Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ዲዛይነሩም አምራቹም ጋ እውነተኛ ዋጋ መኖር አለበት››

‹‹ዲዛይነሩም አምራቹም ጋ እውነተኛ ዋጋ መኖር አለበት››

ቀን:

ወ/ሮ እጅጋየሁ ኃይለጊዮርጊስ፣ የፋሽን ዲዛይነሮች ማኅበር ፕሬዚዳንት

ወ/ሮ እጅጋየሁ ኃይለጊዮርጊስ ከቀደምት ዲዛይነሮች አንዷ ስትሆን፣ እጅግ ጥበብ የተሰኘ የፋሽን ድርጅት አላት፡፡ ዲዛይነሯ የፋሽን ዲዛይነሮች ማኅበር (ፋሽን ዲዛይነርስ አሶሲኤሽን ወይም ኤፍዲኤ) መሥራችና ፕሬዚዳንት ናት፡፡ ኤፍዲኤ የተመሠረበት ሁለተኛ ዓመት ያከበረው ባለፈው ሳምንት ሲሆን፣ በፋሽን ዘርፍ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ ስለ ማኅበሩ እንዲሁም የፋሽኑ ዘርፍ ምሕረተሥላሴ መኰንን ወ/ሮ እጅጋየሁን አነጋግራታለች፡፡

ሪፖርተር፡– የማኅበሩ አመሠራረትና የተነሳችሁበት ዓላማ ምን ይመስላል?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- እዚህ አገር ሁላችንም ዲዛይነሮች በየአካባቢያችን የየራሳችንን ሥራ በተበታተነ መልኩ ነበር የምንሠራው፡፡ ሙያው ከውስጥ ተሰጥኦ የሚመነጭ ስለሆነ ቢዝነስ ላይ ማተኮር ብቻ ሳይሆን ስለሙያው መቆርቆር ይመጣል፡፡ ስለሸጥን ስለለወጥን ብቻ አንረካም፡፡ የግድ ሙያው መስመር መያዝ ነበረበት፡፡ በአገራችን ሙያው ብዙም ያልታወቀና ቦታ ያልተሰጠው ነው፡፡ እንዲሁ ልብስ ሰፊ ተብሎ የሚታለፍ ነው፡፡ ነገር ግን ፋሽን ዲዛይን በውስጡ ብዙ ነገር አለው፡፡ ሁላችንም ዲዛይነሮች ሙያው እንዲታወቅ፣ እንዲወጣና እንዲጎለብት የማድረግ ፍላጎት አለን፡፡ ስለዚህ 11 ዲዛይነሮች ተሰባስበን ማኅበር ለማቋቋም ወሰንን፡፡ ሜኖናይት ኢኮኖሚክ ዴቨሎፕመንት (ሜዳ) የተባለው የውጪ የተራድኦ ድርጅት በመነሻችን ላይ ጠቅሞናል፡፡ ድርጅቱ የሚሠራው በሸማኔዎች ዙሪያ ነው፡፡ ለሸማኔዎች ገበያ ለማፈላለግ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ዲዛይነሮችን በተናጠል ያገኘን ነበር፡፡ የባህል ልብስ ስለምንሠራ ለእነሱ ሥራ እንድንሰጥ ያደርግ ነበር፡፡ በዛ ቡኩል ከድርጅቱ ጋር ተገናኘን፡፡ ሐሳባችንን ስንነግራቸው በጣም ደገፉን፡፡

