Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአሁንስ አለን ብዬ አልዋሽም

አሁንስ አለን ብዬ አልዋሽም

ቀን:

በዕዝራ ኃይለ ማርያም መኮንን

የደርግ ቋሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት ሻምበል ታምራት ፈረደ ለኮሎኔል መንግሥቱ ቅርብ ሰው ነበሩ፡፡ በደርግ ውስጥ በነበረው ሽኩቻና ወከባ የተገፉት እኝሁ ሻምበል፣ ለዶክትሬት ዲግሪ ምሥራቅ አውሮፓ ይላኩና ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ይዘው ወደ አገራቸው ይመለሳሉ፡፡

የደርግ አምባገነናዊ አገዛዝ በማንም ዘንድ የታወቀ ቢሆንም፣ ደንብንና ሥርዓትን በማስከበርና በአገር አፍቃሪነትና አንድነት አይታማምና የሻምበል ታምራት ፈረደ የዶክትሬት ዲግሪ በአገሪቱ የትምህርት ደንብ መሠረት ዕውቅና እንዲያገኝ ከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን ቀረበ፡፡ ኮሚሽኑ ተገቢውን ምዘና ካደረገ በኋላ አያሟላም ብሎ ዕውቅና ይነፍገዋል፡፡ ሻምበል ታምራት በዚህና በሌሎች ብሶቶች በደረሰባቸው የመንፈስ ድቀት እንዳይሆኑ ሆነው ራሳቸውን ከፎቅ ላይ ወርውረው ማለፋቸውን ገስጥ ተጫኔ ‹‹ነበር›› በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ገልጸውታል፡፡

ብዙውን ጊዜ ስለሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሲነሳ ይህ ታሪክ ትዝ ይለኛል፡፡ በወቅቱ የነበረው አስተዳደር  ደንብና ሥርዓትን በማስከበር በኩል የማይደራደር በመሆኑ፣ ማንኛውም ዜጋ ዲግሪውን የሚያገኘው በጥረቱ እንደነበር ከላይ የተጠቀሰው ታሪክ ያመለክታል፡፡ የደርግ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ውዳሴ የሚገባው ባይሆንም፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚቀጠረው ባለሙያ በአብዛኛው በዕውቀት፣ በችሎታና በልምድ ተመልምሎ የመሥራት መብቱና ግዴታው (Meritocracy) የተጠበቀ ነበር፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ሆነ በደርግ ዘመን በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ማጭበርበር በተለይም በዲግሪ ደረጃ አይታወቅም ነበር፡፡ በእነዚያ ዘመናት የቱ ደፋር ነው ይህን የሚያስበው? በበኩሌ በሠራሁባቸው ክፍለ ሀገሮች (በወቅቱ አጠራር) የበርካታ መሥሪያ ቤቶች ሥራ አስኪያጆች የኢሠፓ (የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ፓርቲ) አባል አልነበሩም፡፡ በዚያን ዘመን ክፍለ ሀገር የሚባሉት የዛሬውን አራትና አምስት ዞን የሚያክሉ ሰፊ በመሆናቸው ሥራውም ሰፊ ነበር፡፡ ጎበዝ ከምን ዘመን ላይ ደረስን? በአንዳንድ ሚዲያዎች በሚቀርቡ ፕሮግራሞችና ዜናዎች ያለው የጉዳችንና የነውራችን አበዛዙ ያቃጥለኛል፡፡ እርር ኩምትር ያደርገኛል፡፡

