Wednesday, July 24, 2024

ከአረንቋ ውስጥ መውጣት የሚቻለው በዳበረ አስተሳሰብ ነው!

ኢትዮጵያ ለዘመናት ከተዘፈቀችበት አረንቋ ውስጥ ለመውጣት የምትችለው፣ ያለንበትን ዘመን የሚመጥን አስተሳሰብ የብሔራዊ ጉዳዮች ማዕከል ማድረግ ሲቻል ነው፡፡ በትምህርት፣ በዳበረ ልምድና በቴክኖሎጂ ምጥቀት የሚታገዘው የዘመኑ አስተሳሰብ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሰብዓዊ ፍጡራን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ ወይም በሌሎች ልዩነቶች ሳይገደቡ በእኩልነት ተሳትፎ የሚያደርጉበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባውም፣ ሁሉንም ሰዎች በሰብዓዊ ፍጡርነታቸው ማስተናገድ የሚችል አስተሳሰብ ጎልቶ ሲወጣ ነው፡፡ ይህ ዘመናዊና ተራማጅ አስተሳሰብ ከሌብነት፣ ከሥርዓት አልበኝነት፣ ከዘረኝነት፣ ከጨለምተኝነትና ከመሳሰሉት እኩይ ድርጊቶች የፀዳ ስለሚሆን ለሰላም፣ ለዴሞክራሲና ለብልፅግና ቁልፍ ሚና አለው፡፡ ከጭቆና ይልቅ ለነፃነት፣ ከዘረፋ ይልቅ ለፍትሐዊ ክፍፍል፣ ከአድልኦ ይልቅ ለእኩልነት፣ ከጉልበት ይልቅ ለፍትሕ፣ ወዘተ በጣም የቀረበ በመሆኑ ለአገር ፍቱን መድኃኒት ነው፡፡ በሐሜትና በአሉባልታ ሳይሆን በመረጃና በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የጠፋው ይህ ዓይነቱ የዳበረ አስተሳሰብ ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም በርካታ አሳዛኝ ነገሮች በማጋጠማቸው አገር ከክብሯና ከማዕረጓ ወርዳለች፡፡ አሁን ግን ከዚያ አረንቋ ውስጥ መውጣት የግድ ይላል፡፡

የሥልጣኔ ፋና ወጊ ከሆኑት ቀደምት አገሮች አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ ገጽታዋ ተበላሽቶ የበርካታ አሳዛኝ ድርጊቶች ተምሳሌት ብትደረግም በዚህ ዘመን ግን ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ወደፊት መንደርደር ያዋጣል፡፡ ምንም እንኳ በፖለቲካው መንደር ውስጥ የሚታየው ውዥንብርና ምስቅልቅል ወገንን ከወገኑ ለጊዜው ቢያጋጭም፣ ከዚህ ማጥ ውስጥ መውጣት እንደሚቻል ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ያስተምራል፡፡ አስተዋዩ ሕዝብ እርስ በርሱ እንዴት አብሮ እንደሚኖር በሚገባ ያውቃል፡፡ አንዱ ለሌላው መከታ ሆኖ መኖር ለሕዝባችን ብርቅ አይደለም፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች በየሥፍራው የሚጫር እሳት ቢኖርም፣ በሕዝባችን አርቆ አሳቢነት ፍሙ ወደ አመድነት እንደሚቀየር የታወቀ ነው፡፡ የሕዝባችንን አገር በቀል ዕውቀትና የጋራ እሴቶች ምርኩዝ በማድረግ ዘመናዊውን የዳበረ አስተሳሰብ ማከል ከተቻለና በክፋት ላይ ቀናነት የበላይነት ከያዘ የማይታለፍ ችግር አይኖርም፡፡ ከምንም ነገር በላይ የአገር ህልውና ስለሚቀድም የጎንዮሽ መገፋፋቶችን በማስወገድ፣ የጋራ የሆኑ ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ከአረንቋው ውስጥ መውጣት ግዴታ መሆን አለበት፡፡

