በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች በቅርቡ የተከሰተው ግጭት ደም የማሰባሰብ ሥራ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን በዚህም ለመሰብሰብ ከታቀደው በታች መሰብሰቡን ብሔራዊ ደም ባንክ አስታወቀ፡፡ በክልሉ በሚገኙ ሰባት የደም ማሰባሰቢያ ባንኮች በግማሽ ዓመት ውስጥ 17,800 ከረጢት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ማግኘት የተቻለው 10,862 ከረጢት ብቻ ነው፡፡ ይህም በግጭቱ ምክንያት በዋና ዋና ደም ማሰባሰቢያ ቦታዎች በተለይም በትምህርት ቤቶች ደም ለመሰብሰብ ባለመቻሉ የተፈጠረ መሆኑን ከደም ባንኩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
‹‹ደም ባንክ የተቋቋመው ለችግር ነው፡፡ ዓላማውም በተለያዩ አጋጣሚዎች ጉዳት ደርሶባቸው ደም ለሚፈሳቸው ደም በመተካት ሕይወት ማትረፍ ነው›› የሚሉት የብሔራዊ ደም ባንክ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሀብተማርያም ደመወዝ ማኅበረሰቡ ይህንን ተረድቶ ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ ከክልሉ የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ደም የማሰባሰቡ ሥራ መቀጠሉንም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በአዳማ ከተማ ለመገናኛ ብዙኃንና ለሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች በተዘጋጀው የሁለት ቀናት ዐውደ ጥናት ላይ ተገልጿል፡፡
በክልሉ ከተከሰተው ግጭት በተጨማሪ የደም ባንኮቹ የሥራ ማስኬጃ ማለትም የተሽከርካሪና የሰው ኃይል እጥረትም ለተሰበሰበው ከታቀደው በታች ደም ለመሰብሰቡ ምክንያት መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ለመሰብሰብ ካቀዱት በላይ ማሰባሰብ የቻሉ ክልሎች መኖራቸው ታውቋል፡፡ ከእነዚህም መካከል አማራ ክልል የመሪነቱን ደረጃ ይዟል፡፡ በክልሉ በሚገኙ ስድስት ደም ባንኮች በግማሽ ዓመት ውስጥ 14,500 ከረጢት ለመሰብሰብ ታቅዶ 14,624 ከረጢት መሰብሰብ ተችሏል፡፡ በሌሎች ክልሎችም እንዲሁ አበረታች ውጤት ታይቷል፡፡ የክልሎቹ ተሞክሮ በሌሎችም አካባቢዎች ተግባራዊ እንዲሆን ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አገሪቱ በዓመት ከ250,000 እስከ 300,000 ከረጢት ደም ያስፈልጋታል፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ ችግሮች ይህንን ያህል ደም ማሰባሰብ አዳጋች ሲሆን ይታያል፡፡ ለዚህም የደም ልገሳ ባህል ዝቅተኛ መሆን በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ባለፈው ዓመት መሰብሰብ የተቻለው በዓመት ከሚያስፈልገው የደም መጠን ከግማሽ ያነሰ 128,000 ከረጢት ደም ብቻ ነው፡፡ በየዓመቱ ከሚገኘው ደም 50 በመቶ የሚሆነው ለወላድ እናቶች ይውላል፡፡
አገሪቱ ከወላድ እናቶች ቀጥሎ ከፍተኛ ደም የሚያስፈልጋቸው የትራፊክ አደጋ ሰለባ የሚሆኑ ናቸው፡፡ የተቀሩት በተለያዩ ሕክምናዎች ላይ የሚገኙ፣ የደም ማነስ ያለባቸውና ሌሎችም ደም የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን የሚሰበሰበው ደም አነስተኛ በመሆኑ በተፈለገው መጠን ለማቅረብ አስቸጋሪ ነው፡፡
በመሆኑም በአሁን ወቅት በገዳይነቱ ግንባር ቀደም የሆነው የትራፊክ አደጋ ሲያጋጥም ትራፊክ ፖሊሶች አደጋውን ሪፖርት ከማድረግ ጐን ለጐን ለተጐዱ ሰዎች የሚሆን ደም ኅብረተሰቡ እንዲለግስ ጥሪ ማድረግ እንደሚገባቸው ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩልም ትራፊክ ፖሊሶች አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች ሕይወት ለመታደግ የመጀመሪያ ሕክምና ዕርዳታ ግንዛቤ እንደሚያስፈልጋቸው፣ ብሔራዊ ደም ባንክም ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና እንደሚያዘጋጅ ዶ/ር ሀብተማርያም ገልጸዋል፡፡
ደም የመለገስ ልማድ ዝቅተኛ መሆን ብዙዎች መዳን ሲችሉ በደም እጥረት እንዲሞቱ እያደረገ ይገኛል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ መሠረት ማንም ሰው በደም እጥረት እንዳይሞት አንድ በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ደም ሊለግሱ ግድ ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ባለው ዝቅተኛ የደም ልገሳ ባህል ይህንን እውን ለማድረግ የማይታሰብ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ማይናቅ መሻሻሎችን እያሳየ ይገኛል፡፡
የላቀ ውጤት ለማስመዝገብም የደም ባንኮችን ቁጥር ከማሳደግ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ በቅርቡ የተጀመረውን በታዋቂ ሰዎች ስም ደም የመለገስ ሥርዓት አጠናክሮ በመቀጠል የደም ለጋሾችን ቁጥር ለማሳደግም ደም ባንኩ እንደሚሠራ ዶ/ር ሀብተማርያም ተናግረዋል፡፡