁሉ ለቴኳንዶውም ከስፖርቱ ጋር ፈጽሞ ትውውቅም ሆነ ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች ወደ ውጭ አገር በመሄድ እንዲቀሩ በማድረግ፣ የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግር መንሰራፋቱን ሚኒስትሩ በተለይ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
በስፖርተኞች ስም እንዲላኩ የተደረጉ ሰዎች ሄደው የቀሩበት አግባብ በፌዴሬሽኑ በኩል ምርመራ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