Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየደብረ ማርቆስ ማረሚያ ቤት ተቃጠለ

የደብረ ማርቆስ ማረሚያ ቤት ተቃጠለ

ቀን:

የቃሊቲ ማረሚያ ቤት እስረኞች ተቃውሞ እያሰሙ ነው

በአማራ ክልል የምሥራቅ ጎጃም ርዕሰ ከተማ ደብረ ማርቆስ ማረሚያ ቤትን እስረኞች ማክሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ማቃጠላቸው ተገለጸ፡፡

በማረሚያ ቤቱ ውስጥ የሚገኙ ከ1,200 በላይ የሚሆኑ ፍርደኞች፣ ተከሳሾችና ተጠርጣሪዎች መሀል ማረሚያ ቤቱን ያቃጠሉት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የምሕረት አዋጁን በሚመለከት ሐምሌ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ያስተላለፈውን ማብራሪያ በቴሌቪዥን ካዩ በኋላ እንደሆነ ታውቋል፡፡

- Advertisement -

የማረሚያ ቤቱ የጥበቃ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ገደፋው አስራት ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ‹‹እስረኞቹ ዓብይ አህመድ እንድንፈታ ወስኗል፣ ልቀቁን፤›› በማለት በአንድ ተከሳሽ አስተባባሪነት ሰኞ ሐምሌ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ሌሊቱን ሲበጠብጡ ነበር ያደሩት፣ በነጋታው ሐምሌ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ከጠዋቱ አንድ ሰዓት አካባቢ 20 የሚሆኑ ማደሪያ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ በእሳት ማቃጠላቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

እስረኞቹን በማስተባበር ችግሩ እንዲከሰት ያደረገው ተጠርጣሪ በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎችም በወንጀል የሚፈለግ እንደሆነና የፌዴራል መንግሥትም ተላልፎ እንዲሰጥ ጥያቄ ያቀረበበት መሆኑን ጠቁመው፣ በአማራ ክልልም በርካታ ክሶች ተመሥርተውበት ገና በሒደት ላይ ያለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የወደመው ንብረት ግምት ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ አሁን ትልቅ ችግር የሆነው እስረኞቹ የት ይሆናሉ የሚለው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ የማረሚያ ቤት ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ውቤ ወንዴን ጨምሮ አሥር አባላት በጉዳዩ ላይ እየተወያዩ መሆኑን፣ እስረኞቹ እንዳያመልጡ ልዩ ኃይልና የክልሉ ፖሊስ ሆነው በጋራ እየጠበቁ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡   

ይህ በእንዲህ እንዳለ በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የቃሊቲ ማረሚያ ቤት እስረኞች፣ ማክሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ተቃውሞ ሲያሰሙ ውለዋል፡፡

‹‹እኛም በምሕረት አዋጁ ልንካተት ይገባል፡፡ ከእስር መፈታት አለብን፤›› በማለት ሲጮኹና ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ መዋላቸውን ቤተሰቦቻቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱ ባይታወቅም ከጠዋቱ አንድ ሰዓት አካባቢ የተኩስ ድምፅ ይሰማ እንደነበር ከአካባቢው ነዋሪዎች የሰሙት የታሳሪ ቤተሰቦች፣ ችግሩ ምን እንደሆነ ለማጣራት ቢፈልጉም፣ በአካባቢው የነበሩ የፖሊስ አባላት ከክራውን ሆቴል አካባቢ እንዳያልፉ እንደከለከሏቸው ተናግረዋል፡፡

ለታሳሪዎች ምግብ ለማድረስ የሄዱ ቢሆንም፣ ‹‹ዛሬ ማስገባት አትችሉም፤›› በመባላቸው በአካባቢው ቆይተው ከቀትር በኋላ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ወደ ቤታቸው መመለሳቸውንም ገልጸዋል፡፡

በርቀትም ቢሆን የእስረኞቹ ድምፅ ይሰማቸው ስለነበር ተጨንቀው መዋላቸውንና ግራ እንደገባቸውም ተናግረዋል፡፡ ውስጥ ምን እንደተፈጠረና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ለማጣራት አለመቻላቸውን ገልጸው፣ ቢያንስ ደህና ስለመሆናው የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ለምን መናገር እንደማይፈልጉ እንዳልገባቸው አስረድተዋል፡፡

በማረሚያ ቤቱ አድማ በታኝ ፖሊሶች፣ የእሳት አደጋ ተሽከርካሪዎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ አባላትና የማረሚያ ቤቱ ፖሊሶችን ማየታቸውንም አክለዋል፡፡

በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ምን እንደተፈጠረ ማብራሪያ እንዲሰጡ የማረሚያ ቤቱን ኮሙዩኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገረመው አያሌው ሪፖርተር አነጋግሯቸው፣ ‹‹እኔ ገና መመደቤ ነው፡፡ አዲስ በመሆኔ ስለተቋሙ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ገና ዕቃም አልተረከብኩም፡፡ ኃላፊዎቹ በሙሉ አዲስ ስለሆንን በዚህ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ መስጠት ያስቸግረናል፤›› በማለታቸው ምላሽ ማግኘት አልተቻለም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...