በገዛ ወገን ደም የቆሸሸ እጃቸውን እየተለቃለቁ ሌላ ዙር ግጭት በመቀስቀስና የተዛቡ መረጃዎችን በመልቀቅ አገር ማተራመስ ከሕዝብ ጋር ያጣላል፡፡ ከሕዝብ የሚደበቅ ምንም ነገር ስለሌለ ማታለል አይቻልም፡፡ በጨለማ የተፈጸመን ወንጀል እንደ ፀሐይ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ሕዝብ ማንም አያታልለውም፡፡ የታሪክ መልካም ነገሮችን ለአሁኑ ዘመን መልካም ሥራዎች ስንቅ ማድረግ፣ አሳዛኝ ክስተቶችን ዳግም እንዳያንሰራሩ ምዕራፋቸውን መዝጋት ይገባል፡፡ ያለፉት ዘመናትን ክፉ ሥራዎች እያራገቡ በዚህ ዘመን የባሰ ድርጊት ለመፈጸም ከመንሰፍሰፍ፣ ለዘመኑ የሚመጥን ታሪክ መሥራት ያስከብራል፡፡ በቴክኖሎጂ ምክንያት ዓለም እየጠበበች የመገናኛ ድልድዮች በበዙበት በዚህ የመጠቀ ዘመን፣ ራስን ጉድጓድ ውስጥ እንደተደበቀች እንቁራሪት ለማግለል መሞከር ወይም መጥበብ አይበጅም፡፡ በተለይ ወጣቶች በማኅበራዊም ሆነ በመደበኛ ሚዲያዎች አማካይነት ፈጣን መረጃዎችን በሚለዋወጡበት በዚህ ዘመን፣ ለዕድገታቸውና ለስኬታቸው የሚበጅ ዕገዛ ከማድረግ ይልቅ በሐሰተኛ ወሬዎች በማደናገር አገር ላይ እሳት ለማዝነብ መፍጨርጨር ሊወገዝ ይገባዋል፡፡ ለኢትዮጵያዊያን የማይመጥኑ ድርጊቶች ይወገዱ፡፡ ምክንያቱም አገር በለውጥ ሒደት ላይ ናትና፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ጋር በነበራቸው ቆይታ ከተናገሯቸው ቁም ነገሮች መካከል አንዱ፣ እሳቸው ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ከያዙዋቸው ዓላማዎች ዋነኛው የሚቀጥለው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ሆኖ የኢትዮጵያ ሕዝብ በድምፁ በመረጠው መንግሥት መተዳደር መጀመሩን ማረጋገጥ እንደሆነ ነው፡፡ ይህ እጅግ የተመሠገነና ይበል የሚያሰኝ አስተያየት ሲሰማ መምህራኑ ከመቀመጫቸው ተነስተው በደስታ ማጨብጨባቸው በራሱ ብዙ ይናገራል፡፡ ኢትዮጵያን በመሰለች ታላቅ አገር የይስሙላ ምርጫዎች እየተካሄዱ የደረሱትን አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊቶች፣ በእንዲህ ዓይነት ወሳኝና ዘመኑን የሚመጥን ተግባር መቀየር እንደሚገባ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ ውስጥ ምን ያህል የማደግ፣ የመለወጥና የመዘመን ፍላጎት እንዳለ አነስተኛው ማመላከቻ ነው፡፡ ፍትሐዊ፣ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲኖር ግን በግራና በቀኝ የሚያወላክፉ መሰናክሎች መነሳት አለባቸው፡፡ ትልልቅ አገራዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ ውኃ የማያነሱ ጥቃቅን ነገሮች ላይ ውሎ ማደር ለአገር ፋይዳ የለውም፡፡ አገር የምትለወጠው በምክንያታዊ አስተሳሰብ እንጂ በስሜታዊነት አይደለም፡፡

የምክንያታዊነት አስፈላጊነት ስህተት ሲሠራ ለማረም፣ መልካም ክንውኖችን ለማበረታታት፣ ያልታዩ ምልከታዎችን ዕድል ለመስጠት፣ በተቻለ መጠን ስህተቶችን ላለመደጋገም፣ ወዘተ ነው፡፡ ለውጥ በምክንያትዊነት ሲመራ ለግልጽነትና ለተጠያቂነት ልዩ ቦታ ይሰጣል፡፡ ስሜታዊነትን ግን እንኳን ለመጠየቅና ለማሰላሰል የደረሰ መረጃን ለማመዛዘን ዕድል አይሰጥም፡፡ በዚህ ዘመን በስሜታዊነት የሚነዱ ሰዎች አንድም ዕውቀት ካልሆነም ማስተዋል ይጎድላቸዋል፡፡ ከእነሱ በስተጀርባ የሚሠለፉት አውቆ አጥፊዎች ደግሞ ውስጣቸው በቂምና በጥላቻ የተመረዘ በመሆኑ የጥፋት እጃቸውን በየአቅጣጫው ያስረዝማሉ፡፡ ከአገር በፊት ራስን ማስቀደም ውጤቱ ተያይዞ መጥፋት ይሆናል፡፡ ይህ ዓይነቱ አሳሳቢ ችግር ሲያጋጥም ከቤተሰብ እስከ መንግሥት ድረስ ነቃ ማለት ይገባል፡፡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ተደማጭነት ያላቸው ልሂቃን ደግሞ ግንባር ቀደም መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ለአገር የሚጠቅም ዘመኑን የሚመጥን አስተሳሰብ ወደ ወጣቱ የማስረፅ ኃላፊነትንም መረከብ አለባቸው፡፡ ዳር ሆኖ ከንፈር እየመጠጡ ‹ይህች አገር ወዴት እየሄደች ነው?› ብሎ ማላዘን ከጥፋት ድርጊት አይተናነስም፡፡

ኢትዮጵያ ያሉባት ችግሮች ተዘርዝረው አያልቁም፡፡ አንዱ ከሌላው የበለጠ በደል ደርሶብኛል ብሎ ችግሮችን አግዝፎ ቢያቀርብ፣ ሌላውም ከእሱ የበለጠ ሰቆቃ እንዳለው መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ወደ ኋላ እየተጎተቱ ወደ ፊት መራመድ እንደማይቻለው ሁሉ፣ ለውጥን እየተመኙ ከለውጥ በተቀራኒ መሽከርከርም ፋይዳ የለውም፡፡ ይህ ዘመን ብዙ ጥያቄዎች አሉት፡፡ እያንዳንዱ ሰው ራሱን በግሉ ቢጠይቅ ለአገር ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ ጀምሮ እስከ የገዛ ራሱ አኗኗር ድረስ ለምን? እንዴት? የት? መቼ?…የመሳሰሉ ጥያቄዎች አሉበት፡፡ የዘመኑ ምጡቅ አስተሳሰብ የሚመራውም በዚህ መንገድ ነው፡፡ ከመንገድ ላይ እንደተቆረጠ መፋቂያ ያገኙትን መረጃ ሳይተነትኑ መጉረስ አደጋ አለው፡፡ መተቸትና መሞገት የሚቻለው በተጣራ መረጃ ላይ መመሥረት ሲቻል ነው፡፡ ዘመኑ ደግሞ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የበለፀገ ስለሆነ ያግዛል፡፡ አገር ለማደግ ከሚያስፈልጓት ሁነኛ መሣሪያዎች መካከል ደግሞ አንዱ መረጃ ነው፡፡ የተጣራ መረጃ ለአገር ፍቱን መድኃኒት ሲሆን፣ ያልተጣራው ግን መርዝ ነው፡፡ አገር ከአረንቋ ውስጥ የምትወጣው በዳበረ አስተሳሰብ ነው የሚባለው ለዚህ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከእንቆቅልሽ ጨዋታ ውስጥ ውጡ!

በወርኃ ሚያዝያ ተካሂዶ የነበረው ውይይት ቀጣይ ነው የተባለው መድረክ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የተፎካካሪ ፓርቲዎችን እንደገና ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. አገናኝቶ ነበር፡፡ መንግሥትን የሚመራው...

ለልዩነት ዕውቅና የማይሰጥ ፖለቲካ ፋይዳ ቢስ ነው!

በፍርኃትና በሥጋት የተኮማተረ አገር ለመለወጥም ሆነ ለማደግ ዝግጁ መሆን አይችልም፡፡ አጉል ድፍረትና ምግባረ ብልሹነት በተንሰራፋበት ስለነፃነት መነጋገር አይቻልም፡፡ ፍርኃት እንደ ወረርሽኝ አገር ምድሩን አዳርሶ...

ለሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎቶች ልዩ ትኩረት ይሰጥ!

በዚህ ዘመን ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ ነገሮች ብዛታቸው እየጨመረ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን መሠረታዊ የሚባሉ ፍላጎቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሊቸራቸው ይገባል፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ...