Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርኢትዮጵያና ኤርትራ ያሏቸው ተመሳሳይ ረቂቅና ተጨባጭ የባህል ቅርሶች

ኢትዮጵያና ኤርትራ ያሏቸው ተመሳሳይ ረቂቅና ተጨባጭ የባህል ቅርሶች

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

ውድ የዚህ ጋዜጣ አንባቢያን ሁኔታዎች ለኅብረተሰቡ ጥሩ ሲሆኑ ጊዜ በእጅጉ ፈጣን መሆኑን ከኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ ከጥቂት ወራት በፊት የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት በጥርጣሬ ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ ዛሬ ግን ያ ጊዜ እንደ ጥላ ውልብ ብሎ አልፎ የምናወሳው በመተማመን ላይ ስለተመሠረተ ግንኙነት ሆኗል፡፡ ከትናንት ትውስታዎቻችን መካከል ‹‹የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች›› ማለት ራሱ አገሮችን በኃይል አንድ ከማድረግ ጋር እየተያያዘ ይመጣ ስለነበር፣ ለአንድ ጸሐፊ ጉዳዩ በስሱ የሚያዝና በጥንቃቄ የሚነገር ነበር፡፡ ጸሐፊው ‹‹የሰላም ፍኖት ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝብ አንድነት›› በሚል ርዕስ ከዛሬ ስድስት ዓመት ጀምሮ ሲያዘጋጅ አስተያየታቸውን እንዲሰጡት ያነጋገራቸው በኢትዮጵያ የሚኖሩ ኤርትራውያን ጓደኞቹ፣ ‹‹ሁለቱ የተለያዩ ሕዝቦች እንጂ እንደ ትናንቱ አንድ ሕዝብ አይደሉም፡፡ የሁለቱን አገር ሕዝቦች አንድ ሕዝብ አድርጎ ማቅረብ የትናንት የመሀል አገር ሕዝብ የአገር አንድነት ፍላጎት የሚያንፀባርቅ እንጂ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፤›› ብለውት ነበር፡፡ እነዚህም በጋዜጠኝነት፣ በዩኒቨርሲቲ መምህርነት፣ በአምባሳደርነትና በሕግ ባለሙያነት ከኢትዮጵያውያን ጋር እኩል መብት ተሰጥቷቸው የሚኖሩ ናቸው፡፡ ያ ሁሉ አለፈና ዛሬ በኤርትራና በኢትዮጵያ በሕዝብ አብዮት ሕዝቦች የሚለው ወደ ሕዝብ ተለውጧል፡፡ የሁለቱ አገሮች ሕዝብን ‹‹ሕዝቦች›› የሚል ከሞኞች የሚደመር የሚሆንበት ጊዜ መጣ፡፡ የሚገርምና የሚደንቅ ፈጣን ለውጥ ነው፡፡

ለመሆኑ ይህ አባባል እውነትነት አለው? ታሪካዊ ጽኑ መሠረት አለው? ከኖረው እንደምን ምሁራዊ በሆነ መንገድ እንገልጸዋለን? መገለጫ ባህሪውን በብዙ መንገዶች ማቅረብ የማይገድ ቢሆንም፣ አንደኛው ባላቸው ተመሳሳይ ተጨባጭና ረቂቅ የባህል ቅርስ የሚፈተሽ ይሆናል፡፡ ወደ ጥልቅ ነገር ግን ዝርዝር ተጨባጭና ረቂቅ የባህል ቅርስ ከመግባታችን በፊት ለቅምሻ ያህል የጋራ ታሪካዊ ቅርሳችንን እንመልከት፡፡

ታሪካዊ የጋራ ቅርሳችን

‹‹የቀይ ባህሩ ፐሪፕለስ›› በሚል ስያሜ ስለሮማውያን፣ ግብፆች፣ ቀይ ባህርና ህንድ ውቅያኖስ ጥንታዊ የንግድ መስመሮችና ገበያዎች በግሪክኛ በተጻፈ ማስታወሻ  ‹‹አክሱም ጠቃሚ ገበያ የነበረች ሲሆን ከወደብ ከተማዋ (አዱሊስ) እስከ አክሱም ድረስ አምስት ቀናት ይወስዳል፡፡ ወደዚች ከተማ ከዓባይ ባሻገር ሲየነም (Cyeneum ምናልባት ሰሜን) ተብሎ ከሚጠራ ሥፍራ የዝሆን ጥርስ ይመጣ ነበር፡፡ በአንደኛው ክፍለ ዘመን ዞስካለስ የሚባል ንጉሥ የነበረ ሲሆን፣ ይኼን ንጉሥ በቀይ ባህር ድንበር አዱሊስ (ምፅዋ አጠገብ) እና አዋላይት (አሰብ አጠገብ) የተባሉ ወደቦችና የገበያ ከተማዎች ነበሩት፤›› በማለት አስፍሯል፡፡ ይኼም በኢትዮጵያና በኤርትራ በጥብቅ የተሳሰረ ተጨባጭ (ቦታ)፣ ከንግድ ጋር የተያያዙ ቅርሶች (ረቂቅ)፣ ከዘመን ጋር የተያያዘ ታሪክ መኖሩን እንገነዘባለን፡፡

ጥንታዊቱ አዱሊስ በቀይ ባህር ዳርቻ ያለች የወደብ ከተማ ናት፡፡ ይህች በዙላ የባህር ወሽመጥ የምትገኝ የወደብ ከተማ በጥንት ሮማውያንና ባይዛንታይን ሥርወ መንግሥት በጥንት አክሱም ዘመን ጀምሮ የምሥራቅ ኢትዮጵያ የባህር ወደብ እንደነበረች ይታወቃል፡፡ አዱሊስ ‹‹ቀደም ማሲፍ›› ተብሎ የሚጠራ ተራራ እንዳላት የሚታወቅ ሲሆን ይኼም ተራራ ዛሬም ቢሆን እንደ ጥንቱ ከሜዲትራንያን ባህር ወደ ህንድ ውቅያኖስ ለሚደረገው የባህር ጉዞ እንደምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይሁንና ‹‹ቀደም ማሲፍ›› ዛሬ የሚገኘው በቀይ ባህር ዳርቻ ሳይሆን ከባህር ዳርቻው ሰባት ኪሎ ሜትር ገባ ብሎ ‹‹ሐዳስ›› ተብሎ በሚጠራው ወንዝ አካባቢ ነው፡፡ ‹‹ሐዳስ›› ተብሎ የሚታወቀው ሸለቆ የባህር ዳርቻውንና ‹‹ቋሒቶ›› ተብሎ የሚጠራውን ደጋማ ሥፍራ የምትገኘውን ‹‹ኮሎኤ›› ተብላ የምትጠራ የአክሱም የመናኸሪያ ሥፍራ ያገናኝ ነበር፡፡  በመጀመርያው ምዕተ ዓመት የተጻፈው የታሪክ መረጃ እንደሚያመለክተው አዱሊስ የዝሆን ጥርስ፣ የአውራሪስ ቀንድ፣ የኤሊ ሽፋንና የከበረ ድንጋይ ወደ ውጭ አገር የሚነገድባት፣ በምትኩም ጨርቃ ጨርቅ ከግብፅና ከምሥራቅ አገሮች፣ መስታወት፣ ብረታ ብረት ከህንድ፣ ወይንና ዘይት ከሶሪያና ከቬኒስ (ከኢጣሊያ) የሚገባባት ወደብ ነበረች፡፡ የባይዛንታይኖች ምንጮችም አዱሊስ በአፍሪካ በተለይም በቀይ ባህር የታወቀች ወደብ እንደነበረች ይጠቅሳሉ፡፡ በመጀመርያ በብሪታንያውያን ሙዚየም ባለሙያዎች፣ በኋላም ሪቻርድ ሰንደስቶርም (1907) እና ሮቤርቶ ፓሪኒ (1907)፣ ፍራንሲስ አንፍሬይ በ1960 (1963፣ 1966፣ 1974) የአዱሊስ ከተማ ጠቃሚነቷንና ሀብቷን በሚመለከት ምርምር አካሂደዋል፡፡ በእነዚህ ሊቃውንት አማካይነትም የቅርስነት ባህሪ ያላቸው ፍርስራሽ ግንቦች፣ አብያተ ክርስቲያናት፣ የትልልቅ ቤቶች ግቢዎችም ተገኝተዋል፡፡ ፓሪቤኒ በተባለው ተመራማሪ ባካሄደው የቁፋሮ ሥራም አዱሊስ በተለያዩ የሥልጣኔ ዘመናት እየተገነባችና በተለያዩ ጦርነቶች እየፈረሰች የኖረች መሆኗን የሚያመለክቱ ድርብርብ የጥንታዊ ከተማ ፍርስራሾች ተገኝተዋል፡፡ በቅርቡም በተደረገው ምርምር የአዱሊስ የመሬት አቀማመጥ ምን እንደሚመስል አመልክቷል (Peacock and Blue 2007)፡፡ ፓሪቢኒና አንፍሬይ በሮም ሙዚየም የሚገኙትን የሸክላ ስብስቦችን በመመርመር በወደቧ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች እነማን እንደነበሩ፣ የተገኙት ቅርሶችም ጥንታዊ አክሱማውያን ከእነማን አገሮች ጋር የንግድ ልውውጥ ያደርጉ እንደነበረ የሚያመለክቱ እንደሆኑ የዛዛሮ ምርምሮች ያመለክታሉ (Zazzaro 2004 እስከ 2005)፡፡ በኢጣሊያውያንና በኤርትራውያን ተመራማሪዎች እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 2011 በአዱሊስ የተገኙ የሸክላ ስብርባሪዎችም ተገጣጥመው ጥንታዊ መልካቸውን ከመያዛቸውም በላይ፣ ምርምሩም መቼ እንደተሠሩ ለማወቅ አስችሏል፡፡

አንድ ስሙና የንግሥ ዘመኑ የማይታወቅ ነገር ግን በ250ዎቹ ዓመተ ልደት የኖረ ይሆናል ተብሎ የሚገመት የአክሱም ንጉሥ በአዱሊስ ወደብ ባስተከለው ሐውልት ላይ ያካሄዳቸው ጦርነቶችና ያገኛቸውን ድሎች የገለጸ ከመሆኑም በላይ፣ መንግሥቱ በወቅቱ ከነበሩት ገናና መንግሥታት ማለትም ከቻይና፣ ከሮማ፣ ከፋርስ አንዱ እንደነበረ ያስረዳል፡፡ ዶ/ር ላጲሶ ጌዴሌቦ የኢትዮጵያ ታሪካዊ መሠረቶችና መሣሪያዎች በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ እንደገለጹት፣ ‹‹በ300 ቅድመ ልደት በቀይ ባህር ዳርቻ አዱሊስ ወደብ በሜዲትራኒያን ባህርና በህንድ መካከል በተስፋፋው ዓለም አቀፋዊ ንግድ፣ ቋንቋ፣ ባህልና ሥልጣኔ ኬላ፣ ማዕከልና መናኸሪያ ሆኖ አደገ፡፡ ማለትም የአዱሊስ ወደብ ለአክሱም መንግሥትና ሥልጣኔ የመካከለኛው ምሥራቅና የሜዲትራኒያን ሥልጣኔዎች የመግቢያ በርና መንገድ ሆነ››፡፡ (ዶ/ር ላጲሶ የኢትዮጵያ ታሪካዊ መሠረቶችና መሣሪያዎች፣ 1999 ዓ.ም. ገጽ 27)፡፡ አፄ ኢዛናም እንደ ሌሎቹ ጥንታዊያን ነገሥታት ሁሉ ከአዱሊስ እስከ መሀል አገር የተዘረጋ የንግድ መስመር እንደነበራቸው የተለያዩ የታሪክ መጽሐፍት መግለጻቸው ይታወቃል፡፡ ከእነዚህም መጻሕፍት መካከል ዶ/ር ስርግወን፣ ኮንቲሮዚኒንና አባ ጋስፓሪኒን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የአፄ ኢዛናም ሆነ የሌሎቹ አፄዎች ታሪክ ከኢኮኖሚ ታሪኩ ጋር በስፋት ተተንትኖ በዚህ ጥናት ተካቷል፡፡

በአዱሊስ ምን ያህል የተደራጀ የመርከብ ሥራ እንደነበርና ምን ያህል ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደነበር የምንረዳው አፄ ካሌብ ወደ ዓረቢያ ካደረጉት ዘመቻ ነው፡፡ ስለዚህም ዘመቻ የተጻፈው መረጃ እንደሚያመለክተው ‹‹በመጨረሻ በሰኔ ሐምሌ 525 ዓ.ም. አፄ ካሌብ በራሱ መሪነትን አዝማችነት ሠራዊቱን በ70 መርከቦች አደራጅቶ፣ በአዶሊስ ወደብ አጠገብ ከሚገኘውና ገበዛን ከተሰኘው ወደብ ቀይ ባህርን ተሻግሮ በየመን የይሁዳውያኑን የአመፅ መንግሥት ጦር በአንድ የግንባር ውጊያ ደመሰሰ፡፡›› ዶ/ር ስርግው ደግሞ አፄ ካሌብ 230 መርከቦችን በአገር ውስጥና በውጭ አገር አሠርተው እንደዘመቱ ይገልጻሉ፡፡ ወደ ዓረቢያ የተደረገው ዘመቻ እጅግ ግዙፍ እንደነበረ የሚገልጹት ዶ/ር ተወልደ ደግሞ ዘመቻው ግዙፍ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ወታደሮች ቀይ ባህርን አቋርጠው የመን የደረሱት በ191 የቤዛንታይን የንግድ መርከቦችና አፄ ካሌብ ባሠራቸው በ170 መርከቦች ተሳፍረው ነበር፡፡ አፄ ካሌብ ዘመቻ ያካሄደው በሁለት ዙር ነበር (ዶ/ር ተወልደ የኢትዮጵያ አንድነትና ኢጣሊያ፣ ገጽ 48) ይላል፡፡ በመሠረቱ ቀደም ሲል የተጠቀሰው ለቅምሻ ያህል እንጂ የሁለቱ አገሮች ሕዝብ የሚጋራቸው ታሪካዊ ቅርሶች እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ እጅግ በጣም ሰፊና የማያፈናፍን ታሪካዊ መሠረት ያላቸው ናቸው፡፡ ይኼን ያህል ስለጥንታዊ የጋራ ቅርሳችን ካወቅን ወደ መነሻ ሐሳባችን ማለትም ወደ ተጨባጭና ረቂቅ ቅርስ እናተኩርና ተጨባጭና ረቂቅ የባህል ቅርስ ምንድነው?

ባህላዊ ቅርስ ምንድነው?

ባህላዊ ቅርሶች የሚባሉት በኅብረተሰቡ ዘንድ እንደ ባህላዊ ቅርስ የሚታዩ ከጥንት አያት ቅድመ አያቶች ሲተላለፉ የመጡ ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶች ሲሆኑ እነዚህም በዘልማድ የሚሠሩ፣ የሚተገበሩ፣ ወይም ተለይተው የሚታወቁ ሥፍራዎች፣ ቁሳቁሶች፣ የሥነ ጥበብና የኪነ ጥበብ ውጤቶች ናቸው፡፡ እነሱም ተጨባጭ ወይም ረቂቅ ቅርሶች ተብለው የሚታወቁ ናቸው፡፡ ይህም ሲባል በተጨባጭ የባህል ቅርስ ውስጥ ረቂቅነት፣ በረቂቅ ቅርስ ደግሞ ተጨባጭነት የለም ማለት አይደለም፡፡ በባህላዊ ቅርስ ባህል፣ እሴትና ልማድ ሲኖር (‘Culture,’ ‘Values,’ and ‘Customs’) የሚባሉ ቃላትን መሰሎች እያለዋወጡ የሚጠቀሙባቸው ቢሆንም ሁሉም የየራሳቸው የሆነ ሰፊ ትንታኔ ያላቸው ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት ባህልና ባህላዊ ቅርስ ስንል ቀደም ሲል ለመተንተን እንደሞከረው ሁሉ በረቂቅና በተጨባጭ ባህላዊ ቅርስነት የሚገለጽ ሲሆን፣ ባህላዊ እሴት በሚባልበት ጊዜ ደግሞ በባህል ውስጥ ሥር ሰዶ ሰዎች የእኔ ባህል ነው፣ የእኔን ማንነት ይገልጻል፣ ሁለንተናየን ያንፀባርቃል፣ ባህላዊ ቅርሴንና ሀብቴን ያጠቃልላል ብለው የሚቀበሉትና በልዩ ልዩ መልኮች የሚገልጹት ነው፡፡

የባህል እሴትን በተግባር የመግለጽ ሁኔታም ልማድ ተብሎ ይጠራል፡፡  ለምሳሌ የገና በዓል አንድ የባህል ቅርስ ሲሆን፣ ሰዎች የገና በዓልን በውስጣቸው የእኔ ነው፣ እኔን ይገልጸኛል፣ እምነቴን ያንፀባርቃል ብለው እንደ እሴት የወሰዱት ሲሆን የገና በዓልም በልዩ ልዩ ልማዶች ማለትም ገና በመጫወት፣ የገና ለገና በዓል የሚሆን ንፁህ ልብስ በማዘጋጀት፣ ራስም ንፁህ ሆኖና ተኳኩሎ በመውጣት ይገለጻል፡፡ ጉዳዩን በምግብ ስንመስለውም ኢትዮጵያውያን የእንጀራ ምግብ መመገብ ባህላቸው ነው፡፡ ለእንጀራ ምግብም ከፍተኛ ዋጋ ይሰጡታል፡፡ በወጥ ወይም በሌላ ማጣፈጫ የመብላት ልማድም አላቸው፡፡ ስለዚህም ባህል፣ የባህል እሴትና ልማድ የአንድ ትልቅ ዛፍ ሥር ግንድና ቅርንጫፍ ወይም የሰው ልጅ ተጨባጭና መንፈሳዊ ባህሎች መገለጫ ባህሪ አካል ናቸው በጥቅሉ ማለት ይቻላል፡፡ ባህል የምንለው የጋራ የሆነ እሴት ያለው ሲሆን ይኼም የጋራ መግባባትን፣ ውብና መጥፎ ነገሮች፣ አስደሳችና አሳዛኝ ክስተቶችን፣ አዝናኝና አሰልቺ ሒደቶችን፣ ለይቶ ለማወቅ ያስችላል፡፡ ይህን የበለጠ ለመገንዘብ እንችል ዘንድ በወቅታዊና በአካባቢ ምሳሌ በጥቅሉ እንደሚከተለው እንመልከተው፡፡ በመሠረቱ ጥሩ ባህላዊ እሴት የምንለው የኅብረተሰቡ ተግባብቶ፣ ተስማምቶ፣ ተቻችሎ መኖር ነው፡፡ ይህም ባህላዊ እሴት እንዲሁ የተፈጠረ ሳይሆን፣ ከረዥም ዘመናት በፊት ኅብረተሰቡ ሥር እንዲሰድ አድርጎ ኮትኩቶ ስላሳደገው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ቤተሰብ ልጆችን ከጨቅላ ዕድሜያቸው ጀምሮ ጥሩና መጥፎ ሥነ ምግባሮችን ለይተው እንዲያውቁ በልዩ ልዩ መንገዶች፣ ልምዶች፣ ትውፊቶች፣ ሥነ ቃሎችና ዘፈኖች እንዲያድጉ ያልተቆጠበ ጥረት ማድረጉ እንደ ዓይነተኛ ምሳሌ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

ጉዳዩን በሌላ ቀላል ምሳሌ ለመረዳት እንችል ዘንድ በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝብ ውስጥ የሚገኝ ባህላዊ ሠርግን እንውሰድ፡፡ በአንድ ሠርግ ውስጥ ኅብረተሰቡ ያዳበራቸው እሴቶችና ልማዶች ተሟልተው ይገኙባቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት የሠርግ ቀን ይቆረጣል፣ በወንድና በሴት ቤት ሲደገስ ይሰነበታል፡፡ ተጋባዦች ይታደማሉ፡፡ የሠርጉ ዋዜማ ዘፈን አለ፡፡ ሙሽራው ወደ ሙሽሪት ሲመጣ የሚዘፈን ዘፈንና የሚዘፍን ቡድን አለ፡፡ ሙሽራው ሙሽሪትን ይዞ ወደ ቤቱ ሊወስድ ሲል የሚዘፈን ዘፈን አለ፡፡ ሙሽራው ሙሽሪትን ይዞ ወደ ቤቱ ሲደርስ የሚዘፈን ሌላ ዘፈን አለ፡፡ ይህ በየዕርከኑ የሚዘፈን ዘፈን እስክስታ ይታጀባል፡፡ ሙሽሪትና ሙሽራው ትዳር መጀመራቸው፣ አዲሱን የሕይወት ምዕራፍ ‹‹ሀ›› ብለው መጀመራቸውና ልጅ ወልደው መሳም፣ ወላጆቻቸውን ማስደሰት እንዳለባቸው ይነገራቸዋል፡፡ ሌሎችም ከዚህ ጋር የሚሄዱ ባህላዊ እሴቶችና ባህላዊ እሴቶቹ የሚገለጡባቸው ልማዶች አሉ፡፡ ባህላዊ እሴት በጥቅሉ ወይም በተናጠል (አንዱን ነገር ነጥሎ በመውሰድ) ማኅበረሰቡ በጎ ነው፣ ትክክል ነውና አስፈላጊ ነው ብሎ በጋራ የሚጠቀምበት ረቂቅ የሆነ መርህ መሆኑን በመተንተን የማኅበራዊ ኑሮ ባለሙያዎቹ በተጨማሪ ያብራራሉ (Williams, 1970)፡፡ በእነዚህ ማኅበራዊ ሳይንቲስቶች ትንታኔ መሠረት ነፃነት፣ ብልፅግናና ደኅንነት በተግባር ለሚገለጹ እንደ ቤተሰባዊ፣ ትምህርታዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ እምነታዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ወዘተ. . . ልማዶች ሁሉ ዋነኛዎቹ የባህላዊ እሴቶች መሠረቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ የግለሰቦች ታላቅ ነገር ለማግኘት የመፈለግና ፍላጎቱንም ማሳካት የባህል እሴት በሆነበት አካባቢ የኢኮኖሚውና የፍትሕ ሥርዓቱ ይኼንን ተግባር ለማከናወን የሚያስችል መሆን አለበት፡፡ የኅብረተሰቡ ደኅንነት የተመሠረተ እንዲሆን ካስፈለገም ኢኮኖሚያዊ ሥርዓቱና የፍትሕ ሥርዓቱ አብሮ የሚሄድ መሆን ይኖርበታል፡፡ በዚህ ታሪካዊ ወቅት ስለጋራ ተጨባጭና ረቂቅ ቅርስ ማውሳት በሁለቱ አገሮች ሕዝብ ጥቅሙ ምንድን ነው? የሚለውን ደግሞ እንመለከታለን፡፡

የቆየ፣ የኖረና ሥር የሰደደ የባህል ቅርስ የማወቅ ጥቅም

ባህላዊ ቅርሶች የሚባሉት በኅብረተሰቡ ዘንድ እንደ ባህላዊ ቅርስ የሚታዩ ከጥንት አያት ቅድመ አያቶች ሲተላለፉ የመጡ ቁሳዊና መንፈሳዊ ቅርሶች ናቸው፡፡ እነዚህም በዘልማድ የሚሠሩና የሚተገበሩ ወይም ተለይተው የሚታወቁ ሥፍራዎች፣ ቁሳቁሶች፣ የሥነ ጥበብና የኪነ ጥበብ ውጤቶች፣ ወይም ተጨባጭ ወይም ረቂቅ ቅርሶች ተብለው የሚታወቁ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝብ ውስጥ ያለው የቆየ፣ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ሕይወቱ የሚንፀባረቅ ወይም የሚገለጽ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረ፣ ሥር የሰደደ የመገኛ ምንጭ ያለው፣ በሰዎች ታሪክ የሚረጋገጥ፣ የራሱ የሆነ ዕድገትና ክስመት እንዲሁም አዲስ ውልደት ያለው፣ ልማድን፣ ቦታዎችን፣ ቁሶችን፣ ኪነ ጥበባዊ መገለጫዎችን፣ የሚያንፀባርቅ የባህል ቅርስ ነው፡፡ ይህም የባህል ቅርስ ተጨባጭና ረቂቅ የባህል ቅርስ ተብሎ በሁለት ዓበይት ክፍሎች ተለይቶ የሚተነተን ነው፡፡ ትንታኔውም ዓለም አቀፍ አካሄድን የተከተለ ስለሆነም ጭምር በዚህ መሥፈርት ብናየው ቀላል ከመሆኑም በላይ፣ የእንግሊዝኛውን (Tangible and Intangible Heritage) በሚል ከማንኛውም የመረጃ ምንጭ የሚለውን ርዕስ ተከትሎ ተጨማሪ ጥናት ለማድረግ ይጠቅማል፡፡  

በመሠረቱ ቀደም ሲል በተጠቀሰው መንገድ የሚከሰቱት የኢትዮጵያና የኤርትራ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች፣ የሁለቱ አገሮች ሕዝብ ኅብረተሰብ መተኪያ የሌላቸው  ተጨባጭና ረቂቅ እሴቶች ሲሆኑ እነሱም ያለውንና መጪውን ትውልድ ድልድይ ሆነው የሚያገናኙ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ዕድገት እንዲጨምር ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች የማውሳቱ መሠረታዊ ዓላማም ቅርፃቸውን፣ ጥልቀታቸውንና ይዘታቸውን በመፈተሽ ወደ ፊት ሊደረግ ስለሚገባው ዘላቂ የሆነ ግንኙነት በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አስተያየት ለመስጠት ነው፡፡ የኢትዮጵያንና የኤርትራን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ገጽታ ከነበረው የተሻለ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የአካባቢውን የታሪክና የባህል ቅርሶች ገጽታ ማቅረብ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል በእውነት ላይ የተመሠረተ ታሪክ መዳበር አስተዋጽኦ ከማበርከቱም በላይ ሕዝብ ያለውን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለይቶ በማወቅ ማንነቱን እንዲረዳ፣ የአካባቢውን የታሪክና የባህል ቅርሶችን ማጥናት የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እንዲጎለብት ለማድረግ ወደፊት በሕዝብ ታሪክ ላይ ተጨማሪ ጥናት ለማድረግ ለሚፈልጉ አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር ወዘተ. ይጠቅማል ተብሎ ይታመናል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ታሪኩ በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝብ እንዲታወቅ፣ ግንዛቤ እንዲዳብር፣ የዕውቀት መወራረስ እንዲኖርና የታሪኩ ባለቤት የሆነው እያንዳንዱ የኅብረተሰብ አባል መንፈሳዊ ኩራት እንዲሰማው፣ ብሔራዊ ማንነቱ እንዲጎለምስ፣ አካባቢው ታሪካዊ ቦታ መሆኑን ተረድቶ እንዲንከባከበው፣ እንዲጠብቀው አስፈላጊ ሲሆን፣ ዕድሳት እያደረገ እንዲጠብቀውና እንዲያሳድገው ለማድረግ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

እንዲሁም ደግሞ ስለታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶቹ በዕውቀት ላይ በተመሠረተ ግንዛቤ ተንተርሶ ተገቢ የአሠራር ሥርዓት እንዲዘረጋና በአካባቢው የሚገኙ ታላላቅም ይሁኑ ጥቃቅን ታሪካዊ ቅርሶች አንድ በአንድ ተመዝግበው እንዲያዙ፣ ስለተመዘገቡትም ታሪካዊ ቅርሶች ዝርዝር መረጃ እንዲኖር እንዲሁም በአካባቢው የተጀመረውን ጥናት አጠናክሮ እንዲቀጥል አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ያለውና መጪው ትውልድ የተሟላ ሰብዕና እንዲኖረው ያስችላል፡፡ ወጣቶች በማንነታቸው እንዲኮሩና መጥፎውን በመተው ጥሩውን እንዲያዳብሩ  ያደርጋል፡፡ ልዩ ልዩ ጥናቶች፣ ሲምፖዚየሞች፣ ኮንፈረንሶችና ሥልጠናዎች እንዲካሄዱ መንገድ ይከፍታል፡፡ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ ደራሲያን፣ ጋዜጠኞች፣ ሠዓሊያን ስለታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶቹ ተገንዝበው ሙያቸው በሚፈቅደው መሠረት እንዲገልጹት ሰፊ በር ይከፍታል፡፡ ለመሆኑ የሁለቱ አገሮች የጋራ ታሪካዊና የባህል ቅርሶች ምንድን ናቸው?

ተጨባጭና ረቂቅ ቅርሶች

ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው በኢትዮጵያና በኤርትራ የሚገኙት ባህላዊ ቅርሶች በሁለት ተከፍለው የሚታዩ ሲሆን፣ አንደኛው ተጨባጭ ሁለተኛው ረቂቅ ነው፡፡ ተጨባጭ ባህላዊ ቅርስ (Tangible Cultural Heritage) ዓይነቱ በዛ ያለ ቢሆንም፣  ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ በማለት በሁለት ከፍለን ልንመለከተው እንችላለን፡፡  ተንቀሳቃሽ ቅርስ (የሥዕል፣ በመጠናቸው አነስተኛ የሆኑ ጠረጴዛ ላይ፣ በጓሮ፣ በበረንዳ ላይ የሚቀመጡ የሐውልት፣ የሳንቲም፣ የጽሑፍ ሥራዎች) ሲሆኑ፣ እነዚህ ተጨባጭ ባህላዊ ቅርሶች የሚገኙባቸው ቦታዎች፣ እነዚህን ሥራዎች ዕውን ለማድረግ የተጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች፣ ቀለሞች፣ ሥፍራዎች ሁሉ የዚሁ አካል ናቸው፡፡ የማይንቀሳቀስ የባህል ቅርስ በብዙ መንገድ ከፋፍለን የምንመለከተው ሲሆን፣ እንደ አክሱም፣ የሓ፣ ውቅሮ፣ መጠራ፣ ቋሒቶና አዶሊስ ያሉ ታላላቅ ሐውልቶችና ከዲንጋይና ከሸክላ የተሠሩ ሲሆኑ በከርሰ ምድር ቁፋሮ በኢትዮጵያና በኤርትራ የተገኙ ቅሪተ አፅምና ቅርስ የተገኘባቸው ሥፍራዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ ውስጥ የሚገኙ ተጨባጭ ቅርሶች ተመሳሳይነት ስንገነዘብም የሕዝቡን ማንነት የበለጠ በግልጽ እንረዳለን፡፡

ረቂቅ ቅርሶች (Intangible Cultural Heritage) የሚባሉት ደግሞ ሥነ ቃላት፣ ትውፊቶች፣ ተረቶች፣ አፈ ታሪኮች፣ እስክስታ፣ ጭፈራ፣ ዘፈኖች፣ እንጉርጉሮዎች፣ ቀረርቶዎች፣ ሽለላዎች፣ ደቦዎችና ከደቦ ጋር የተያያዙ የሥራ ማሳለጫና ማደፋፈሪያ የኅብረት ዜማዎች፣ ከእምነት ጋር የተያያዙ ሥርዓቶችና መገለጫ ባህሪያቸው ቅዳሴዎች፣ ውዳሴዎች፣ መንዙማዎች፣ ልጅ ከተፀነሰ ጊዜ አንስቶ አርጅቶ እስከሚሞት የሚደረጉ እምነት ነክ ወይም መንፈሳዊ ልማዶች፣ እንደ ደብረቢዘን፣ ሰነአፈ በምትገኘው ጥንታዊት የኪዳነ ምሕረት ገዳም፣ በጽሑፍ የሚገኙ ትውፊቶች ከተቀሩት የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ከእስልምና ጋር በተያያዘ  ከዳህላክ ደሴቶች አንስቶ እስከ ነጋሺ (ትግራይ) የሚገኙ ትውፊቶች፣ የመሻኢኾች (ሙስሊም ሊቃውንት) ሥራዎች ተመሳሳይ መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡ በክርስትናና እስልምና እምነት ተከታዮች የሚተገበሩ እንደ ሠርግ፣ ተዝካር ሰደቃ፣ መውሊድ፣ አራስ ጥየቃና ማስተዛዘን፣ ወዘተ. የመሳሰሉት በሚጠቀሱት የአስተምህሮት ምንጮች ይለዩ እንደሆነ እንጂ አንዱ ከሌለው የሚወርሰው ብዙ ነው፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ በዓላትን የሚቀበሉት በዋዜማው ብቻ ሳይሆን ትንሽ ቀደም ብለው ነው፡፡

ይህም ተያያዥነት ያለው የመገለጫ ባህሪ ከሌላው አጎራባች አገሮች ልማድ የሚለይ መሆኑን ያመለክታል፡፡ ለአቅመ አዳም የደረሰ ወንድና ለአቅመ ሔዋን የደረሰች ሴት በጋብቻ የሚተሳሰሩበት ልምድም ከአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተወራራሽ ነው፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ እንግዳን የሚቀበሉት (ቤት ከሆኑ) ከተቀመጡበት ብድግ ብለው፣ ‹‹ንበር፣ በእግዜር ወይም በልጆቻችን›› ብለው፣ ውጭ ከተገናኙ ደግሞ ክንብንባቸውን አውርደው፣ ጎንበስ ብለው፣ ወይም አቅፈውና ጉንጭ ለጉንጭ ተሳስመው ወዘተ. ነው፡፡ በመሳል አንዳች የተመኙትን ማግኘት፣ ካገኙ በኋላ ስለትን ማድረስ የጋራ መገለጫ ባህሪያቸው ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከጥንታዊ አምልኮ ጋር የተያያዙ እንደ ገድ፣ ፋል የመሳሰሉ እምነቶች በኤርትራና በኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ እንዳለ አሌ አይባልም፡፡ ለምሳሌ በጠዋቱ ‹‹ደስታ›› የሚል ስም ከተጠራ በደስታ ያውለን ይባላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ቀልዶቻቸው፣ እንቆቅልሾቻቸው፣ ልዩ ልዩ ዘውጎች ያሏቸው ተረቶቻቸው፣ ምሳሌያዊ አነጋገራቸው፣ ከቅድመ ክርስትናና እስልምና የነበሩ በኋላም ጎን ለጎን ይተገበሩ አማልክቶቻቸው ይመሳሰላሉ፡፡ ምናልባትም የማኅበራዊ ግንኙነት መገለጫዎች ከዚህ አኳያ የሚተነተኑ የሁለቱ አገር ሕዝብም ረቂቅ ቅርሶች እጅግ በጣም ብዙ ናቸው ብሎ ከመግለጽ ይልቅ አንድ ናቸው ብሎ ማጠቃለል ሊቀል ይችላል፡፡

ባህላዊ ቅርሶች የሁለቱን አገሮች ሕዝብ በማጣመር የሚጫወቱት ሚና

የሁለቱ አገር ሕዝብ ተጨባጩንም ሆነ ረቂቁን የባህል ቅርስ ዋጋ ሊኖረው የሚችለው ስለቅርሱ ጠቃሚነት እንደሚበላ ምግብ፣ እንደ ልብስ፣ እንደ ቅመምና እንደ መድኃኒት ሁሉ የታወቀ እንደሆነ ነው፡፡ ስናውቀው ዋጋ እንሰጠዋለን፣ ዋጋ ስንሰጠው እንንከባከበዋለን፡፡ ስንንከባከበው ሰዎች ስለራሳቸው ማንነት በመገንዘብ ደስታን ያገኙበታል፡፡ እነሱ ሲደሰቱበት ሌሎች የማያውቁት እንዲያውቁት ያደርጋሉ፡፡ እንዲያውቁት ሲያደርጉት በዝና የሰሙትን ለማየት ይመጣሉ፡፡ ሲመጡ እንደማንኛውም ሀብት የገቢ ማስገኛ ምንጭ ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ የታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች፣ መተኪያ የሌላቸው ውድ ተጨባጭና ረቂቅ እሴቶች ሲሆኑ ያለውንና መጪውን ትውልድ ድልድይ ሆነው የሚያገናኙ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ዕድገት እንዲጨምር ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በመሠረቱ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶቹ ከባቢያዊ ይዘትና ይዞታ ቢኖራቸውም እንደ ሰው ልጅ ቅርሶች ተደርገው እንደሚወሰዱም ማስተዋል ይገባል፡፡

ይሁንና ታሪካዊ ቦታዎች ሲባሉ ትልልቅ ሐውልቶች፣ ወይም ሕንፃዎች፣ ወይም የሕንፃ ፍራሾች፣ ወይም የተሟላ የጽሑፍና የቃል መረጃዎች ያሏቸው ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ በምትኩ ክብ ካብ፣ ወይም የካብ አካል፣ ወይም አንዳች ጥንታዊ የሥራ መሣሪያ፣ ምንም ነገር የሌለው የጦር ሜዳ ወይም ምሽግ የመሰለ ነገር፣ መቃብር ወይም መቃብር የሚመስል ቦታ፣ ወዘተ. ሊሆን ይችላል፡፡ ታሪካዊ ቅርሶቹ ጥንታዊ ሰዎች የሚጫወቱባቸው በድንጋይ ላይ የተቀረፁ ገበጣዎች፣ የምግብ ማብሰያ ጉድጓዶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ጥንታዊ የገበያ ቦታዎችን ማወቅና ማጥናት በዚህ ረገድ ጠቀሜታ እንዳለው የተረጋገጠ ነው፡፡ ጊዜ ከዚህም ሌላ ስሜታችንን ለማወቅ የሚያነሳሱ ተጨባጭና ረቂቅ ቅርሶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከዚህም ጋር ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶቹ ሲጠኑ የሚገኙበት አካባቢ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጡ፣ የአየር ንብረቱና መንገዶቹ ወዘተ. የሚጠቀሱ ስለሆነ ጠቀሜታው እጥፍ ድርብ ይሆናል፡፡  ታሪካዊ ቦታዎች ለሥራ ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በተግባር የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ በራሳቸውም በቱሪዝም መስክ የሚያስገኙት ገቢ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ የአገር ውስጥም ሆኑ የውጭ አገር ቱሪስቶች ወደ ታሪካዊ ቦታዎች ሲመጡ ለመማርና ለመመራመር ቢሆንም፣ ከልዩ ልዩ የዕውቀት ዘርፍ በመሆኑ ከዚህ ጋር የተያያዘ ፋይዳ እንዳለው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ስለተጨባጭና ረቂቅ ቅርስ እንዲሁም የታሪክ ቅርስ በመጠኑ ካየን ዘንድ ባህላዊ ቅርስ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ደግሞ ቀጥለን እንመልከት፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ባህላዊ ቅርሶቻቸውን በጋራ መንከባከብ ይኖርባቸዋል

ቀደም ሲል ባህላዊ ቅርስን የመጠበቅ አስፈላጊነት በመጠኑም ቢሆን ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ስለነዚሁ ባህላዊ ቅርሶች ክብካቤና የክብካቤው ሥልት ለማቅረብ ይሞከራል፡፡ ባህላዊ ቅርሶችን የምንከባከበው፣ በወንዝ፣ በሐይቆችና በባህሮች ዳር ወይም መሀል የሚገኙ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ቅርሶች፣ በዝናብ በጎርፍና በማዕበል እንዳይወሰዱ መከላከያ በማድረግ፣ የቆሙ ሐውልቶች እንዳይወድቁ ድጋፍ በማድረግ፣ ሥዕሎች ቀለማቸው ጠፍቶ እንዳልነበሩ እንዳይሆኑ በነበረ መልካቸው ማደስ፣ መጻሕፍት በውኃ፣ በብል፣ በኬሚካላዊ ለውጥ እንዳይበላሹ በየጊዜው በመፈተሽ፣ የአየር ብክለትን በማስወገድ፣ ደኖችን በመንከባከብና በመተካት፣ የሚንከባከብና የሚከታተል አካል በማቋቋም፣ ኅብረተሰቡ የባህል ቅርሶችን ጠቃሚነት ተገንዝቦ እንዲንከባከባቸው በማድረግ፣ ባህላዊ ቅርሶች እንዲጠበቁና ክብካቤ እንዲያገኙ የሚያግዙ ሕጎችንና ድንጋጌዎችን በማውጣትና በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ መጪው ትውልድ ባህላዊ ቅርሶችን የመጠበቅና የመንከባከብ ጥቅም እንዲደረግለት፣ እንዲሁም ተግባራዊ ዕርምጃ የሚወስድ ዜጋ እንዲሆን ማብቃት፣ የአንድ አካባቢ ኅብረተሰብ በአካባቢው የሚገኙ ባህላዊ ቅርሶች ከባቢያዊ፣ ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ እንዳላቸው ተረድቶ እንዲጠብቃቸውና እንዲንከባከባቸው ማድረግ፡፡  ሌሎችም በርካታ የክብካቤ ሥልቶችን በመቀየስ ባህላዊ ቅርሶች እንዳይበላሹ እንዳይወድቁና እንዳይጠፉ ማድረግ ይቻላል፡፡

እርግጥ ነው፣ ባህላዊ ቅርሶች እንዳይጠፉና ክብካቤ አግኝተው እንዲጠበቁ ማድረግ ከባድ ሥራንና ኃላፊነትን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ ይኼንን ከባድ ሥራና ኃላፊነት የሚጠይቅ ሥራ ግን ቀስ በቀስም ቢሆን የምንጀምረውና የምናዳብረው እንጂ በጭፍን የምንተወውና ከአቅም በላይ ነው ብለን የምንተወው አይደለም፡፡ ስለሆነም ባህላዊ ቅርሶችን ተጠብቀው እንዲቆዩና ክብካቤ እንዲያገኙ የማድረግን ሥራ መጀመርና እስከ መጨረሻው መቀጠል ይኖርብናል፡፡ በዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ ስለባህል አጠቃላይ ግንዛቤና የጥናቱ መሠረታዊ ዓላማ፣ የባህልን ምንነት፣ ባህል እንደ ግል ማንነት መለያ መሣሪያ እንደሚያገለግል፣ ስለባህላዊ ብዝኃነት፣ ስለድንበር ተሻጋሪ ባህል፣ ስለባህላዊ ቅርስ ምንነት፣ ስለተጨባጭ ባህላዊ ቅርስ (Tangible Cultural Heritage) እና ረቂቅ ቅርሶች (Intangible Cultural Heritage)፣ ስለባህላዊ እሴት ምንነት፣ ባህላዊ እሴት እንዴት አለካክ፣ የባህላዊ እሴት ገለጻ፣ የባህላዊ እሴት ለውጥ፣ በባህልና በቀጣይ ልማት መካከል ያለው ግንኙነት፣ የባህል ቅርሶችን ጠብቆ ስለማቆየት፣ ባህላዊ ቅርሶችን መንከባከብ፣ ዓለም አቀፍ ባህሪ ያላቸው የባህል ቅርስ ማዕከላት በጥቅሉም ቢሆን ሐሳብ ለመግለጽ ተሞክሯል፡፡ ሆኖም በዚህ ጥናት የቀረቡት ሁሉ ራሳቸውን ችለው መጽሐፍ የሚሆኑ ሐሳቦች እንደሆኖ ተገንዝቦ በዚህ ረገድ ያለንን ግንዛቤ ለማዳበር አስፈላጊ መሆኑን ማውሳት ተገቢ ይሆናል፡፡

ማጠቃለያ

ምንም እንኳን ቀደም ሲል ለማቅረብ እንደተሞከረው በልማት የሚለወጡ የባህል እሴቶች ቢኖሩም የማይለወጡ፣ የማይተኩና ምንም ዓይነት መተመኛ ዋጋ የማይገኝላቸው፣ የአንድ አካባቢ ኅብረተሰብ ማንነት መለያ የሆኑ ወይም ሁሉ አቀፋዊ የሆነ ነገር ግን በአንድ አካባቢ የሚገኙ የባህል ቅርሶች እንዳይበላሹ ወይም እንዳይሰረቁ መጠበቅና ክብካቤ ማግኘት ያለባቸው የባህል ቅርሶች አሉ፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያና የኤርትራ የባህል ቅርሶች የምንላቸው፣ ከሰው ልጅ ታሪክ ጋር የተያያዙና በጠንካራና በማያጠራጥር ረቂቅና ተጨባጭ ቅርሶች ላይ የተመሠረቱ ከመሆናቸውም በላይ፣ የሁለቱን አገሮች ሕዝብ ማንነት የሚያሳውቁ ከመሆናቸውም በላይ ላለውና ለመጪው ትውልድ ምን እንደሆነና ምንስ መደረግ እንዳለበት ሐሳብ የሚፈነጥቁ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ያለፈውን ዘመን ወደ ኋላ መለስ ብለን ለማየት ሰዎች በነበሩበት ዘመን በአካባቢያቸው አንዳች ለውጥ ለማምጣት ያደረጉትን ጥረት የሚፈነጥቁ ናቸው፡፡  የባህል ቅርሶች ካለፈው ትውልድ ጋር የሚያገናኙ ድልድዮችም በመሆናቸው የፈረሱት ተጠግነው፣ ለአደጋ የተጋለጡት ከጥፋት የሚያድን መከላከያ ተሠርቶላቸው ለመጪው ትውልድ መተላለፍ አለባቸው፡፡ ይልቁንም አንዳንዶቹ ባህላዊ ቅርሶች በውስጣቸው በሚካሄድ ኬሚካላዊ ውህድ ምክንያት ሊጠፉ እንደሚችሉ በመገንዘብ ከዚህ ጥፋት እንዲድኑ ዘዴ መፈለግ ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ አደጋ ከሚዳረጉት በርካታ የባህል ቅርሶች መካከል በአብያተ ክርስቲያናት፣ በመስጊዶችና በሌሎችም የሚገኙ መጻሕፍትና ውስጣቸው የሚገኙ ጽሑፎችና ሥዕሎች፣ የሥነ ሕይወት ቅርሶች፣ ተክሎች፣ ሕንፃዎችና ፍልፍል ዋሻዎች ይገኙባቸዋል፡፡

በተፈጥሮ ለውጥ ምክንያት ሊከተል ከሚችለው ጥፋት በተጨማሪ በግዴለሽነት፣ በራስ ወዳድነትና በስርቆት ወዘ. ሊጠፉ የሚችሉ የባህል ቅርሶች ስላሉም በዚህ ረገድ የሚደረገው ጥበቃና ክብካቤ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ በጦርነት ምክንያት መተኪያ የሌለው ልዩ ልዩ ባህላዊ ቅርሶች የወደሙ ቢሆንም ወደፊት ጦርነት ሲካሄድ ባህላዊ ቅርሶች እንዳይወድሙ ማስተማር ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ኢስላም የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች እንዳይጠፉ፣ በእርሻ ያለ ሰብል፣ ከብትና ንብ የመሳሰሉት እንዳይነኩ አጥብቆ የሚያስገነዝብ ሲሆን ይህን ግንዛቤ ለማዳበር ኅብረተሰቡን በሰፊው ማስተማር ይገባል፡፡ ሁሉም ኅብረተሰብ በግልጽ ሊገነዘበው የሚገባው ሌላው ዓብይ ጉዳይ ቢኖር፣ ከአያት ቅድመ አያቶቻችን የወረስነውን ቅርስ ለልጅ ልጆቻችን አጠናክረንና ጠብቀን ልናቆየው እንጂ ለወቅታዊ ፍላጎታችን ስንል ልናጠፋው የሚገባው አለመሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ የሚመለክባቸው ዛፎች፣ ወይም መቃብሮች፣ ወይም ሕንፃዎች ወይም ሐውልቶች ቢኖሩ ማስተማሪያ አድርገን መጠቀም እንጂ የማውደም ሥልጣንና ሀብት ስላለን ብቻ ልናወድማቸው አይገባም፡፡ በዚህ ረገድ በአሁኑ ጊዜ በአገራችንና በሌሎች አገሮች በመጥፋት ላይ ያሉትን የጥንታዊ ዛፎች፣ መቃብሮች፣ ሕንፃዎች፣ ቅርሶች በቅርሶቹ መውደም ምክንያት የሚከተለውን መዘዝ አውስቶ በሰፊው መነጋገር እንደሚገባ በዚህ አጋጣሚ ለማውሳት እወዳለሁ፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ መገንዘብ የሚኖርብን በአንዱ ትውልድ ከፍተኛ ጥቅም ያለው ቅርስ ተብሎ የሚታሰብ በሌላው ትውልድ የማይጠቅም ተደርጎ የሚወሰድ ቢሆንም፣ ነቃፊውን በመንቀፍ ቀዳሚውን ትውልድ የሚያደንቅ ሌላ ተተኪ ትውልድ ሊመጣ የሚችል መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም አያት ቅድመ አያቶቻችን ትተውልን የሄዱ ቅርሶችን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ እንጂ የማውደም መብት የሌለን መሆናችንና መጪው ትውልድ ሊጠይቀን የሚችል መሆኑን ተገንዝበን ልንንከባከበውና ልንጠብቀው ይገባል፡፡ ይህም ሆኖ የኢትዮጵያና የኤርትራ እንደ ስሚንቶ አጣብቀው አንድ የሚያደርጉ ቅርሶችን መጠበቅ የሚቻለው ከሁሉ አስቀድሞ ቅርሶች መሆናቸውንና ጥቅማቸውን ለትውልድ ማሳወቅ ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ማለትም እንደ ባህልና ቱሪዝም፣ እንደ ኢኮኖሚ ልማት፣ እንደ ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት፣ ሚዲያዎች፣ የታሪክና የሥነ ምድር፣ ወዘተ. ምሁራን ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከአዘጋጁጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...