ሪፖርተር፡–  ባለፈው ዓመት በኦሮሞ ባህል ማዕከል የፋሽን ሳምንት አዘጋጅታችሁ ነበር፡፡ ከዝግጅቱ ዓላማዎች አንዱ በአልባሳት ባለሙያዎች መካከል የገበያ ትስስር መፍጠር ነበር፡፡ ከጥጥ ፈታይ አንስቶ ሸማኔዎች፣ ዲዛይነሮችና ሌሎችም ባለሙያዎችን በማስተሳሰር ረገድ ያመጣችሁት ለውጥ ምንድነው?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ፕሮግራሙን ያዘጋጀነው ከሜዳና የባህልና ቱሪዝም ሚኒቴር ጋር ነበር፡፡ በተለይም የባህል ኢንዱስትሪ ልማት ዳይሬክቶሬት በጣም ደግፈውናል፡፡ ዛሬ የባህል ልብስ በዘመናዊ መልኩ ጥሩ እየሆነ እየወጣ ነው፡፡ ይሄ የመጣበት የራሱ የሆነ ሰንሰለት አለው፡፡ በፋሽን ሳምንቱ ጥጥ ሲፈተልና ተፈትሎ ድርና ማግ ሆኖ ሸማኔው ሲሸምን አሳይተናል፡፡ ከአምስት ክልሎች ሸማኔዎችን ከነሽመና መሣሪያቸው አምጥተን ሲሸመን ይታይ ነበር፡፡ ሸማኔዎቹ ራሳቸው ያመረቱትንም እዛው ሰቅለው ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ደግሞ የዲዛይነሮች ልብስ አምሮ ታይቷል፡፡ ማሳየት የፈለግነው ጥጥ ሲፈተል ጀምሮ ልብሱ አምሮ እስኪቀርብ ያለውን ነበር፡፡ በጣም ጠቅሞናል፡፡ ከክልል ከመጡ ሸማኔዎች ጋር የገበያ ትስስር መፍጠር ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡– ዲዛይነሮች በተደጋጋሚ የሚያነሱት ቅሬታ ማምረቻና ምርቶችን ማቅረቢያ ቦታ አለማግኘታቸውን ነው፡፡ ችግሩ ሙያውን ምን ያህል ተጭኖታል ምን ቢደረግስ መልካም ነው?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- የማምረቻ  ቦታ አለመኖር ጥራት እንዳንጠብቅ ያደርጋል፡፡ ማምረቻ ቦታ ሲኖረን ከጥሬ ዕቃው ጀምሮ ሽመናውንም ምርቱንም እናየዋለን፡፡ አሁን ግን የተበታተነ ነው፡፡ ሸማኔ ያለበት ቦታ ድረስ ሄደን የምናሠራው ቦታ ስለሌለን ነው፡፡ እዛ ስንሰጥ ደግሞ ክሩ በምንፈልገው ጥራት ላይወጣ ይችላል፡፡ ከሜዳ ጋር የማምረቻ ቦታ ለመጠየቅ ሞክረን ነበር፡፡ ዲዛይነሮች ጥሩ ሥራ ሠርተው ምርታቸውን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ይፈልጋሉ፡፡ ቦታ ከሌላቸው ይህን ለማድረግ የሚፈለገውን ጥራት ማምጣት አይችሉም፡፡ ዲዛይነሮች ቦታ ሲጠይቁ የንግድ ፍቃዳቸውን መልሰው ሥራ አጥ መሆናቸውን ማስረጃ አቅርበው በአነስተኛ ደረጃ መደራጀት እንዳለባቸው ይነገራቸዋል፡፡ ዲዛይነሮች ደግሞ ይህንን አይፈልጉም፡፡ ምክንያቱም ትንሽም ቢሆን ጀምረዋል፡፡ አሁን የሚፈልጉት የተሻለ ነገር እንጂ እንደገና ወደ ታች ለመመለስ አይደለም፡፡ ይህንን ለመፍታት ከፌዴራል ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ጋር ተነጋግረናል፡፡ በቀጣይ ዓርብ ትልቅ ስብሰባ ይኖረናል፡፡ መመሪያውን ለማሻሻል ወይም እኛን የሚመለከት እንዲሆን እንወያያለን፡፡ ጀማሪ ብቻ ሳይሆን ምርቶቻቸውን ውጪ የሚያሳዩና ፋሽን ሾው የሚያቀርቡም ባለሙያዎች አሉ፡፡ መንግሥት ባዘጋጀው መዋቅር ያለንበት ቦታ መታወቅ አለበት፡፡ እኛ የተሰበሰብነው የግል ሥራችንን ከማሳደግ አኳያ ብቻ ሳይሆን ምርታችንን በዓለም ገበያ አቅርቦ የኢትዮያን ገጽታ ማስተዋወቅ ነው፡፡ ሥራችንን ከማሳደግ ባሻገር ልማት ውስጥም ስለምንገባ መንግሥት ለእኛ የተለየ መስኮት እንዲኖረው እንጠይቃለን፡፡ የማምረቻ ቦታና ማቅረብያ ሊኖረን ይገባል፡፡ በእቅዳችን መሠረት ዋን ስቶፕ ሾፕ የተባለ ማዕከል ለማቋቋም ቦታ እንፈለጋለን፡፡ የኢትዮጵያን ድንቅ ሥራዎች ለማየት የሚመጡ የውጭ ዜጎች ያለ ምንም ችግር ወደ አንድ ማዕከል መሄድ አለባቸው፡፡ አሁን ሸሮሜዳ ወይም አስጎብኚዎች የሚወስዷቸው ቦታ ነው የሚሄዱት፡፡ ማዕከል ካለ ከእደ ጥበብ ጀምሮ ልብስ፣ ጌጣጌጥ፣ የባህል ቁሳቁስ ለማግኘት ቀጥታ ወደ አንድ ቦታ ይሄዳሉ፡፡ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም አዘጋጅተን ድጋፍ እንጠይቃለን፡፡ ቦታ ደግሞ ከመንግሥት እንፈልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡– የኢትዮጵያ ዲዛይነሮችና የአገሪቱ ምርቶች በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸው ተወዳዳሪነት ምን ይመስላል?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ከቀደመው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ትንሽ የተሻለ ነው፡፡ የእኛ አባላት ኒውዮርክ ፋሽን ሾው አሳይተው መጥተዋል፡፡ በሌሎችም የአውሮፓ አገሮች አሳይተዋል፡፡ ይሄ እኛ ከጀመርነበት ጊዜ አንፃር አንድ ለውጥ ነው፡፡ የዛሬ 20 ዓመት አካባቢ መጀመሪያ ፋሽን ሾው ሳሳይ ምንም አልነበረም፡፡ ዛሬ ስለፋሽን የተለየና ደስ የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ ጎልቶ የሚታይ ነገር ባይኖርም ለውጥ አለ፡፡ ድሮ ልብስ ሰፊ ተብሎ የተገደበውን ሙያ የሚፈልግ ወጣት አልነበረም፡፡ አሁን ግን በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ይሰጣል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይንን ትምህርት ቤት ስኬች ብቻ ነው እንጂ ትምህርት ተጀምሯል፡፡ ወጣቱ ሲመርጥ የፋሽን ትምህርት ቤት አማራጭ አለው፡፡ በውስጣቸው ተሰጥኦ ኖሯቸው የት ማውጣት እንደሚችሉ ለማያውቁ ወጣቶች ዕድሉ አለ፡፡ ለውጡ ደስ ይላል፡፡

ሪፖርተር፡– ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚሠሩ ዲዛይነሮች በተጨማሪ ውጭ አገር ከሚሠሩ ኢትዮጵያዊ ባለሙያዎች ጋር ምን ዓይነት ትስስር አላችሁ?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ቀደም ያሉ ትላልቅ ዲዛይነሮች ስለ ማኅበራችን አውቀዋል፡፡ አባል የሆኑም አሉ፡፡ በቅርብ ጊዜ ሌሎቹም እንደሚገቡ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ምክንያቱም በጣም እንፈልጋቸዋለን፡፡ እነሱ አሉ ማለት ለጀማሪው ተስፋ ነው፡፡ እውነት ፋሽን ቦታ እንደተሰጠው ያመላክታሉ፡፡ ድጋፍም ያደርጋሉ፡፡

ሪፖርተር፡–  በዓለም አቀፍ ገበያ ከሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ነፃ የሆኑና የተፈጥሮ ሁኔታን ያገናዘቡ ምርቶች ተቀባይነት ያገኛሉ፡፡ አልባሳት ይህን መስፈርት ተከትለው መመረታቸውን የሚያረጋግጥ ሌብል ለማግኘት እያደረጋችሁ ያለው ጥረት ከምን ደረሰ?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ከአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ጋር መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል፡፡ ምርቶች ከሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ነፃ መሆን አለባቸው፡፡ እንደ ዜጋ ሕፃናት ሲጎዱ ማየት ማንም አይፈልግም፡፡ የእኛ ልጆች ትምህርት ቤት እየሄዱ ሌላ ሕፃን ደግሞ በጨለማ ጉልበቱ ተበዝብዞ የሚመረተው ምርት ያንቀናል፡፡ የማምረቻ ቦታ ያላቸው ዲዛይነሮች አሉ፡፡ እንዲፈተሹ ጠይቀናል፡፡ በመመሪያው መሠረት ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በላይ ሆኖ መሥራት የሚችሉ ቢሆኑ እንኳን የመማሪያ ጊዜ እንዳላቸውና የሥራ ቦታቸው ጥሩ ስለመሆኑ መፈተሽ አለበት፡፡ ብርሃን ያለውና ብናኝ የሌለው ሆኖ ለጤንነታቸው አስጊ አለመሆኑ መፈተሽ አለበት፡፡ እኛ እንዲፈተሹ ዝግጁ ብንሆንም ማኅበራዊ ጉዳይ ዘግይተዋል፡፡ በቅርቡ ፍተሻው ተጀምሮ ከሕፃናት ጉልበት ብዘበዛ ነፃ መሆኑ ታይቶ ሰርተፍኬት ይሰጣል፡፡ ለወደፊት ሌብሉ ለኛ እንዲሰጠን እንፈልጋለን፡፡ በዓለም ገበያ ምርታችን ሲቀርብ ለምሳሌ አንድ ሻርፕ በኢትዮጵያ የተሠራ፣ መቶ በመቶ ኮተን ተብሎ ቢጻፍበትም ገበያውን ለመስበር ከሕፃናት ጉልበት ብዝበዛ ነፃ የሚል መግለጫ መግባት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡– በዲዛይነሮች ደረጃ ያሉ የፋሽን ባለሙያዎች ከዘርፉ የሚያገኙት ጥቅም እንደ ሸማኔዎች ካሉ ጥሬ ዕቃ አቅራቢዎች ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ነው፡፡ ባለሙያዎች መካከል ያለውን የጥቅም ክፍፍል ለማመጣጠን ምን መደረግ አለበት?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- አሁን እሱ ነገር መለወጡን አፌን ሞልቼ እናገራለሁ፡፡ ከዛ ቀደም  ብሎ ሸማኔዎችና አምራቾች በጣም ይጎዱ ነበር፡፡ በጥቂት ብር አምርተው እዚህ በብዙ ብር ይሸጣል፡፡ ትልቅ ክፍተት የፈጠረው እሱ ነበር፡፡ አሁን ሸማኔ የሚጠይቀው ዋጋ ዲዛይነር ከሚሸጠው ዋጋ እኩል ነው፡፡ እውነት ለመናገር ሸማኔዎች ዋጋቸውን ሊያገኙ ይገባል፡፡ በጣም የተጎዳ ሙያ ነው፡፡ እነሱ የሚሠሩት ጥበብ ያስደንቃል፡፡ ትናንት ለተጎዱ ማኅበረሰቦች ዛሬ መከፈሉ ምንም አያጠያይቅም፡፡ መጨመር ሲባል ግን አላስፈላጊ ጭመራ ላይ መጣ፡፡ ይሄ የአገሬን ምርት እለብሳለሁ የሚለውን ሰው ቦታ ያሳጣል፡፡ ዛሬ የሐበሻ ልብስ የሚለብስ ኢትዮጵያዊ ብዙ ሺሕ ብር ማውጣት የሚችል እየሆነ ነው፡፡ በጣም አስፈሪ ደረጃ ላይ ነው ያለነው፡፡ ሸማኔውም አምራቹም በአግባቡ መጠቀም አለበት፡፡ በቅርቡ ከሐብ ኦፍ አፍሪካ ጋር የምናዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ ‹‹ዘ ትሩ ኮስት›› (እውነተኛ  ዋጋ) የሚል ጉዳይ እናነሳለን፡፡ አምራቹ የሚወስድበት ጊዜና ዲዛይነሩ ጋር መጥቶ እሴት ሲጨመርበት ምን ያህል ያወጣል ስለሚለው እንወያያለን፡፡ ሌላው ያስቸገረን ነገር ጥራት ነው፡፡ የፋብሪካ ክር ጥራት እየወረደ ነው፡፡ የዛሬ አሥር ዓመት እሠራበት የነበረው ድርና ማግ ዛሬ የለም፡፡ አንድ ዓይነት ቀለም ክር ሲጠፋ ዋጋው በእጥፍ ይጨምራል፡፡ ሸማኔው ክር በእጥፍ ገዝቶ ሠርቶ እንዴት በርካሽ ይሸጣል? አምራቹ በዕቃ እጥረት ይቸገራል፡፡ መጀመርያ ከአምራቹ ጋር ከተነጋገርንበት ዋጋ በበለጠ ጥሬ ዕቃዎች ላይ ሲጨመር አምራቹም ይጨምራል፡፡ ስለምንግባባ እየተነጋገርን እየሄድን ነው እንጂ የአቅርቦት እጥረት ፈታኝ ነው፡፡ ዲዛይነሩም አምራቹም ጋር እውነተኛ ዋጋ መኖር አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ አና ጌታነህ ያሉ ዓለም አቀፍ ሞዴሎች የሚያዘጋጁዋቸው ዓመታዊ የፋሽን ትርዒቶች አሉ፡፡ የጨርቃ ጨርቅና ዲዛይን ዐውደ ርዕዮችም በተወሰነ ጊዜ ልዩነት ይዘጋጃሉ፡፡ እነዚህ ዓለም አቀፍ መድረኮች ለፋሽን ዲዛይነሮች ምን ዕድል ፈጥረዋል?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- በጣም ዕድል ከፍተዋል፡፡ ከፋሸን ዲዛይነሮች ማኅበር ቀደም ብለው  ከሐብ ኦፍ አፍሪካ ጋር ጥሩ ግንኙነት የፈጠሩ አሉ፡፡ ዲዛይነሮች ሥራዎቻቸውን ከአና ጌታነህ ጋር ያቀርባሉ፡፡ አብረን ስንሠራ ግሞ የበለጠ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የባህል ፖሊሲው የፋሽን ዲዛይነሮች የሚበረታቱበት ዕድል ፈጥሯል ብለሽ ታምኛለሽ?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- ሁሉም ነገር የተመቻቸ ነው ለማለት አልችም፡፡ በሩ ግን ተከፍቷል፡፡ በሩን የማንኳኳት ዕድል አለን፡፡ የተመቻቸ የሚባለው ክፍተታችን ሲደፈንና የሚገጥሙን ችግሮች ሲቀረፉልን ነው፡፡ ይህንን ለማስተካከል የፊታችን ዓርብ ስብሰባ አለን፡፡ ፖሊሲው ተሻሽሎ ዲዛይነሮችንም ያማከለ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በሩን ከፍቶልናል፡፡ ለወደፊትም የሚመቻችልን ነገር ይኖራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የተመቻቸ ነገር አለ ለማለት አልደፍርም፡፡ እኛም ፖሊሲው ላይ መሻሻል አለባቸው የምንላቸው ነገሮችን ማለትም ከማምረቻ ቦታ ጀምሮ ማቅረቢያ ቦታ  ማጣትንና ሌሎች ችግሮቻችንን ያካተቱ ሐሳቦች እናቀርባለን፡፡ በሥርዓተ ትምህርቱ የፋሽን ዲዛይን ትምህርት መግባት አለበት፡፡ የፋሽን ዲዛይን ተሰጥኦ ነው፡፡ የስፖርትና የሥዕል ክፍለ ጊዜ እንዳለው የፋሽንም መኖር አለበት፡፡ የፋሸን ትምህርት ክፍል በኮሌጆች እንዲኖር የመጠየቅ ሐሳብም አለን፡፡

ሪፖርተር፡– በዲዛይነሮች የሚሠሩ የአገር ባህል አልባሳት የኢትዮጵያን ባህል የሚወክሉ ናቸው?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- እየሄድን ያለነው ወደሱ ነው፡፡ አሁን ወደ ዘመናዊው እያመጣነው ነው፡፡ በግብዓት ደረጃ የሁሉንም ብሔረሰብ ጥሬ ዕቃ እንጠቀማለን፡፡ ዘመናዊ ስናደርገው ለውጥ አለ፡፡ ለምሳሌ በደቡብ ዙሪያ ያሉ አካባቢዎች ሠርተው የሚያወጧቸውን ምርቶች ቀሚስና ጃኬት እናደረጋቸዋለን፡፡ ፋሽን ጋር ሲመጣ ባህሉን እንደ መነሻ እንወስደውና ዲዛይን አድርገን እናወጣዋለን፡፡ መነሻችን ግን የብሔር ብሔረሰቦች ልብስ ነው፡፡ ለዚህ ጉዳይ በደንብ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡

ሪፖርተር፡- የዲዛይነር ልብሶች ዋጋ መወደድ አልባሳቱን የጥቂቶች ምርጫ ብቻ እንዲሆኑ እያደረጋቸው ነው፡፡ በሌላ በኩል የፋሽን ዘርፍ በተለያዩ መንገዶች ለውጥ እያሳያና ዕድገቱም እየጨመረ መጥቷል፡፡ አልባሳቱን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግና የዘርፉን ዕድገት በማመጣጠን ረገድ ምን ሊደረግ ይገባል?

ወ/ሮ እጅጋየሁ፡- የዋጋ አወጣጡንና የምርት ሒደቱን ስናይ የአገር ልብስን ዘወትር እንዲለበስ ከማድረግ አንፃር ነው፡፡ ከጥራት ጋር ጥንካሬ ካለ ለምን የአገር ባህል ልብስ የዘወትር አይሆንም የሚለውን እያጠናንነ ነው፡፡ ለጤናም የሚመጠረው የኛ ምርት ነው፡፡ ፖሊስተርና ከተረፈ ምርት የሚሠሩ ላይነኖች ለቆዳ ችግር ያጋልጣሉ፡፡ ስለዚህ ባህላዊ ልብሶቹ በርካሽ ተሠርተው በቀላሉ መቅረብ አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በደንብ ዋጋ የሚያስወጡ ምርጥ ዲዛይነሮችም ሊኖሩን ይገባል፡፡ ለሠርግ፣ ለክብረበዓል ወይም እንዲሁ የወደድናቸው ልብሶች በዲዛይን ይሠራሉ፡፡ እነዚህ ዋጋቸው ከፍ ያለ ይሆናል፡፡ ሁለቱን የምናስታርቀው በጣም ስንፈልጋቸው ዋጋ አውጥተን የምንጠቀምባቸውና መካከለኛ ሆነው ደግሞ ለሥራ የሚለበሱ ሲኖሩ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ዋጋው ተወደደ ይላል፡፡ እውነት ነው ተወዷል፡፡ ለበዓልና ለሠርግ ብቻ ሳይሆን ቀለል ያለ ቦታ በትንሽ ዋጋ አሳምሮ ማቅረብ የኛ የዲዛይነሮች ኃላፊነት ነው፡፡

 

 

 

                

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...