Monday, February 6, 2023

የባሌ ጎባና የደምቢዶሎ ግጭቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ ክፍሎች የተከሰቱ ተቃውሞዎችና አመፆች፣ በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ያስከተሉ ነበሩ፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ጊንጪ ተነስቶ ክልሉን ያዳረሰው አመፅና ተቃውሞ፣ በአማራ ክልል በሰፊው የታየው ሕዝባዊ ተቃውሞና አመፅ የበርካቶች ሕይወት እንዲያልፍ፣ የአካል ጉዳቶች እንዲደርሱ፣ በርካቶች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉና የአገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጎዳ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡

በእነዚህ አመፆችና ግጭቶች የመንገዶች መዘጋት፣ የገበያዎች ሥራ ማቆም፣ የትራንስፖርት መቋረጥ፣ የመንግሥትና የግል ንብረቶችና ተቋማት መውደምና ሌሎች ተመሳሳይ ክስተቶች የተለመዱ ሆነው ነበር፡፡ ይህንንም ለመቆጣጠር መንግሥት ያደረጋቸው ጥረቶች ባለመሳካታቸው፣ በመደበኛው የፀጥታ ማስከበር ሥራዎች ችግሮቹን ማስወገድና የኅብረተሰቡን ሰላማዊ የዕለት ተዕለት ኑሮ መመለስ ባለመቻሉ፣ በወራት ልዩነት ሁለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ታውጀው ነበር፡፡

በእነዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች የነበሩትን የፀጥታ ችግሮች ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ ባለመቻሉም፣ አገሪቱን የሚመራው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከ17 ቀናት ስብሰባ በኋላ፣ በአገሪቱ እየተከሰቱ ለነበሩ ችግሮች ሙሉ በሙሉ በከፍተኛ አመራር ደረጃ ኃላፊነት እንደሚወስድና ማስተካከያም እንደሚያደርግ አስታውቆ ነበር፡፡

በዚህም ውሳኔ መሠረት የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች በውስጣቸው ግምገማ በማድረግ ከብአዴን ውጪ የአመራር ሽግሽግ ያደረጉ ሲሆን፣ የደኢሕዴንና የኢሕአዴግ ሊቀመንበር የነበሩት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከፓርቲና ከመንግሥት ኃላፊነት ለመልቀቅ መወሰናቸውን የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. አስታወቁ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልቀቅ ተከትሎ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኢሕአዴግ ሊቀመንበር በማድረግ መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. የመረጠ ሲሆን፣ ፓርላማው መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በማድረግ አቶ ኃይለ ማርያምን እንዲተኩ ሰየማቸው፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መሰየም ማግሥት ሁሉም ነገር ወደ መረጋጋትና ወደ ሰላማዊ ኑሮ የተመለሰ ይመስል፣ በአገሪቱ በርካታ ሥፍራዎች ደስታና ጭፈራዎች ነግሠው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመረጣቸውም በስፋት ሲታዩ የነበሩ የፀጥታ ችግሮች መርገብ ማሳየታቸውም ዕሙን ነው፡፡ ይሁንና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሰዎች መፈናቀልና ግጭቶች ይስተዋሉ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሥልጣነ መንበሩን ከተቆናጠጡ በኋላ መጀመርያ ሥራቸው ያደረጉት በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በመዘዋወር ንግግሮችን ማድረግ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎች ጋር ያሉባቸውን ችግሮች በሚመለከት ውይይቶችን ሲያደርጉ ነበር፡፡

በዚህም አንፃራዊ መረጋጋቶች ታይተው የነበረ ቢሆንም፣ የፀጥታ ችግሮቹ ሙሉ በሙሉ ግን ስላልተወገዱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች ሲከሰቱ ተስተውሏል፡፡

በደቡብ ክልል በስፋት በሲዳማ፣ በወላይታ፣ በጉራጌ፣ በካፋና በቤንች ማጂ ዞኖች ብሎም በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ታይተው የነበሩ ግጭቶች አሁን የረገቡ ቢሆንም፣ በኦሮሚያ አካባቢ ደግሞ በድጋሚ የሚያገረሽ ግጭት ሲታይ ከርሟል፡፡

