Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ዩኔስኮን የመጨረሻ ግብ አድርገን ከያዝነው ችግር ነው››

አቶ ኤፍሬም አማረ፣ የቅርስ ምዝገባ ቁጥጥርና ደረጃ ማውጣት ዳይሬክተር

 ‹‹ቅርሶች በታሪክ ምስክርነታቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ሳይንሳዊ ምዝገባና ቁጥጥር ማከናወን፣ ቅርሶችን ከሰው ሠራሽና ከተፈጥሮ አደጋዎች መከላከል፣ ከቅርሶች የሚገኙ ጥቅሞች ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማቶች እገዛ እንዲያደርጉ ማስቻል፣ ቅርሶችን  ማግኘትና ማጥናት›› የሚሉ ዐበይት ዓላማዎችን እንዲይዝ ተደርጎ በ1992 ዓ.ም. በዓዋጅ የተቋቋመው የቅርስ ጥናትና ምርምር ባለሥልጣን፣ በቀደሙትና በአሁን መንግሥታት የተለያዩ አደረጃጀቶችን አሳልፏል፡፡ በሰባ ሁለት ዓመታት ቅርሳዊ ጉዞው ካሳያቸው አደረጃጀቶች ቀዳሚው በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የአርኪዎሎጂ ሙዚየም የተመሠረተበት 1945 ዓ.ም. አንዱ ነው፤ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክርም ሌላው ነው፡፡ በ1958 ዓ.ም ተጠሪነቱ ለጽሕፈት ሚኒስቴር ሆኖ የታሪካዊ ቅርሶች አስተዳደር ሲባል ከቆየ በኋላ በ1967 ዓ.ም. በኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር መንግሥት (ደርግ) በባህል ስፖርትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር፣ በመቀጠልም በባህል ሚኒስቴር፣ ለጥቆም በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር ሆኖ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በ1987 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት በማስታወቂያና ባህል ሚኒስቴር ሥር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ድርጅት ሲባል ከቆየ በኋላ በ1992 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊክ የማስታወቂያና ባህል ሚኒስቴር (በአሁን ወቅት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር) ሥር ወደ ባለሥልጣን ደረጃ አድጎ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት ባለሥልጣኑ ባለው አወቃቀር ካሉት የተለያዩ ዳይሬክቶሬቶች መካከል አንዱ የቅርስ ምዝገባ ቁጥጥርና ደረጃ ማውጣት ዳይሬክቶሬት ነው፡፡ በዳይሬክቶሬቱ (ዋና መምሪያ) ነባርና ወቅታዊ የሥራ እንቅስቃሴ ዙሪያ ዳይሬክተሩን አቶ ኤፍሬም አማረን ሔኖክ ያሬድ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የእናንተ መምርያ ተግባሩ ምንድን ነው?

አቶ ኤፍሬም፡- የቅርስ ምዝገባ፣ ቁጥጥርና ደረጃ ማውጣት ዳይሬክቶሬት ስንል ከስሙ እንደምንረዳው በአገሪቱ ያሉትን ቅርሶች ከክልሎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የመመዝገብ፣ የተመዘገቡትን ደግሞ ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ እንድንችል የክትትልና የቁጥጥር ሥራ እንሠራለን፡፡ በሕገወጥ መንገድ እንዳይዘረፉ፣ ካያያዝ ከጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ በቅርሶች ላይ ጉዳት እንዳይደርስባቸው መከላከል አንዱ ተግባሩ ነው፡፡

ሌላው በቅርብ ጊዜ የመጣው ተግባር ደረጃ ማውጣት ነው፡፡ በተግባር ብዙ የገባንበት አልነበረም፡፡ በቅርብ በወጣው ዓዋጅ ቁጥር 839/2006 መሠረት የቅርሶች የአስተዳደር ደረጃዎች በክልልና በፌዴራል መንግሥት የሚመሩበት አሠራር ተመቻችቷል፡፡ ምክንያቱም የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በሁሉም ቅርሶች ላይ ተደራሽ መሆን አይችልም፡፡ ለአያያዝና ለጥንቃቄያቸው ሲባል እንደይዘታቸው ደረጃ ይወጣላቸዋል፡፡ ቅርሶቹን በሚገባ ለመጠበቅና ለመንከባከብ እንዲቻል ዓዋጁ ላይ መሥፈርቶች አሉ፡፡ በፌደራል የአስተዳደር ደረጃ ላይ የሚወሰኑ ቅርሶች ምንድን ናቸው የሚለውን በትክክል አውጥተናል፡፡

ደረጃ ማውጣት ሲል ለአስተዳደራቸው ለጥበቃና ክብካቤያቸው አመቺነት መፍጠር ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ይህ የፌዴራል ይህ የክልል ሥራ ነው የሚል በጣም ከፍተኛ ችግር ስለነበረ ነው ዓዋጁ እንዲወጣ የተደረገው፡፡        

ሪፖርተር፡- ቅርሶች የምትሏቸው የትኞቹን ነው?

አቶ ኤፍሬም፡- የትኞቹን ቅርሶች ለሚለው መሠረት የምናደርገው በዓዋጅ ቁጥር 209/92 ነው፡፡ ዓዋጁ ቅርሶቹን በሦስት ደረጃ ይከፍላቸዋል፡፡ ተነቅለው ወደየትም ቦታ መሄድ የማይችሉ ሐውልቶች፣ የእምነት ተቋማት ቤተ ክርስቲያንና መስጊዶች፣ የአርኪዮሎጂና ፖሊዎንቶሎጂ ቦታዎች የመሰሉት ቋሚ ቅርሶች ሲሆኑ ሌሎቹ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ናቸው፡፡ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስ ለሕገወጥ ዝውውርም የተጋለጡ እንደ ብራና ጽሑፎች፣ ጥንታዊ የዕደ ጥበብ ሥራዎች፣ የየብሔረሰቡ የወግ ዕቃዎችና ሌሎችም ተንቀሳቃሽ ናቸው፡፡ ሦስተኛው ዓይነት የቅርስ ዓይነት ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርስ የምንለው ነው፡፡ በቅርቡ ነው ወደዚህኛው ዓይነት ቅርስ የገባነው፡፡ ቀደም ሲል በዓዋጃችን ላይ እንደተመለከተው የየብሔረሰቡ ጨዋታዎች የደስታ የሐዘን መገለጫዎች የሚል ነበር፡፡ አሁን ግን ሰፍቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ. በ2003 (1995 ዓ.ም.) በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ቅርሶች ሀብቶችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ለማስተዋወቅ አንድ የወጣ ኮንቬንሽን (ስምምነት) አለ፡፡ ኢትዮጵያም በ1998 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. በ2006) ከፈረመች በኋላ የማይዳሰሱ ቅርሶች ብለን የያዝናቸውን ቅርሶች በአምስት ምድቦች (ዶሜይንስ) ከፍለን ነው ሥራውን የምንሠራው፡፡ ምድቦቹም አፋዊ ትውፊቶችና መገለጫዎቻቸው፣ ትውን ጥበባት፣ አገር በቀል ዕውቀት፣ የዕደ ጥበብ ክህሎትና ማኅበራዊ ክዋኔዎች፣ ፌስቲቫሎች ጭምር እነዚህን ለይተን እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስትመዘግቡ መለኪያችሁ ምንድን ነው?

አቶ ኤፍሬም፡- መመዝገብ ስንል መዘርዘር ሳይሆን የቅርሶቹ ፋይዳ ምንድን ነው የሚለውን እናያለን፡፡ ባለን ማንዋል መሠረት እነዚህ ቋሚ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን በአምስት መሥፈርቶች እንመለከታቸዋለን፡፡ ለታሪክና ባህል ጥናት ያለው ጠቀሜታ፣ በሥነ ጥበባዊና በኪነ ሕንፃዊ አሠራር ጥበብ ልዩ መሆናቸው፣ በዕድሜው ጥንታዊ የሆነና የአንድን ዘመን የታሪክና የባህል አሻራ የሚያሳይ መሆኑ፣ አስደናቂና ብቸኛ የተሠራበት ቁስ ውድ መሆኑ፣ ሌላው ለሳይንስና ምርምር ያላቸው ጠቀሜታ የጎላ ከሆነ በሚል ቅርሶችን እንመዘግባለን፡፡ ምዝገባ ወይም ኢንቬንተሪ የምንለው መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ በአንዳንዶች ዘንድ ያለው ግንዛቤ ዝም ብሎ የመመዝገብ፣ ሊስት የማድረግ ዓይነት ነው፡፡ ለምሳሌ የቤተ ክህነት ሰዎች ቅርሶችን ይመዘግቡና 10 መስቀሎች፣ አምስት መጻሕፍት፣ ስድስት ፅናዎች ብለው ነው የሚረካከቡት፡፡ ይህ አሠራር ግን ቅርሶቹን አያሳይም፣ ሌላ ቢተካበት የምናውቅበት መንገድ የለም፡፡                        

