Thursday, June 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ባንክ የጠቀለለው የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ሠራተኞች በአዲሱ የሥራ ምደባ ላይ ቅሬታቸውን አሰሙ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ባንኩ በሚያስፈልገው ቦታ ሠራተኞች ስለሚመድብ የማይመቸው መልቀቅ ይችላል›› አቶ በቃሉ ዘለቀ የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት

የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ በመንግሥት ውሳኔ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከተጠቀለለ በኋላ፣ ከሁለት ሺሕ በላይ ሠራተኞች በአዲሱ ምደባ ያደረባቸውን ቅሬታ ለንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አሰሙ፡፡

መጋቢት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. መገናኛ አካባቢ በሚገኘው አዲሱ የንግድ ባንክ ህዳሴ ሕንፃ ውስጥ በተካሄደው ስብሰባ፣ ምደባ አላገኘንም ከሚሉ ጥያቄዎች ጀምሮ ባንኩ የቀድሞውን የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ሠራተኞች የሥራ ልምድና የትምህርት ደረጃ ያላገናዘበ የደረጃ ምደባ ማካሄዱን በመቃወም ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ ሪፖርተር ስብሰባውን በተመለከተ ከታማኝ ምንጮች ባገኘው መረጃ መሠረት፣ ወደ ንግድ ባንክ እንዲቀላቀሉ የተደረጉት ሠራተኞች ቀድሞ የነበራቸው የሥራ ደረጃና እርከን በንግድ ባንክ ተቀባይነት ማጣቱ ብቻም ሳይሆን፣ ዝቅተኛ በተባሉ የባንኩ መሥፈርቶች እንኳ ሊስተናገዱ አለመቻላቸው አድሏዊ አሠራር እንዳለበት እንዲገምቱ እንዳስገደዳቸው ተናግረዋል፡፡

ከአምስት ዓመት በላይ በኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ የሥራ ልምድ እንዳላቸው የገለጹ አንድ ሠራተኛ፣ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸውና የስድስት ወራት የሥራ ልምድ ያላቸው በደንበኛ አገልግሎት ኦፊሰርነት በሚመደቡበት ተቋም ውስጥ ከአምስት ዓመታት በላይ የሠሩበት ልምድ ዋጋ የሌለው መሆኑ፣ ‹‹ፍትሐዊ ያልሆነ፣ እንድትወጣ የሚገፋፋና ለሠራተኛውም ንቀት እንዳለ የሚያሳይ እንደሆነ ተሰምቶኛል፡፡ ስለዚህ እንዲብራራልኝ እጠይቃለሁ፤›› በማለት ቅሬታቸውን ለንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ አሰምተዋል፡፡

በኢንፎርሜሽን ሲስተም ዘርፍ በቀድሞው ባንክ ሲሠሩ የቆዩ የተለያዩ የሥራ ልምዶች፣ የትምህርት ደረጃዎችና የአገልግሎት ዘመን ያላቸው ከ20 ያላነሱ ሠራተኞች፣ በአንድ ዓይነት የሥራ መደብ ተባባሪ የቴክኒክ ኦፊሰር ተብለው ከትምህርት ደረጃና ከሥራ ልምድ ደረጃቸው ውጪ መመደባቸውን በመግለጽ፣ የሥራ ሞራላቸውን የነካ አካሄድ ንግድ ባንክ መከተሉን ኮንነዋል፡፡ ይልቁንም እንዲህ ያለውን ችግር ባንኩ ሳያስተካከል ሥራ እንዲጀምሩ ባያደርግ ተገቢ እንደሚሆንም ጠይቀዋል፡፡ ‹‹በዚህ መንፈስ ውስጥ ሆነን ባንሠራ ደስ ይለናል፡፡ እንደገና እንደሚታይ ተስፋ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡

በተጨማሪም፣ ‹‹ትክክለኛውን ቦታ አላገኘንም፡፡ ከአሥር ዓመታት በላይ አገልግለን፣ የማስትሬት ዲግሪ ይዘንና ከሃያ ያላነሱ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን ብንከታተልም ሁላችንም አንድ ዓይነት ደረጃና ቦታ ላይ ተመድበናል፤›› ያሉ የቀድሞው የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ሠራተኞች፣ ንግድ ባንክ ለሠራተኞች ያሠራጨው ደብዳቤ እንዴት የሥራ ልምድና የትምህርት ደረጃን እንዳገናዘበ እንዲታይላቸው ጠይቀዋል፡፡ ሌሎችም በኦፕሬሽንና በዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ በልዩ ልዩ መስኮች ሲሠሩ የቆዩ ሠራተኞች፣ በጠቅላላው አሁን የተመደቡበት የሥራ መደብና ቀድሞ የነበራቸው ቦታና ደረጃ ያልተጣጣመ፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ ከነበራቸው ብቃት ጋር ያልተገናኘ መሆኑን በመግለጽ፣ ንግድ ባንክ የሠራተኞቹን ቅሬታ የሚያስተናግድበት አግባብ ምን እንደሆነ ጠይቀዋል፡፡

ለቀረቡላቸው ቅሬታዎች ምላሽ የሰጡት የንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ፣ የቀድሞው የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ሁሉም ሠራተኞች ንግድ ባንክ መመደባቸውንና ከፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በስተቀር ለሁሉም የምደባ ድልድል ወጥቶ ለሠራተኞች ይፋ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ይሁንና አንዳቸውም የንግድ ባንክን መጠይቆች እንደማያሟሉ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ስፔሲፊኬሽን በብዙ ቦታ ከእኛ ያነሰ ነው፤›› ያሉት አቶ በቃሉ፣ ወደ ንግድ ባንክ የመጡትን ሠራተኞች ከዚህ ቀድሞ ይዘዋቸው ከነበሩ የሥራ መደቦች አንድ ደረጃ ወደ ታች ዝቅ ተደርገው፣ ንግድ ባንክ ውስጥ ባለ በማንኛውም ቦታ መመደባቸውን ገልጸዋል፡፡

ባንኩ ለየትኛውም የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ሠራተኛ የሥራ ደረጃም ሆነ የደመወዝ ዕደገት እንደማይሰጥና ይልቁንም፣ ‹‹ደመወዝ እንደተጠበቀ ሆኖ ባንኩ ሠራተኞቹን በየትኛውም የሥራ እርከን ያሠራል፡፡ የተሰጠኝ የሥራ ደረጃና እርከን አልተመቸኝም የሚል ካለ መልቀቅ ይችላል፤›› በማለት ከገለጹ በኋላ ሠራተኞች በተመደቡበት ቦታ እንዲሠሩ ጠይቀዋል፡፡  

ጊዜያዊ የኃላፊነት ቦታዎችን ሲመሩ የነበሩ ሠራተኞችም ቢሆኑ በንግድ ባንክ ምደባ ወቅት ጊዜያዊ የሥራ መደቡ እንደማይታይላቸው፣ ይልቁንም ከዚያ ቀድሞ በነበራቸው ደረጃ መሠረት እንደሚስተናገዱ አቶ በቃሉ አስታውቀዋል፡፡ 

ከ2,000 በላይ ሠራተኞች የነበሩት የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ፣ ከ23 ሺሕ በላይ ሠራተኞች ያሉት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥር በመጠቃለል ቀድሞ ከነበሩት 123 ቅርንጫፎች ውስጥ 88 ብቻ እንዲቀጥሉ መደረጉን አቶ በቃሉ አስረድተዋል፡፡ የቀሩት ቅርንጫፎች አገልግሎት መስጠት እንደሚያቆሙም ገልጸዋል፡፡

የተመሠረተበትን 40ኛ ዓመት ለማክበር ሽር ጉድ በጀመረ ማግሥት በንግድ ባንክ እንዲጠቀለልና ህልውናው እንዲያከትም የተደረገው የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ፣ ሞርጌጅ ባንክ ተብሎ በሰፊው ይታወቅ የነበረና በንጉሡ ዘመን የተመሠረተ ነበር፡፡ በአንፃሩ ንግድ ባንክ በመጪው ዓመት 75ኛ ዓመቱን የሚያከብር ሲሆን፣ የኮንስትራከሽንና ቢዝነስ ባንክ ቅርንጫፎችን ከጠቀለለ በኋላ በመላ አገሪቱ ከ1108 ያላነሱ ቅርንጫፎችን በሥሩ ያስተዳድራል፡፡ በቅርቡ በአሜሪካና በዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ እከፍታለሁ ካላቸው ቅርንጫፎች በተጨማሪ፣ በደቡብ ሱዳን የባንክ አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች