Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትችግሩን መለየት የማያስችል የክለቦች ግምገማ

ችግሩን መለየት የማያስችል የክለቦች ግምገማ

ቀን:

ሁለት አሥርታት ለማስቆጠር እያኮበኮበ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር መርሐ ግብር በዓመት ሁለት ጊዜ ራሱን ሲገመግም ኖሯል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም ከ35 ጊዜ በላይ የውድድሩን ሒደት ሲገመግምና ለውይይት ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ የግምገማዎቹ ማጠንጠኛዎች ደግሞ የዳኝነት ችግሮች፣ የውድድሮች መቆራረጥ፣ የፀጥታና ስፖርታዊ ጨዋነትና ሌሎችም ነጥቦች ሆነው ቆይተዋል፡፡ እየተካሄደ ያለው የፕሪሚየር ሊግ ግማሽ የውድድር ዓመት ምን ዓይነት መልክና ቁመና ይዞ ተጠናቀቀ የሚለውን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑና የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ባለፈው ቅዳሜ ሚያዝያ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዳማ ገምግመዋል፡፡

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ ስለተደረጉ ክርክሮችና ግምገማዎች፣ የተለዩ አጀንዳዎች ስለመኖራቸው አፍን ሞልቶ መናገር አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱ፣ ሁሌም የዓመቱ የፕሪሚየር ሊግ ውድድሮች በተጠናቀቁ ቁጥር ክለቦች የራሳቸውን ከታች ከፕሮጀክት ጀምሮ ማዘውተሪያ ስለመገንባትና ለዋናው ቡድናቸው ድጋፍ ሰጪ የ‹‹ሲ››፣ የ‹‹ቢ›› ተብለው በየደረጃው ስለሚቋቋሙ ቡድኖችና በአጠቃላይ ክለቦቹ የሚፈጠሩበት መዋቅር የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ እንዲሁም ስለዘመናዊ እግር ኳስ ጥራትና ብቃት ላይ ከመነጋገር ይልቅ በየዓመቱ የግምገማዎቻቸው ትኩረት የዳኝነት ብቃት፣ የውድድር መቆራረጥ ወዘተ የሚሉ ቋሚና ተደጋጋሚ ጉዳዮች መሆናቸው ለትችትና ወቀሳ ዳርጓቸዋል፡፡

አንድ ለእናቱ በሆነ ስታዲየም፣ ‹‹ከአንድ ክለብ ከሦስት በላይ ተጨዋቾች ያስመረጠ ክለብ ለመጫወት አይገደድም›› የሚል ደንብ ባለበት ሁኔታ፣ ቁመናና መዋቅር በሌለበት ክለቦች፣ ‹‹ሰሚ አጣን›› በማለት እየሄዱበት ያለው አግባብ የተለመዱና እንዲህ ያሉ ለጆሮ የሰለቹ  የግምገማ አጀንዳዎች ዛሬም መቀጠላቸው ከማነጋገርም በላይ አሳሳቢ ቸልተኝነት መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡ እንደ እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች ከሆነ፣ ካለፉት ዓመታት የዘንድሮውን የሚለየው የግምገማው ቦታ ከአዲስ አበባ 100 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው አዳማ ከተማ መደረጉ ብቻ መሆኑን ነው የሚያስረዱት፡፡

በጉዳዩ ማንነተቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የእግር ኳስ ዳኞች በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ ‹‹ለእግር ኳሱ ባለድርሻ ተብለው ከሚጠቀሱ አካሎች የእግር ኳስ ዳኞች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ክለቦች በክለብ ባለቤትነታቸው ለውጤታቸው ማሽቆልቆል ምክንያት አድርገው የሚያቀርቡት ወቀሳም ሆነ ትችት ይመለከታቸዋል፡፡››

ሆኖም ከዳኝነት ክፍተት ከውድድር መቆራረጥና መሰል ችግሮች በተጓዳኝ ክለቦች የራሳቸው ተጨዋቾች እንቅስቃሴ፣ ከዘመናዊ የእግር ኳስ ባህሪያት ጋር ያላቸው ቁርጠኝነትና የግንዛቤ ደረጃ ምን እንደሚመስል ወደ ውስጥ ተመልክተው ራሳቸው ሲፈትሹና ሲገመግሙ ግን ታይቶ እንደማይታወቅ ነው የሚገልጹት፡፡

ከተመሠረተ 18ኛው ዓመቱ ላይ በሚገኘው ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፉት የአገሪቱ ክለቦች፣ የዘመናዊ እግር ኳስ አስተሳሰብ ተቃኝተው ከአገር ውስጥ የውድደር መርሐ ግብር አልፈው በአህጉራዊና ዓለም አቀፍ መድረኮች የመሳተፍ እንዲሁም የብሔራዊ ቡድኑ ጥንካሬ መሠረት እነሱ መሆናቸውን አውቀው የሚንቀሳቀሱ ስንቶቹ ናቸው? ሲሉ የሚጠይቁት ዳኞቹ፣ ክለቦች በየዓመቱ የሚያነሱት ችግር ሁሉ አቀፍ ውይይትና ግምገማ ወደ ሁሉ አቀፍ አቅጣጫ ተቀይሮ መታየት እንደሚገባው ያስረዳሉ፡፡

በውድድር ዓመቱ መርሐ ግብር እስካሁን ባለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ፕሪሚየር ሊጉን በ29 ነጥብ ሲመራ፣ ደደቢት በ25 ነጥብ፣ አዳማ ከነማ ደግሞ በ23 ነጥብ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ይመራሉ፡፡ በወራጅ ቀጣና ውስጥ ዳሽን ቢራ በ13 ነጥብ 13ኛ ሲሆን፣ ሐድያ ሆሳዕና በአምስት ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው በሁለተኛው ዙር የጨዋታ መርሐ ግብር ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸውን የሚወስኑ ሆነው የሚጠበቁ ናቸው፡፡ፕሪሚየር ሊግ ራሱን የሚያስተዳድርበትን አቅጣጫ በተመለከተ ልምዳቸውን እንደሚያካፍሉ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...