የመርስዔ ሐዘን ወልደ ቂርቆስን የሕይወት ታሪክ የሚዘክረው ‹‹ትዝታዬ›› መጽሐፍ ስለ ‹‹ብቃት›› የሚከተለውን ትርጉም ይሰጣል፡፡ ‹‹ብቃት ማለት ፍፁምነት ነው፡፡ ሕይወታቸውን ለእውነት አሳልፈው ሰጥተው፣ ዓለማዊ ፍላጎታቸውን አሸንፈውና ሕይወታቸውን በእምነት በተስፋና በፍቅር ሞልተው የተጓዙ ከአምላክ ጋር ይገኛኛሉ፡፡ ይህን ፀጋ የተጎናፀፉ የበቁ ይባላሉ፤›› ይላል፡፡ ይህ መንፈሳዊ ትርጉሙ ቢሆንም ለዓለማዊውም ይሠራል፡፡ በእርግጥ ካሁኑ ዘመን አንዳንድ ባለሥልጣን ይህን ብቃት ባንጠብቅም ነሁላላነትንና ውርደትን ግን አንሻም፡፡

በተለያዩ  ክልሎች የሐሰተኛ ትምህርት ማስረጃ መስፋፋትን በተመለከተ ኢቲቪ የተለያዩ እማኞችን ጠቅሶ በሚያዝያ ወር ውስጥ ፕሮግራም ሠርቷል፡፡ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ያልገባበት ሙያ የለም፡፡ በሕክምና ሙያ ላይ ሲገባ ሕይወትን፣ በመምህርነት ሙያ ላይ ሲታከል ደግሞ ትውልድን ያጠፋል፡፡ ለየክልሉ የሥራ ኃላፊዎች በተደረገ ቃለ ምልልስ ለማወቅ እንደተቻለው ሠራተኞች ከሚያቀርቡዋቸው የትምህርት ማስረጃዎች ውስጥ ከ30 በመቶ በላይ ሐሰተኞች ናቸው፡፡ ይልቁንም በጋምቤላ ክልል የቢሮ ኃላፊዎችን ጨምሮ የበርካታ አመራሮች ማስረጃ ሐሰተኛ መሆኑ ያሳፍራል፡፡ ባለሥልጣናቱ ባያፍሩም ይህን ጉድ የምናይና የምንሰማ ዜጎች ስለነሱ መሸማቀቃችን አይቀርም፡፡ በዚህ ዘመን በአገራችን ያለው ሙስና ቢወራ አያልቅም፡፡ በቅርቡ ብዙ አሳፋሪ ጉዶችና ገመናዎች ይወጣሉ፡፡ አሁን የምንሰማቸው ጉዶች ‹‹ዓባይን በጭልፋ›› እንዲሉ ተቆጥረው የሚያልቁ አይደሉም፡፡ አንድ ንጉሥ በአንድ ወቅት አንድ አባይ ጠንቋይ ጠርተው ‹‹መቼ ነው የምሞተው?›› ብለው ሲጠይቁት ‹‹እርስዎ የሚሞቱት እኔ በሞትኩ በማግሥቱ ነው›› የሚል ምላሽ ይሰጣል፡፡ ንጉሡም ‹‹ይህ ሰውዬ እንዳይሞት ተንከባከቡት›› ብለው ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ ከዚያን ዕለት ጀምሮ ልክ እንደ ዙፋናቸው ለጠንቋዩ መሳሳት ጀመሩ፡፡

ልክ እንደ ጠንቋዩ፣ አጭልጎችና መሰሪዎች አጥምደው በተለያዩ ዘዴዎች የባለሥልጣናትን እጅ ይጠመዝዛሉ፡፡ እነዚህ ባለሥልጣናትም ታዛዥነታቸው ለህሊናቸውና ቃል ለገቡለት ሕዝብ ሳይሆን ለሙሰኞችና ለአጭልጎች ይሆናል፡፡ የህሊናቸው ብርሃን የጠፋባቸው አንዳንድ ልሂቃንም በወጥመዳቸው ውስጥ ከገቡ በኋላ፣ ‹‹ሙሰኞቹ ከሞቱ በማግሥቱ እንሞታለን›› ብለው ስለሚያስቡ ሥራቸው ሙሰኞችን መንከባከብ ይሆናል፡፡