በቅርቡ ደግሞ በባሌ ጎባና በቄለም ወለጋ ደምቢዶሎ ከተሞች የፀጥታ ችግሮች ተስተውለዋል፡፡

እስከ እሑድ ሐምሌ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ ለሦስት ቀናት በባሌ ጎባ የቆየው ግጭት የተከሰተው በከተማው መሀል አደባባይ ላይ የተተከለ የቀይ ቀበሮ ምሥል ሐውልት በማፍረስ፣ በአካባቢውና በኦሮሚያ ክልል በጀግንነት የሚታወቁት ሐጅ አደም ሳዶን ሐውልት በሥፍራው ለማቆም በፈለጉና በቦታው ባንዲራ አውጥተው በሰቀሉ ወጣቶች መካከል የተፈጠረ መሆኑን፣ የኦሮሚያ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ግጭቶቹን ሃይማኖታዊና የብሔር ግጭት ገጽታ ለማስያዝ ጥረቶች እንደነበሩ የገለጹት ኃላፊው፣ ‹‹የሃይማኖትና የብሔር ግጭት በጭራሽ የለም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ግጭቱ ይህንን ገጽታ እንዲይዝ የተደረገውም በፌዴራልም ሆነ እስከ ዞን ድረስ ባሉ በተለያዩ ምክንያቶች ጥቅማቸው የተነካባቸው ‹‹በኮንትሮባንድ የደለቡ››፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲፈጥሩና በደሎችን ሲያደርሱ የነበሩና ከኃላፊነታቸው የተነሱ አካላት መሆናቸውን ገልጸው፣ ‹‹የእነዚህ አካላት ሥውር እጆች›› ችግሩን እያባባሱ ናቸው ብለዋል፡፡

በባሌ ጎባ በተከሰተ ግጭት የ11 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ፣ ከ100 በላይ ሰዎች ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ያሉት የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው፣ በርካቶቹ ታክመው ወደየቤታቸው የሄዱ መሆናቸውን፣ አሥር ያህል ተጎጂዎች በሆስፒታል አሁንም የሕክምና ዕርዳታ እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት በሥፍራው የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራልና የክልሉን ፖሊስ ኃይሎች በጥምር ችግሩን ለመፍታት እንዳሰማራና አጥፊዎችንም ወደ ሕግ በመቅረብ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹በግጭቱ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ 35 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው፤›› ሲሉም  ነገሪ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የሐውልት ጥያቄ ለዚህ ግጭት ሊደርስ እንደማይችል የገለጹት የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በክልሉ የፖሊስ ኮሚሽነር፣ በኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አዳነች አቤቤና በሌሎች የሚመራ ልዑክ በሥፍራው በመገኘት ለኅብረተሰቡ ችግር ውይይት እያደረጉ እንደሆነ፣ የአካባቢው የሃይማኖት አባቶችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን፣ የአካባቢው ወጣቶችን፣ ምሁራንና ሌሎችን ያቀፈ ኮሚቴ ተቋቁሞ ለዘላቂ መፍትሔ እየሠራ እንዳለ ገልጸዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ጊዜ የክልሉንና የፌዴራል መንግሥት እንቅስቃሴ ለማዳከም የሚሠሩ፣ አካላት እንዳለ በግልጽ ይታወቃል፡፡ በአንድ በኩል በሥውር የሚሠሩ፣ የሚንቀሳቀሱና ስፖንሰር የሚያደርጉ አካላት ሕዝብን ስሜታዊ የማድረጊያ መንገዶችን የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ መንግሥት ይህንን ድርጊት እየመረመረና አስፈላጊውን ዕርምጃ እየወሰደ ይቀጥላል፡፡ ሕዝቡ የሚታወቀው በጨዋነት ነው፡፡ ይህ ክስተት ሕዝቡን የማይገልጽ እንደሆነ መታወቅ አለበት፤›› ሲሉም የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

