ወያላው ድንገት ተበሳጭቶ፣ ‹‹ቆንጨራ የያዘ ሰው አየሁ ልበል?›› በማለት ለሾፌሩ ጥያቄ አቀረበለት፣ ‹‹እንዲህ ዓይነቱን በቁሙ የሞተውን ነበር ወደ ጆሮው ጠጋ ብለህ . . . ተነሳ›› ማለት ሲለን የገባንም ያልገባንም ፈገግ አልን፡፡ ሰሞኑን የሞተ ሰው አስነሳለሁ ካለው ሰው ጋር አመሳክረን፡፡ ሾፌሩ እንዳለው ከሆነ ጎበዝ በቁሙ ከሞተ ሰው ይሰውረን እንጂ ነገሮች እየከበዱ ናቸው፡፡
ጉዟችን ከሜክሲኮ መካኒሳ ያደርሰናል፡፡ አንድ ብስጭት ያለ የሚመስል ሰው፣ ‹‹አብዛኛው ሰው ዘረኝነትን እንደ ልብስ ነው የለበሰው፤›› ሲለን ሌላው እንደሱ የተበሳጨ የሚመስል ደግሞ፣ ‹‹ልብስማ ቢሆን አውልቆ ባሽቀነጠረው ነበር፤›› ሲለን ምን ሊወራ ይሆን ብለን በዓይናችንም በጆሮአችንም ትኩረታችንን ሰጠነው፡፡ ሰውየውም፣ ‹‹ንቅሳት ሆኖባቸው ነው እንጂ፤›› ብሎ እንደገና ተማረረ፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹አንዳንዱማ ከቁመቱ ጋር ተመትሮ ነው የተሠራለት፤›› ሲል ‹‹ዘረኛ፣ ዘር፣ . . . የሚል ድምፅ መስማት አልፈልግም፡፡ እባካችሁን ስለኢራንና አሜሪካ ፍጥጫ እናውራ፤›› ያለን አንዱ ጎልማሳ ነው፡፡
ይኼን ጊዜ ወያላው፣ ‹‹ኢራንም የመፋጠጥ ደረጃ ላይ ደርሳለች ማለት ነው?›› ብሎ ሲጠይቅ አንዱ ዘው ብሎ፣ ‹‹መቼም ፈርቶ ከመሞት ጀግኖ መሞት ይሻላል ብለው ነው፤›› ሲለን ፈገግ ብለን ፍጥጫውን በጥቂቱ ጠረጠርነው፡፡ ‹‹ኢራን በምን አቅሟ ነው የምታፈጠው?›› ያለን ሾፌሩ ነበር፡፡ ይኼን ጊዜ ሌላው፣ ‹‹ባይሆን ሩሲያ ታፍጥጥ፤›› ብሎ ሳቁን ለቀቀው፡፡ ያስቃል እንዴ?