ኢቲቪ ወደ ሠራው ፕሮግራም ልመልሳችሁ፡፡ እንደ አገር ሲታሰብ አስደንጋጭ ነው፡፡ ሕክምና በቀጥታ ከሰው ሕይወት ጋር የተያያዘ ሙያ በመሆኑ ከፍተኛ ብቃትንና ጥንቃቄን ይሻል፡፡ ጎበዝ እስኪ ቆም ብለን እናስብ፡፡ በቂ የሕክምና ሙያ ብቃት ሳይኖረው በሐሰተኛ ምስክር ወረቀት አክሞኝ ለሞት ብበቃ፣ ባልሞትም በሽተኛ ብሆን፣ በባለቤቴ፣ በልጆቼ፣ በወንድሞቼና በእህቶቼ ላይ ይህ ጉዳት ቢደርስ በእኔና በቤተሰቦቼ ላይ የሚደርሰው የኢኮኖሚ፣ ሥነ ልቦናና ማኅበራዊ ችግር ምን ያህል አስከፊ መሆኑን ሳስብ እደነግጣለሁ፡፡ እስኪ ሁላችንም በዚህ መንገድ እናስተውል፡፡

አልፎ አልፎ በጤና ባለሙያ ቸልተኝነት ወይም ስህተት ለሕክምና የሄደ ሰው ብሶበት ወይም ለሌላ ጉዳት ተጋልጦ የሚመለስበት ሁኔታ ያጋጥማል። በቸልተኝነትና በሙያው በቂ ዕውቀትና ክህሎት በሌለው ሐኪም የሚፈጠረው የሕክምና ሙያዊ ጥፋት በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ጉዳዮች ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ በ‹‹የተዘጋው ዶሴ›› የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ በሕክምና ባለሙያ ስህተት የተነሳ በታዳጊነቱ የዕድሜ ልክ በሽተኛ ሁኖ ያለ ሰው ዕርዳታ የማይንቀሳቀሰውን ስንመለከት እንቅልፍስ ያስወስዳል? እዚህ ላይ ብቃት ያላቸው ምስጉን የሕክምና ባለሙያዎች መኖራቸውንና ሕሙማንን ለመርዳት ያላቸውን አቅም አሟጠው የሚጠቀሙ መኖራቸውን አልዘነጋም፡፡ ጥረታቸውንም አደንቃለሁ፡፡ በሕክምና ላይ የሚፈጠር ስህተት ሻል ሲል ለክፉ ደዌ ሲብስ ደግሞ ለሞት ይዳርጋል፡፡ አሁን አሁን በሕዝብ መገናኛዎች የምንሰማውና የምናየው በሕክምና ስህተት በሰው ሕይወት ላይ የሚደርሰው ጉዳት እየጨመረ መምጣቱን ነው፡፡ እስኪ አስቡ፣ መድኃኔዓለም ይጠብቀን እንጂ በፎርጂድ የሕክምና ባለሙያ ታክመን የሚደርስብንን ጉዳት? በራስ ሲደርስ ያማል፡፡ ባለሥልጣናትና ሀብታሞች ውጭ ሄደው ስለሚታከሙ ችግሩ የእኛን ያህል ላይሰማቸው ይችላል፡፡

በዚያው የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ የቀረበው ሌላው ጉድ፣ በጉራጌ ዞን በአንድ ወረዳ በሚገኝ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ከሚያስተምሩ መምህራን ውስጥ በርካታዎቹ በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የተቀጠሩ ከአንድ አካባቢ የመጡ ዘመዳሞች መሆናቸው መነገሩ ነው፡፡ ድርጊቱ ‹‹ለመሆኑ መንግሥት አለ እንዴ?›› ያሰኛል፡፡ ውጭ ሲወጡ ያገለገሉትን ሥርዓት ከሚያወግዙ ባለሥልጣናት በቀር ብዙውን ጊዜ ኢትዮጵያዊ ባለሥልጣን የሚመራው መሥሪያ ቤት ተልዕኮን መወጣት ሲያቅተው፣ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ሲያጣና ነውር ሲበዛበት ራሱን ከሥልጣን የሚያገል (Resign) ባለሥልጣን የለንም፡፡ ቢኖሩም ተፅዕኖውና ንስሐ ገብተው የለቀቁበትን ምክንያት በግልጽ ለሕዝብ አሳውቀው ሳይሆን ሥልጣንን የሚለቁት በተጉደበደበ ሁኔታ ነው፡፡

የሕግ ሊቃውንት እንደሚሉት ወንጀልን ፈጻሚው ብቻ ሳይሆን ዓይቶ ያለፈውም ቢሆን በሕግ ከተጠያቂነት አያመልጥም (Crime by Commission and by Omission)፡፡ ግዴለሽነት፣ ግብዝነት፣ ንዝህላልነትና ደንታ ቢስነት በማኅበረሰባችን ውስጥ ተንሰራፍቷል፡፡ ሆቴል የሚቀርብልን እንጀራ የጀሶ፣ የወጡ በርበሬ የሸክላና አፈር ላለመሆኑ ምን ማስተማመኛ አለን? በእውነት እንነጋገር ከተባለ ቤተ እምነቶቻችንን ጨምሮ ፈሪኃ እግዚአብሔር ጠፍቷል፡፡ ይሉኝታ ቢስነቱ፣ ዓይነ ደረቅነቱ፣ የአዕምሮ ድርቀቱ፣ እንዲሁም በመንግሥት ላይ የሚታዩ ነውሮች ተጨማምረው በሁሉም ዘርፍ የሞራል ድህነትና የመንፈስ ውርደት ደርሶብናል፡፡ አልፎ አልፎ ግን እውነትን መሠረት ያደረጉ የጋለ ልቦናና የሞቀ አዕምሮ ያላቸው ዜጎች መኖራቸው ጨርሰን ተስፋ እንዳንቆርጥ ያደርገናል፡፡ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ከመስፋፋቱ የተነሳ መንግሥት በየመሥሪያ ቤቱ ኮሚቴ አቋቁሞ የማጣራት ሥራ መጀመሩን፣ በየመሥሪያ ቤቱ ማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ በሚለጠፉ ማስታወቂያዎች ማየት ይቻላል፡፡ ችግሩ ጠንቷል፡፡ ግን ማን የማንን ያጣራል? ወዲህም በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ትልልቁን ቦታ የያዙት እነማን ናቸው? የተደረሰባቸውስ ምን ሆኑ? እንደ ፈረንጆቹ አባባል ‹‹በመስታወት ቤት ውስጥ የሚኖር ሰው በሌላ ሰው ቤት ላይ ድንጋይ አይወረውርም፤›› ነው፡፡

የምወደውን የኮንፊሽየስ አባባል እጠቅስ ዘንድ ይፈቀድልኝ፡፡ አፈሩን ገለባ ያድርግላቸውና ታዋቂ ጸሐፊ የነበሩት አቶ ሙሉጌታ ሉሌ በአንድ ጽሑፋቸው ላይ ኮንፊሽየስን እንዲህ በማለት ጠቅሰውታል፡፡ ‹‹አንድ አገር በትክክል እየተመራ ግለሰቦች ደሃና ተዋራጅ ከሆኑ ያሳፍራል፡፡ እንዲሁም የአንድ አገር አመራር ተበላሽቶ ሳለ ግለሰብ ሀብታሞች አንገታቸውን ቀና የሚያደርጉ ከሆነ በዚያው ልክ ያሳፍራል፤››  በሐሰት የምስክር ወረቀት ማስረጃ ትልልቁን ቦታ ሳይቀር የያዙ ባለሥልጣናት እንዳሉ የጋምቤላው አንድ አመልካች ነው፡፡ ያለንበት ዘመን ክፉ ነው፡፡ የዚህ ዓለም ፈሊጥና የመኖር ጥበብም የአባይ ጠንቋዩን ብልጠት ያደንቅ እንደሆን እንጂ አያስተሀቅርም፡፡ በንፅህናችን የፀናን ግን በመደኃኔዓለም ኃይል በመታመን ውስጣችንን በእውነት እሳት አቀጣጥለን ከቆምን፣ ለልጆቻችን ነውርንና እንቶ ፈንቶን አናወርስም፡፡ ዛሬ የሐሰት ማስረጃ ማቅረብ ተራ ነገር ነው፡፡ የሐሰት ማስረጃ ይዘው የሚቀርቡ ባለጉዳዮች ማስረጃቸው የሐሰት እንደሆነ ሲረጋገጥ፣ መደንገጥና ማፈር ሲገባቸው ይብስኑ ድንፋታቸው አይጣል ነው፡፡ የሚያስተናግዳቸውን ሠራተኛ ተሳድበውና ደንፍተው እንደሚሄዱ አንድ ወዳጄ አጫውቶኛል፡፡

ከመኖር የምናገኘው ደስታም የሚወሰነው በነውር በተሰበሰበ ቁሳቁስ ሳይሆን፣ በንፅህናችንና በአዕምሮ ሰላማችን ብቻ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ የሞራልና የሥነ ምግባር ሀብታችንም ንፅህና ይሆን ዘንድ መትጋት ይገባናል፡፡ በአፄው ዘመነ መንግሥት እንደ ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ፣ አቶ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ አቶ ከበደ ሚካኤል፣ ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ፣ ደጃዝማች ግርማቸው ተክለ ሐዋርያት፣ አቶ ከተማ ይፍሩና አቶ ምናሴ ለማ በደርግም ሻለቃ ግርማ ይልማ፣ ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ፣ አቶ ተስፋዬ ዲንቃ፣ አቶ አማኑኤል አምደ ሚካኤልንና የመሳሰሉትን በዕውቀት፣ በሙያ ብቃትና በሥነ ምግባር አርዓያ የሆኑ ከአገራቸው አልፈው የአፍሪካ ኩራት የነበሩ ጎምቱ ባለሥልጣናት ነበሩን፡፡ ዛሬ መንግሥት የሚከተለው የፖለቲካ ሥርዓት ካለፉት ሁለት ሥርዓቶች በይዘትም ሆነ በቅርፅ የተለየ ቢሆንም፣ አገር ግን ምን ጊዜም የማይለዋወጥ ነውና ከባለሥልጣናት አንፃር በሰው ድርቅ የተመታን ይመስለኛል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ከሥነ ምግባር ያፈነገጡ፣ ንግግራቸው ተራና ሕዝብን የሚያስከፋ ‹‹መሶብ ሃይማኖቱ›› የሆኑ ሙሰኛ ባለሥልጣናትን ከምንም ዓይነት የፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ በሆነ መንገድ ለሕዝብ ይፋ አድርጎ በሕግ እንዲጠየቁ ማድረግ ነው፡፡ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ማጣራት ከእነሱ ይጀምር ዘንድ ምኞቴ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአጭር ጊዜ ውስጥ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያስገኘላቸው በ‹‹ፍቅር፣ በይቅርታና በመደመር›› መርህ የኢትዮጵያዊነት እሴቶች ከወደቁበት ለማንሳት ያደረጉት ጥረትና ለሰላም፣ ለልማትና ለአገር አንድነት የሚያደርጉት እልህ አስጨራሽ ትግል ነው፡፡ ባለፉት 40 ዓመታት በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ማኅበራዊ እሴቶቻችን በፍጥነት እየተሸረሸሩ ነው፡፡ በተለይም የመንግሥት ባለሥልጣናት የሹመት ቅድሚያ መመዘኛ የፖለቲካ ታማኝነት እንጂ ሥነ ምግባር ባለመሆኑ ከላይ እንደ ጠቀስኳቸው ዓይነት አገርን የሚያኮሩ ባለሥልጣናትን በማፍራቱ በኩል አልታደልንም፡፡ በመሆኑም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቃላቸውን ከጠበቁና የባለሥልጣኖቻቸው መገምገሚያ መሥፈርት በቅድሚያ ሥነ ምግባር ከሆነ፣ በርካታ ችግሮች ይቃለላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ቅድሚያ ከአናት ይጀመር፡፡ መደኃኔዓለም ኢትዮጵያን ይባርክ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...