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ያሉት ቅርሶች ብዛት አሁን በዘረዘሩት መልክ በአኀዝ ተለይተው ይታወቃሉ?

አቶ ኤፍሬም፡- ሥራችን ያሉትን ቅርሶች ለይቶ ማወቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ በሁሉም አቅጣጫ ያሉት ቦታዎች በሙሉ ቅርስ አላቸው፡፡ የመጀመሪያ ሥራ መለየትና መመዝገብ ቢሆንም እስካሁን ድረስ አልተጠናቀቀም፡፡ ቅርሶችን መዝግበን ይኸን ያህል ቁጥር ቅርስ አለን ብለን ለመናገር የምንችልበት ሁኔታ ላይ አይደለንም፡፡ ሒደቱን ግን ጀምረናል፡፡ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ላይ ለክልሎች የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች በመስጠት ሥራዎቹ እንዲሠሩ የማድረግ ነገር አለ፡፡ ከዚያም በፊት አንድ ወቅት ላይ ከማዕከል በመነሣት የቅርስ ምዝገባ ሥራም እስከ 1985 ዓ.ም. ተከናውኗል፡፡ ስለዚህ እስካሁን ድረስ የመዘገብናቸው ቅርሶች ስናይ በተንቀሳቃሽ ቅርሶች ደረጃ ወደ 70,000፣ በቋሚ ቅርስ ደረጃ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት፣ መስጊዶችን፣ መንደሮች እንደ ሾንኬ ዓይነት፣ የአርኪዮሎጂና ፖሌዎንቶሎጂ ቦታዎች በተመለከተ 2,500 ተመዝግበዋል፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ 80 በመቶ ያህሉ ተመዝግቧል የሚል ግምት አለ፡፡                     

ሪፖርተር፡- እነዚህን የመዘገባችኋቸው ቅርሶች አስቀድሞ እንደገለጹት በወጣው የቅርሶች ደረጃ መሠረት በፌዴራልና በክልል የታየበት አግባብ እስከ ምን ድረስ ነው?

አቶ ኤፍሬም፡- ወደየምደባው ከመኬዱ በፊት መጀመሪያ መጠናቀቅ ያለበት ሥራ አጠቃላይ ምዝገባ ነው፡፡ በፌዴራል በክልል ደረጃ አንድ ወጥ የምዝገባ ሥርዓት ዘርግተንና ማኑዋል አዘጋጅተን ምዝገባው ከተጠናቀቀ በኋላ ነው የቅርሶቹን ደረጃ ለመወሰን የሚቻለው፡፡ በመሥፈርት ደረጃ የፌዴራል ቅርሶች የምንላቸውን ለይተናል፡፡ ለምሳሌ የሰው ዘር አመጣጥና አኗኗር ሁኔታዎች ዓይነት፡፡ ቅርሶች እንዲመዘገብላቸው አቅራቢዎቹም፣ ጠያቂዎቹም ክልሎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ተገቢው የሆነ ጥበቃና ክብካቤ እንዲደረግላቸው የሚያስፈልጋቸው ቅርሶችን ወደዚህ የመላክ ኃላፊነት አለባቸውና፡፡ የፌዴራል መሆናቸው ትልቁ ጠቀሜታ ወደ ዓለም አቀፍ ቅርስነት ለመግባት ጥሩ መንገድ ይከፍታል፡፡ እኛ በአገር ደረጃ በቅርስነት ያልተቀበልነው ነገር በዓለም ቅርስነት ይመዝገብ የምንለው አጠያያቂ ስለሚሆን መጀመሪያ ቅርሶቻችንን እንለያቸው፤ ፋይዳቸውንም ለይተን የፌደራል መንግሥቱ ጥገናና የእንክብካቤ ሥራና እገዛ ታክሎባቸው የፌዴራል ቅርስ መሆን ይገባቸዋል፡፡ በክልሉም ሊጠበቁም እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይችላል የሚለውን ነገር ለመለየት ማለት ነው፡፡                     