ከወደ ጥግ በኩል፣ ‹‹ለኢራን ከአሜሪካ በላይ የማትተኛው እስራኤል ናት፤›› ሲለን በዚህ ዙሪያ ጥቂት ማጠናከሪያዎች የሚሰጠን ተናጋሪ በዓይናችን ፈላለግን፡፡ በግምት ትውልደ እስራኤላዊ የሚመስል ሰው ማለትም ከሰጠው ማብራሪያ ጥልቀትና ብዛት የተነሳ፣ ‹‹በዚህ ጊዜ እንደ እስራኤል የተሳካለት የለም፤›› ሲለን አሁንም ድጋሚ ዓይን ዓይኑን ተመለከትነው፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹ኢራን በሥውር ልትገነባ የነበረውን ኑክሌር መረጃ ያጋለጠባት የእስራኤሉ ሞሳድ ነው፤›› ሲለን ሌላው ተቀበለውና፣ ‹‹ኢራን ኑክሌር ብትታጠቅ የመጀመርያ ዒላማዋ የምትሆነው አሜሪካን ሳትሆን እስራኤል ናት፤›› አለን፡፡
የመጀመርያው እንደገና፣ ‹‹እውነት ብለኻል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ነበር የኢራን የጦር ጄኔራል እስራኤል ከምድረ ገጽ ላይ መጥፋት አለባት ብሎ የተናገረው፡፡ የኢራንና የአሜሪካ ፍጥጫ ወደ ጦርነት ቢያመራ እስራኤል ዳር ላይ ቆማ ጮቤ ነው የምትረግጠው፤›› አለን፡፡ ‹‹እንዴት ያለ ነገር ነው፡፡ ሁለት አገሮች ሲፋጁ የሚደሰት ጎረቤት አለ ማለት ነው?›› የሚል ጥያቄ ያነሳቸው እንደኛ ዝም ብላ ስታዳምጥ የነበረች ወይዘሮ ናት፡፡
መጀመርያ ስለዘር ሲወራ መስማት አልፈልግም ያለው ጎልማሳ በተነሳው ሐሳብ ላይ ተመርኩዞ ሐሳቡን መሰንዘር ጀመረ፡፡ ‹‹አያችሁ በኢራንና በአሜሪካ ፍጥጫ የሚደሰት ሌላ ወገን እንዳለ? ልብ በሉልኝ . . . ›› አለና በዓረፍተ ነገሩ ላይ አሰመረበት፡፡ ‹‹ . . . አያችሁ የእኛን ሰላም የሚጠሉና ከመቼው ተባልተው ባለቁ የሚሉን በርካታ ጠላቶችን በዙሪያችን እንደያዝን ልንገነዘብ ይገባል፤›› የሚል በሳል አስተያየት ሰጠ፡፡ ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው እንደ ማለት እኮ ነው፤›› ያለችን ያቺ ወይዘሮ ናት፡፡ እስራኤል ምንም ጥይት ሳታባክን አሜሪካ በእጅ አዙር በኩል ዶግ አመድ ብታደርግላት፣ ጦርነቱን ራሷ ተሳትፋ ያሸነፈች ያህል ነው የሚያስደስታት፤›› ያለን ስለእስራኤል ሲያብራራልን የነበረው ነው፡፡
ያ የዘረኝነት ወሬ የታከተው ሰው፣ ‹‹አያችሁ እኛ እርስ በርስ በመባላት የምናስደስተው ሌላ ጠላት አለ፡፡ ስለዚህ መበታተናችን ለሚጠብቁ የደስታ ምክንያት አንሁናቸው፤›› አለን፡፡ ‹‹ይህንን ነው መሸሽ፤›› አለ ወያላው፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹የት ትሸሻለህ ይህንን ነው መቀበል፤›› በማለት መለሰለት፡፡ ይኼን ጊዜ፣ ‹‹ኧረ በምሕረት ዘመን ላይ በቀል አታንሱ፤›› በማለት የምሕረት አዋጁ ፊርማ ገና አልደረቀም እያለች ወይዘሮዋ ሞገተች፡፡ ሐሳቡን በሌላ መንገድ እንደተረዳነው የገባው ሾፌር፣ ‹‹እኔ ያልኩት የበቀል ዓይነት አሁን አንቺ ያልሽውን ዓይነት ነው፤›› አላት፡፡ ጊዜ ወያላው ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹የእኛን መበታተን የሚፈልጉትን ጠላቶቻችንን በምሕረትና በይቅርታ እንበቀላቸው ነው የምትለኝ?›› ሲለው ሾፌሩ፣ ‹‹እኔ፣ አንተና ጠቅላዩ ብቻ ነን እየተናበብን ያለነው፤›› ብሎ አሳቀን፡፡ ያ ሰው አሁንም፣ ‹‹አያችሁ የወሬ ርዕሳችንን መቀየር እንችላለን ማለት ነው፡፡ ተራ የማይጠቅም የዘረኛነት ወሬ ከማውራት የሌሎች አገሮችን ልምድ መካፈል እንችላለን፤›› አለን፡፡
አንድ ወጣት እጁን እንደማውጣት አለና ከደሙ ንፁህ ነኝ በሚል ስሜት፣ ‹‹እኔ በበኩሌ ማንኛውንም የዘረኝነት ጽሑፎችን የሚያራምዱ ሰዎችን ከፌስቡኬ ላይ ‹ብሎክ› እያደረግኩ ነው፤›› ሲለን ሌላኛው ተቀበለና፣ ‹‹የፌስቡክንስ ብሎክ አድርገኸው ተገላገልክ፡፡ የጎረቤትህን ምን ልታደርገው ነው?›› በማለት ለጠየቀው ጥያቄ ሲመልስ፣ ‹‹እሱንም ቢሆን ጥርቅም አድርገህ መዝጋት ነው፡፡ ያን ጊዜ ይገባዋል፤›› ሲል ዕፎይታ ፊቱ ላይ ይነበብ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ስንቱ እየተቃጠለ ይሆን?
