Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየኤርትራና የትግራይ ሕዝቦች ዕረፍት ያስፈልጋቸዋል

የኤርትራና የትግራይ ሕዝቦች ዕረፍት ያስፈልጋቸዋል

ቀን:

በሰለሞን መለሰ ታምራት

በከተማ ለምንኖር ለብዙዎቻችን እሑድ ማለዳ በስስት የምናየው የዕረፍት ጊዜያችን ነው፡፡ በቀድሞው የደርግ ዘመን እንኳን ይኼንን ችግራችንን የተረዳልን ብቸኛው የኢትዮጵያ ሬዲዮ (አቶ ታደሰ ሙሉነህና ባልደረቦቹ ምሥጋና ይድረሳቸውና) ከአልጋችን ሳንወርድ የምናረፋፍድበትን ምርጥ ምርጥ ዝግጅቶችን ያቀርብልን ነበር፣ በእሑድ ጠዋት ፕሮግራሙ፡፡ ዛሬ ደግሞ በየሳምንቱ እሑድ ጠዋት እንዲያመልጠኝ የማልፈልገውን የሸገር ካፌን እየሰማሁ በአንድ እጄ የምነካካው ሪሞት ኮንትሮል ጣቢያው ኤርትራ ቲቪ ላይ ሲደርስ ዓይኔን ለማመን የከበደኝን ነገር አሳየኝ፡፡ ከሳምንቱ ሱሴ ከሸገር ካፌዬ ላይ ቀልቤን አንስቼ ምን እየተፈጠረ እንደሆነ ማየት ጀመርኩኝ፡፡ ለካስ የእኛው ጉደኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ለዓመታት ዓይኗን ላፈር ብለን ያኮረፍናትን ኤርትራን ለመጎብኘት መንገድ መጀመራቸው ነበር፡፡

የአስመራ ከተማ ሕዝብ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን ያደረገውን አቀባበል ተመልክቶ ስሜቱ ያልተነካ ሰው ካለ በእውነትም ጠንካራ ነው ሊባል ይገባዋል፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ በማከታተል በአገራችን የሚገኙት ሌሎች የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም መስመራቸውን ከኤርትራ ቴሌቪዥን ጋር በማገናኘት ክስተቱን ያስተላልፉን ጀመር፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃንን ቀልብ የያዘ ጉዳይ ሆኖም ሰነበተ፡፡

በአቀባበሉ ሥነ ሥርዓት ላይ የታየው የአስመራ ሕዝብና የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እውነተኛ ደስታ ልብ የሚነካ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ በጠቅላይ ሚኒስትራችን በዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተወሰደው ውሳኔና ፍፁም ትህትናን የተላበሰ (የፕሮቶኮል ገደቦችን የበጣጠሰ) የእንግድነት መንፈስን ላስተዋለው የሁለቱም አገር ሕዝቦች በባህል፣ በቋንቋና በሥነ ልቦናም ጭምር ምን ያህል አንድ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ፈጽሞ ተለያይተው መኖር የማይችሉና ናፍቆት በእጅጉ የጎዳቸው አሳዛኝ ሕዝቦች መሆናቸውን ጭምር ነበር፡፡

በቀደሙት ሁለት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ላይ የሚታይ የነበረውን የታላቅነትና የበላይነት መንፈስን (Ego) ሰብረው በርካታ አመራሮቻቸውን ይዘው፣ ከቶም ይሆናል ተብሎ ባልታሰበ ሁኔታ አስመራ የተከሰቱት ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያለምንም ጥርጥር ትልቁን ሌጋሲያቸውን አኑረዋል፡፡

      በዚህ መካከል ግን ቅር ካሰኙኝ ጉዳዮች መካከል ዋነኛው ለኤርትራ አዋሳኝ የሆነው የትግራይ ክልል ተወካይ የተባለ ሰው (የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከተጓዙት የልዑካን ቡድኖች መካከል አብረው መኖራቸውን የመገናኛ ብዙኃኑ ነግረውናል) አለመታየቱ ነው፡፡ ሁለቱ ሕዝቦች አንድን ቋንቋ ከመጋራታቸውም ባለፈ ለዘመናት ያሳለፉት መከራና ስቃይ አንድ ያደረጋቸው፣ በአንድ ኩባያ አብረው የጠጡና በአንድነት ታግለው ለድል የበቁ፣ ወዘተ. . . ብዙ ብዙ ሊባልላቸው የሚችሉ ታሪኮችን ያሳለፉ ናቸው፡፡