ሪፖርተር፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ ወካይ ቅርስ ሆነው የተመዘገቡ የማይዳሰሱ (ኢንታንጀብል) ባህላዊ ቅርሶች አሉ፡፡ ሰነዶቹን ስንመለከት የመጀመሪያው ተመዝጋቢ የመስቀል ክብረ በዓል ሲሆን፣ ቀጣዩ ፊቼ ጫምባላላ ነው፡፡ በዓለም ለመመዝገብ በመጀመሪያ በብሔራዊ ደረጃ መመዝገብ ግዴታ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከሁለቱ በዓላት ሌላ በብሔራዊ ደረጃ የተመዘገቡ ሌሎች የማይዳሰሱ ቅርሶች አሉ?

አቶ ኤፍሬም፡- የኢንታንጀብሉን ለየት አድርገን ልናይ ይገባናል፡፡ እስካሁን እየተሠራ ያለው በብሔረሰብ ደረጃ ነው፡፡ እጃችን ላይ ባለው መረጃ መሠረት ከአማራ፣ ከትግራይና ኦሮሚያ በስተቀር የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ተሰንደዋል፡፡ ወደ ዓለም አቀፍ ወካይ ቅርስ ለመግባት መጀመሪያ ኢንቬንቶሪ ተካሂዷል ወይ? ይዘታቸውስ ምንድን ነው? የሚለው መለየት አለበት፡፡ ዩኔስኮ በወካይ ቅርስን በሚመለከት ግንኙነት የሚያደርገው የሚያውቀውም ሌላ አካልን ሳይሆን ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንን ነው፡፡ በመሆኑም ባለሥልጣኑ ቅርሶቹን ለመለየት በመጀመሪያ ኢንቬንቶሪ ማከናወን አለበት፡፡ በአንዱ አካባቢ የሚገኘው ቅርስ በሌላ አካባቢ ልታገኘው ትችላለህ፡፡ ለምሳሌ መስቀል በዓል እንዲመዘገብ ያደረገው በብዙ ብሔረሰቦች ውስጥ የሚተገበር ባህላዊ ቅርስ በመሆኑ ነው፡፡

ስለዚህ በዚህ በኩል አሁን ባለን ሁኔታ በዩኔስኮ ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርስ ማስመዝገብ የሚቻለው በየዓመቱ አንድ ጊዜ ነው፡፡ መረጃዎችን በተመለከተ ግን ከአማራ፣ ኦሮሞና ትግራይ ውጪ የአብዛኛዎቹ ብሔረሰቦች ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች በሰነድ ደረጃ ከሰባት ቅጾች አሳትመናል፡፡ ከዚያ እየወሰድን ለዓለም አቀፍ ወካይ ቅርስ ውስጥ የሚገባበት መንገድ ይሠራል፡፡

የእነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ ቅርሶች ምዝገባ ከተጠናቀቀ በኋላ የምንሠራው ግን እንደ አገር ያሉ ኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ምንድን ናቸው? በአገር ደረጃ ልንይዛቸው የሚገባ የትኞቹ ቅርሶች ናቸው? እንደ አገር የሚወክሉን ቅርሶች የሉም ወይ? ለምሳሌ የኢትዮጵያ ፊደል፣ የዘመን አቆጣጠር፣ እንደ የጥምቀት በዓል ዓይነቶቹ እንደ አገር ጎልተው ሊወጡ የሚችሉ ቅርሶች ስለሆኑ እነርሱን ለመሥራት መንገዱ የተመቻቸ ነው፡፡                      

ሪፖርተር፡- ግዙፍ (ታንጀብል) ቅርሶችንስ በተመለከተ በተለይ በዓለም ቅርስነት በተመዘገቡት ላይ የለሙትም ሆነ ያለሙት ላይ ያላችሁ ተግባር እንዴት ይገለጻል?