አንዲት ሴት አፏን እያሟሸች፣ ‹‹ያውም በዚህ የፖለቲከኛ እስረኞች እንኳን ይቅር እየተባሉ ባሉበት ዘመን ነው አፍንጫዬ ሥር ካለው ጎረቤቴ ጋር የምቃቃረው?›› ለሚለው ጥያቄዋ ሞጋች መልስ አላገኘችም፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ዕድለ ቢስ ነው፡፡
አንዱ በድንገት፣ ‹‹ሕግ ባይኖር እንዴት አሪፍ ነበር?›› ሲለን ሾፌሩ፣ ‹‹ባይሆን ይህንን ነው መሸሽ፤›› አለን፡፡ ‹‹ሕጉ ላልቷል፣ የሕግ የበላይነት ተሸርሽሯል፣ ሕገወጦች ተበራክተዋል እያልን ባለንበት ዘመን ላይ ተነስቶ ‹ሕግ ባይኖር› ይለናል እንዴ እባካችሁ?›› ያለን በሰውዬው አመለካከት የተበሳጨ ጎልማሳ ነበር፡፡ ወይዘሮዋ ተደርባ፣ ‹‹እንኳን ያለ ሕግ፣ ሕግ ኖሮም አልቻልነው፡፡ ፤›› ብላ አሁንም ሕግ ባይኖር ያለውን ሰውዬ ወቀሰችው፡፡ የሰውየውን ሐሳብ የተረዳው ሰው ያለ አይመስልም ነበር፡፡ እሱ ግን እንዲህ በማለት ሐሳብን አብራራ፡፡
‹‹በቃ አትጫወት ነው የምትሉት?›› የሚል ጥያቄ ሰነዘረ፡፡ ወያላው ፈጠን ብሎ፣ ‹‹ኧረ ተጫወት ሙሉ መድረኩ የአንተ ነው፤›› እያለ ዕድሉን ሰጠው፡፡ ሰውየውም እንዲህ ብሎ መናገር ጀመረ፣ ‹‹እኔ እኮ ለማለት የፈለግሁት እንዲያው እንዲህ ዓይነቱን ሰው ነበር መንገጭ መንገጭላውን ብሎ ወጥ በወጥ ማድረግ፤›› ሲለን ሐሳቡ ትንሽ ተገለጠልን፡፡ ይኼን ጊዜ ጎልማሳው፣ ‹‹አይዞህ በደንብ ተግባር ላይ መዋል ቢጀምር እኮ ምን የመሰለ ሕግ ነው ያለን፡፡ ስለዚህ ምንም ዓይነት ፍርድ ውስጥ መግባት የለብህም፡፡ ሕጉ ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት ያደርስልሃል፤›› በማለት ሐሳቡን አፀዳለት፡፡ ይኼን ጊዜ እኛም መካኒሳ ደርሰን ነበር፡፡ በምናየው ችግር ምክንያት ለመፍረድ ድንጋይ ማንሳታችንን ትተን ወደ ሕግ ማቅረቡ ይሻላል እያልን ለዛሬው እንሰነባበት፡፡ ከመሰነባበታችን በፊት ግን ሕግ ባይኖር ኖሮ ምን እንሆን ነበር ብንልስ? መልካም ጊዜ!