በተለምዶ የአባቴ ዘመዶች ወይም የእናቴ ዘመዶች እንደምንለው ሁሉ፣ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ኤርትራውያንን የሚዛመደው እኮ በትግራውያን ወገኖቹ በኩል ነው፡፡ እናም በምን ምክንያት ነው በዚህ ታሪካዊ ክስተት ላይ የትግራይ ሕዝብ ባይተዋር የሆነው? ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ታላላቆቹ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ፕሮግራሙን በቀጥታ ሲያስተላልፉት፣ የትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ግን ‹አላየሁም አልሰማሁም›ን ሲጫወት ነበር፡፡ እርግጥ ነው የዕለቱን ከኤርትራ የሚተላለፈውን ፕሮግራም የትግራይ ሕዝብም ጭምር ከሌሎች ጣቢያዎች ላይ ሊከታተለው የሚችል ቢሆንም፣ ጣቢያውም ያሻውን ፕሮግራም የማቅረብ ሙሉ መብት ቢኖረውም፣ በየትኛውም የጋዜጠኝነት መሥፈርት ግን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ሁነት መሆን ነበረበት፡፡

የትግራይና የኤርትራ ሕዝቦች በጣም በቅርብ ጊዜው ታሪካቸው አንድ ሆነው በአንድ ንጉሠ ነገሥት ሥር ኢትዮጵያውያን ሆነው ይኖሩ ነበር፡፡ ተመሳሳይ ቋንቋ፣ ተመሳሳይ እምነትና ሥነ ልቦናም ጭምር የነበራቸው እነዚህ የአንድ አባት ልጆች፣ የአብራካቸው ክፋይ የነበሩት ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ዮሐንስ በመጋቢት 1881 ዓ.ም. በደርቡሾች እስከ ተገደሉበት ጊዜ ድረስ የሁለት አገር ሕዝቦች መሆናቸውን ያውቁት ነበር ለማለት ማንም አይችልም፡፡ እነሱም ራሳቸው እንዲህ ወንዝ ለያይቶን እንቀራለን ብለው ማሰባቸውን እጠራጠራለሁ፡፡ ጣሊያንን በ1879 ዓ.ም. ዶጋሊ ላይ ልኩን እንዲያውቅ ያደረጉት ታላቁ ራስ አሉላ ‹የኢትዮጵያ ድንበር ቀይ ባህር ነው› ባሉበት ጊዜ፣ የትግራይና የኤርትራን ጎረቤት አገርነት አይደለም በዕውኑ በህልሙም ቢሆን የሚያስበው ሰው ከቶም ቢሆን አይኖርም፡፡

የአፄ ዮሐንስን ሞት ተከትሎ ሥልጣኑ ወደ ልጃቸው ራስ መንገሻ መሄዱ ያሰጋቸው ዳግማዊ ምኒልክ የንጉሡን አርባ መውጣት እንኳን ሳይጠብቁ ከመረብ ወዲያ ያለውን የኢትዮጵያን ግዛት ለጣሊያኖች መርቀው ከጣሊያኖች ጋር በዶጋሊ ከተፈራረሙ በኋላ፣ በቀሪው የትግራይ ግዛት ላይም እጅ የሰጡትን ራሥ መንገሻን ሾመው ቀን እስኪወጣላቸው ቀሪዋን ኢትዮጵያን ማስፋፋት ጀመሩ፡፡ መረብ ምላሽን ያለምንም የጥይት ተኩስ የተቆጣጠረችው ጣሊያንም አስመራ ላይ ከትማ አዲሲቷን አገር ኤርትራን መሠረተች፡፡