ከባሌ ጎባ በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ አካባቢዎች ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በተደጋጋሚ ሲከሰት የነበረው የታጠቁ አካላት ጥቃት፣ ሰኞ ሐምሌ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. አስከፊ ገጽታ ይዞ በቄለም ወለጋ ደምቢዶሎ ብቅ ያለ ሲሆን፣ ምሽት አምስት ሰዓት ተኩል አካባቢ አንዲት ነፍሰ ጡርን ለወሊድ ወደ ሆስፒታል እያደረሰ የነበረ ባጃጅ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የነፍሰ ጡሯ ሕይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ፣ አሽከርካሪውን ጨምሮ አራት ሰዎች ጉዳት እንደ ደረሰባቸው ተሰምቷል፡፡

በአካባቢ በርካታ ኦነግ ነን የሚሉ የታጠቁ ኃይሎች እንዳሉና በተደጋጋሚም ጥቃት እንደሚሰነዝሩ፣ ነገር ግን መንግሥት የሰላም ጥሪ በማቅረብ ኦነግንም ሆነ ሌሎችን ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ አድርጎ ሳለ ኦነግ ይህንን ለማድረግ ምክንያት ሊኖረው እንደማይችልና ለጥቃቱ ኃላፊነት እንዳልወሰደ የገለጹት ነገሪ (ዶ/ር)፣ በኦነግና በቄሮ ስም የሚነግዱ አካላት ሊሆኑ ይችላሉ ሲሉም ተናግረዋል፡፡

‹‹አሁን መንግሥት ከኦነግ ጋር እየተዋጋ አይደለም፣›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን በተለያዩ ወረዳዎች መሣሪያ መዝረፍና የፖሊስ መኪናዎችን ማጥቃት እንደሚስተዋል፣ ነገር ግን ኦነግ ለጥቃቱ ኃላፊነት እየወሰደ ስላልሆነ በኦነግ ስም እየተንቀሳቀሱ ያሉ አካላት ሊኖሩ እንደሚችሉ ጥርጣሬ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ ኦነግ የተኩስ አቁም መግለጫ ማውጣቱና በሰላማዊ መንገድ ድርድር እየተካሄደ ባለበት ጊዜ ይህንን የሚያካሂድ ከሆነ፣ የኦሮሞ ሕዝብን የማይወክል ስለሆነ ይህንን አሳውቆ ግልጽነቱ መታወቅ አለበት ብለዋል፡፡

‹‹በቄሮ ስም የሚነግዱ ሌሎች ቡድኖች ስላሉ እነዚህን የኦሮሞ ወጣቶች እንዲታገሏቸው፣ የትኛውም አካል ደግሞ በሕገወጥነት፣ ደም በማፍሰስ፣ ሕይወት በማጥፋት ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመደራደር ሥልጣን መያዝ ስለሚችል፣ የትኛውም አካል ጥፋት እያደረሰ የኦሮሞን ሕዝብ እወክላለሁ ለማለት የሚችል አካል ስለሌለ ይህንን ሕዝቡ ማወቅ አለበት ማለት ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በምዕራብ ኦሮሚያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በታጠቁ አካላት ጥቃቶች እንደሚደርሱ፣ መሣሪያ የመዝረፍና ሰዎችን አፍኖ የመውሰድ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

ምንም እንኳን ኦነግ ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ የተኩስ አቁም ማድረጉን ቢያስታውቅም፣ በኋላ ባወጣው ሌላ መግለጫ ደግሞ መንግሥት የተኩስ አቁሙን እየጣሰ ስለሆነ ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡

በቄለም ወለጋ ደምቢዶሎ በተከሰተው ጥቃት ሦስት የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑም ታውቋል፡፡

ኦነግ በቅርቡ የአሸባሪነት ፍረጃ በፓርላማ ከተነሳላቸው ድርጅቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን፣ ቀድሞ የነበሩ የኦነግ መሥራቾችና አባላት በተለያዩ ምክንያቶች ከኦነግ በመገንጠል የየራሳቸውን ፓርቲ መሥርተዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የኦነግ መሥራች በሆኑት በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) ተጠቃሽነው፡፡ ኦዴግን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች መንግሥት ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ያቀረበውን ጥሪ ተቀብለው፣ በአገር ውስጥ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -