Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተወደሱበት ዝክረ ልደት

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የተወደሱበት ዝክረ ልደት

ቀን:

‹‹ባለፉት አምሳ ያህል ዓመታት የአገራችንን ታሪክ በመከለስ፣ በመበከልና በማንኳሰስ የቀድሞ ነገሥታት መሪዎቻችን በጎ አስተዋጽኦዎች እንዲጣጣሉና እንዲረሱ ያላሰለሰ ዘመቻ ተካሂዷል፡፡ በተለይ የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ስም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ልብ አልወጣም ብሎ አስቸገረ እንጂ፣ ይጠሩበት ከነበሩት ተቋሞች ስያሜም ቆይተዋል፡፡›› ይህንን ስለ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ምስክርነት የሰጡት በቅርቡ በአሜሪካ የማኅበር ግዮራን ዘረ ኢትዮጵያ 26ኛ ዓመታዊ በዓል ላይ የተገኙት ዶ/ር ዳዊት ዘውዴ ናቸው፡፡

እንደ ዶ/ር ዳዊት አገላለጽ፣ ለረዥም ዘመን መሪዎችና ነገሥታቱ ኢትዮጵያን በነፃነቷና በአንድነቷ ጠብቀው አቆይተዋል፡፡ በዘመኑ በነበረው ሥርዓት የአገር አስተዳደርን በማስፈንና የሕዝቡንም ኑሮ በማጎልበት ረገድ ጊዜያቸው ያስቻላቸውን ፈጽመው አልፈዋል፡፡ መዘከር የሚገባቸውም በነበሩበት ዘመን ልክ መሆን አለበት፡፡

የአፄ ኃይለ ሥላሴ ስም ከተፋቀባቸው ተቋማት መካከል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ፣ ብሔራዊ ቴአትር፣ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ የካቲት ሪፈራል ሆስፒታልና ሌሎችም ይገኙባቸዋል፡፡ የመጀመርያዎቹና ፋና ወጊዎች የበጎ አድራጎትና ሽልማት ድርጅቶች እንዲፈርሱና የገቢ ማስገኚያቸው የነበሩ ልዩ ልዩ ንብረቶች በአዋጅ መወረሳቸው የንጉሠ ነገሥቱ የበጎ አስተዋጽኦቸው እንዲረሱ ወይም እንዲጣጣሉ ከተደረጉት ተግባራት መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ታሪክ በአገር ውስጥና በውጭ የታሪክ ምሁራንና የሥነ ፖለቲካ ጸሐፊዎች በሰፊው ተዘክሯል፡፡ ተነግሯልም፡፡ ተጨልፎ የማያልቅ ምንጭ ነውና ይህ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ በሕይወት በነበሩባቸው ዘመናት በጣሉት ፅኑ መሠረት ላይ በመቆም በጎ በጎውን ይዞ የሚንቀሳቀስና በስማቸው የተሰየመ ማኅበርም ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ውሎ አድሯል፡፡

የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ ሊቀ ካህናት ዓባይነህ አበበ እንደገለጹት፣ የማኅበሩ የትኩረት አቅጣጫው በአካባቢው የልማት የበጎ አድራጎት ሥራዎችን ማከናወን፣ ትምህርታቸውን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) ገብተው ለመማር አቅም በማጣት ያልቻሉትን ዜጎች ስኮላርሺፕ መስጠትና ማስተማር ይገኝበታል፡፡

በኢትዮጵያ የዕድገትና ልማት ምርምርና ጥናት ለሚያካሂዱ ድኅረ ምረቃን ድጋፍ መስጠት፣ እጅግ ዘመናዊ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር፣ ማቋቋምና መርዳት፣ ድንቁርናን፣ በሽታን፣ ድህነትንና ሥራ አጥነትን መዋጋት የትምህርትና የሥልጠና ተቋማትን ማደራጀትና ማቋቋም ከትኩረት አቅጣጫዎች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ 126ኛ ልደት ዝክረ በዓል እሑድ ሐምሌ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በዋቢ ሸበሌ ሆቴል በተከበረበት ሥነ ሥርዓት ላይ ሰብሳቢው እንዳብራሩት፣ እስካሁን ድረስ በኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማነት ብቻ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ያልቻሉ ከ300 በላይ ተማሪዎችን ማኅበሩ ስኮላርሺፕ በመስጠት በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ሠልጥነው ለምረቃ እንዲበቁ አድርጓል፡፡ በዚህ ዓመትም ከ120 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡

ይህንን ሁሉ ሥራ  ማኅበሩ ያከናወነው ዓላማውን ለአባሎቹ በማሳወቅና ድጋፍ እየጠየቀ በተገኘ የገንዘብ ዕርዳታ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱን የትምህርት ድጋፍ የሚሹ ተማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ መሄዱንና የተጠየቀውንም ድጋፍ ለመቀጠል የማኅበሩ አቅም እንደማይፈቅድ ወይም የአቅም ማነስ ችግር እንደተጋረጠበት ነው የተናገሩት፡፡

ወገን ለወገን ደራሽ ነውና እያንዳንዱ የማኅበሩ ደጋፊ አንድም ሁለትም ተማሪ እናስተምራለን የሚል ቃል እንዲገቡ ተማጽነዋል፡፡ ከዚህም ግንዛቤ በመነሳት ከማኀበሩ አባል ደጋፊዎች ከ2.3 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ገንዘብ ውስጥ አቶ ዓለሙ ታፈሰና አቶ በቀለ ኃይሌ እያንዳንዳቸው አንድ ሚሊዮን ብር፣ ወ/ሮ ዓይዳ ኃይለ ማርያም 175,000 ብር፣ ዳዊት ዘውዴ (ዶ/ር) እና ወ/ሮ ብርሃኔ የራስወርቅ በነፍስ ወከፍ 50,000 ብር፣ እንደሁም አቶ ጌታቸው ቅጣውና ወ/ሮ አስካለ በንቲ እያንዳንዳቸው 25,000 ብር ለግሰዋል፡፡

የማኅበሩ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር ዳዊት ዘውዴ እንደተናገሩት፣ ማኅበሩ ያጋጠመውን የአቅም ማነስ ችግር ለመወጣት ብቸኛው መፍትሔ የተወረሱ የበጎ አድራጎት ድርጅት ንብረቶች እንዲመለሱለት ማድረግ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ንብረቶቹ እንዲመለሱለት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በተደጋጋሚ ጊዜ በደብዳቤ ያቀረባቸው ጥያቄዎች የውኃ ሽታ ሆነው ቀርተዋል፡፡ ወይም ንብረቶችን ለማስመለስ እስካሁን ድረስ የተደረገው ጥረት ውጤት አላስገኘም፡፡

የቀድሞ ፕሬዚዳንትና የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ‹‹የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ሐውልት የሌኒን ሐውልት ቆሞበት በነበረው ቦታ ላይ ለማቆም የሚያስችል አንዳንድ እንቅስቃሴ በመከናወን ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በዋቢ ሸበሌ የስብሰባ አዳራሽ በተከናወነው በዚሁ ሥነ ሥርዓት ላይ ንጉሣውያን ቤተሰቦች፣ በቀድሞው ሥርዓት አገራቸውን በልዩ ልዩ የኃላፊነት ቦታ ላይ ያገለገሉ አረጋውያን፣ የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች፣ ሁለገብ የዓይነ ሥውራንና አካል ጉዳተኞች ማሠልጠኛና ማቋቋሚያ ማዕከል አባላት፣ ወጣቶችና ወይዛዝርቶች ታድመዋል፡፡ የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት የቀድሞ ተማሪዎች ማኅበር አፄ ኃይለ ሥላሴ በአፀደ ሥጋ በነበሩባቸው ዘመን ለአገሪቱ ዕድገትና ብልፅግና የተጫወቱትን አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ትግሎች የሚያንፀባርቅ በሙዚቃ የታጀበ ድራማና ሥነ ግጥም አቅርበዋል፡፡  

ከዚህም ሌላ በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያቋቋሙት የማኅበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ 26ኛ ዓመታዊ በዓል በዋሽንግተን ዲሲ ግንቦት 19 ቀን 2010 ዓ.ም. በተከበረበት ሥነ ሥርዓት ዶ/ር ዳዊት ስለ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ የሰጡትን ምስክርነት የሚያስረዳ መጽሔትና በራሪ ጽሑፎች ለታዳሚዎቹ ታድሏል፡፡

መጽሔቱ ላይ ከሠፈረው ምስክርነት ለመረዳት እንደተቻለው፣ የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን አስተዋይነትና ብልህነትን የተላበሰ ዓላማ ለማሳየት አራት የአገልግሎት ዘርፎችን ለአብነት ያህል ጠቁመዋል፡፡ ዘርፎቹም ዘመናዊ ብሔረ መንግሥት ግንባታ፣ የትምህርት ዕድገት መስፋፋት፣ የውጭ ግንኙነቶች ጥንካሬና የልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዕድገት ናቸው፡፡ አርቀው ካስቡበትና ከተለሟቸው ተግባራት ቀዳሚው የተሟላ ብሔረ መንግሥት ግንባታ ላይ ያነጣጠረ ሥራቸው ነው፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ብልጭ ብሎ በሚታየው የተስፋ ድባብ ጭምር ተነሳስተን ታሪካችንን ለማደስ የጥላቻ ፖለቲካን እናስወግድ፡፡ ችግሮቻችንን ደረጃ በደረጃ በዕውቀትና ብልህነት በታገዘ አመራር እየፈታን፣ ጃንሆይ በጣሉት ፅኑ መሠረት ላይ በመቆም በጎ በጎውን ይዘን እንድንጓዝ ጥሪዬን አቀርባለሁ፤›› ማለታቸውን መጽሔቱ አመልክቷል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...