አንድ የነበረውን ሕዝብም በቻሉት አቅም ለማራራቅ የሥነ ልቦናና የሃይማኖት ልዩነቱን ይለጥጡት ጀመር፡፡ ከስድስት ዓመታት በኋላ ኤርትራን ከአዲሷ ቅኝ ገዥዎቿ ለማዳን ዕድሉን አግኝተው የነበሩት ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ እስካሁንም ድረስ እንቆቅልሽ በሆነ ምክንያት ይኼንን ሳያደርጉት ቀሩ፡፡ ወንድማማቹም ለተጨማሪ አርባ ዓመታት በልዩነት ግንብ ታጥረው ቀጠሉ፡፡ በዚህ መሀል የተፈጠረው የሥነ ልቦና መራራቅ ቀላል አልነበረም፡፡

      የትግራይና የኤርትራ ሕዝቦቹና መሬቱም ጭምር ያለማቋረጥ በጦርነት እሳት ሲለበለቡ የኖሩ ናቸው፡፡ ቀሪው የኢትዮጵያ ግዛት ‹ለምለሚቷ አገሬ› እያለ ማርና ወተቱን ያለሐሳብ እንዲጎነጭ ያስቻለው፣ እነዚሁ መከረኛ ሕዝቦች የእሳቱን ወላፈን እየተጋፈጡ ያበርዱለት ስለነበር ነው፡፡ ከዓድዋ ድል ማግሥት ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ዕፎይ ለማለት የቻለ የመሰለው የሁለቱ አገሮች ሕዝብ፣ በተለይ ከኤርትራውያን ወገኖቹ የተነጠለው ቀሪው የትግራይ ሕዝብና መሬት፣ ከ40 ዓመታት በኋላ የተሞከረውን የኢጣሊያንን ዳግም ወረራ ለመመከት በተካሄደው ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ይኼው የጣሊያን ወረራ ተጀምሮ የተጠናቀቀውም በዚሁ መከረኛ የትግራይ መሬት ላይ መሆኑን ልብ ብለናል፡፡ ዓድዋ ላይ ተጀመረ፣ ማይጨው ላይ ንጉሡ ጦራቸውን በትነው ወደዋና ከተማቸው ከዛም ወደ ውጭ አገር ሄዱ (ፈረጠጡ፣ ሸሹ፣ ተሰደዱ የሚለው ቋንቋ ብዙም አይመቸኝም)፡፡ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በመላው ኢትዮጵያ ከሚገኙት አርበኞች ጋር ጣሊያንን ዕረፍት በማሳጣት የኤርትራና የትግራይ አርበኞች ሚናም ቀላል አልነበረም፡፡

      ጣሊያን በመጣበት እግሩ ሲባረርና ድል አድራጊ የተባሉት ንጉሥም ወደ መንበራቸው ሲመለሱ ከፍተኛውን ትኩረት ሰጥተው የነበሩት ለ40 ዓመታት በጣሊያን ቁጥጥር ሥር የነበረችውን ኤርትራን በማስመለሱ ላይ ስለነበረ፣ ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ጋር በመከራ ሲቆስል የከረመውን የትግራይን ሕዝብ ባይተዋር አድርጎት ቆይቶ የቀዳማይ ወያኔ እንቅስቃሴ ሊፈጠር ቻለ፡፡ ለጥቂት ጊዜ ዕፎይ ብሎ የነበረው የሕዝቡ መከራም እንደ አዲስ አገረሸ፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥትም ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል በአንፃራዊነት የሰላሙን ትሩፋት ሲቋደስ፣ የሰሜኑ የአገራችን ሕዝብ (በተለይ የትግራይ ሕዝብ) ግን እንደ አመፀኛና የዙፋን ተቀናቃኝ ተቆጥሮ ብዙ መገለል ይደርስበትና በዓይነ ቁራኛም ይጠበቅ እንደ ነበር ይታወቃል፡፡

በዚህ መካከልም ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን ያስተሳሰረው ሕግ ፈርሶ ‹ከእናት አገሯ› ትዋሀድ ሲባል ዕርምጃው ያላስደሰታቸው ኤርትራውያን የትጥቅ ትግላቸውን በመጀመራቸው፣ ምድሪቱ ዳግም የስቃይ ዘመን ታሪኳን ጀመረች፡፡ በአንድ በኩል የተከፋፈሉት የኤርትራ ነፃነት ተዋጊዎች፣ በሌላ በኩል የመንግሥት ጦር እያንዳንዱን የኤርትራን ግዛት ቁም ስቅሉን ያሳዩት ገቡ፡፡ በዓለም ላይ ሁሉ እንደሚስተዋለው ወታደር የረገጠው መሬት ሰላም ብርቁ ነውና (የአገርን ድንበር ከወራሪ ለመጠበቅ ሕይወታቸውን ሰውተው ጠዋትና ማታ ለሚታትሩት ወታደሮች ከፍተኛ ክብር አለኝ፡፡ ነገር ግን በዓለም ላይ የሚታዩት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሙሉ የሚፈጸሙት ወይ በወታደሮች ወይም ወታደሩን ከለላ አድርገው በሚነሱ ክፉ መሪዎች መሆኑን ግን ማስተባበል አይቻልም፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ‹‹የሰላም አስከባሪ›› የሚባሉት እንኳን በአቅማቸው የሚያደርሱትን አሰቃቂ የመብት ጥሰት ጆሮዎቻችን እስከሚጠግቡት ድረስ ሰምተነዋል)፣ እስከ 1966 ዓ.ም. የአብዮት ዋዜማ ድረስ ያዝ ለቀቅ ሲል የቆየው ቋያ ከአብዮቱ ጋር አብሮ በመገንፈል፣ ኤርትራን ከጫፍ እስከ ጫፍና የትግራይን ምዕራባዊ ክፍል ጨምሮ ለሰሜን ጎንደርም ተርፎ አካባቢው ታይቶ በማይታወቅ የጦርነት ወላፈን ይለበለብ ጀመር፡፡

ወንድ የተባለ ሁሉ ‹በነፃነቱ› ትግል ላይ ተሳታፊ ሆነ፡፡ ወላዶች መካኖች ሆኑ፡፡ ወታደሩ በሚስቶች ተንበሸበሸ፡፡ ከመሀል አገር ያኮረፈ ‹አብዮተኛ› ሁሉ ጠመንጃውን እየተሸከመ መሸሸጊያውን ይህንኑ የሰሜን የአገራችንን ክፍል አደረገው፡፡ ምድሪቷ ዳግም አኬልዳማ ሆነች ብቻ ሳይሆን ጨቀየች፡፡ ኤርትራና ትግራይ በታሪካችን ከፍተኛው የጦርነት አውድማ የነበሩ መሬቶች ናቸው፡፡ ለዚያውም ታሪክ የመዘገበው በውጭ ወራሪ ኃይሎች የተፈጸመውንና የእርስ በርስ ጦርነት ተብሎ በማዕከላዊ መንግሥትና በሽምቅ ተዋጊ ቡድኖች መካከል የነበረውን ይፋ የወጣ ጦርነት ነው፡፡ ነገር ግን እነዚሁ ሕዝባችንን ነፃ ልናወጣ ነው ብለው የተነሱት ኃይሎች በገዛ ወገናቸው ላይ ያደረሱት ሰቆቃና ግፍ አንዳንዶቹ እንደሚሉት በመደበኛው ወታደር ከተፈጸመው ግፍ የትናየት የበለጠ ይሆናል፡፡ መቼም ለዘመናት ጠዋትና ማታ በጦርነት እሳት ሲነድ የኖረ መሬት፣ መሬት ሆኖ ዳግም ዘር ለማብቀል መቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ ሕዝቡም ከዚህ ሁሉ ጥይት መካከል ተርፎ ዛሬ ታሪክ ነጋሪ ለመሆን መታደሉ የፈጣሪ ፀጋ በዝቶለት እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

ለ30 ዓመታት የዘለቀው የነፃነት ትግል በድል ተጠናቀቀ ተብሎ ይኼው መከረኛ ሕዝብ ከየተበታተነበት ተሰባስቦ የአገሩንና ከዚያ ሁሉ ዕልቂት የተረፉትን የዘመዶቹን ናፍቆት በአግባቡ እንኳን ሳይወጣ፣ በታሪክ እጅግ አሰቃቂ ነው የተባለ ጦርነትን ለማስተናገድ የተመረጠ አውድማ ሆኖ ቁጭ አለ፡፡ ምን ዓይነት መከራ መሆኑን ለማወቅ መሀል አገር ተቀምጦ ዜናውን በሬዲዮና በቴሌቪዥን እየተከታተሉ ለመረዳት እንዴት ይቻላል? ለሁለት ዓመት የዘለቀው ዘግናኝ (Barbaric) ተብሎ በውጭ አገር የመገናኛ ብዙኃን የተዘገበ ውጊያ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ላለፉት ሃያ ገደማ ዓመታት ሰላምም ጦርነትም የሌለበት (ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ እንደገለጹትም ‹‹ሞት አልባ ጦርነት›› የነገሠበት) ቀጣና በመሆን ዘልቋል፡፡

እንግዲህ ከላይ በጣም በአጭሩ እንደ ተመለከትነው የትግራይና የኤርትራ ሕዝብ ካለፉት 150 ዓመታት ገደማ ውስጥ የሰላም አየር የተነፈሰበት ዓመት ቢቆጠር፣ ከጣቶቻችን ቁጥር ላይበልጥ ነው ማለት ነው፡፡ ለዚህ መከራ የበዛበት ሕዝብና ምድር ሐዘኔታን አለመግለጽና ርህራሔን አለማሳየት እንዴት ሰብዓዊነት ሊሆን ይችላል? እነዚህኑ በመከራ ሲማቅቁ የነበሩ ሕዝቦችን ተገን በማድረግ የፖለቲካ ቁማር ለመጫወት የሚሞክሩ በሁለቱም አገሮች ውስጥ ያሉ ቡድኖችስ እንዴት ዓይነት የሥነ ልቦና ችግር ውስጥ ያሉና የሞራል ልዕልናቸውም የወደቀ ይሆን? በእውነት የትግራይና የኤርትራ ሕዝቦች ማንም የማያዝበትን የሰላም አየር ይናፍቃሉ፡፡ ሁለቱ የአንድ እናት የአንድ አባት ልጆች እጅግ በጣም ተነፋፍቀዋል፡፡ ሲሆን ሲሆን የኤርትራ ፕሬዚዳንት ጉብኝት መጀመር የነበረበት ከትግራይ ሆኖ፣ በደሴ በኩል አቋርጠው ወደ አዲስ አበባ ቢመጡ ነበር የሚያምረው፣ ግን አልሆነም፡፡ አንድ ቀን ይሳካ ይሆናል፡፡

እኔም ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ሊቀበል ከወጣው ሕዝብ ጋር ‹ተደምሬ› እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ቆምኩኝ፡፡ በእርግጥ በትክክል የወጣሁበትን ምክንያት ለማወቅ አልቻልኩም፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ያለኝን አክብሮት ለመግለጽ ይሁን ወይም የወጣውን ሕዝብ ለመታዘብ፣ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትራችንን በአስመራ አደባባዮች በዕልልታ ለተቀበለው የኤርትራ ሕዝብ ውለታ ለመክፈል ይሁን ቤተ ክርስቲያን ልሳለም ወጥቼ (ዕለቱ የዓመቱ ሥላሴ ነበር) እግረ መንገዴን ጎራ ያልኩ መሆኔን በትክክል አልተረዳሁትም፡፡ በዕለቱ የነበረው የደስታና የፍቅር መንፈስ እጅግ አስደናቂ እንደነበር እንኳን በመካከሉ ለተገኘና በወሬ ወሬ የሰማውም ሰው የሚረዳው ነው የሚመስለኝ፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ግን ይኼ የደስታና የፍቅር መንፈስ ይነግሥ ዘንድ የኤርትራና የትግራይ ሕዝቦች የከፈሉትን ዋጋ ስንቶቻችን እንደተረዳነው ፈጣሪ ይወቅ፡፡ ከዚህም በኋላ እነዚህ ምስኪን ሕዝቦች ዘላቂ የሆነ የሰላምን አየር ይተነፍሱ ዘንድ ሁሉም ቢሆን ሊሟገትላቸው ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...