Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበኦሮሚያ ለግጭት ምክንያት የነበረው የከተሞች አዋጅ ሦስት አንቀጾች ተሰረዙ

በኦሮሚያ ለግጭት ምክንያት የነበረው የከተሞች አዋጅ ሦስት አንቀጾች ተሰረዙ

ቀን:

በኦሮሚያ ክልል ሕዝባዊ ጥያቄ የተነሳበት የከተሞች አዋጅ ሦስት አንቀጾች ተሰረዙ፡፡ እነዚህ አወዛጋቢ የተባሉ አንቀጾች ከተሰረዙ በኋላ ባለፈው ሳምንት የተሰበሰበው ጨፌ ኦሮሚያ አዋጁን አፅድቋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል ተነስቶ ለነበረው ረብሻ የአዲስ አበባና ዙሪያዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የጋራ ማስተር ፕላንና የኦሮሚያ ከተሞች አዋጅ ምክንያት እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የማስተር ፕላኑን ተግባራዊነት ማቆሙን በወቅቱ በይፋ የገለጸ ሲሆን፣ ለውዝግቡ መባባስ ምክንያት የነበሩ የኦሮሚያ ከተሞች አዋጅ ሦስት አንቀጾች እንዲሰረዙ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

የተሰረዙት ሦስት አንቀጾች ከተሞችን መቀላቀል፣ የተቀላቀሉ ከተሞች ስያሜና ራዲዮ ፖሊ (የክልሉን ትልልቅ ከተሞች በተመለከተ) የሚያትቱ ናቸው፡፡ የኦሮሚያ ከተሞች አዋጅ አንድ የክልሉ ከተማ በዙሪያው ካሉት አነስተኛ ከተሞችን (ሳተላይት) በመያዝ እንደ አዲስ ይደራጃል ይላል፡፡

ለፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የሆነው የኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ ያሉ ከተሞችን ከአዲስ አበባ (ፊንፊኔ) ጋር ለመቀላቀል ነው የሚሉ ግምቶችን ከተለያዩ ወገኖች በመስጠቱ ነው ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል የክልሉ ከተሞች ሲቀላቀሉ አንድ ስም የግድ ይመርጣሉ፡፡ ይህ ሁኔታ የክልሉን ታሪክና ባህል ያጠፋል፣ ልዩ ዞኑን ከአዲስ አበባ ጋር ለመቀላቀል ያለመ ነው የሚል ትንታኔ አሁንም በመስጠቱ ለችግሩ መንስዔ ነው ተብሏል፡፡

በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የራዲዮ ፖሊ ትንታኔ ነው፡፡ የአገሪቱ መዲና አዲስ አበባ የፌዴራል መንግሥት ከተማ ነች፡፡ የክልል ከተሞች ባህር ዳር፣ መቐለ፣ ሐዋሳ፣ ጅማ፣ አዳማና የመሳሰሉት ከተሞች በራዲዮ ፖሊ ምድብ ይገኛሉ፡፡

የፌዴራል መንግሥት ባወጣው የከተሞች ፖሊሲ ራዲዮ ፖሊ ከተሞች ከፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ታቅዷል፡፡

የኦሮሚያ ክልል በከተሞች አዋጅ ላይ ስለ ከተሞቹ የገለጸ ሲሆን፣ ለዚህ ጉዳይ ከተለያዩ ወገኖች የተሰጠው ምላሽ ግን የኦሮሚያ ከተሞች በፌዴራል ሥር ሊገቡ ነው የሚል ነው፡፡ እነዚህ ሦስት ጉዳዮች በኦሮሚያ ተከስቶ ለነበረው ደም አፋሳሽ ግጭት መንስዔ እንደነበሩ ተገልጿል፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊና የካቢኔ አባል አቶ ፈቃዱ ተሰማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሕዝብ ጥያቄ በማንሳቱና የኦሮሚያ መንግሥት ሕዝብ የማይስማማበትን አንቀጾቹን ከአዋጁ ውስጥ ፍቆታል፡፡

አቶ ፈቃዱ ‹‹እነዚህ አንቀጾች ጉዳት ኖሯቸው ሳይሆን ፅንፈኞች በአሉታዊ መንገድ ጉዳዩን እጅግ ያስተጋቡት በመሆኑና እኛ ደግሞ በተገቢው መንገድ ግልጽነት ስላልፈጠርን የተፈጠረው ብዥታ ከፍተኛ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

‹‹እነዚህ ጉዳዮች የሕዝቡን ጥቅም የሚጎዱ ሆነው አይደለም፤›› በማለት ክልሉ ሐሳቡ የሕዝብ እስከሆነ ድረስ የሕዝብን ጥያቄ እንደሚቀበለው አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡

እነዚህ አንቀጾች ከመሰረዛቸው በተጨማሪ በሌሎች ሁለት ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ መደረጉን አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡ ፀድቆ በነበረው የከተሞች አዋጅ የክልሉ ከተሞች የሚሰበስቡትን ፋይናንስ ለራሳቸው ይጠቀማሉ የሚል አንቀጽ ነበር፡፡ ነገር ግን ገቢ የማመንጨት አቅም የሌላቸውን ከተሞች ስለሚጎዳ፣ በማዕከል ደረጃ በጀት ቢከፋፈል የተሻለ መሆኑ ስለታመነበት ማሻሻያ ተደርጓል፡፡

ቀደም ሲል በክልሉ ከተሞች በላይኛው የአስተዳደር እርከንና በቀበሌ መካከል ራሱን የቻለ የመንግሥት መዋቅር አልነበረም፡፡ ቀደም ብሎ ፀድቆ በነበረው አዋጅ የወረዳ መዋቅር እንዲከፈት ተደንግጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ከወረዳ ይልቅ ክፍለ ከተማ የተሻለ መዋቅር ነው ተብሎ ማሻሻያ መደረጉን አቶ ፈቃዱ ገልጸው፣ ትልልቅ ከተሞች የክፍለ ከተማ መዋቅር እንዲመሠርቱ በአዲሱ አዋጅ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...