አቶ ኤፍሬም፡- የእኛ ተግባር ቅርሶቹን መለየት፣ መመዝገብ፣ ጥገናና ክብካቤ መሥራት ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉ የመዳረሻ ሥራዎች፣ ቅርሶቹን በጣም ተደራሽ የማድረጉ፣ የማስተዋወቁ ሥራዎች በቱሪዝሙ በኩል ነው፡፡ ቱሪዝሙ የኛን ፕሮዳክት (ምርት) ወስዶ መሸጥ ነው፡፡ እስከዚያ ድረስ ነው እየተሠራ ያለው፡፡

የጥገናና ክብካቤ ሥራው በእኛ ነው ሲሠራ የቆየው፤ ከሁለት ዓመት ወዲህ የግሉ ዘርፍ ወደዚህ ለማምጣት ተደጋጋሚ መድረኮች ተፈጥረዋል፡፡ ጥገናን በተመለከተ ግን በዋነኛነት በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ቅርሶች የመጠገኑ ኃላፊነት የባለሥልጣኑ ነው፡፡ ምን ያክል አከናውኗል፡፡ ማን ያክል ቅርሶች ተጠግነዋል የሚለው አጠያያቂ እንዳለ ሆኖ፡፡ ስለዚህ በዓለም አቀፍ ቅርሶቹ ላይ ግን በዩኔስኮ ደረጃ ትኩረት የሚሰጠው በመሆኑ የጥገናና ክብካቤ ሥራው በተከታታይ ይከናወናል፡፡ በላሊበላ በቤተ ገብርኤልና በቤተ ሩፋኤል እየተሠሩ ያሉት ሥራዎች አንዱ ማሳያ ናቸው፡፡ ጥገናውን ወደ ግሉ ዘርፍ ሙሉ በሙሉ አድርገን የተውነው ሒደት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቅርሶቹን የሚጠግነው ሰው በጥገና፣ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ወይም በአርክቴክቸር ብቻ መማሩ በቂ አይደለም፡፡ ስለቅርስ በቂ ግንዛቤ ሊኖረው ስለሚገባ፡፡ አሁን ለተለያዩ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ቢሰጥ ቅርሶቹ ላይ አደጋ ቢደርስ ተመልሰን አናገኛቸውም፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ጥገናው በባለሥልጣኑ ባለሙያዎች ቁጥጥርና ሱፐርቪዥን አማካይነት እየተከናወነ ነው፡፡                     

ሪፖርተር፡- ከዘጠኙ የዓለም ቅርሶቻችን አንዱ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡ የላሊበላ መገለጫ ግዙፉ ቅርስ ብቻ አይደለም፡፡ የማይዳሰሰው ባህላዊ ቅርስም አብሮት አለ፡፡ የማስተዋወቁ ነገር ከሕንፃው ባለፈው ሲሠራ አናይም?

አቶ ኤፍሬም፡- ዩኔስኮ እ.ኤ.አ. በ1970 ያወጣው የዓለም አቀፍ ቅርሶች ኮንቬንሽን (ስምምነት) ዓላማ እንደነ ላሊበላ፣ አክሱም፣ ጢያ ያሉትን ታንጀብል ቅርሶችን ለመመዝገብ ነበር፡፡ በጣም ረዥም ጊዜ አልፎ ሲመለከቱት ግን ታንጀብሉ ያለ ኢንታንጀብሉ ሊቆም አልቻለም፡፡ ረቂቁ የግዙፉ ትርጉም ማለት ነው፡፡ ላሊበላ ካለቤዛ ኵሉ (ልደት)፣ ካለ ጥምቀትና ካለ መስቀል በዓላት ሊታሰብ አይችልም፡፡ ስለዚህ እ.ኤ.አ. የ2003 ስምምነት ሲወጣና እኛም ስንፈርመው ትልቁ መነሻ ሐሳቡ ኢንታንጀብሉ ያለ ታንጀብሉ ረቂቅ ነገር ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ የምትከውንበት ቦታ ከሌለው አይታይም፡፡ ታንጀብሉም በተመሳሳይ ካልተደገፈ ቅርሱ ተጠብቆ ሊቆይ አይችልም፡፡ አንዳንድ ቦታ ቅርሶች ላይ ጉዳት የሚደርሰው የዚያ ቅርስ ኢንታንጀብል ክፍሉ በትክክል ስለማይታወቅ ወይም ሲጠፋ፣ አለያም በርዕዮተ ዓለም ምክንያት በሌላ ነገር ሲተካ ነው፡፡

