‹‹ከፍትሐዊ ጦርነት ይልቅ ፍትሕ የነገሠበት ሰላም!››
ፓክስ ክሪስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው ተቋም ያንፀባረቀው መሪ ቃል፡፡ በቫቲካን ‹‹ዓመተ ምሕረት›› በሚል መጠሪያ እየተከበረ ባለው ኢዮቤልዩ አጋጣሚ በተዘጋጀው የሦስት ቀን ኮንፈረንስ፣ 80 ሊቃውንትና የሰላም ተሟጋቾች በተገኙበት የሚያዝያ 3 ቀን 2008 ዓ.ም. መድረክ ላይ የተንፀባረቀ መሪ ቃል፡፡ በኮንፈረንሱ ላይ ከግጭት ቀጣናዎች ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኮሎምቢያ፣ ፓኪስታንና ፊሊፒንስ ጨምሮ ከተለያዩ አካባቢዎች ታዳሚዎች ተገኝተው ነበር፡፡ በዓለማችን ‹‹ጦርነት›› ከሚለው እሳቤ ይልቅ ፍትሕ ወደ ነገሠበት ሰላም መሸጋገር አስፈላጊነት ላይ አፅንኦት ተሰጥቶበታል፡፡ ፓክስ ክሪስቲ ኢንተርናሽናል በዓለም ዙሪያ ሰላም እንዲነግሥ፣ ሰብአዊ መብቶች እንዲጠበቁ፣ ፍትሕና ዕርቅም እንዲሰፍኑ የሚሠራ ተቋም ነው፡፡