ለየቅርሶቹ ትርጉም የሚሰጠው የኢንታንጀብል ክፍሉ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በመሥሪያ ቤታችን እየተሠራ ያለው በጎንደር፣ ላሊበላ፣ አክሱም ያሉት ኢንታንጀብል ሀብቶችን መለየት ሥራ ነው፡፡ በላሊበላ ጀምረናል፡፡ እርሱም መስህብ ሆኖ በበለጠ እንዲወጣ ማለት ነው፡፡

ታንጀብሉን ያለ ኢንታንጀብሉ ማሰብ ብቻውን የሚቆም ነገር ማለት ነው፡፡ ኢንታንጀብሉን ያለ ታንጃብል ማሰብ ዝም ብሎ ረቂቅ መሬት ላይ የማይወርድ ነገር ማሰብ ነው፡፡ ፊቼ ጫምባላላን ስንወስድ ጉዱማሌ የሚባለው ስፍራ ከነደኑ ከጠፋ መከወኛ ቦታ ስለሌለው በዓሉ ይጠፋል ማለት ነው፡፡ አንዳንዴ ኢንታንጀብሉን የሚያጠፋው በተለያየ ምክንያት መከወኛ ቦታዎች መጥፋት ነው፡፡ በከተማ መስፋፋት የገና ጨዋታ መከወኛ እየጠፋ ነው፡፡                      

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ እንዳላት በርካታ የማይዳስሱ ባህላዊ ቅርሶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስመዘገበችው ሁለት ብቻ መሆኑ ለምን እያስባለ ነው፡፡ እንደ ግብፅ፣ አልጀሪያ፣ ያሉት ከእኛ በተሻለ ቁጥር አስመዝግበዋል፡፡ በሌላ በኩል በየክልሉ ቅርሶቻቸው እንዲመዘገብ የሚጠይቁ አሉ፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከበሩት ላይ ትኩረቱ አነስተኛ ነው ይባላል፡፡ አንዱ የጥምቀት በዓል ነው፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታት ከባለሥልጣኑ ከፍተኛ ሹማምንት፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሮች አንደበት ጥምቀትን ለማስመዝገብ እየሠራን ነው ቢባልም ሥራው አልተጀመረም የሚሉ አሉ?

አቶ ኤፍሬም፡- አንዱ ትልቁ ነገር እኛ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች አገር መሆናችንን መረዳት አለብን፡፡ ዩኔስኮ ከሃይማኖት ጋር ተያይዘው የሚሄዱ ባህላዊ እሴቶች ጎልተው የሚወጡበት በዓላትን ይመዘግባል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚታወቀው ባህል ከሃይማኖት ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው፡፡ መስቀል አንዱ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ በተለያዩ ባህሎች ውስጥ በዓሉ ይንፀባረቃል፡፡ የጥምቀት በዓልም በተመሳሳይ ከባህል አንፃር ትልቅ አቅም ያለው ነው፡፡ ከሃይማኖታዊ መገለጫው ባሻገር በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን የሚያሳትፍ የበርካታ ባህሎች መስተጋብር የሚፈጥር ነው፡፡ ነገር ግን ኢንታንጀብልን በተመለከተ ብዙ ጊዜ የሚመጡብን ፌስቲቫሎች ብቻ ይመስሉናል፡፡ አንዳንድ አገሮች የዕደ ጥበብ ክህሎታቸውን፣ ባህላዊ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም፣ ባህላዊ የፖለቲካ ሥርዓት የሚመስሉ ነገሮችን የመሥራት ነገር አለ፡፡

እኛ ብዙ ብሔረሰብ ስላለን የሚዳረስም ሥራ አይደለም የምንሠራው፡፡ ግን ትልቅ እሴት ያላቸውን በዓለም ደረጃ ሊታወቁ የሚገባቸውን የማውጣት ነው፡፡ ስለዚህ በፈለግነው መጠን ሊሄድ አይችልም፡፡ ትልቁ ሥራችን አገራዊ የባህል እሴቶቻችን እየለየን መሥራት ይገባናል፡፡ ስለ ጥምቀት በዓል እየሠራን ነው፡፡ ዩኔስኮ ይመዘግበዋል አይመዘግበውም የሚለውን ብቻ ይዘን ከተነሳን አስቸጋሪ ነገር ነው የሚሆነው፤ እኛ እንደ አንድ የአገራችን ሀብት መያዛችን በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡

የገዳ ሥርዓት ለዩኔስኮ ቀርቧል፤ በሚቀጥለው ዓመት ለውይይት የሚቀርብ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ አቅም ያላቸው የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች እነማን ናቸው የሚለውን በመሥሪያ ቤታችን ለይተን ይዘናል፡፡ ከእነዚህም አንዱ ጥምቀት ነው፡፡ በተለያዩ ባህሎች ውስጥ በትግራይ፣ በአገው፣ በላስታ፣ በጎንደር ያለውን የሴቶች በዓል አሸንዳንም የማየት ነገር አለ፡፡  

ሪፖርተር፡- በተለያዩ ክብረ በዓላት ላይ ‹‹በዓሉን በዩኔስኮ እንዲመዘገብልን እንጠይቃለን›› የሚሉ ድምፆች እንሰማለን፡፡

አቶ ኤፍሬም፡- ዩኔስኮ በባህላዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ላይ ጥበቃና ክብካቤን ጨምሮ የሚሠራ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው፡፡ ቅርሶቹ በዩኔስኮ ሲመዘገቡ የበለጠ የመታወቅ ዕድልን ይፈጥራል፡፡ ዓለም አቀፍ ትብብርን ለየአገሮቹ የማዳበርን ሥራ ይሠራል፡፡ ግን ዩኔስኮን የመጨረሻ ግብ አድርገን ከያዝነው ችግር ነው፡፡ ዩኔስኮ ነው ወይ ቅርሶቻችንን የሚጠብቅልን? ግንዛቤው እያጠረ ያለ ይመስላል፡፡ በማንኛውም የሚዲያ ተቋም የምናየው፣ በየክብረ በዓላቱ የምናዳምጠው ነገር፣ ‹‹ቅርሶቹን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ጥረት ላይ ነን›› የሚል ነው፡፡ ቅርሶቹን በመጀመሪያ መዝግበናቸዋል? መጀመሪያስ ተገቢውን ጥበቃና ክብካቤ እያደረግንላቸው ነው? መጀመሪያ እኛስ አውቀናቸዋል? እንደ አገር ይህን በብዛት የማናይበት ነው፡፡ የሚዲያ ተቋማቱ በአብዛኛው በማንኛውም ክብረ በዓል ላይ ሲገኙ መጀመሪያ የሚናገሩት ነገር ‹‹ቅርሱን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ ነው›› የሚል ነው፡፡ እዚህ አገር ላይ የተዛባ አስተሳሰብ እየተፈጠረ ነው፡፡ አሁን በምናየው ሁኔታ ግን ሁሉም ሰው ፖለቲካዊ አመራር ላይ ያሉ አካላት፣ የባህልና የቱሪዝም ቢሮ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞችም የትም ብንሄድ ይህንኑ ያስተጋባሉ፡፡ በጣም የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡ ለቅርሶቻችን መድረስ የሚገባን ጥበቃና ክብካቤ ማድረግ ያለብን እኛ ነን፡፡ ከእኛ በላይ ዩኔስኮ እንዲያደርግልን የሚለው መስተካከል የሚገባው ነው፡፡

እንደተቋማችን ቅርሶቹን መጀመሪያ መዝግበናቸው፣ ተገቢውን ጥበቃና ክብካቤ እያደረግንላቸው፣ ተደራሽም እያደረግንላቸው በተመሳሳይ ጊዜ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡና ዓለም አቀፍ ትብብር እንዲፈጠር ለማድረግ በዩኔስኮ እንዲታወቁ ማድረግ ተገቢ ነገር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሃይማኖት ተቋማት ጋር ትብብር አላችሁ?

አቶ ኤፍሬም፡- ትብብርን በተመለከተ በተለይ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ፣ በታሪክ አጋጣሚም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በቅርሶች ደረጃ ትልቅ ድርሻ ያላት  እርሷ ናት፡፡ ቋሚም ተንቀሳቃሽም ቅርሶች አሏት፡፡ በኢንታንጀብሉም ያሬዳዊ ዜማ፣ የኢትዮጵያ ካሌንደር፣ የጥምቀትና የመስቀል በዓላት አሉ፡፡ ሌሎች ከእነርሱ ጋር የሚያያዙ የዕደ ጥበብ ሙያዎች፣ ሀገር በቀል ዕውቀት እንደ ብራና ጽሑፎች ያሉት አሉ፡፡ ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር አብረን እንድንሠራ የሚያስገድዱ በርካታ ነገሮች ቅርሶች ናቸው፡፡ በቅርስ ጥበቃና ክብካቤ ዙርያ ለእነርሱ ግንዛቤ እንሰጣለን፤ መድረኮችንም እንፈጥራለን፡፡

የቅርስ አመዘጋገብን በሳይንሳዊ መንገድ እንዲሠሩ የሚያስችል መንገድ እናመቻቻለን፡፡ የቤተ ክርስቲያን ቅርሶችን በሚጠብቁ ቄሰ ገበዞች መካከል የሚደረገው ርክክብ ሙሉነት የለውም፡፡ በቄስ ገበዝና በቄስ ገበዝ መካከል ያለው ርክክብ በፍጹም ለቅርሶቹ ጥፋት እየሆነ ነው፡፡ ምክንያቱም አራት መስቀል ብቻ ብሎ ይመዘግባል፡፡ መቼ ነው የተሠራው? በማን ጊዜ ተሠራ? አሮጌዎቹ ነባሮቹ ወጥተው በአዲስ ከተተካ ማንም አያውቀውም፡፡ ስለዚህ እዚያ አካባቢ ያለው በቅርስ ጥበቃና ክብካቤ በቅርስ ምዝገባ ላይ ያለው ሥርዓት ካልተስተካከለ አስቸጋሪ ስለሚሆን ይህን የማሳወቅ ሥራ እንሠራለን፡፡

ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጋርም ቅርስን በሚመለከት ከፍተኛ ጥረት እናደርጋለን፡፡ በተለይ ከ12ኛው እስከ 14ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩ ከመካከለኛው ሸዋ እስከ ሐረር ድረስ ባሉት መስመሮች በርካታ ቅርሶች አሉ፡፡ የማይዳሰሱ ቅርሶችም እንደ መንዙማ የመሳሰሉት አሏቸው፡፡ የትም ቦታ የማናገኘው ትልቅ ቅርስ ነው፡፡ በዚህ ዓመት እርሱን የማጥናት ሥራ ጀምረናል፡፡ በጡርሲና መስጊድም ታንጀብልም ኢንታንጀብልም ቅርስ አለ፡፡ የቡና ሥነ ሥርዓቱ አንዱ ማሳያ ነው፡፡                        

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን

ቢሻን ጋሪ ፒውሪፊኬሽን ኢንዱስትሪ ወደ ውኃ የማከም ቴክኖሎጂ ሥራ የገባው በየጊዜው በኢትዮጵያ የተከሰቱ ውኃ ወለድ በሽታዎች መደጋገምን ዓይቶና ጥናት አድርጎ ነው፡፡ በ2000 ዓ.ም. ቢሻን...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...

ሕይወትን ለመቀየር ያለሙ የቁጠባና ብድር ማኅበራት

ወ/ሮ ቅድስት ሽመልስ በግሎባል ስተዲስ ኤንድ ኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በፕሮጀክት ማኔጅመንት እንዲሁም በኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ ሠርተዋል፡፡ በኮርፖሬት ፋይናንስ ካናዳ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ...